Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የተወካዮች ምክር ቤት መወከል...
የተወካዮች ምክር ቤት መወከል... E-mail
Wednesday, 08 October 2008

የተወካዮች ምክር ቤት መወከል
የማይችለውን ጉዳይ እንዳይወክል"


በ1997 ዓ.ም ምርጫ ውጤት መሰረት የተቋቋመው የሶስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአራተኛ ዓመት የስራ ዘመን በይፋ የተጀመረው ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፍቻ ንግግር አማካኝነት ነው፡፡ የዚህ ንግግር ፋይዳ እንደሚታወቀው የመንግሥትን የዚህ ዓመት እቅድ ማመላከት ያለበት መሆኑ ነው፡፡

 

ፕሬዚዳንቱ ሁለቱ ምክር ቤቶች "ባለፉት ዓመታት ለዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ሥርዓት መጠናከር የሚበጁ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን" የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገመንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ለኢኮኖሚያችን እድገት ለዴሞክራሲያችን መጎልበትና ለሰላማዊና ሕጋዊ ሥርዓታችን መዳበር የሚበጁ ልዩ ልዩ አዋጆችን ማውጣቱን ገልፀው የዚህን ዓመት የስራ ዘመን እቅድ በተለይም የተወካዮች ምክር ቤትን "የሕግ ማውጣት መርሃ ግብርን ዘርዘር አድርጎ ማቅረብ" አስፈላጊነት አስገንዝበው ይህንኑ አስፈላጊነት ያሟላል ያሉትን ዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሰረት "በያዝነው ዓመት ሁለቱም ምክር ቤቶች እንደሚያከናውኗቸው የሚጠበቁት ተግባራት ከያዝነው አጠቃላይ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዞ የፈለቁ" መሆናቸውን ገልፀው በልማቱ (ኢኮኖሚው) መስክ በማህበራዊው ዘርፍ እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር አኳያ ለምክር ቤቱ ቀርበው የሚፀድቁ ወይም ይፀድቃሉ ተብለው የሚጠበቁ የረቂቅ ሕጎችን ዝርዝር አሳውቀዋል፡፡

"በልማቱ መስክ ከምናደርገው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ግብ እንደሆነ" የሚታወቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ በዚህ መሰረት "መንግሥት የሕዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥማት ለማርካት የሚያስችል ፕሮግራም ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለመቀጠል" እንደተዘጋጀ አስረድተው "ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ በያዝነው ዓመት መልካም አስተዳደርን ለማጎልበት አስተዋፅኦ ያላቸው ልዩ ልዩ ሕጎች ለተከበረው ምክር ቤት እንዲቀርቡ ይደረጋል" በማለት በዚህ ረገድ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል፡፡ እዚህ የመጀመሪያ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሁሉ ደግሞ (ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከፀደቀው ከፕሬስ ህጉ እና አሁን በምትኩ ከተጨመረው አማራጭ የክርክር መፍቻ ስርዓት ከተባለው በስተቀር) በፕሬዚዳንቱ የ2000 ዓ.ም የመክፈቻ ንግግር ውስጥ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡

ከሁሉም ይበልጥ እያደረ አስገራሚ እየሆነ መምጣቱ ያልቀረው የዚህ ጽሁፍም ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በፕሬዚዳንቱ የ2001 ዓ.ም የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር አማካኝነት የሚለውን እንመልከት "አገራችን የተያያዘችውን የልማትና የመልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት በየጊዜው ሁኔታው የሚጠይቀውን ለውጥና ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በዚህ መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአገራችን እድገት መጫወት ያለበትን ሚና በጥቂት እንዲጫወት"". በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ የሚቋቋም እንደሚሆን የሚገልጸው የመንግሥት የዚህ ዓመት የሕግ ማውጣት መርሀ ግብር "በተመሳሳይ መልኩ የመረጃና የኮሚውኒኬሽን አገልግሎት በብቃት ለማስፋፋት የሚዲያ እድገትን ብዙሃዊነት በማረጋገጥ ዘርፍ ለአገራችን እድገት ተገቢውን አስተዋፅኦ ያበረክት ዘንድ አሁን ያለው የማስታወቂያ ሚኒስቴር አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ይላል፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ የመንግሥት አስፈላጊ አካላት አደረጃጀትን የተመለከተ ሌላም ተጨማሪ ጉዳይ እንደሚኖር የዘንድሮው የመንግሥት መርሃ ግብር የሚገልጸው አለ፡፡ በዝርዝሩ በቂ በይዘቱ ብዙ የተፍታታ አይደለም እንጂ የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር የመንግሥት የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት በተለይም የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አሁን ስራ ላይ ያለው አዋጅ የሚሻሻልበትን ምክንያት እንደሚከተለው ይገልጻል፡፡

"በተጨማሪም ከሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊነት ጋር ተያይዞ የመንግሥት አመራርና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ የመንግሥት አደረጃጀት ለውጦች በሚያስፈልጉበት ጊዜ መንግሥት የተቀላጠፈ አሰራር እንዲከተል ማድረግ ይቻል ዘንድ ያስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር የሚወስነውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም በነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ለተከበረው ም/ቤት እንዲቀርቡ ይደረጋል" ይላል፡፡

ከዚህ በመነሳት የኢፌዴሪን አስፈጻሚ አካለት ሥልጣንና ተግባር እና ወይም አደረጃጀታቸውን ለመወሰን በየጊዜው እየተሻሻሉ ከወጡት ከሚወጡት ሕጎች አንጻር እና እዚያ ውስጥ ብቻ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄና ጉዳይ በዚያው ልክ አጠቃላይ የሆነው የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ጉዳይ ምነው ሁልጊዜ የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ በዚያ ማሻሻያ መሰረት የተመደበው በጀትና የበጀት ዓመቱ ሳያልቅ ደግሞ እንደገና "በአረም የምንመለስበት" የማደራጀት ስራ እየደጋገመ አላባራ እያለ አስቸገረን? የሚለው ነው፡፡

ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁና የሚከታተሉት ያንን ያህልም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እንደሚረጋግጡት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ብቻ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ አስር ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ ይህ የአስፈጻሚ አካላት አባላት ወይም ተጠሪነታቸው ለካቢኔው የሆኑ የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከዚህ የሕግ ማዕቀፍ ውጭ የተቋቋመበት ሕግ የተሻሻለበትንና የዚያን ድግግሞሽ ሳይጨምር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊው ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው የመጨረሻውና አሁን በስራ ላይ ያለው ሕግ መስከረም 1998 ዓ.ም ለ3ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያው ዓመት የስራ ዘመን ውስጥ ገና አንድ "ሀ" ተብሎ ስራ ሲጀምር ነው፡፡ የምርጫ 97 ውጤትን ተከትሎ ለተቋቋመው ለሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ምክር ቤቱም ከሚኒስትሮች ሹመት ጋር ተቀብሎ ያፀደቀው፡፡ ይህ ሕግ መጀመሪያ በ1987 ዓ.ም አስራ አምስት የነበሩትን፣ በ1994 ዓ.ም ደግሞ ወደ 18 ከፍ ያሉት እንደገና ደግሞ የገጠር ልማትና የግብርና ሚኒስትሮች እንዲወርዱ ሲደረግ 17 የነበሩት የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ወደ ሀያ ከፍ ያደረገ የተጠሪነትን የስያሜ ለውጥና የሥልጣንና ተግባር ሽግሽግን ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሰረት ከ1987 ዓ.ም ማለትም ከአዋጅ ቁጥር 7/87 ጀምሮ በየጊዜው የወጡ አስፈጻሚው አካላት በርካታ ማሻሻያ አዋጆችን ጨምሮ የሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የየብቻ ማቋቋሚያ አዋጆች ተሽረዋል፡፡ መብትና ግዴታዎች ተላልፈዋል፡፡ ይህ የሆነው በ1998 ዓ.ም ነው፡፡ በሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን እንደተለመደው በፕሬዚዳንቱ የፖሊሲና የሕግ ማውጣት መርሀ ግብር ንግግር አማካኝነት ሲከፈትና ሲጀመር በዚያ የመስከረም 29/1999 ዓ.ም ንግግር የተባለው፤

"ምክር ቤቱ በያዝነው ዓመት ትኩረት ሰጥቶ ከሚያወጣቸው ሕጎች መካከል በአገራችን የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለማጎልበትና መልካም አስተዳደሩን ለማስፈን የሚያስችሉ ሕጎች በቀዳሚነት" እንደሚጠቀሱ "".ከዚህ መሰረታዊ ግንዛቤ በመነሳት አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን በአመለካከት በአሰራር በአደረጃጀት ለማስተካከልና ለተፋጠነ ልማትና ለተሟላ መልካም አስተዳደር ብቁ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ተብሎ የታመነበትን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም በያዝነው ዓመትና በተጠናከረ አኳኋን" እንደሚቀጠልበት፤

"ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ በተካሄደ ጥረት ከሞላ ጎደል የሁሉም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ተልዕኮና አደረጃጀት ምን መሆን እንዳለበት የተሻለ ግንዛቤ" መያዙን፤

"አሁን ያለው የመስሪያ ቤቶቹ ተልዕኮና አደረጃጀት አስፈጻሚ አካላቱ ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ የተሟላ ሆኖ ባለመገኘቱ የመስሪያ ቤቶቹን ተልዕኮና አደረጃጀት መድረኩ የሚጠይቀውን ባህርይ እንዲይዝ አድርጎ ማስተካከል" እንደሚገባ "ለዚህም ሲባል የአስፈጻሚ አካላቱን የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ አስፈላጊ ሆኖ" መገኘቱን የገለጸው የ1999 ዓ.ም የፕሬዚዳንቱ ንግግር ነው፡፡ ለሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን መጀመሪያ ላይ ያቀረበውን የአገር ወይም የመንግሥት ይፋዊ የሕግ ማውጣት መርሀ ግብር ነው፡፡

በፕሬዚዳንቱ የ1999 ዓ.ም አመታዊ "የሕግ ማውጣት መርሀ ግብራችን ዝርዝር" ውስጥ "በዚህ መሰረት በያዝነው ዓመት የበርካታ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን ተልዕኮና አደረጃጀትን በአዲስ መልክ የሚወስኑ የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያዎች ለምክር ቤቱ ቀርበው እንደሚፀድቁ ይጠብቃል፡፡ አዋጆቹ የአስፈጻሚ መ/ቤቶችን የማስፈጸም ብቃት ከፍ የሚያደርጉና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉን መሆናቸው ምክር ቤቱ በሚገባ መርምሮ እንደሚያፀድቃቸው እምነቴ የፀና ነው" መባሉን አንዘነጋም፡፡ የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ከዚህ አንጻር አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን በአመለካከት በአሰራርና በአደረጃጀት ለማስተካከልና ለተፋጠነ ልማትና ለተሟላ መልካም አስተዳደር ብቁ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ተብሎ ስለታመነበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ስለምናውቀው "በተጠናከረ አኳኋን ይቀጠልበታል" ብለው አጠቃልለው ከገለጹት "የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም" ውስጥ በተለይ ስም ጠርተው ለይተው የተናገሩት የአንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጉዳይ ነበር፡፡ ይህም በ1999 የመስከረም 29 ንግግራቸው የማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተልዕኮና አደረጃጀት ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ያሉት ነው፡፡

እንደተባለውም በሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን የመጀመሪያው (ወይም የመጀመሪያዎቹ) መደበኛ ስብሰባ የፀደቀው የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ሕግ ከዚያ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻሻለው ነሐሴ 15 ቀን 1999 ዓ.ም የፀደቀው የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን የዚያን የ1998 ሕግ ድንጋጌ ለማሻሻል ብቻ በታወጀው አዋጅ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ማስታወቂያ ሚኒስቴር "ተልዕኮና አደረጃጀት ምን መሆን እንዳለበት የተሻለ ግንዛቤ ተይዟል" ተብሎ የዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት "ተልዕኮና አደረጃጀት መድረኩ የሚጠይቀውን ባህሪ እንዲይዝ አድርጎ" ተሰተካከለ ተብሎ (ይህ በፕሬዚዳንቱ የ1999 ዓ.ም የመክፈቻ ንግግር ቋንቋ ነው) ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባር ተሻሻለ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ማቋቋሚያ ሕግ ተሻረ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አካል ሆነ፡፡

የማስታወቂያ ሚኒስቴር በምክር ቤቱ ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን መጨረሻ ላይ የወጣውን የዚህ መስሪያ ቤት "ተልዕኮና አደረጃጀት ምን መሆን እንዳለበት የተሻለ ግንዛቤ ተይዞ የታወጀውን ሕግ አንድ ዓመት ብቻ ከ"ሰራበት" በኋላ እንደገና ደግሞ ሊሻሻል ነው የተባለው አሁን 2001 መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ "አሁን ያለውን የማስታወቂያ ሚኒስቴር አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" የተባልነው፡፡ ራሱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከተሻሻለው የ1999 ዓ.ም (መጨረሻ) አዋጅ በኋላና ከአዲሱ ከተባለው ተልዕኮና አደረጃጀቱ አኳያ ገና "የጫጉላ" ጊዜውን አጣጥሞ ሳያውቀውና ሳይሰራበት ነው፡፡

የሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአራተኛው ዓመት የስራ ዘመን ዓመታዊ መርሀ ግብር ወይም የ2001 ዓ.ም የፕሬዚዳንቱ ንግግር የማስታወቂያ ሚኒስቴር አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በማለት ብቻ አልተወሰነም፡፡
አገራችን የተያያዘችውን የፈጣን ልማትና መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት በየጊዜው ሁኔታውን የሚጠይቀው ለውጥና ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ይታመናል"ም ይላል፡፡

ይህ ሁለተኛው ተመልሰን በአጭሩ የምንመለከተው ጉዳይ ቢሆንም እስካሁን የተመለከትነው የመጀመሪያውንና "የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት በየጊዜው ሁኔታው የሚጠይቀው ለውጥና ማሻሻያ የማድረግ ጥያቄ በእጅጉ ቅጥ ያጣ ከመሆን በላይ ያለፈ ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም መጨረሻ ያለውን ሳይጨምር እያንዳንዱ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤት ለየብቻው የሚመለከቱ ሕጎችን ሳያካትት በየጊዜው የተደረገው "ሁኔታው የሚጠይቀው ለውጥ" የሕግ ማውጣት መርሀ ግብርና እቅድ በጭራሽ ለእቅድ የማይመች ነው፡፡ በየዓመቱ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላ ሲካሄድ የቆየው ለቁጥር የሚያታክት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ለአስፈጻሚ አካላቱ "ሪከርድ" እንኳን የማይመች የአደረጃጀት ለውጥ ሕግ አንቅቶ (አመንጭቶ) የሚያቀርበውም ሆነ ሕግ የሚያወጣው ፓርላማ "ሽርሽር" ሆኖ ቆይቷል፡፡ አንድ አደረጃጀት በጭራሽ ዘለዓለማዊ ባይሆንም አለመረጋጋትን በእቅድ መስራት እስኪከለክል ድረስ በየቅፅበቱ የሚቀያየር መሆን የለበትም፡፡

ነባሩና ያለፈው ተደጋጋሚ ሙከራችን ሁሉ ያልተሳካለት መሆኑን የሚያሳጣው አሰራር አልበቃ ብሎ ትርጉሙና ዝርዝሩ በውል ባይታወቅም ሌላው "".የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" የተባለበት አዝማሚያና አንደምታም ይበልጥ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህም "የመንግሥት አመራርና አገልግሎትን ለማሻሻል በተለይ ደግሞ ከሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ተግባራዊነት ጋር በማዛመድ የተለያዩ የመንግሥት አደረጃጀት ለውጦች በሚያስፈልጉበት ጊዜ መንግሥት የተቀላጠፈ አሰራር እንዲከተል ማድረግ ይችል ዘንድ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ለአስፈጻሚው አካል (ለካቢኔው ለራሱ) ይህን የማድረግ ሥልጣን ሰጥቻለሁ እንዳይባል እሰጋለሁ፡፡ የዚህ ምክንያት የተወካዮች ምክር ቤት ዴሊጌት የሚያደርገው (በውክልና ሊሰጠው የማይችለው) ጉዳይ ስላለ ነው፡፡

ሶስኛውና ከአሁኑ በዝርዝር ሊኬድበት የማይችለው ጉዳይ የሚቀየቀረው የማስታወቂያ ሚኒስቴር አደረጃጀት ከ"የመረጃና ኮሚውኒኬሽን አገልግሎት በጥቂት ለማስፋፋትና የሚዲያ እድገትና ብዙሀንነት በማረጋገጥ ዘርፍ"". የተባለው ነው፡፡ ዝርዝሩን ወደፊት ማየታችን ባይቀርም አደገኛው ጉዳይ የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት ለመቀየር የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን "በተጠናከረ አኳኋን ለማስቀጠል" የሚወጣ የመዋቅርና የአደረጃጀት ሕግ ሰብሰተንቲቭ ሕግ ሆኖ መብትና ግዴታ የሚያቋቁም መሰረታዊና የይዘት ሕግ ሆኖ እንዳያርፍ ያለው ስጋት ነው፡፡

ካፈጣሪካ ለፍጡሩ መስጠት የማይችለው ሥልጣን እንዳለም ማወቅ ሌላው የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡
 
< Prev   Next >