Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "ለአገራችን ከ17 ዓመት በኋላ...
"ለአገራችን ከ17 ዓመት በኋላ... E-mail
Wednesday, 08 October 2008

Image"ለአገራችን ከ17 ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ሻምፒዮና ነው"
አቶ ታምራት በቀለ፣ የጽ/ቤት ኃላፊ

የምሥራቅ አፍሪካ ክለቦች የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ከጥቅምት 18 እስከ 22 ቀን 2001 ድረስ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ስፖርትና ትምህርት ማዕከል ይካሄዳል፡፡ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ይሳተፋሉ፡፡ በሻምፒዮናውና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ታምራት በቀለን አነጋግረናቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- ቅርጫት ኳስ በኢትዮጵያ ደረጃው ምን ይመስላል?

አቶ ታምራት፡-
የቅርጫት ኳስ ስፖርት በአገራችን መዘውተር የጀመረው ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ መዛግብቶች ይነግሩናል፡፡ ስፖርቱን፣ በርካቶች ያዘወትሩታል፡፡ ተወዳጅም ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፌዴሬሽኖች በአዲስ መልክ ተዋቅረው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ የእኛም ፌዴሬሽን እንደ አንድ አገር ብሔራዊ ፌዴሬሽን በእንቅስቃሴው ውስጥ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የቅርጫት ኳስ ምስረታና እድገቱ አይመጣጠንም፡፡ እንዲያውም የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንጂ፣ ስፖርቱ የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡-

አቶ ታምራት፡-
እንደዚህ ለማለት እንኳ አያስደፍርም፡፡ ስፖርቱ በአገሪቱ ውስጥ በተለይ በከተሞች አካባቢ በስፋት እየተዘወተረ ነው፡፡ ይኸው እንቅስቃሴ ከከተሞች አልፎ መላ አገሪቱን እንዲሸፍን ፕሮጀክቶች በመዘርጋት ላይ ናቸው፡፡ በተጠናከረ መልኩ ሊካሄድበት ይገባል በሚል በተለይ ከ2001 ጀምሮ በርካታ የስልጠና ጣቢያዎችን በትምህርት ቤት ደረጃ እንዲቋቋሙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በሚቀጥለው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የኢትዮጵያን ቅርጫት ኳስ ቡድን ለማሳተፍ፣ ለዝግጅቱ የአሰልጣኞች ምርጫ እያካሄድን ነው፡፡ በተለይ ተተኪ ወጣቶች የሚገኙት ክልሎች ላይ ስለሆነ፣ ክልሎችን ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው አገር አቀፍ ሻምፒዮና በርካታ የክልል ወጣቶች ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ውጤቱም አበረታች ነበር፡፡ እነዚህን ወጣቶች በማዕከል ደረጃ አሰባስቦ ስልጠና ለመስጠት እቅድ ተይዟል፡፡ ከጥቅምት 18 እስከ 22 የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና አገራችን በመሆኑ ቢያንስ ከወንድ ሶስት ከሴት ሶስት ቡድኖችን ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ የዞን አምስት አገሮች ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ኬንያ ላይ ይካሄዳል፡-

አቶ ታምራት፡-
ቀኑ መቼ እንደሆነ አልታወቀም እንጂ ሻምፒዮናው እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሻምፒዮናም ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በአገራችንም ሆነ ኬንያ በሚካሄደው ሻምፒዮና፣ ተሳትፎ የምናደርገው በወጣቶች ብቻ ይሆናል፡፡ ይህን የምናደርግበት ዋናው እቅዳችን በ10ኛው መላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ከዞናችን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን ለመቅረብ ነው፡፡ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በቅርቡ የአሰልጣኞች ስልጠና አካሂዷል፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ አራት አሰልጣኞቻችን ተሳትፈዋል፡፡ ስለዚህ ስፖርቱ አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስፖርቱ በአገሪቱ እንዲስፋፋ የክለቦች መበራከት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ያህል ክለቦች አሉ?

አቶ ታምራት፡-
በአዲስ አበባ ከ34 በላይ ክለቦች አሉ፡፡ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ (በቡድን ደረጃ"፣ ሐረርና በሌሎችም ከተሞች በርካታ ክለቦች እየተሳተፉ ነው፡፡ በእርግጥ ስፖርቱ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል እየተዘወተረ ቢሆንም ዘልቆ አልገባም፡፡ ይህንን ለማጠናከር በትምህርት ቤቶች የምንዘረጋቸው ፕሮጀክቶች አስተዋጽኦ አላቸው ብለን እናስባለን፡፡ ሌላው ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በተለይ በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው ኦሊምፒክ የተገኘውን ውጤት መነሻ በማድረግ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ለፌዴሬሽኖች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡ በእኛ በኩል በጥናት ላይ የተመሰረተ ፕሮጀክት እየተሰራ ነው፡፡ ይህ በሥራ ላይ ከዋለ ቢያንስ ከሶስትና አራት የማያንሱ የስልጠና ማዕከላት ይኖሩናል ብለን እናስባለን፡፡ በእነዚህ ማዕከላት ወጣት ሴትና ወንዶች በአዳሪነት ገብተው ስልጠናውን የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ እንደሌሎቹ የምሥራቅ አፍሪካ ቡድኖች የእኛም ቡድኖች ጠንካራ የማይሆኑበት ምክንያት ስለሌለ ለተግባራዊነቱ ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የቅርጫት ኳስ ስፖርት አለ፣ ወይም በእንቅስቃሴ ላይ ነው፣ የሚያስብለው በኢንተርናሽናል ደረጃ እንኳ ባይሆን በአገር ውስጥ ስፖርቱ ደጋፊ ሲኖረው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰራን ማለት ትችላላችሁ?

አቶ ታምራት፡-
እንደተባለው እንቅስቃሴው በተጠናከረ መልኩ ነው ባይባልም፣ አለ፡፡ በእርግጥ በቂ ደጋፊ የለውም፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ለማቅረብ ጊዜው ባይሆንም ማንሳት ይቻል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በ1940ዎቹና ከዚያ ወዲህ በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪዎች እንደነበሩ ነው የሚነገረው፡፡ አሁን ግን ያ ሁኔታ የለም፡-

አቶ ታምራት፡-
ቀደም ሲል ስፖርቱ ይዘወተር የነበረው በአብዛኛው በሰራዊቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ በሚቋቋሙ ቡድኖች ነበር፡፡ ያ ሁኔታ አሁን አይስተዋልም፡፡ ለምን፣ የራሱ ሂደት ስላለው ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ከውድድሩ ስፋት አንፃር በዞን ደረጃ ሁሉ ይደረግ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከስርዓቱ ለውጥ በኋላ የሠራዊቱ ቡድኖች ፈረሱ፡፡ ከዚያም ክለቦችንና ቡድኖችን መያዝ የሚችሉ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች በመጥፋታቸው ስፖርቱ እየቀዘቀዘ መጣ፡፡ ነገር ግን ከአራትና አምስት ዓመት ወዲህ በርካታ ድርጅቶች ክለቦችን እያቋቋሙ በመሆኑ፣ የክልል ከተሞችን ጨምሮ አመቱን ሙሉ ውድድሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ አመታዊ የፕሮጀክት ውድድሮችን ክረምት፣ ክረምት እናደርጋለን፡፡ የአዋቂዎች ውድድርም በአመት አንድ ጊዜ እናደርጋለን፡፡ የክለቦችንም እንደዚሁ እያካሄድን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ውድድሩን የስፖርት ቤተሰሰቡ እንዳይከታተላቸው ችግሩ ምንድ ነው?

አቶ ታምራት፡
- እዚህ ላይ የእኛም ድክመት እንዳለ እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱን የስፖርት ቤተሰቡ እንዲከታተለው ከሚዲያ ጋር ተቀናጅተን ያለመስራታችን ነው፡፡ ሁኔታውን ለማስተካከል ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በአገራችን የቅርጫት ኳስ ስፖርት እንደሌሎቹ ስፖርቶች አይደለም፡፡ በአብዛኛው የሚዘወተረው በምዕራባውያኑ ዘንድ ቢሆንም፣ በተለይ ኮሚዩኒቲ ስኩል በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ስፖርቱ የመጀመሪያ ተመራጭ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ስፖርቱን የሚያዘወትሩ ወጣቶች በክለብ ደረጃ እንዲዋቀሩ መንገዶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ ወደ ቀድሞ ስሙ ብቻም ሳይሆን በተሻለ ደረጃ ስፖርቱን ለማስፋፋት ሁኔታው እየተመቻቸ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የተለያዩ ስፖርቶችን ለማስፋፋት በ1989 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 54 የሚጠጉ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ተቋቁሞ ነበር፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ?

አቶ ታምራት፡-
በፕሮጀክቶቹ እስከ አሁን ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሰልጣኞች ሰልጥነው ወጥተዋል፡፡ አሁን በቡድንና በክለብ ደረጃ፣ በተጨማሪም በትምህርት ቤት ደረጃ ወጣቶችን እንዲያሰለጥኑ እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይስ ምን የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ታምራት፡-
በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናከረ መልኩ ለመሄድ የገንዘብ አቅማችን ቢወስነንም፣ በቀጣይ ግን ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ስፖርቱን ከሚረዱ ድርጅቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር የተሻለ ሥራ እንሰራለን ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በየትኛውም የአገሪቱ የስፖርት ዘርፍ እንደምክንያት የሚነሳው የገንዘብ አቅም ነው፡፡ ዋናው ችግር ግን የገንዘብ አቅም ሳይሆን የሲስተምና አፈፃፀም መሆኑ የሚስማሙ አሉ፡-

አቶ ታምራት፡-
ሲስተም ሲባል እንዴትና ምን ዓይነት የሚለውን አሁን ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ ሲስተምን በአደረጃጀት እንመልከተው ከተባለ ግን፣ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አደረጃጀት ሕዝባዊ መሠረት የያዘ ነው፡፡ መንግሥት የበጀት ድጋፍ ይሰጣል፣ ቢሮ ይሰጣል፣ ሰራተኛ ይመድባል፡፡ የማዘውተሪያ ስፍራም ፌዴሬሽኖች በጋራ እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ስፖርቱን የሚወዱ የግል ድርጅቶችም የተለያየ እገዛ እያደረጉ ነው፡፡ ክለቦችን በማቋቋም ማለት ነው፡፡ ክልሎችም እንደዚሁ ስፖርቱን ለማስፋፋት ፈንድ እያደረጉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የሲስተም ችግር እንደሌለ የሚገልፁ ይመስላል፡-

አቶ ታምራት፡-
አዎን፡፡ ምክንያቱም ችግሩ የሲስተም ሳይሆን ሲስተሙ ስፖርቱን ኮሜርሻላይዝ እንዲያደርግ አልተደረገም፡፡ ስፖርቱን ወደ ገበያ ማስገባቱ ላይ ነው፡፡ በአደጉ አገሮች ቅርጫት ኳስ ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ሆኗል፡፡ ይህን በአገራችን እንዲፈጠር ማድረጉ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሲስተም ሲባል እነዚህን አያጠቃልልም?

አቶ ታምራት፡-
በእርግጥ ያጠቃልላል፡፡ ምክንያቱም ሲስተሙ ስፖርቱን ወደ ገንዘብ የሚለውጥ የንግድ ማዕከል ሊሆን ይገባል፡፡ በርካታ የግል ድርጅቶች በስፖርቱ እንዲሳተፉ እየተደረገ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ ምንድ ነው?

አቶ ታምራት፡-
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት አልተሰሩም፡፡ በእኛም ሆነ በክልሎች የዚህ ችግር አለ፡፡ በዚህ በኩል በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በተለይ ከብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች ጋር በመገናኘት ጠንካራ ሥራ መስራት እንዳለብን እናስባለን፡፡ እንቅስቃሴውንም አንድ ብለን ጀምረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽናችሁ ሙያተኞችን ለማፍራት ምን እያደረገ ነው?

አቶ ታምራት፡-
በአመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ውድድር ያደርጋል፣ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ይሰጣል፣ ክልሎችን ይደግፋል፣ የክልሎችን አቅም የማጎልበት ሥራ ይሰራል፣ በፌዴራል ደረጃ ዳኞች ያፈራል፣ ኢንተርናሽናል ዳኞች አሉ፡፡ ተጨማሪ እንዲኖሩ እድሉን አመቻችቷል አያመቻችም ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ቅርጫት ኳስ ስፖርት ከአገር ውስጥ ባለፈ ኢንተርናሽናል ደረጃው ምን ይመስላል?

አቶ ታምራት፡-
በየዓመቱ በተለያዩ ኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ አገራችን ትሳተፋለች፡፡ እዚህ ላይ የእኛም ድክመት ሊሆን ይችላል፣ የሚደረጉ ውድድሮችን እየተከታተልን ለስፖርት ቤተሰቡ አልገለጽንም፡፡ ባለፈው ዓመት በኢንተርናሽናል ደረጃ የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ክለብ ተሳትፎ፣ ከተካፈሉት ስምንት የዞኑ አገሮች አራተኛ ወጥቶ አበረታች ውጤት አስመዝግቦ ተመልሷል፡፡ ከዚያ በፊት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን ሩዋንዳ ላይ ተሳትፎ እንደዚሁ አበረታች ውጤት አግኝቶ ተመልሷል፡፡ እንደዚሁም በ1999 ዓ.ም አኖካ በተባለ ሻምፒዮና ላይ በወንዶች ተካፍለን ጥሩ ውጤት አግኝተናል፡፡ ውድድሩ የተካሄደው ናይሮቢ ላይ ነበር፡፡ ይህንን የስፖርቱ ቤተሰቡ ያውቀዋል? እርግጠኛ አይደለሁም፣ አሁንም በሌለን አቅም የምሥራቅ አፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ለማዘጋጀት ስንወስን፣ ስፖርቱ በስፖርት ቤተሰቡ እንዲሰርጽ ነው፡፡ እግረ መንገዱን የቅስቀሳ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ወደ አገራችን የሚመጡ ወደ 12 ክለቦች አሉ፡፡ የእኛ ስድስት ሲሆኑ፣ ሦስት ወንድና ሦስት ሴት ክለቦቻችን ይሳተፋሉ፡፡ እውነት ነው፡፡ በዘጠነኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ማጣሪያ ማለፍ ሳንችል ቀርተን፣ አልተሳተፍንም፡፡

ሪፖርተር፡- በጀታችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ታምራት፡-
ዓመታዊ በጀቱ በአሁኑ ሰዓት 105 ሺህ ብር ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከመንግስት ካዝና የተመደበ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በአሁኑ ሰዓት የምንገኘው የስፖንሰሮች ድጋፍ እንዳለ ሆኖ፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይደጉመናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ድጎማ ይደረግላችኋል?

አቶ ታምራት፡-
ትክክለኛውን ቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ እንደ ሁኔታው ሊለያይ ስለሚችል ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጥቅምት 18 እስከ 22 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ የምሥራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና በአገራችን ይካሄዳል፡፡ ከወጭው ጀምሮ እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው?

አቶ ታምራት፡-
ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ችግሮች ይኖራሉ በሚል እንደነዚህ ያሉ ሻምፒዮናዎችን የማዘጋጀቱ እድል ስናገኝ ወደኋላ የምንልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም፣ ሻምፒዮናው የአገራችንን መልካም ገጽታ የምናስታውቅበት እስከሆነ ድረስ እንደቀድሞ ሁሉ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴንና ስፖንሰሮችን በማፈላለግ ሻምፒዮናውን በተሳካ ለማከናወን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌላው እንደዚህ ያለ ሻምፒዮና ከየካቲት ወር 1983 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ አጋጣሚውን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ በቅርጫት ኳስ ማለት ነው፡፡ በ17 ዓመት ታሪክ ውስጥ፣ ምንም ዓይነት ኢንተርናሽናል ውድድር አለመካሄድ ማለት ቀደም ሲል እንደተነሳው ጥያቄ የስፖርት ቤተሰቡ ስፖርቱን እስከ መኖሩ እንኳ ሊጠራጠር ስለሚችል፣ ይህን መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት ግድ ነው፡፡ ከስፖንሰሮች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ ጁፒተር ሆቴል የተቻለውን ሁሉ አያደረገልን ነው፡፡ ከሌሎችም አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሻምፒዮናው ኮሚቴ ተቋቁሟል፡-

አቶ ታምራት፡-
ሁሉም የኮሚቴ አባላት እጅግ የተጠናከረ ሥራ እየሰሩ ናቸው ባንልም፣ ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች የስፖንሰር ሺፕ፣ የመስተንግዶ፣ የፀጥታ፣ ሎጂስቲክ (አቅርቦት) ኮሚቴዎችና ሌሎችም ተቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሳተፉትን አገሮች ዝርዝር ቢገልፁልን፡-

አቶ ታምራት፡-
ወደ ስምንት የሚጠጉ አገሮች ይሳተፋሉ፡፡ ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፣ ከውጭ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ጅቡቲና ታንዛኒያ እንደሚሳተፉ አሳውቀዋል፡፡ ከውጭ 12 ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ሦስት በወንዶችና ሦስት በሴቶች ተሳትፎ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ክለቦች ኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች፣ ኢትዮ-ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ቴስቲስ ቦለር በወንዶች፣ የሚሳተፍ ሲሆን፣ በሴቶች ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ፣ ኢትዮ-ኢንቨስትመንት ግሩፕና ቪጅአይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና በአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ኮንፌዴሬሸን ትብብር እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡ የኮንፌዴሬሽኑ እገዛ ይኖራል?

አቶ ታምራት፡-
የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ገዛ ሳይሆን የሚያደርግልን ገንዘብ ያስከፍለናል፡፡ እንደ አገር በማዘጋጀታችን ብቻ 4ሺህ ዶላር እንከፍላለን፡፡ ምክንያቱም ሻምፒዮና እስከተባለ ድረስ እኛ ከውድድሩ እንደተጠቃሚ ተደርገን ነው የምንታየው፡፡
Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 )
 
< Prev   Next >