| "ኦነግና መንግሥትን ለማስማማት... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
ኦነግ ሶስትና አራት ቦታ የተከፈለ ድርጅት በመሆኑ አንዱን ወገን ብቻ በማነጋገር ወደ ድርድር መግባት እንደማይቻል ፓስተር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ ፓስተር ዳንኤል እንደሚሉት የተወሰኑ የኦነግ አባላት አዲስ አበባ መግባታቸው ወደፊት ለሚታሰበው የእርቅ ድርድር ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች የእርቅ ሥራ የሚሰሩት ከሞራል አንፃር እንጂ ህጋዊ መሰረት ኖሯቸው እንዳልሆነ ያመለከቱት ፓስተር ዳንኤል የአባቢያ አባጆቢርና የአገር ሽማግሌዎችን መቀራረብ ወደፊት ይጀመራል፣ ሲጀመር ሪፖርት ይቀርብበታል ለተባለው ድርድር አስፈላጊ መነሻ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ የአባቢያም ሆነ የሌሎች የኦነግ አባላት ወደ አገር ቤት መመለስ በራሱ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ የአገር ሽማግሌዎች ያምናሉ፡፡ በይፋ የተጀመረ ድርድር እንደሌለ ቢገልጹም ወደ ይፋዊ ድርድር የሚያመራ ሥራ ስለመጀመሩና ምልክቶች ስለመኖራቸው ተጠይቀው አላስተባበሉም፡፡ እንዲያውም ጥናት እየተካሄደበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በትግል እንዳሳለፈ የሚነገርለት ኦነግ የተለያዩ ጊዜያት የመከፋፈል አደጋ ቢያጋጥመውም እንደ አሁኑ አይነት አደጋ ውስጥ የገባበት ጊዜ እንደሌለ በየአቅጣጫው ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡ በተለያዩ የአመራር ደረጃ ያሉ የድርጅቱ አባላት ይፋ እንዳደረጉት፣ የድርጅቱ ደጋፊዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዳስታወቁትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛዎች እንደዘገቡት ሶስት ቦታ የተከፈለው የኦነግ አመራሮች አንድ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ አስቀድመው ሊግባቡ እንደሚገባ የሚመክሩ አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመደራደር ለኦሮሞ ሕዝብ ችግር መፍትሄ መስራት እንደሚሻል የሚጠቁሙትና ነፍጥ አንስቶ ከመዋጋት የሸሹት ቡድኖች "ሙሉ በሙሉ ከጦርነት አስተሳሰብ እንውጣ" ይላሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር በመደራደር የሚያምኑ ነገር ግን ለድርድሩም ቢሆን ጊዜ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙና በአንድ ጊዜ የትጥቅ ትግል አቁመው ወደ ሌላ የትግል ስልት መግባትን የሚነቅፉ ለዘብተኛ አቋም ያላቸውና በትጥቅ ትግል ብቻ የኦሮሞ ጥያቄ መልስ ያገኛል የሚል አቋም ያላቸው በአንዱ ኦነግ ላይ ያሉ ሶስት አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የኦነግ አባል የነበሩ ከ50 የማያንሱ በአንድ ወር ጊዜ ውሰጥ ወደ አገር ቤት እንደገቡ በይፋ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የፓርላማ አባል የነበሩ እንደሚካተቱበት ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ወደ አገር ቤት ከገቡት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት አቶ አባቢያ አባጃቢር ባለፈው ሐሙስ የአገር ሽማግሌዎች መግለጫ ሲሰጡ ተገኝተው ነበር፡፡ የእሳቸው አመጣጥና በመግለጫው ላይ መገኘት "አብሮ ለመስራት የተደረገ መቀራረብ ነው" በማለት ምላሽ ቢሰጠውም አባቢያ የራሳቸውን ሥራ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እንዲሰሩ እንደሚያስገድዳቸው አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ "ኢስት አፍሪካን ፎረም" የሚባል፣ በሰላም ዙሪያ የሚሰራ የግል ድርጅት ያቋቋሙት አባቢያ ወደ አገር ቤት የገቡት በዋናነት በኦነግ ጉዳይ እንዳልሆነም የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት "አባቢያ በሰላም ዙሪያ ይሰራሉ፡፡ ሥራቸው የአገር ሽማግሌዎች እየሰሩ ካሉት ሥራ ጋር ይመሳሰላል" ዶ/ር መረራ ጉዲና የማደራደሩን ሥራ አስመልክቶ ሲናገሩ አባቢያ ሰላም ላይ የሚሰራ ድርጅት እንዳላቸው፣ ለዚህም ሥራቸው አዲስ አበባ መግባታቸውን ነው የሚገልፁት፡፡ ድርድሩን አስመልክቶ ግን አሁን ለድርድር በሚል ወደ አዲስ አበባ የመጡት የኦነግ አባላት እድሜያቸው የገፉ፣ የጡረታ ጊዜ ላይ ያሉ፣ በረዥም ጊዜ የትግል ስልት ተስፋ የቆረጡ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እድሜ ሲገፋና ትግል ሲሰለች ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ አገር ቤት መግባት የመረጡት ክፍሎች "ጡረታቸውን ለማስከበርም ይፈልጋሉ" የሚሉት ዶ/ር መረራ የኦሮሞን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በድርድር ምላሽ ለመስጠት በመንግሥት (በኢህአዴግ) በኩል ተነሳሸነት እንደማይታይም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የኦሮሞን ጥያቄ ራሱ ቢመልስ ከማንም ጋር መደራደር አያስፈልገውም የሚሉት ዶ/ር መረራ "በአብዛኛው የኦሮሞ ልጆች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ኦነግም ቢሆን ከኢህአዴግ ጋር ተስማማ ሲባል መሰረታዊ ጥያቄዎችን ህዝቡ ይጠይቀዋል" ብለዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |