| "ከህግ ውጪ የመስቃን ወረዳን... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
"ከህግ ውጪ የመስቃን ወረዳን "መስቃን ዶቢ" ማለት አይቻልም"
የመስቃን ብሔር ተወላጆች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የኢፌድሪ ህገመንግሥት በሚያዘው መሰረት የመስቃን ወረዳ ስያሜ ያገኘችው በወረዳው ምክር ቤት ውሳኔ ነው፡፡ መስከረም 10 ቀን 1995 ዓ.ም የተካሄደው የወረዳው ምክር ቤት ስብሰባ የወረዳዋን ስያሜ ለመሰየም በቀረቡት ስሞች ላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መሰረት መስቃን 90፣ መስቃን ዶቢ 2፣ ድምጽ ሲያገኙ 19 የምክር ቤቱ አባላት ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸውን በወቅቱ የተመዘገበው ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ ቃለ ጉባኤውንና የኢትዮጵያን ህገመንግሥት በመያዝ አቤቱታ የሚያቀርቡት የመስቃን ብሔረሰብ አባላት "የወረዳው ምክር ቤት በህጋዊ ስብሰባ በህገመንግስት የተሰጠውን መብት ተጠቅሞ የወሰነውን ውሳኔ ለመገልበጥ በሚደረገው ሩጫ ንፁሃን የብሄሩ አባሎች እየታሰሩ ነው" ብለዋል፡፡ መስቃን ወረዳ መስቃን ዶቢ እንድትባል ከተፈለገ ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ለወረዳው ምክር ቤት ቀርቦ መታየት ያለበት እንጂ በእስርና በማስፈራራት እንዳልሆነ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ለኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥትና ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ ማስገባታቸውን የሚገልፁት የመስቃን ብሔር አባላት "በተወሰኑ ኃይሎች ግፊት አብሮ የኖረን ህዝብ የማጣላት ቅስቀሳ እየተደረገ ነው" በማለት አቤቱታው የቀረበላቸው ክፍሎች መፍትሄ እንዲፈልጉ ያሳስባሉ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ 200 የሚደርሱ የመስቃን ብሔረሰብ አባላት ታስረው እንደነበር የጠቆሙት እነዚሁ ክፍሎች አብዛኞቹ በዋስ ቢለቀቁም፣ አሁን ድረስ በእስር ላይ ያሉና የተቀሩት የብሔሩ አባላት በስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |