Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow በቴዲ አፍሮ ክስ የፍ/ቤት ውሎ
በቴዲ አፍሮ ክስ የፍ/ቤት ውሎ E-mail
Sunday, 12 October 2008

በሰለሞን ጐሹ

እለተ ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2000 ዓ.ም በልደታ የፍትህ አዳራሽ የተሰየመውን 8ኛ ወንጀል ችሎት ለመታደም ከ250 በላይ ሰዎች አዳራሹን ሞልተውታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮውን የሰጠው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሰው ገጭቶ በመግደል በማምለጥና ያለመንጃ ፈቃድ በማሽከረከር ወንጀል አቃቤ ሕግ ክስ ከመሰረተበትና ማስረጃዎቹን አቅርቦ ምስክሮቹን ካሰማ በኋላ ተከሳሹ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 142"1) መሠረት መከላከያውን ማቅረብ እንዲጀምር በመታዘዙ ነው፡፡

 

በዕለቱ ከቀኑ 7፡50 እስከ 10፡57 ሥራ ላይ የነበረው 8ኛው ወንጀል ችሎት 8 የተከላካይ ምስክሮችን በተከሳሽ ጠበቆች ዋና ጥያቄና ድጋሜ ጥያቄ ሲጠየቁ፣ በዓቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቄ ሲያስተናግዱና የቀድሞውን ዳኛ ልዑል ገ/ማርያምን የተኩት ዳኛው መሐመድ ዑመር የፍርድ ቤቱን ማጣሪያ ጥያቄ ሲጠይቁ ከመስተናገዱም ባሻገር ተከሳሹ ቴዲ አፍሮ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 142"3) መሠረት ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ከምስክሮቹ በፊት ቃሉን እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

በእለቱ አርቲስት ቴዎድሮስ ከወትሮው በተለየ በነበሩት ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ላይ አመሐ በልሁን በመጨመር በሁለት ጠበቆች ተወክሎ ቀርቧል፡፡ የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 142"2) መሠረት መከላከያቸውን ሲከፍቱ አጭር መግለጫም ሰጥተዋል፡፡ ምስክሮቹም ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት እንዲምሉ አድርገዋል፡፡

አቶ ሚሊዮን ከ1ኛ - 14ኛ የመከላከያ ምስክርነት ከዘረዘሯቸው አቶ ምትኩ ግርማ፣ አቶ ያሲን ከድር፣ አቶ ሣምሶን ወርቁ፣ ዶ/ር ይርዳው አሻግሬ፣ አቶ እሱባለው፣ ዶ/ር ካሳሁን አደም፣ አቶ አብርሃም መለሠ፣ ኮንስታብል ታምራት፣ ኮንስታብል ከበደ፣ ሳጂን ጌትነት፣ ወጣት ያሬድ፣ ም/ኢንስፔክተር መሐመድ፣ አቶ ታደሰ እና ዶ/ር ላዲስፔርቶ መካከል 13ኛው ከሀገር በመውጣታቸው አለመገኘታቸውን 5ኛ እና 11ኛው ሀገር ውስጥ እያሉ አለመገኘታቸውን አመልክተው 8ኛው፣ 9ኛውና 10ኛው ግን የፍርድ ቤት የመጥሪያ ትዕዛዝ ላይ ፈርመው አለመቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የ8ቱን የመከላከያ ምስክሮች ብቻ ለመስማት ተገዷል፡፡

ዓቃቤ ሕጉ አቶ ፈቃዱ የመከላከያ ማስረጃው አስቀድሞ ስላልደረሳቸው በእኩልነት ክርክር ማድረግ እንደሚያስቸግራቸው በመግለጽ ተቃውሞ አቀረቡ፡፡ የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን በበኩላቸው ማስረጃዎቹን ለፍርድ ቤቱ ማድረሳቸውን ተናገሩ፡፡ በመሐል ዳኛው አቶ መሐመድ ዑመር ማስረጃዎቹ የቆዩት በፍርድ ቤቱ እንጂ በተከላካይ አማካኝነት አለመሆኑን ገልፀው ለዓቃቤ ሕጉ ወዲያውኑ ማስረጃዎቹን የሰጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹን ለዓቃቤ ሕግ ያልሰጠው ለዓቃቤ ሕግ ክርክሮች ወሳኝ ናቸው ብሎ ያላመነ በመሆኑና ዓቃቤ ሕግ ለክርክሬ ወሳኝ ናቸው የሚል አሳማኝ መከራከሪያ  ካቀረበ እንደሚታይ ገለፁ፡፡ ዓቃቤ ሕጉ በተጨማሪም ለ14ኛው ምስክርና ለኩባ ዜጋው ለዶ/ር ላዲስፔርቶ አስተርጓሚነት በተከሳሹ ጠበቆች በኩል የቀረቡት ሁለት አስተርጓሚዎች ጉዳይ ከአሠራር ውጭ መሆኑን የተከራከሩ ሲሆን "የማናውቀውን ቋንቋ በማናምነው ሰው ሲተረጎም ለማመን እንቸገራለን" ብለዋል፡፡ ዳኛው አቶ መሐመድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጡ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 127"2) መሠረት ፍርድ ቤቱ የራሱን አስተርጓሚ ካልሆነም ነፃ አስተርጓሚ መመደብ እንደሚችል ጠቁመው ተከራካሪ ወገኖች ካልተስማሙ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንደሚወስን ገልፀዋል፡፡ አቶ ሚሊዮንና ዓቃቤ ሕግ ፈቃዱ በዳኛው ውሳኔ ተስማምተዋል፡፡

በመቀጠልም በእለቱ በችሎቱ የተገኙት የመከላከያ ምስክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከ1ኛ  - 3ኛ ያሉት ምስክሮች ከቴዲ አፍሮ ቃል ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የጥቅምት 23 ቀን 2000 ዓ.ም ውሏቸውና ማምሻቸውን አብራርተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ፈቃዱ ለሦስቱ ምስክሮች ባቀረቡት መስቀለኛ ጥያቄ "ጠዋት"፣ "ከሰዓት" እና "ምሽት" የሚሉትን ቃላት በትክክለኛ ጊዜና ሰዓት እንዲገልፁላቸው ጠይቀዋል፡፡ 1ኛው ተከላካይ ምስክር አቶ ምትኩ ግርማ ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡30 አካባቢ ድረስ ከቴዲ አፍሮ ጋር አብረው እንደነበሩ ሲገልፁ 2ኛው ተከላካይ ምስክር አቶ ያሲን ከድር በበኩላቸው ከቀኑ 7፡30 እስከ ምሽቱ 9 ሰዓት ድረስ አካባቢ ከተከሳሽ ጋር አብረው እንደነበሩ የተናገሩ ሲሆን ሦስተኛው ተከላካይ ምስክር አቶ ሣምሶን ወርቁ ከምሽቱ 4፡30 እስከ 9፡00 ድረስ ከተከሳሽ ጋር እንደነበሩ መልስዋል፡፡ ቴዲ አፍሮ የጉዳዬ አስፈፃሚ ናቸው ሲል የገለፃቸው አንደኛው ምስክር ቴዎድሮስ ግጭት እንደደረሰበት ከ9፡30  - 10፡00 ሰዓት ደጋግሞ እንደደወለላቸውና ምልክቱን አይተው በ12 ሰዓት ሲደውሉ አደጋ ሲኤምሲ አካባቢ እንደደረሰበት ገልፆላቸው መኪናዋን ከቦታው ለማንሳት መሞከራቸውን ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁለተኛውና ሦስተኛው ምስክር ሲኤምሲ አካባቢ ስለደረሰው አደጋ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም መስማታቸውን መስክረዋል፡፡

4ኛው ምስክር ዶ/ር ይርዳው አሻግሬ በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል አደጋው ተፈጥሯል በተባለበት ወቅት የሆስፒታሉ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን የአስከሬን ምርመራ ኃላፊው የአስከሬኑ የሞት እለትን 22/2/99 ዓ.ም ሲል የምርመራ ቀኑን ደግሞ 23/2/99 ዓ.ም ብሎ ቢያሰፍርም ቀኖቹን በተከታታይ 23/2/99 ዓ.ም እና 24/2/99 ዓ.ም ብለው እንዲያስተካክሉት በተጠየቁት መሠረት እንዳስተካከሉ መስክረዋል፡፡ አቶ ሚሊዮን አስከሬን ምርመራ ውጤት ላይ በፖሊስ ጥያቄ ለውጥ ማድረግ በሆስፒታሉ አሠራር ይቻላል ወይ?" ሲሉ ለጠየቁት ጥያቄ ዶ/ር ይርዳው "በእኔ እምነት የሞተበት ቀን ለውጥ የግድፈት ማስተካከያ እንጂ መሠረታዊ ለውጥ አይደለም" ብለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ፈቃዱ ለምስክሩ ባቀረቡት መስቀለኛ ጥያቄ "ህጋዊ የአስከሬን ምርመራ የጠየቀው ፖሊስ ግድፈቱ እንዲስተካከል መጠየቅ አይችልም?" ያሉ ሲሆን ምስክሩ "አግባብ ያለው ግድፈት ከተፈፀመ ይችላል፡፡ ይሠራበትም ነበር" ሲሉ መልሰዋል፡፡

6ኛው ምስክር ዶ/ር ካሳሁን አደም በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የሜዲካል ዲፓርትመንት ኃላፊ እንደሆኑና ሜዲካል ዳይሬክተሩ በሌሉበት ወክለው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም በውክልና እየሰሩ እንደነበር የገለፁ ሲሆን የቀኑን ለውጥ በሚያረጋግጠው ወረቀት ላይ መፈረማቸውን ገልፀዋል፡፡ ለመቀየር ምክንያት የሆናቸው ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ የደረሳቸው ደብዳቤ መሆኑን መስክረዋል፡፡ አቶ ሚሊዮን "መዝገብ ለመቀየር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አያስፈልጋችሁም ወይ?" ሲሉ ለጠየቁት "ለእኛ ፖሊስም፣ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፍርድ ቤት የፍትሕ አካላት ናቸው" ሲሉ መልሰዋል፡፡ "የአስከሬንን ትክክለኛ የሞት እለት መግለጽ የሚችለው ማን ነው?" ተብለው ሲጠየቁም "የአስከሬን ምርመራ ሐኪሙ" በማለት መልሰዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ፈቃዱ "ያስተካከሉት ፖሊስ ስለፃፈ ብቻ ነው ወይስ አምነውበት?" በማለት መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠይቅም "ነገሮችን አይቼና አምኜበት ነው" ብለዋል፡፡

