Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Jan 08th
Home arrow Sections arrow "የላስቲክ ቤቴን ሕገ ወጥ...
"የላስቲክ ቤቴን ሕገ ወጥ... E-mail
Wednesday, 08 October 2008
Image"የላስቲክ ቤቴን ሕገ ወጥ ግንባታ ነው አሉኝ"

በታደሰ ገብረማርያም

ሥፍራው በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15/16 በሚገኘው አንድ መጠለያ ውስጥ ነው፡፡ በዚሁ መጠለያ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በመካከሉ ባለው ገላጣ ቦታ ላይ ደግሞ አንድ ሜትር በ50 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያላት የኘላስቲክ ቤት ለብቻዋ ቆማለች፡፡

የላስቲክ ቤቷ አሠራር በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የሚገኙ ቀይ ሕንዶች (ሬድ ኤንዲያንስ) የሚሠሩት ዓይነት ትኩል ይመስላል፡፡ መጠለያየው ውስጥ ገብተን የጠቅላላውን የቤቶች ሁኔታ በመገረም መንፈስ በመመልከት ላይ እንዳለን ከላስቲክ ቤቷ ውስጥ አጠር ያሉ ቀይ ሴት ወጣ ብለው በራፏዋ ላይ በመቆም ይመለከቱን ጀመር፡፡ እኛም እሳቸውን እሳቸውም እኛን በማየት ለጥቂት ደቂቃ ያህል ተፋጠን ቆየን፡፡

ሁለቱንም እጃቸውን አጣምረው ወደ ቆምንበት ቀረብ አሉና ጐንበስ ብለው እጅ ነሱን፡፡ አፀፋውን ትህትና በተሞላበት መንገድ መለስንላቸው፡፡ "ምን ልርዳችሁ?" ሲሉ ጠየቁን፡፡ ማንነታችንን ከገለጽንላቸው በኋላ "ታዲያ ምን ችግር አለ፡፡ ኑ ወደ ቤት ዝለቁና ቁጭ ብለን እንወያይ" አሉን የቀኝ እጃቸውን ወደ ላስቲኳ ቤት እያማተሩ፡፡ እኛም ሳናንገራግር ተከተልናቸው፡፡

የላስቲክ ቤቷ በጣም ጠባብ ነች፡፡ አንድ አልጋ ተዘርግቷል፡፡ የለሊትና የቀን አልባሳታቸው አልጋው ላይ ተከማችቷል፡፡ በስሩ ደግሞ የእሳት ጢስ ያጠቆራቸው ልዩ ልዩ ብረት ድስቶችና ሌሎች የምግብ ማብሰያዎች ተቀምጠዋል፡፡ በየጥጋጥጉም ትሪ፣ ጠርሙስ፣ ውሀ መያዣ . . . ተደራርበው ተደርድረዋል፡፡ ላስቲክ ቤቷ ሁለት ሰዎችን እንደቆሙ ትይዛለች፡፡ ለመቀመጥ ግን ጠባብ ስለሆነች አይቻልም፡፡ ለነገሩ ከአልጋው በስተቀር ሌላ መቀመጫ የለም፡፡ ላስቲኩ በፀሃይ ኃይል ስለጋለ በጣም ይወብቃል፡፡ መጥፎ ጠረንም አስከትሏል፡፡ "ይሄውላችሁ በዚች ላስቲክ ቤት ብርዱንም የፀሀዩንም ሙቀት እንደአመጣጡ እቀበላለሁ" አሉን መቀመጫ ቢጤ እየፈላለጉልን፡፡ የተፈለገውም መቀመጫ አልተገኘም፡፡ ላስቲኳ ቤት ደጃፍ ላይ ቁጢጥ ብለን ወጋችንን ጀመርን፡፡

ስምዎ ማን ነው?
"ውብ ዓለም አልጣ እባላለሁ"
ዕድሜዎ?
"አላውቀውም"
የት ነው የተወለዱት?
"ጎንደር ፋሲል ግንብ"
ወደ አዲስ አበባ መቼ መጡ?
"በደርግ ሥርዓት ወቅት"
ለምን መጡ?
"ባለቤቴ ስለሞተብኝና ሠርቼ ለመብላት ስለፈለኩ"
ላስቲክ ቤት ሠርተው ከመግባትዎ በፊት የት ነበር የሚኖሩት?

"የግል ቤት እየተከራየሁ እኖር ነበር፡፡ ኪራዩን አልችል ስላልኩ በመጠለያ ውስጥ ያሉትን ነዋሪዎች አስፈቅጄ የላስቲክ ቤት አቆምኩና ገባሁ፡፡ እዚህ ከገባሁም ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡

ምን እየሠሩ ነው የሚኖሩት?

"የቀን ሥራና ልብስ አጠባ እየሠራሁ ነው የምኖረው የቀን ሥራውን የማከናወነው በተለያዩ የሕንፃ ግንባታዎች ላይ ነው፡፡ እሱም ሲሚንቶ በሚጠፋበት ሥራው አልፎ አልፎ ይቆማል፡፡ ዕድሜዬ እየገፋ ስለሄደና ጤንነትም ስለማይሰማኝ የቀን ሥራውን እርግፍ አድርጐ ትቼ በልብስ አጠባው ላይ ብቻ ነው ያለሁት"

ስንት ጊዜ ሆንዎት የቀን ሥራውን ከተዉት?
"ስድስት ወራት አልፎኛል"
በቀን ምን ያህል ያገኙ ነበር?
"አሥር ብር"
ለልብስ አጠባ ስንት ነው የሚያስከፍሉት?

"እንደልብሱ ብዛትና አነስተኛነት እየታየ ነው፡፡ ብዙ ከሆነ አሥር ብር፡፡ ትንሽ ከሆነ ደግሞ አምስት ብር አስከፍላለሁ፡፡ ይኸውም ብዙ ጊዜ አይገኝም፡፡ አልፎ አልፎ ነው፡፡ ይኸውልህ ለቀለቤና ለሌላም ወጪዬ የማውለውን ገንዘብ እማገኘው በዘረዘርኩልህ ዓይነት ሥራ ላይ ደክሜ ነው"

ልጅ አለዉት
"የለኝም፡፡ ብቻዬን ነኝ"
ኑሮን እንዴት እየተቋቋሙት ነው?

"ኑሮ በጣም ከባድ ነው፡፡ ዘይቱ፣ በርበሬው፣ ሽሮው. . . . በጣም ውድ ስለሆነ ከተለያየን ስንበትበት ብሏል፡፡ ቅቤና ሥጋ እንኳን ልበላ ቀርቶ መልካቸው ወይም ዓይነታቸው ሁሉ ተረስቶኛል፡፡ ምን አባቱ" ሆድ እንዳሳዩት ነው፡፡ ስለሆነም ግድ የለኝም፡፡ አሁንማ ጦም መዋል ማደሩን ለምጄዋለሁ፡፡ ዕድሜ ለጎረቤቶቼ ዓመት በዓል ሲሆን ይጠሩኛል፡፡ እኔ ከሁሉም ያሰቃየኝና የተቸገርኩት የመኖሪያ ነገር ነው፡፡ እንደሰው ቤት ውስጥ ብኖር ደስ ይለኛል፡፡ ብርድ እምገላገልበት፣ ብታመም እምታመምበት ነው እምፈልገው እንጂ ሌላ ምንም አልፈልግም"

ለቀበሌ ችግርዎን ገልፀው ነበር?

"ሄጄ ችግሬን ገልጬላቸው ነበር፡፡ ጭርሱን ጥጋበኛ ነሽ አሉኝ፡፡ ሜዳ ላይ የወደቀ አለ፡፡ አንቺ ግን ሕገወጥ ግንባታ አካሂደሻል አሉኝ፡፡ እግዜር ይስጥልኝ ብዬ እያለቀስኩ ተመለስኩ"

ሕገ ወጥ ግንባታ ያሉት የቱን ነው?
"ይህችኑ የላስቲክ ቤት ነዋ" አሉን የተፈታታውን የፀጉራቸውን ሻሽ እያጠባበቁ
ሰው ቤት ለምን አይቀጠሩም?

"ከአገሬ እንደመጣሁ አብዛኛውን ኑሮዬን ያሳለፍኩት ሰው ቤት ተቀጥሬ ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ ዕድሜዬ እየገፋ ሲሄድ አንቺ አሮጊት ነሽ፡፡ ልናዝሽም ያስቸግረናል ማለት አመጡ፡፡ አስፔዛ አልቋል ያልኳቸው እንደሆነ እንዴ" አሮጊት አይደለሽም እንዴ? ከመቼው ያልቃል? በማለት ይጨቀጭቁኝ ነበር፡፡ ከዛም ወጣሁና ቤት ተከራይቼ መኖር ጀመርኩ፡፡ መቋቋም ስላልቻልኩ የላስቲክ ቤቷን ሠርቼ ገባሁ፡፡

ጎንደር ሄደው ዘመዶችዎን ጠይቀው ያውቃለ?
"ከመጣሁ ጀምሮ ሄጄ አላውቅም"
ለምን?

"ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ ከየት ላምጣ? በቃ እንደወጣሁ ቀረሁ፡፡ ከዘመድ ተለያየሁ፡፡ ለዕለት ጉርስ አጥቼ እየተሰቃየሁ ነው እኮ ያለሁት፡፡ በዚህ አቅሜ እንዴት አድርጌ ለመንቀሳቀሰ እችላለሁ፡፡ አሁንማ የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሯል፡፡ ችግሩ አድማሱን እያሰፋና እየተጠናከረ ነው የሄደው፡፡ ከድህነት ወለል በታች እየተባለ ሲወራ አልፎ አልፎ እሰማለሁ፡፡ እኔ ደግሞ የምለው ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ነው፡፡ የትም ክልል ቢኬድ እኮ መኖር አይቻልም፡፡ እዛም ችግሩና ድህነቱ አለ፡፡"
Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 )
 
< Prev   Next >