| አንድነት ፓርቲ የ7.3 ሚሊዮን... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
አንድነት ፓርቲ የ7.3 ሚሊዮን ብር በጀት ያዘ
አንድነት ፓርቲ ከትናንት ወዲያ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ በዘንድሮው አመት 7.3 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ይህንን ለማሳካትም በመላ ሀገሪቱ መደበኛ መዋጮ የሚከፍሉ በርካታ አባላት ይመለመላሉ፡፡ ከአገር ውጭና ከአገር ውስጥ ደጋፊዎች ከሚገኙ የገንዘብ ድጋፎች በተጨማሪ ፓርቲው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ የገንዘብ ምንጩን ለማሳደግ የሚሞክር መሆኑንም የድርጅቱ ም/ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳ ማዕከሎች ከ100 በላይ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች በቀጣዮቹ ሶስት ወራት እንደሚከፍቱ የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሂደት ላይ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ቢታወቅም ፓርቲያቸው በለውጥ የሚያምን በመሆኑ ችግር አለ ብሎ እንደማያፈገፍግ ተናግረዋል፡፡ ..ዛሬ እጃችን ላይ ያለው ሁኔታ በዚያው ይቀጥላል ብለን አናምንም፡፡ እንቅስቃሴ የምናደርገው አንድነት ፓርቲ የራሱ ሚና ያለው በመሆኑ ልዩነት መፍጠር እችላለሁ ብሎ ያምናል እንደዚህ አይነት ተስፋ ከሌለን በራሳችን ማፈርና ማዘን አለብን.. ብለዋል፡፡ ሁልጊዜ ጨለምተኛ ከመሆን ይልቅ እንደ ማህበረሰብ የተሻለ ነገር ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሪት ብርቱካን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በ2002 ሃገራዊ ምርጫ ለመሳተፍና አሸናፊ ለመሆን የሚያስችል ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን የሚያደርግ ቢሆንም የምርጫ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በርካታ ህዝባዊ የኮንፈረንስና የአደባባይ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል፡፡ አዲስ በወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት ለፓርቲዎች ገንዘብ የሚያዋጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ስማቸው ይፋ እንዲሆን ይጠይቃል፡፡ ይህ በገንዘብ ምንጫችሁ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ወይ? ለሚለው ኢንጅነር ግዛቸው ሲመልሱ ..በአዋጁ መሰረት የገንዘብ ምንጫችን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ድብቅ የምናደርገው ነገር የለም፡፡ ይህ የአንድነት ጥያቄ ሳይሆን የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡.. በማለት ፓርቲያቸው ለሚፈሩ ሰዎች ቦታ እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ተመሳሳይ አላማ ካለው ፓርቲ ጋር የመተባበርና የመዋሀድ አላማ ያለው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሀይሉ አርአያ በበኩላቸው ትብብሩና ውህደቱ ከመካሄዱ በፊት ግን ሁሉም ነገር በጥንቃቄ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ካወጣው መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው ከጥቅምት 8 ቀን 2001 ጀምሮ በማዕካለዊና በክልል እንቅስቃሴ ይጀመራል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |