Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Friday
Nov 21st
Home arrow Sections arrow በሁለት ተራራዎች ላይ...
በሁለት ተራራዎች ላይ... E-mail
Monday, 21 January 2008

በሁለት ተራራዎች ላይ የምርምር  ይቋቋማሉ

በሰሜንና በባሌ ተራራዎች ላይ በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮሩ የምርምር ጣቢያዎችን ለማቋቋም አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንደሚደረግ ዶክተር ጌጤ ዘለቀ በአፍሪካ የዓለም አቀፍ የተራራ ፕሮግራም ተወካይ፣ የከተማና የገጠር ግንኙነትና የአየር ንብረት ለውጥ አስተባባሪ ገለፁ፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት አድርጎ ከጥር 5 ቀን 2000 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ያህል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ አዳራሽ የተካሄደውን አውደጥናት አስመልክተው ዶክተር ጌጤ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳብራሩት ጣቢያዎቹን ለማቋቋም ጥረት የሚደረገው የዓለም አቀፍ የተራራ ፕሮግራምና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ሆነው መንግሥትን በማነጋገር ነው፡፡

ጣቢያዎቹ እንዴት እንደሚተከሉ፣ ምን ምን እንደሚያስፈልጋቸው፣ የትኛውን ዓይነት ምርምር እንደሚያካሂዱ፣ ጐን ለጐን የሚከናወነው ሌላው የምርምር ሥራ ምን እንደሆነ፣ ጣበያዎቹን በባለቤትነት ማን መያዝና ጥበቃውንም ማን ማካሄድ እንደሚገባው የሚገልፅ ዝርዝር መረጃ ለመንግሥትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ይቀርባል፡፡

በሁለቱም ተራራዎች ላይ የሚተከሉት እነዚሁ ጣቢያዎች ከአፍሪካና ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ለሀገሪቱ ብሎም ለአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ አላቸው፣ በተለይ በሀገራችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚወሰኑት የፖሊሲም ሆነ የልማት ውሳኔዎች በዕውቀትና በመረጃ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እገዛ ያደርጋሉ፡፡

እነዚህ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ሀሳቡ የመነጨው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ካምፓላ ኡጋንዳ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ስብሰባው ያተኮረው በአፍሪካ ተራራማ ቦታዎች ዙሪያ የአየር ንብረትን ለውጥ ጨምሮ አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ለውጥ (ግሎባል ቼንጅ) ጋር በማያያዝ ምን መደረግ አለበት? ምን ዓይነት ምርምርና ቅንጅት መካሄድ አለበት የሚለውን ለመመካከር ነበር፡፡

በምክክሩም ወቅት የታየው ክፍተት በኢትዮጵያ ተራራዎች ዙሪያ እየተካሄደ ያለው ምርምር የተበጣጠሰ ወይም በተፈለገው ደረጃ የደረሰ አለመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለሀገሪቱ የሚጠቅም፣ ከአፍሪካ ጋር የተያያዘ፣ በኋላ ደግሞ ከግሎባል ኔትወርክ ወይም የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ኔትወርክ ጋር የሚያያዝ ቢያንስ በሰሜንና በባሌ ተራራዎች ላይ ጣቢያዎቹ መቋቋም አለባቸው ከሚል ውሳኔ ላይ መደረሱን ከዶክተር ጌጤ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች (ተራራዎች) ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ያህሉን የያዙ ናቸው፡፡ የኢኮኖሚውም ምንጭ ከመሆናቸውም ሌላ በአየር ንብረት መዛባትና በተፈጥሮ ሀብት መራቆት ሳቢያ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ለዝቅተኛ ቦታዎች የውሀና የሕይወት ምንጮች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ ሱዳን፣ ግብፅ፣ በተወሰነ ደረጃ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ተራራማና ከፍተኛ ቦታዎች በሚፈሱ ወንዞች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፍ ጥቅምም አላቸው፡፡

እነዚህ ተራራዎች እየተራቆቱና የመሬት ክለቱ እየሰፋ በመሄዱ ሳቢያ በብዙ ወንዞችና ምንጮች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ እንዲያውም የሀርሚያና የአደሌ፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ ዙሪያ  ሐይቆች እየደረቁ ነው፡፡

ዶክተር ጌጤ እንዳብራሩት ኢትየጵያ ከፍተኛ የሆነ የዕፅዋትና የእንስሳት ሀብት አላት፡፡ ይህም ሀብት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በየጊዜው እየተመናመነ መጥቷል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መብዛትና የኢኮኖሚው መቀጨጭ የአየር ንብረት ለውጥንና የመሬት መራቆትን እያበዛው ይገኛል፡፡ በተለይ ዝናብ መቀነሱ ወይም አንዳንድ ቦታ ላይ መጨመሩ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ አለመዝነቡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ነው፡፡

የበልግ አምራች አካባቢዎች የበልግ ዝናብ በአብዛኛው በመቀነሱ ወይም ጊዜውን ጠብቆ ባለመምጣቱ ከምርት ውጭ እየሆኑ የመጡባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚወሰደው የፖሊሲ እርምጃ በተቻለ መጠን ረጅም ይዘት ወይም ዘላቂነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በዳበረ ዕውቀት ወይም በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ግድ ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ለአካባቢ መራቆት በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የኃይል ምንጩን በዕፅዋት፣ በእንጨት፣ በሰብል ቅሪትና በኩበት ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ያሉት ዶክተር ጌጤ ይህም በጭሰና በሌላም ለአካባቢ ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ እያደረገ የሚሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ኔትወርክ ዩኒቨርሲቲዎችንና የምርምር አካላትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መጠናከር እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ለጥንካሬውም መንግሥት በሀሳብና በፋይናንስ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከምርምሩ ጋር ተቀናጅተው የሚሄዱበት የሚነጋገሩበትና ከምርምሩ የሚገኙ ውጤቶችም በሥራ የሚተረጎሙበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባቸዋል፡፡

ግሎባል ማውንቴን ፕሮግራም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በደቡብ አፍሪካ የዊትወተርስራንዳ (ዊትዋተርስራንድ) ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካ ቀንድ የአካባቢ (ኢንቫይሮንመንት) ማዕከልና ኔትወርክ ተባብረው ባዘጋጁት በዚሁ አውደጥናት ላይ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርት፣ ባብዛሕ ሕይወትና በሀይድሮሎጂ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ፣ የኢነርጂ አጠቃቀምና የአየር ንብረት ለውጥ፣ እንዲሁም በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥና የአፍሪካ ልማት፣ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ (ኢንቫይሮመንት) ምርምር እንቅስቃሴና በሌሎችም ተዛማጅ ርዕሶች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ በጽሁፎቹም ተንተርሶ የቡድን ውይይት ተካሂዷል፡፡

በታደሰ ገብረማሪያም

 
< Prev   Next >