| ኦነግ እና ሠላማዊ ትግል"? |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
በጌታቸው ንጋቱ
የፖለቲካ መቻቻል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ባህል ውስጥ ባለመኖሩም በእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች አገሪቱ ከፍተኛ ውድመት ሲደርስባት ኖራለች፡፡ ይህም ለአገሪቱ ኋላ ቀርነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሠሞኑን እየተሰማ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ድርድር በተደጋጋሚ ጥረት ሲደረግበት የነበረ ሲሆን የተለያዩ የአገር ሽማግሌዎች ያደረጉት ጥረት ሊሰምር እንደተቃረበ የሚገልፁ ወገኖች አሉ፡፡ ኦነግ በ1973 እ.ኤ.አ ከተቋቋመ በኋላ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ላይ ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም በተፈጠሩ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ከመንግሥት ጋር ባለመስማማትና በትጥቅ ትግል ለመቀጠል ወስኖ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለያዩ ጊዜያት በሠላማዊ ሕዝብ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የኦነግ አሸባሪ ቡድን እንደፈፀማቸው ሲያስረዳ ቆይቷል፡፡ ኦነግ የኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ በደል እየተፈፀመበት ነው በማለት የኢትዮጵያን መንግሥት ሲወነጅል፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ኦነግ የተለያዩ የሽብር ተግባራት በሠላማዊ ሕዝቦች ላይ እንደሚጥል በመግለፅ ሲኮንን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን የሚናፈሰው የኦነግ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሊስማሙ ነው ወሬ ምን ያህል የተሳካ ይሆናል? የኦነግ አመራሮች ይህንን ውሣኔ ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ እንዴት ሊያሳልፉ ቻሉ? የኦነግ አመራሮች ተከፋፍለው ከአንዱ ወገን ጋር ድርድር የሚደረግ ከሆነ ምን ውጤት ያመጣል? የሚሉት ጉዳዮች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩበት ነው፡፡ ኦነግ በውስጡ የተነሱ የፖለቲካ ልዩነቶችን ማስታመም ባለመቻሉ አመራሮቹ በየፊናቸው እየተከፈሉ መሆኑ ሲዘገብ ጠንካራ ተሰሚነት ያለውና ከፍተኛ አመራር በመስጠት የሚታወቀው እንዲሁም በውጭ አገር ለኦነግ ድጋፍ ሲያሰባስብ የኖረው ቡድን ወደ አገር ቤት ተመልሶ ሠላማዊ ትግል ለማድረግና ከመንግሥት ጋር ተስማምቶ ለመሥራት መወሰኑን የተለያዩ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡም ብዛት ያላቸው የኦነግ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የሰለጠኑ ወታደሮች "ከእንግዲህ ጦርነት ለሕዝባችን አይበጅም" በማለት ወደ ሠላማዊ የትግል መስመርና ኑሮ እየተመለሱ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኦነግ አሁን የሌንጮ ባቲ ቡድን፣ የነጋሣ ዲልቦ ቡድንና የዳውድ ኢብሣ ቡድን ተብሎ መከፈሉን በተለያዩ ወቅቶች የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሠላማዊ ድርድር ይሻሉ የተባሉት ወገን የሆኑ አቶ አባቢያ ኦባጆቢርም አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቡድኖች ክፍፍል በትግል ሂደቱ መስመር ላይ የመጣ ልዩነት ሲሆን በጦርነት መፍትሄ አይኖርም የሚሉና በጦርነት እንቀጥላለን በሚሉ ምክንያቶች ልዩነቶቹ እየሠፉ መምጣታቸው ይገለፃል፡፡ ሠላማዊ ትግል መስመርን የመረጡት ወገኖች ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸው ሲገለፁ ሌሎቹ ግን በኤርትራ መንግሥት እየተደገፉ ያሉና በጦርነት ለመቀጠል የፈለጉ መሆናቸው ይገለፃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከኦነግ አመራሮች ጋር ድርድር እንደሚደረግ ከረጅም ጊዜ በፊት ገልፀው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ስለተደረሰበት ደረጃ ግልፅ ያለ ነገር ተነግሮ አያውቅም፡፡ ከመንግሥት ጋር የሚደረገውን ድርድር የአገር ሽማግሌዎች ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካና አወሮፓ በመመላለስ ለማሳካት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ሲገለፅ የአገር ሽማግሌዎቹ የኦነግ አመራሮችንና መንግሥትን ለማስማማት እያደረጉ ያለው ጥረት እየሰመረ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦነግ አመራሮች ሥምምነት ያደርጋሉ ቢባል እንኳን መንግሥት ድርድርና ሥምምነት የሚያደርገው ከየትኛው ወገን መሆን አለበት? የተቆረጠው የኦነግ አመራር የሚጣርለት ሠላም እንዳይመጣ የማደናቀፍ ኃይል የለውም ወይ? የሚለው መታየት አለበት የሚሉ ለፖለቲካው ቅርበት ያላቸው ሰዎች አክራሪውና በጦርነት መቀጠል እፈልጋለሁ የሚለው ቡድን ያለው ጫና ምን ያህል መሆን እንደሚችል መጠናት እንደሚያስፈልገው ይገልፃሉ፡፡ ሠላማዊ ትግልና ጦርነት በሚል የተለያዩት የኦነግ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ አንድ ላይ መጥተው መስማማት ከተቻለ መልካም ውጤት ተብሎ ሊቆጠር እንደሚችል፤ ይሁን እንጂ የተወሰነው ኃይል ተቆርጦ ከቀረ የሚደረገው ድርድር ውጤት አጠያያቂ እንደሚሆንም እነዚሁ ወገኖች ይገልፃሉ፡፡ ኦነግ ሠላማዊ ትግል ብቸኛ አማራጭ መሆኑን የተረዳው አሁን ባሉ አገራዊም ይሁን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በጦርነት ውጤት ሊያስመዘግብ ስለማይችል መሆኑን የሚገልፁ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ኦነግ በስፋት ይንቀሳቀስበት የነበረው የኬንያና የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በኢትዮጵያና በኬንያ መንግሥታት ትብብር ፀጥታው የተጠናከረና ለትጥቅ ትግል የማይመች በመሆኑ እንዲሁም ለኦነግ ተዋጊዎች መጠጊያና ከለላ በመሆን ያገለግሉ የነበሩ የድንበር አካባቢ ነዋሪዎችና አገር ሽማግሌዎች አዲስ አበባ መጥተው መግለጫ ከተሰጣቸው በኋላ ከኦነግ ኃይል ጋር ባለመተባበራቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የኦነግ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመደራደር ከሚያስገድዷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሆናል በማለት በጉዳዩ ተንታኞች የሚቀርበው ምክንያት የአመራሮቹ የእድሜ መግፋትና በጦርነት ከጥፋት የተሻለ ምንም ነገር አይገኝም ብሎ በሰከነ አእምሮ ማሰብ መጀመር መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በኦነግ ትግል ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የድርጅቱ አመራሮች አሁን እድሜያቸው መግፋቱ ከትጥቅ ትግል ወጥተው እንዲያስቡ እንደሚያስገድዳቸው አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ከ5ዐ በላይ የሚሆኑ የኦነግ አባላት የጦርነት ትግል እንደማያዋጣ በማመን የተዋጊነት አስተሳሰብ ካለው ኃይል ተለይተው መውጣታቸውንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ከፓርላማ ወደ ጫካ ገብተው የነበሩም እንደሚገኙበት፤ ለዚህም የኦነግ የፖለቲካ መሪዎች መለያየታቸው አንደኛው ምክንያት መሆኑን አመልክቷል፡፡ ኦነግ በ1973 እ.ኤ.አ አቆጣጠር የተመሰረተ ቢሆንም ድርጅቱ በአይዲዮሎጂም ይሁን በትግል ታክቲክ ምንም ዓይነት ለውጥ አለማሳየቱ፣ ከ3ዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ድርጅት እስካሁን ድረስ እርባና ያለው ሥራ ባለመሥራቱ አባላቱና ደጋፊዎቹም በተንዛዛው ትግል ተስፋ መቁረጣቸው፣ የያዙት የትግል አቅጣጫ ጥራት የጐደለው በመሆኑና ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ ከጉዳት በስተቀር የተጨበጠ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት ባለመቻላቸው ወደ ሰላማዊ ድርድር መምጣት ይሻላል የሚለው አመለካከት በአንዳንድ አመራሮች መታሰቡ የሚያስደንቅ አለመሆኑንም ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ኦነግ፤ ሠላማዊ ኦነግና አክራሪ ኦነግ በሚል በዋነኛነት ለሁለት እንደተከፈለ ሲነገር ሠላማዊ ኦነግ በአገሪቱ ባለው አደረጃጀትና ሕጋዊ በመሆን በሠላማዊ ትግል ለመቀጠል የሚያስብ መሆኑ ሲገለፅ በአክራሪው ወገን የተለያዩ ወንጀላዎች እየተሰነዘሩበት ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውንጀላዎች መካከል ከኢሕአዴግ ጋር በመሆን የኦሮሞ ሕዝብን ትግል ለማዳፈን እየሰራ ነው፤ የሚል ይገኝበታል፡፡ በኦነግ ውስጥ ክፍፍል መፈጠር የጀመረው ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ1970ዎቹ እ.ኤ.አ ሲሆን ልዩነቶች በአካባቢና በሃይማኖት ጭምር በድርጅቱ ውስጥ ይከሰቱ እንደነበር የድርጅቱን ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚያውቁ ያስረዳሉ፡፡ የድርጅቱ መሪ ማን ይሁን በሚልም አለመግባባቶች የነበሩ ሲሆን የድርጅቱ አመራሮች እርስ በርስ ስም የመሰጣጠትና የመጠላለፍ ታሪክ የነበራቸው ሲሆን ሚስተር ዳቦር የተባሉ እንግሊዛዊ እንደፃፉት ለድርጅቱ መዳከምና ውጤት አልባ መሆን ከሚነሱ ምክንያቶች የመጀመሪያው ይኸው የእርስ በርስ መጠላለፍ ነው፡፡ በኦነግ ውስጥ በተፈጠሩ መከፋፈሎች ኢብሶ፣ ኦፒ.ኤል.ኤፍ፣ ኦ.ኤል.ሲ እና ኢ.ደብሊው.ኦ የሚባሉ የተለያዩ ክፍሎች ተፈጥረው የነበረ ሲሆን በኦነግ አመራሮች በኩል "ኢትዮጵያዊነትን" የሚያራምዱና "አካባቢዊነት" የሚያቀነቅኑ ኃይሎች ከዕለት ወደ ዕለት ልዩነታቸው መስፋቱን ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱት ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመደራደር ለኦሮሞ ሕዝብ መብት መከበር በሠላም ለመታገል በአገር ሽማግሌዎች በኩል ድርድር የጀመሩት መሆናቸውም እየተገለፀ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ የትኛውም ቡድን ወጥቶ እኔ ከመንግሥት ጋር እደራደራለሁ ባይልም በአቶ አባቢያ አባጆቢር የሚመራው ቡድን ሠላማዊ መፍትሄ ለችግሮች የሚል ሲሆን ይህንን የሚቃወመው የአቶ ዳውድ ኢብሣ አያና ወገን እነ አቶ አባብያ የኦነግ ውክልና እንደሌላቸው ያስታውቃል፡፡ የተጀመረው አካሄድም የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም የማያስከብር ሲሉ ይገልፁታል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ በሰላማዊ መንገድ በአገር ውስጥ እየታገሉ ያሉ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁን ባለው ሁኔታ በኦነግና በመንግሥት መካከል ድርድር እየተካሄደ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ፍንጭ አለማየታቸውንና ይህም በቀላሉ ይሳካል ብለው እንደማይጠብቁ ይናገራሉ፡፡ የሚሆን ከሆነ ግን፣ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ ትግል ነው ብለው እንደሚያምኑና ድርድሩ ቢፈፀም እንደሚመርጡ ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት ከኦነግ ጋር ድርድር የሚያደርግ ከሆነ እንኳን መደራደር ያለበት ከተወሰነ ቡድን ጋር አለመሆኑን የሚገልፁት ተቃዋሚዎች ኦነግን ቆራርጦ ለማጥፋት በሚል ብቻ የመከፋፈልና የመደራደር ሥራ ከተሰራ ትርፍ እንደማይኖረው ይገልፃሉ፡፡ ከ3ዐ ዓመታት በላይ የኦነግ አመራር የሆኑት ግለሰቦች ቢደራደሩ እንኳን የሚያስደንቅ አለመሆኑን የሚገልፁት ሰላማዊ ተቃዋሚዎች እነዚህ ግለሰቦች እድሜያቸው በመግፋቱ የተሰላቹ ስለሆኑ እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን ብለው እንደማይሆን ይገልፃሉ፡፡ ከኦነግ ጋር መደራደርና ልዩነትን መፍታት የሚደገፍ ቢሆንም ዋነኛው ጉዳይ መሆን ያለበት ከአንድ የፖለቲካ ቡድን ጋር መደራደር ሳይሆን የሕዝብን ጥያቄ አይቶ ማስተናገድና ሕዝብ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች መመለስ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅት ችግር እንደሌለበትና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው ኦሕዴድ በተገቢ መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ ቢመልስና ቢያስተናግድ ኦነግ የሚባለው ድርጅት ተፈላጊነት እንደማይኖረውም ያስረዳሉ፡፡ የኦነግ አመራሮች በድርድር ቢመጡ እንኳን ላለፉት 3ዐ ዓመታት መረዳት ያልተረዷቸው ተብለው የተቀመጡ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ባለመቻላቸው እንደሚሆን ሲገለፅ ችግሮች ተብለው የሚቀመጡትም ድርጅቱ ምንም ዓይነት ስትራቴጂ የሌለውና የፖለቲካና የወታደራዊ አቅጣጫው መሠረት ማጣት፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን ዓለም አቀፋዊ ስርዓት ለትጥቅ ትግል የማይመች መሆኑን አለማጥናት፣ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር መላመድና ራስን አጠናክሮ መቀጠል አለመቻል፣ ለ3ዐ ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አለመቻል ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ገዢ ፓርቲ የሆነው ኢሕአዴግ አወቃቀር ህብረ ብሔራዊ መሆኑና ካሉት ድርጅቶች መካከል አንደኛው ፓርቲ የኦሮሞ ብሔር ፓርቲ የሆነው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የኦሮሞ ሕዝቦችን ጥያቄ ለመመለስና የኦሮሞ ሕዝብን መብት ለማስጠበቅ ቆሜያለሁ ማለቱ፣ ኦሕዴድም በኦሮሚያ ክልል ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ አመራሮች ማስቀመጡና በአሁኑ ወቅትም በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የፓርቲው አባል በማድረግ ድርጅታዊ አቅሙን ሲያጠናክር ድርጅቱም የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ እየመለሰ መሆኑንና የኦነግ አካሄድ ፋይዳቢስ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኦነግ ከዓለም አቀፋዊ ሥርዓት አንፃር የማያራምዱ እውነታዎች ከፊቱ የተጋረጡበት ሲሆን በተለይም በጦር መሣሪያ ኃይል የሚያምኑ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያገኙበት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አብቅቶ፤ ጦርነትና ነፃ አውጭ ነን የሚሉ ኃይሎች ከየትኛውም መንግሥት ድጋፍ በማጣታቸው ድርጅቱ የሚከተለው ስርዓት ያለፈበት የትግል ፋሽን ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ኦነግ ድጋፍ እያገኘ ያለው ከኤርትራ መንግሥት ሲሆን ኤርትራና ኢትዮጵያ ሠላማዊ ጐረቤቶች ቢሆኑ የትኛው አገር ይደግፈዋል የሚለውን መመለስ እንደማይቻልም ይገልፃሉ፡፡ የኦነግና የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድር ተካሄደም አልተካሄደ በኢትዮጵያ የሕዝቦች መብት የሚከበር ከሆነ ብቻ ያሉት ችግሮች መፍትሄ ያገኛሉ የሚሉ ወገኖች መብቶች ሳይከበሩና ልማት ሳይረጋገጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊስማሙ እንደማይችሉ፣ ቢስማሙም ሥምምነታቸው ፋይዳ ቢስ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚችሉ ከሆነም በአገሪቱ የጠፋው የመቻቻል ባህል ለማበብ ስለሚረዳ መንግሥት ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ሊደራደርና አብሮ ሊሰራ ይገባል በማለት ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ጥቅም የተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ኢሕአዴግም ተጀምሮ የተቋረጠውን የፓርቲዎች ድርድር ይቀጥል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |