Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ለአደጋ የተጋለጠው የዓለም ቅርስ
ለአደጋ የተጋለጠው የዓለም ቅርስ E-mail
Monday, 21 January 2008

በዩኒስኮ ለአደጋ የተጋለጠ የዓለም ቅርስ ተብሎ የተመዘገበውን የሰሜን ብሔራዊ ፓርክን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሰሜን ጐንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ጀምበር ገለፁ፡፡

ሃያ የገጠር ወረዳዎችንና ሦስት የከተማ አስተዳደሮችን በሚያጠቃልለው የሰሜን ጐንደር ዞን የሚገኘው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ በጦርነትና በአካባቢው ኗሪ ያልተገባ እንቅስቃሴ በዓለም ቅርስነት ሊያስመዘግቡት የቻሉት ብርቅዬ እንስሳት ቁጥር መቀነስ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጠ የዓለም ቅርስ ሊባል መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ፓርኩ በጃናሞራ፣ በደባርቅ፣ በአዳርቃይና በበየዳ ወረዳዎች መካከል የሚገኝ ሲሆን በእነዚህ ወረዳዎች የሚገኘው ህብረተሰብ ስለተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ስለ ብሔራዊ ፓርክ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ምክንያት እንስሳቱን (ዋልያዎችን) ለስጋ ያርድ እንደነበር፣ ከብቶቻቸውን ለግጦሽ በፓርኩ ያሠማሩ እንደነበርና ደን ይጨፈጭፉ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ለረዥም ዓመታት በአገሪቱ የተደረገው ጦርነትም ለፓርኩ ህልውና መዳከም አስተዋፅኦ እንደነበረው ይገልፃሉ፡፡

"ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ በማጤን የዞኑ መስተዳድር የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው፡፡ መንግሥትም ለፓርኩ በሰጠው ትኩረት የተከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ የዞኑ መስተዳድርም ከተለያዩ አካላት ጋር ስምምነት በመፈራረም በጋራ የሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በፊት ፓርኩ ሲከለል የነበረው ስፋት መቶ ሠላሳ ስድስት ኪሎ ሜትር ስኩዬር ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ስፋት መንደሮችንና የእንስሳት መሠማሪያዎችን ሁሉ ያካተተ ነበር፡፡ የመንደሮቹ በፓርኩ ክልል ወስጥ መካተት ለፓርኩ ደህንነት ጥሩ ስላልሆነና እንደ ሊማሊሞ፣ ራስ ዳሸን ተራራንና ወደ ራስ ዳሸን የሚወስደው ኮሪደር በፓርኩ ውስጥ መካተት እንዳለባቸው ስለታመነበት፣ መንደሮቹን ከፓርኩ ክልል በማስወጣት መካተት ያለባቸው ቦታዎችን የማካለል ሥራ ተከናውኗል"

መንደሮቹን ከፓርኩ ክልል ውጭ የማድረጉን ሥራ በማስመልከት፣ ፓርኩ አሁን ያለውን ሥፋት (4 በመቶ ስኩዬር ኪሎ ሜትር) የማካለሉ እንቅስቃሴ 1995 ዓ.ም. ላይ ተጀምሮ ደረጃ በደረጃ እየሄደ በመጨረሻ ራስ ዳሸን ተራራና ወደዚያ የሚወስደው ኮሪደር መከለሉን ገልፀዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ሲካተቱ ከፓርኩ ውጭ መሆን የሚገባቸውን መንደሮች ከክልሉ ውጭ በማድረግ መከለሉንና አሁንም ፓርኩ መሀል ላይ ሁለት መንደሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ከአንዱ መንደር ኗሪዎች ጋር ለቤቶቻቸው ማካካሻ በመስጠት ለማንሳት ስምምነት ላይ ሲደርስ በሌላኛው መንደር ያሉት ነዋሪዎች ፍቃደኛ ባለመሆናቸውና አስገድዶ ማስነሳትም አለመቻሉን አልደበቁም፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ፣ መካተት ያለባቸውን ቦታዎች ማካለል፣ ከፓርኩ ክልል ውጭ መሆን የሚገባቸውን ማስወጣት አንድ እርምጃ እንጂ ለፓርኩ ደህንነት በራሱ መፍትሔ መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም በይበልጥም ፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን መንደሮችና ውጭም ያሉ ነዋሪዎችን ከፓርኩ እድገት እነሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መኖሩን በማስተማር ዋልያ እንዳይገድሉ፣ ደን እንዳይጨፈጭፉና እንስሳት እንዳያሰማሩ ተደርጓል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የደን ልማት እንዲያካሂዱና የደጋ ፍራፍሬዎች እንዲያመርቱ የዞኑ መስተዳድር የተለያየ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በፓርኩ አስጐብኚ እንዲሆኑ፣ በጥበቃ ሥራ ላይ እንዲሠማሩ በማድረግ እንዲሁም ለቱሪስቶች የአካባቢው ባህላዊ ምርት የሆኑ ቁሳቁሶችን በመሸጥና በቅሎ በማከራየት ከፓርኩ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ተመቻተቷል፡፡

የፓርኩን ክልል ከማካለል ባሻገር የተለያዩ አገልግሎቶችን የማሻሻል ሥራ ተሠርቷል ወይ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ "ከደባርቅ እስከ መካነ ብርሀን ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ አዲስ የተሠራ ነው፡፡ ሎጂዎች ተሠርተዋል፡፡ የመፀዳጃ ቤቶችም ተሠርተዋል፡፡ ሶላር ኢነርጂ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ባይኒኩላር መነፅሮችም ተሟልተዋል፡፡ እስከ አሁን የተሠሩት ሥራዎች ጥሩ ቢሆኑም ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ" በማለት መልሰውልናል፡፡

የፓርኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው በክልል ደረጃ የተቋቋመው የፓርኮች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሲሆን የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ፅህፈት ቤትም ከፓርኮች ባለሥልጣን ጋር በጋራ ይሠራል፡፡ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት፣ የዞን አስተዳደርና ወረዳዎች የጋራ ኮሚቴም ፓርኩን በሚመለከት በሚደረግ እንቅስቃሴ በቀጥታ ይሳተፋል፡፡ ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ ለማሻሻል ተቀርፀው ከነበሩ ኘሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት አንዱ እንደነበርና የአካባቢውን ህብረተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ የፓርኩን ዘላቂ ህልውና ለማረጋገጥ ዋነኛ መንገድ መሆኑ ታምኖበት ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የገምጋሚ ቡድን ወደ ፓርኩ በመምጣት የብርቅዬ እንስሳቶቹን ለመጠበቅና በፓርኩ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የተሠሩ ሥራዎችን በመመልከት ጥሩ አስተያየት ቢሰጥም ፓርኩ አደጋ ውስጥ ካሉ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር አለመውጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የቀረበው ወደ ፓርኩ የሚወስደው እንዲሁም ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበት መሆኑ እንስሳቶቹ እንዲበረግጉ ያደርጋል የሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው እንደገለፁት ለዚህ መንገድ አማራጭ የሚሆን ሌላ መንገድ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሠራ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለፓርኩ እየሠጠ ያለው ትኩረት መልካም ነው፡፡ ፓርኩ ለአገሪቷ ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ከፓርኩ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚመለከታቸውን አካላት የአካባቢውን ህብረተሰብ ጨምሮ ጥረት ማድረግ እንዳለበትና በፓርኩ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጐት ላላቸው ባለሀብቶች የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

በምሕረት አስቻለው

 
< Prev   Next >