| የሚኒስትሮች ምክር ቤት ገደብ... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ገደብ የሌለው ስልጣን ተሰጠው የተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም በተካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በቀጥታ በጸደቀው አዋጅ መሠረት ቀደም ሲል የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን የነበረው፣ አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ ወይም ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሀድ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም የማድረግና የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ስልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጥቷል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በፈለገው ጊዜ ደንብ በማውጣት ከላይ የተገለጹትን ተግባሮች ማስፈጸም ይችላል፡፡ በረቂቅ አዋጁ የቀረበው መግለጫ እንደሚጠቁመው ይህንን ስልጣን ለሚኒስትሮች ም/ቤት መስጠት ያስፈለገው በመካሄድ ላይ ያለው መሰረታዊ የተቋማዊ ለውጥ ሂደት የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከልን ስለሚጠይቅ በየጊዜው የአዋጅ ማሻሻያ ማቅረብ ሳያስፈልግ የሚፈልገውን ማስተካከያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በማጽደቅ በተቻለ ፍጥነት ወደ ትግበራ ለመግባት እንዲችል ሲባል ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ግን የአዋጁ መጽደቅ የሥራ አስፈፃሚውን የሥልጣን ጥመኝነት የሚያሳይ መሆኑንና ተወካዮች ም/ቤትም ትልቁን ስልጣን በዚህ አዋጅ የተነጠቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸውን ተቃዋሚዎች ያሳዘነው ሌላው ጉዳይ ም/ቤት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋምን ወደሚኒስትር መሥሪያ ቤት በሚያሳድገው አዋጅ ስር የተወካዮች ም/ቤትን ስልጣን ለሚኒስትሮች ም/ቤት አሳልፎ የሚሰጠው አዋጅ ተጣምሮ መቅረቡና መግለጫውም እንደቀላል ነገር በአንድ አንቀጽ ብቻ መቅረቡ ነው፡፡ በአዋጁ መፅደቅ ላይ ተቃውሟቸውን የሰጡት የህብረት ተወካይ አቶ ገብሩ ገብረማርያም የአንድ አገር የአስፈፃሚ አካል ስልጣንና ተግባር በምክር ቤቱ የማይታይ ከሆነና ምን እንደሚከናወን የማይመለከት ከሆነ አስፈጻሚ አካሉ ብቻውን ይሄድና የፓርላማ መሰረታዊ መርህ የሚባለውን ቸክ ኤንድ ባላንስ (ሚዛን የመጠበቅና የመቆጣጠር) ጉዳይ ቦታ የሚያሳጣ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አዋጁ የዚህችን አገር ስልጣን እንዳለ ጠቅልሎ በአስፈጻሚ አካል ስር የሚያስገባ መሆን የገለጹት አቶ ገብሩ የተወካዮች ምክር ቤትም ቁጥጥር ማድረግ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ አይይዘውም "ይህ ጉዳይ የዚህ ፓርቲ ነው የዚያ ፓርቲ ነው የሚባል ሳይሆን በዚህ ምክር ቤት ያለነውን ሰዎች በሙሉ በታሪክ የሚያስጠይቅና ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ዛሬ ማለፉ ቀርቶ እንደገና ቢታይ ይሻላል" ብለዋል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋምን ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማደግን አስመልክቶ በቀረበው አዋጅ ላይ በሰጠት አስተያየትም ተቋሙ ወደሚኒስቴር አሳድጐ የተሻለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ከጉዳዩ ክብደት አንፃር ረቂቅ አዋጅ በአቅም ግንባታ ኮሚቴ ተመርምሮና ባለሙያዎች ተሳትፈውበት ቢጸድቅ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የኢዴአፓ መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ሁለት ነገሮችን አጣምሮ የቀረበና የአጀንዳው አቀራረብም ግልጽነት የጐደለው መሆኑን ጠቁመው በይዞታና በክብደታቸው የተለያዩ ነገሮችን አንድ ላይ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደሚኒስቴርነት የሚያሳድገው አዋጅና አስፈጻሚ አካል ስለሚኖረው ስልጣን የሚገልጹት አዋጆች ተነጣጥለው መቅረብ እንደነበረባቸው የገለጹት አቶ ልደቱ የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳልፎ የሚሰጠው አዋጅም በዓለም ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ "አስፈጻሚ አካላትን የማሻሻል ወይም አሰራራቸውን የመለወጥ ጉዳይ ለሚኒስትሮች ም/ቤት የሚሰጥ ከሆነ ለምንድነው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳይ ለተወካዮች ም/ቤት የቀረበው" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በህገ መንግሥቱ በሶስቱ የመንግሥት ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም በህግ አውጭው በህግ አስፈጻሚውና በሥራ አስፈጻሚው ቼክ ኤንድ ባላንስ (ሚዛን የመጠበቅና የመቆጣጠር) መኖር እንዳለበት የተቀመጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ልደቱ በአሁኑ አዋጅ ግን ህገ መንግሥቱ ከሚለው በተቃራኒ የም/ቤቱ 50 በመቶ የሚሆነው ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |