| "ክብር የሚገባው የአገልግሎቱ... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
"ክብር የሚገባው የአገልግሎቱ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ነው"አቶ ደስታ ዳንኤል የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የሐዋሳ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የሚባል እድገት እያሳየች ነው፡፡ በተቃራኒው የከተማዋ አስተዳደር የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት በተለያየ አጋጣሚ የሚነገር ነው፡፡ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱትን ችግሮችና የከተማዋን እድገት በተመለከተ አዲሱ አስተዳደር እያከናወነ ስላለው ተግባር የከተማውን ከንቲባ አቶ ደስታ ዳንኤልን አሰግድ ተፈራ አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ ደስታ በክልሉ የተለያዩ ኃላፊነት ደረጃ የሰሩ ሲሆን ከንቲባ የሆኑት ለሁለት ዓመት የፕሬዚዳንቱ የአቅም ግንባታና የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው እየሰሩ እያለ ግንቦት 20 ቀን 2000 ዓ.ም ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በከተማዋ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንደነበር ያውቃሉ፡፡ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ሆነው ሲመደቡ በመጀመሪያ ምን አደረጉ? አቶ ደስታ፡- በሐዋሳ ግልፅ ያልሆኑና በግልፅ የሚታዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ግልፅ ያልሆኑትን ችግሮች ከንቲባ ከመሆኔ በፊት እንደ አንድ የከተማዋ ነዋሪና አመራር ሰጪ አካል ነዋሪዎች የሚያነሱት በርካታ ችግሮች ናቸው፡፡ በተለይም ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሮሮ የሚሰማበት፣ ከመሬት ጋር በተያያዘ አገልግሎት ጠያቂዎች ለወራት የሚመላለሱበትና ባለጉዳዮች አገልግሎት ማግኘት መብታቸው መሆኑ ተዘንግቶ የሚሸማቀቁበት ሁኔታ ነበር፡፡ ተስፋ ያልቆረጡ ተገልጋዮች ለዓመታት ተመላልሰው ጉዳያቸውን በተለያየ መንገድ ሲያስጨርሱ ተስፋ የቆረጡ ጉዳያቸውን የሚያቋርጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ ከንቲባ ሆኜ ኃላፊነቱን ስረከብ በመጀመሪያ ርምጃ እንዲወሰድ ያደረኩት በመሬት አስተዳደር ላይ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከመሬት ጋር በተያያዘ በሐዋሳ ያለው ዋንኛ ችግር እንዴት ይገልፁታል? አቶ ደስታ፡- የአገራችን ዋንኛ ሀብት መሬት ነው፡፡ መሬት የሁሉም ዜጋ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን ዋና ሀብት ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለመኖሪያ ቤት ለኢንቨስትመንትና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች መሬት በብዛት ይጠየቃል፡፡ ስለዚህ ከተማዋ ያላት መሬት በአግባቡ መለየት ነበረበት፡፡ መሬቱ በየዘርፉ ተለይቶ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመሬት ጥያቄ መስተናገድ አለበት፡፡ በማዘጋጃ ቤቱ ላይ የነበረው ዋና ችግር ከዚህ በተቃራኒ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያለማስተናገድ ነበር፡፡ ህብረተሰቡ በግልፅ አውቆት የሚሰራ ሥራ አልነበረም፡፡ ይህ ችግር ጊዜ ስለማይሰጥ አዲሱ ካቢኔ ከነባሮች ጋር ውይይት በማድረግ የመሬት አሰጣጥ ሁኔታ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ አሰራር እስኪዘረጋለት እንዲቆም ተስማማን፡፡ በአጭሩ ለኢንቨስትመንት ካልሆነ በስተቀር የሌላ ዓይነት የመሬት አሰጣጥ ታገደ፡፡ ሪፖርተር፡- አገልግሎት ማቋረጥ እንዴት መፍትሄ ይሆናል? አቶ ደስታ፡- ሁሉም እየተነሳ በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሰው መሬት በመሸጥ ነው፡፡ መሬት ውስን ሀብት በመሆኑ ዝም ብለን ካደልን ወደፊት ከተሞች ሲያድጉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የት እንተገብራለን? ማንኛውም የልማት ራዕይ የሚተከለው መሬት ላይ ነው፡፡ አቅደን ወደ ተግባር ስንገባ መሬት አጣን ራዕያችንን ማስፈፀም አንችልም፡፡ አዳዲስ ማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፋት አይቻልም፡፡ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎች ፋብሪካዎች መሬት ከሌለ የት ይገነባሉ? ከዚህ አንፃር በመሬት ላይ ያለንን መረጃ ለማጠናከር በየዘርፉ እንዲጠና ኮሚቴ አቋቋምን፡፡ በአዲሱ አወቃቀር 11 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ወደ ከተማችን እንዲቀላቀሉ ስለተደረገ፡፡ ገበሬ ማህበራቱ በመዋቅር ወደ ከተማ ይቀላቀሉ እንጂ በአርሶ አደሩ ይዞታ ስር ናቸው፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ስለአገልግሎት አሰጣጥ መቋረጥ ስናስብ እነዚህ ችግሮች እንዴት ይታዩ? የሚለው አሳሳቢ ስለሆነ". ሪፖርተር፡- በከተማ ክልል ባለው ቦታ ላይ ማዘጋጃ ቤቱ መረጃ የላቸውም ማለት ነው? አቶ ደስታ፡- እያስጠናን ነው ስል በከተማ ክልል ያለውን መሬት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ መሐንዲሶች ቦታ ሲሰጡ አስቀድመው የሸነሸኑትን ቦታ በቅደም ተከተል ሳይሆን ከመሀል ከመሀል እየዘለሉ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ለምን እየዘለሉ ይሰጣሉ? አቶ ደስታ፡- ሕዝቡ አምርሮ ሲቃወም የነበረው ይህንን ነው፡፡ ከመሀል እየዘለሉ የሚያልፉት ከቦታ በጥቅማ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ አጥኚው ቡድን የሚያጠናው ይህንንም ጭምር ነው፡፡ ከመሀል የተዘለሉትን መሬቶች እየነቀሱ ያወጣሉ፡፡ በኢንቨስትመንትም መስክ በተመሳሳይ እየተሰራ ነው፡፡ የሚጠበቀው የኮሚቴው ሪፖርት ነው፡፡ በሪፖርቱ ለመኖሪያ ቤት፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለማህበራዊ አልግሎት የሚውለው ቦታ በሄክታርና በካሬ ሜትር ተለይቶ ይቀርባል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ አቅማችንን አውቀን አገልግሎቱን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጀምራለን፡፡ ሪፖርተር፡- እስከመቼ? አቶ ደስታ፡- በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ለኢንቨስትመንት የማስፋፊያ ቦታ ጠያቂዎች ሌላው ችግር ፈጣሪዎች እንደሆኑ ይነገራል፤ አቶ ደስታ፡- መሬት የወሰደ ባለሀብት በገባው ውል መሠረት ማልማት ይገባዋል፡፡ አሁን የሚታየው መሬት ወስደው ግንባታ ሳይጀምሩ ማስፋፊያ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ የወሰዱትን መሬት ሳያለሙ ማስፋፊያ የሚጠይቁትን አናስተናግድም፡፡ መሬት እየወሰዱ ለሌላ ዓላማና ለንግድ አጥሮ ማስቀመጥ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁለት ሶስት መሬት ወስደው አጥረው የሚጠፉ አሉ፡፡ ከወሰዱት መሬት ላይ ጠፍተው ሌላ መሬት ይጠይቃሉ፡፡ አዳዲስ አልሚ ባለሀብቶች ሲመጡ ከየት አምጥተን መሬት እንስጥ? እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከአልሚ ባለሀብቶች ተጠቃሚ የሚሆነውን የክልሉን ነዋሪ እንጐዳለን፡፡ የመኖሪያ ቤት ቦታ ላይም በተመሳሳይ ዋስትና አራት ቦታ የሚወስዱ አሉ፡፡ ዝርዝራቸው ተይዟል፡፡ ማጣራት እየተደረገ ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት ከ600 በላይ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ሁሉም አዲስ አይደሉም ይህንንም እያጣራን ነው፡፡ ለጊዜው አገልግሎቱ በመቋረጡ መተራመሱ ቆሟል፡፡ ሪፖርተር፡- ሕገወጥ መረጃ የሐዋሳ ከተማን ፣የናጠ፣ ችግር ነው ይባላል፣ አቶ ደስታ፡- ቀደም ሲል በወሬ የሰጠሁት፣ ከንቲባ ከሆንኩ በኋላ ደግሞ በተጨባጭ ያየሁት ችግር ነው፡፡ ፎርጅድ ካርታ እየተሰራ የባለቤትነት መዝገብ የተነሳበት ሁኔታ ነበር፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የሐሰተኛ መረጃ ምንጮችን በማጥናት ይህንን የሰሩት ላይ ክስ ተመስርቶ ነበር፡፡ የክልሉ የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ጉዳዩን ይዞት እየሰራበት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ችግሩ ከፍተኛ ስለነበር አመራሩ ደርሶበት ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ኮሚሽኑ ምርመራውን ሰያጠናቅቅ ይፋ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይፋ መሆንም አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ሀሰተኛ ካርታ የሚያዘጋጁት ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው አዲስ አበባ ድረስ የዘለቀ ቁርኝት ያላቸው እንደነበሩ፣ ሐዋሣ ያሉት እንደጠፉ፣ ከአዲስ አበባ በጥቆማ የተያዙ አሉ ይባላል፡፡ አቶ ደስታ፡- ከተማ ውስጥ የነበረው አላመለጠም፡፡ ተይዞ ታስሯል፡፡ የተፈረደበት አራት ዓመት ነው፡፡ ሊያንስ ይችላል፡፡ ተባባሪ የነበሩት ታስረው ተፈተዋል፡፡ እንዴት እንደተለቀቁ አላውቅም፡፡ ጉዳዩ የተፈፀመው እኔ ከንቲባ ከመሆኔ በፊት በመሆኑ ብዙ ማለት አልችልም፡፡ ሪፖርተር፡- በእርስዎ ደረጃ የወሰዱት ርምጃ አለ? አቶ ደስታ፡- አዲሱ ካቢኔ ግንቦት 20/2000 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ ቀደም ሲል ከነበሩ መሀንዲሶች መካከል በግምገማ አንድ መሀንዲስ ብቻ ነፃ ሲሆን የተቀሩት ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ርምጃው ምንድነው? አቶ ደስታ፡- ከማዘጋጃ ቤት መዋቅር ወደ ሌላ ሥራ እንዲዛወሩ የተደረጉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የወሰዱትን ትርፍ መሬት እንዲመልሱ ተደርጐ በህግ አግባብ ጉዳያቸው እንዲታይ ለማዘጋጃ ቤቱ መመሪያ ሰጥተናል፡፡ የሚገርመው ሁሉም መሀንዲሶች ከተመደቡበት አዲስ የሥራ መደብ በራሳቸው ፈቃድ ለቀዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ክስ ተመስርቶባቸው? አቶ ደስታ፡- መረጃ ተጠናክሮ ክስ እንዲመሰረትባቸው ለህግ ክፍል መመሪያ ተሰጥቷል፡፡ አፈፃፀሙን በተለያዩ የስራ መደራረቦች አልገመገምንም፡፡ ሪፖርተር፡- አዳዲስ መሀንዲሶች መመደብ መፍትሄ ይሆናል? አቶ ደስታ፡- ችግሩ የህብረተሰቡም ነው፡፡ ጥቅም ሰጥቶ ህገወጥ ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ ጥቂት አይደሉም፡፡ በዜግነት አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል መታወቅ አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ህብረተሰቡ የሚሽቆጠቆጥላቸው፣ ካለው ውስን ገንዘብ ላይ ጥቅም የሚሰጣቸው የሥራ ኃላፊዎች በሕዝቡ በራሱ ቀረጥ ደሞዝ የሚከፈላቸው የሕዝብ ቅጥረኞች መሆናቸውን ማወቅ ስላለበት እዚህ ላይም እየሰራን ነው፡፡ የሕዝብ አገልጋዮች በአግባቡ ሲያገለግሉ ይቀጥላሉ፡፡ በአግባቡ ካልሰሩ ይባረራሉ፡፡ ይህንን የሚያደርገው ሕዝብ ነው፡፡ ክብር የሚገባው አገልጋዩን የቀጠረው ሕዝብና የአገልግሎቱ ባለቤት ነው፡፡ ሕብረተሰብ ባይኖር ከንቲባም መንግሥትም፣ ተቋማትም አያስፈልጉም በዚህ ረገድ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ እያስተማርን ነው፡፡ በእጅ አትሂዱ እያልን ነው፡፡ በአዲሱ አሰራር ማሻሻያ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራንበት ለውጥም እያየንበት ነው፡፡ የሙከራ ሥራ በተሰራባቸው ሁለት ክፍለ ከተሞች ስራዎች በደቂቃዎች ውስጥ እያጠናቀቁ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በትስስር በህጋዊ የመንግሥት ተቋማት ስም ወንጀል ይሰራል ይባላል፣ አቶ ደስታ፡- በርካታ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች አሉ፡፡ ፕራይቬታይዜሽንና ፍርድ ቤት መልሷል እያሉ የሚያጭበረብሩ አሉ፡፡ በተለይ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጠ እያሉ ያጭበረብራሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ከሙስና ተባባሪ ሠራተኛና ኃላፊ ሲኖር ነው፡፡ ውሳኔዎች በግልባጭ ለአስፈፃሚው መስሪያ ቤት ይገልፃሉ፡፡ በትስስር ግን ይሰራል፡፡ የኤጀንሲው ውሳኔ በቀጥታ የሚመጣው ለአስፈፃሚው አካል በመሆኑ ማጭበርበር የሚፈፀመው እጃቸው ባልፀዳ ሠራተኞች ነው፡፡ አሁን እንደዚህ ዓይነት ችግር የለም፡፡ ሪፖርተር፡- ለከተማዋ ማማር ሕዝብ የምታስተባብሩት እንዴት ነው? አቶ ደስታ፡- አስፋልት በተፈጥሮው ንፁህ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ በጀት የተሰሩ መንገዶች ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ በቀን ሦስቴ የሚያፀዱ ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህንን ሥራ በባለቤትነት የሚቆጣጠሩ አካላት አሉ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ዋንኛ ተቆጣጣሪ ነው፡፡ ሕዝቡ በከተማ ፅዳት በማመኑ ገንዘብ ያዋጣል፡፡ በጉልበቱ ያግዛል፡፡ በየክፍለ ከተማው የፅዳትና የአካባቢ ጥበቃ ቡድን የራሱን አካባቢ ፅዳት ይጠብቃል፡፡ በግል የንፅህና አጠባበቅ ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶችም አሉ፡፡ ከተጠቃሚዎች ጋር ውል ገብተው ይሰራሉ፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር የሚጠራቀሙ ቆሻሻዎችን የከተማዋ አስተዳደር በአግባቡ ያስወግዳቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የሚወገዱ ቆሻሻዎች ለወደፊቱ ችግር እንዳይፈጥሩ ምን እያደጋችሁ ነው? አቶ ደስታ፡- የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ረገድ ከዓለም ባንክ ጋር በመፃፃፍ ጥናት እያስጠናን ነው፡፡ በጥናቱ ሥራው ለአንድ ባለሀብት ይሰጣል፡፡ ቆሻሻ ከተሰበሰበ በኋላ ቆሻሻ የሚጠራቀምበት ቦታ በዘመናዊ መንገድ ይሰራል፡፡ ቆሻሻ ሲከማች ወደ መሬት ይሰርጋል፡፡ መሬት ሰርጐ የአካባቢ ብክለት እንዳያመጣ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ሦስት ቦታዎች መርጠን ዲዛይን ሰርተን አጠናቀናል፡፡ መቃጠል የሚገባው ቆሻሻ ተቃጥሎ አመዱ ይቀበራል፡፡ መቃጠል የማይችለውም ወደ መሬት ሊሰርግ በማይችል መልኩ ይቀበራል፡፡ ፕሮጀክቱ ለ20 ዓመታት የሚሰራ አስተማማኝ ፕሮጀክት ነው፡፡ ለ20 ዓመት የቦታ ችግር ሳይኖር ቆሻሻ መቀበር የሚያስችለው ጥናት ተጠንቶ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ለፕሮጀክቱ በጊዜያዊነት 45 ሚሊዮን ብር ይዘናል፡፡ በሃገራችን ላይ ከዓለም ባንክ በላይ ሀብታችን ሕዝቡ ስለሆነ በቀዳሚነት እናሳትፈዋለን፡፡ ሪፖርተር፡- ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ሰርታችኋል፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ ግን ዘመናዊ ሥራ አልሰራችሁም፤ አቶ ደስታ፡- የትራንስፖርት ሲስተሙ በጥናት እንዲሰራ እየሰራን ነው፡፡ አሁን ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት ከበቂ በላይ ቢሆንም ዘናዊና ስምሪት ያለው፣ ሁሉንም የከተማ ነዋሪዎች ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ መሆን አለበት፡፡ ከፍተኛ የከተማ አውቶቡሶች ለማሰማራት ዘርፉን ለባለሀብቶች ክፍት አድርገን እየጠበቅን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሐዋሳ የመዝናኛ ማዕከል እንደመሆንዋ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ/ ስርጭት ላይ ምን እየሰራችሁ ነው? አቶ ደስታ፡- የመንግሥት፣ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የሐይማኖት ተቋማት ሰፊ ሥራ ይሰራሉ፡፡ በከተማዋ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከዓመታዊ በጀታቸው ሁለት በመቶ ይሰጣሉ፡፡ ሠራተኞች ከደሞዛቸው 0.5 በመቶ በየወሩ ያዋጣሉ፡፡ በተገኙት አጋጣሚዎች ትምህርት ይሰጣል፡፡ የክልሉ መንግሥት በቂ በጀት መድቦ ይሰራል፡፡ በእኛም አቅም በቂ በጀት መድበን እየሰራን ነው፡፡ ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት አንድ ሰው ለመቅበር ስንሄድ አራትና አምስት ሰዎች ሲቀበሩ እናይ ነበር፡፡ በሁኔታው እንደ ህብረተሰብ ተሸማቀን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተሻሽሏል፡፡ ብዙም የሚዳፈሩ የሉም፡፡ ለውጥ አለ፡፡ ግን ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሐር ረድቶን ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባንቀርፈውም ትውልድ የመጠበቅ ኃላፊነት የተሞላበት ሥራ መሥራት ግድ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከስራ በኋላ ይዝናናሉ? አቶ ደስታ፡- ስብሰባ ከሌለኝ በስተቀር እስከምሽቱ ሁለት ሰዓት ቢሮዬ እቆያለሁ፡፡ ከቢሮ ስወጣ በቀጥታ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ከንቲባ ብዙ ፈላጊ አለው፡፡ እርስዎስ? አቶ ደስታ፡- ከማንም ጋር ሻይ እንኳን መጠጣት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም እንክፈል የሚል ነገር ይመጣል፡፡ ከእንክፈል በኋላ በየደረጃው ሌላ ጥያቄ ይነሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አዝማሚያ ኃላፊነትን የመወጣት ችግር ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ቤቴን እመርጣለሁ፡፡ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር መዝናናት የምመርጠው ለዚህ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ጋባዥም ተጋባዥም የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለኝ የእረፍት ጊዜ እፀልያለሁ፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ አነባለሁ፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |