Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ኢትዮጵያውያኑ በአትሌቲክሱ...
ኢትዮጵያውያኑ በአትሌቲክሱ... E-mail
Wednesday, 08 October 2008

ኢትዮጵያውያኑ በአትሌቲክሱ የበላይነታቸውን እያረጋገጡ ነው

ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን እውቋ አትሌት ጌጤ ዋሚና ፀጋዬ ከበደ አሸንፈዋል፡፡ ኒውካስል ግሬት ኖርዝ ራን በሚል ስያሜ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአስገራሚ ብቃት ማሸነፋቸው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማሕበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) ዘገባ አመልክቷል፡፡

 

ከዓለም ምርጥ አስር አትሌቶች አንዷ የሆነችው ጌጤ ዋሚ በኒውካስል ግሬት ኖርዝ ራን ግማሽ ማራቶን ከኬንያዊቷ ኩንዚ እና እንግሊዛዊቷ ፓቬይ ብርቱ ፉክክር የገጠማት ቢሆንም ርቀቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ማይሎች እስኪቀሩ ድረስ ሦስቱም አንድ ላይ እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡

ውድድሩ ሊጠናቀቅ 400 ሜትር ሲቀረው አትሌት ጌጤ ኬንያዊቷን ኩንዚን አምልጣ በመውጣት 69 ደቂቃ 53 ሰከንድ አጠናቃ ማሸነፍ ችላለች፡፡ ሰዓቱም ጌጤ ቀደም ሲል ከነበራት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ በላይ አሻሽላ ማጠናቀቋ ታውቋል፡፡

አትሌት ጌጤ በቀጣዩ ወር በሚካሄደው ኒዮርክ ማራቶን ላይ ከእንግሊዛዊቷ የዓለም ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ፓውላ ራድ ክሊፍ ጋር እንደምትሮጥ ዘገባው አመልክቷል፡፡ አትሌቷ በቅርቡ በተካሄደው ቤጂንግ ኦሊምፒክ በማራቶን ተሳትፋ ሳይሳካለት መቅረቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ ቦታ በወንዶች በተደረገው ግማሽ ማራቶን የቤጂንግ ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ወጣቱ አትሌት ፀጋዬ ከበደ ርቀቱን 59 ደቂቃ 45 ሰከንድ አጠናቆ የወርቅ ባለቤት ሆኗል፡፡ ሁለተኛ በመውጣት ውድድሩን ያጠናቀቀው ሌላው ኢትዮጵያዊ ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ሲሆን፣ አሜሪካዊው አብዱርአህማን ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኑ ተነግሯል፡፡

በሌላ ዜና በስሎቫኪያ ኮሲክ ከተማ በተካሄደው ማራቶን አትሌት ደጀኔ ይርዳው ማሸነፉ ታውቋል፡፡

በ35ኛው የዓለም ሰላም በሚል በተካሄደው ማራቶን አትሌት ደጀኔ ይርዳው ሁለት ኬንያውያንን በማስከተል እንዳሸነፈ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዘገባ አመልክቷል፡፡ አትሌቱ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2፡10፡51 ሰከንድ እንደፈጀበት ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እሁድ በሚካሄደው የብራዚል ግማሽ ማራቶን ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ማታ ያመራል፡፡

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ቴክኒክ ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እሁድ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ በሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ማታ ወደ ስፍራው የሚያመራው በአትሌት ድሪባ መርጊያ መሪነት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በወንዶች አትሌት ድሪባ መርጊያ፣ አበበ ድንቄሳ፣ እሸቱ ወንድሙ፣ ጉዲሳ ሸንተማና ራጂ አሰፋ የሚወዳደሩ ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ በሚሳተፈው የሴቶች ቡድን ውስጥ በቤጂንግ ኦሊምፒክ በሴቶች ማራቶን የተቀነሰችው አትሌት ብዙነሽ በቀለ አለመካተቷ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በሴቶች ቡድን ውስጥ አትሌቷ ለምን እንዳልተካተተች በፌዴሬሽኑ በኩል እስከ አሁን የተሰጠ አስተያየት ባይኖርም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ "አትሌቷ ብቃቱ አላት፤ የፌዴሬሽኑን ድክመት በመናገሯ ብቻ እየተበደለች መሆኑን" ተናግረዋል፡፡

የሴቶች ቡድን አባላት አፀደ ሀብታሙ፣ አሰለፈች መርጊያ፣ ገነት ጌታነህ እና መሠረት መንግስቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
 
< Prev   Next >