7ኛው ምስክር አቶ አብርሃም መለሰ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአስተዳደርና የፋይናንስ ኃላፊ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን አቶ ሚሊዮን "በፃፉት የቀን ማስተካከያ ደብዳቤ ስህተቱ የተፈፀመው መርማሪው ሐኪም ወደ ዋናው መዝገብ ሲያሰፍሩ መሆኑን ለፖሊስ ገልፀዋል፡፡ መዝገቡ በ22/2/99 ዓ.ም መሞቱንና ምርመራው በ23/2/99 ዓ.ም መደረጉን ይገልፃል፡፡ ስህተቱ የቱ ነው?" ብለው ሲጠይቁ ምስክሩ "እያንዳንዱን መዝገብ አላይም" ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከፍርድ ቤት ውጭ ማረሚያ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ማረሚያ ሊጠይቁ ይችላሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡

12ኛው ምስክር ም/ኢንስፔክተር መሐመድ በተከሳሹ መኪና ላይ ምርመራ ከሌላ አንድ ባልደረባዬ ጋር አድርጌያለሁ ያሉ ሲሆን መኪናው የቴዲ አፍሮ መሆኑን ግን በአካል እንዳላረጋገጡ ገልፀዋል፡፡ "የአደጋው መንስኤና የደረሰበትን ቦታ በምን አወቁ?" ተብለው ሲጠየቁ "ፖሊስ በሰጠን መረጃ መሠረት" ብለዋል፡፡ "በምርመራችሁ ከሰው ጋር መኪናው ግጭት የፈጠረ ስለመሆኑ ማስረጃ የሚሆኑ እንደ ደም ዓይነት ነገሮች አይታችኋል?" ለተባሉትም "አላገኘንም" ሲሉ መልሰዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ "አሽከርካሪው የተመረመረው መቼ ነው?" የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠይቃቸውም "ህዳር 6 ቀን 1999 ዓ.ም" ብለዋል፡፡ በመከተልም "አደጋው ከደረሰበት ጥቅምት 23 እስከ ህዳር 6 ቀን ደም መሠል ቀጥተኛ ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል ወይ?" ብሎ ዓቃቤ ሕጉ መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠይቅ "አይችልም" ብለው መልሰዋል፡፡ አቶ ሚሊዮን "እስከ ህዳር 6 ቀን ምርመራው ለምን ዘገዬ?" ብለው ሲጠይቁ ዓቃቤ ሕጉ "ከመስቀለኛ ጥያቄ ከተሰጠው ምላሽ ውስጥ አዲስ ጥያቄ መጠየቅ በህግ የተፈቀደ አይደለም" በማለት ተቃውሞ ያቀረቡ ሲሆን ዳኛው በመስማማታቸው ምስክሩ ጥያቄውን እንዳይመልሱት ተደርገዋል፡፡ ሆኖም ጥያቄውን ዳኛው በማጣሪያ ጥያቄው ጠይቀውት ምስክሩ "ተከሳሹ በአካል ባለመቅረቡ ተቸግረን ነው" ሲሉ መልሰዋል፡፡

14ኛውን ምስክሩ አስመልክቶ ዳኛው በትርጉም ላይ በተፈጠረው አለመግባባት ተከራካሪዎች ካልተስማሙ ከአስፈላጊ አካላት ጋር ፍርድ ቤቱ ተፃፅፎ መፍትሔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 148 መሠረት የክርክር ማቆሚያ ንግግር ለማድረግ ሁለቱም ወገኖች በጠየቁት ተጨማሪ ጊዜ መጥሪያ ደርሷቸው ያልመጡ ሦስቱ ምስክሮች በቁ.125 መሠረት ታስረው እንዲቀርቡና በተከላካይ ማስረጃነት የቀረቡት ሰነድ ቁጥር 3፣7፣8፣9 እና 10ን ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ ጽ/ቤት በጽሑፍ እንዲያቀርብ ዓቃቤ ሕጉም እስከ ነገ ሰኞ ድረስ በጽሑፍ አስተያዬቱን እንዲልክ አዟል፡፡ በተጨማሪም መጥሪያ ያልደረሳቸው ምስክሮች እንዲደርሳቸውና የኩባ ኤምባሲ አንድ የኩባ ቋንቋ የሚችል ኢትዮጵያዊ አስተርጓሚ እንዲመደብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመጭው ሐሙስ ጥቅምት 6 ቀን 2000 ዓ.ም 8፡00 ቀጣይ ቀጠሮውን በተመሳሳይ ቦታ አድርጓል፡፡ 
 
< Prev   Next >