Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ተቃዋሚዎች የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን አወገዙ
ተቃዋሚዎች የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን አወገዙ E-mail
Sunday, 12 October 2008

በየማነ ናግሽ

በቅርቡ መንግሥት ለነዳጅ መድቦት የቆየው የድጎማ በጀት ማንሳቱ "ፍትሃዊነትና ግልጽነት የጎደለው" በማለት የኑሮ ውድነቱ ችግር ሊያባብሰው እንደሚችል አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስጋታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡

 

በቅርቡ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በበርሊን ከ1450 ብር ወደ 900 ብር ወይም በሊትር ከ15 ወደ 8ብር ያሽቆለቆለ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ መንግሥት በነዳጅ ላይ መድቦት የነበረው እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጎማ ማንሳቱ መስከረም 24 ቀን 2001 ዓ.ም ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

መንግሥት ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው፣ ድጎማው ወደ የእህል ምርቶች ለማዛወር ስለፈለገ በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የድጎማው መጠን በመንግሥት ሪዘርቭ (አቅም) ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ይህንን የመንግሥት እርምጃ የአገሪቱ የኑሮ ውድነት ቀውስ ሊያባብሰው እንደሚችል የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚዎች አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት፣ ኢዴአፓ-መድህን፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና (ኦፌዴን) እና ብርሃን ለአንድነትን ለዴሞክራሲ መንግሥት በነዳጅ ላይ የነበረው ድጎማ ማንሳቱ አግባብ እንዳልሆነና በአገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ የባሰ ሲያናጋው እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ "ለመሆኑ ለነዳጅ ካልተደጎመ ለምን ሊደጎም ነው?" በማለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው እርምጃ አግባብነት እንደሌለው ያስረዳል፡፡

"የእያንዳንዱ ድሃ ጎጆ በሀዘንና በጨለማ ድባብ ተውጧል" የሚለው የፓርቲው መግለጫ፣ ልጆቻችን ምን እናብላ የሚል የብዙ እናቶች ጭንቅ በሞላበት በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ላይ የነበረው ድጎማ መነሳት ተቃውሟል፡፡

"ዓለም በገንዘብ ምንዛሬ ቀውስ እየተናጠ ቢሆንም የእኛ ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ህዝባችን ስለበለጸገና የመግዛት አቅሙ ስላደገ ነው እያሉ በፓርላማ ውስጥ መሳለቅ ዛሬ የሚያዋጣ አይደለም" ይላል የፓርቲው መግለጫ፡፡

ጣሪያ እየነካ የመጣው የዋጋ ንረት በነዳጅ መወደድ ምክንያት ነው የሚለው እና የመንግሥት አቋም የሚያሳምን እንዳልሆነ የሚያትተው "የብርሃን" መግለጫ፣ ችግሩ ገጠር ከከተማ ሳይለይ እኩል ሕዝቡን እያሰቃየ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ እህል ጥረት አሳሳቢ ደረጃ በደረሰበት፣ በድርቅ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ የዓለም የምግብ ድርጅት ይፋ ማድረጉን ይታወቃል፡፡ "በዚህ ዓይነት ብሔራዊ ሰቀቀን ውስጥ ሆነን ለነዳጅ የተመደበው የድጎማ ባጀት እንዲነሳ መደረጉ በፍፁም ፍትሃዊ አይደለም" በማለት መግለጫው ያትታል፡፡  

ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ህዝቡ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲፈጥር ተቃዋሚ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፍ እንዲጠሩም ጠይቋል፡፡ ". . .በተንሰራፋው ተደራራቢና ቁልል ችግር ምክንያት የሚስተጋባውን የህዝብ ኡኡታና ሰቆቃ የምናዳምጥበትን ጆሮና ህሊና ዘግተን ልንቀመጥ የምንችልበት ጊዜ አይደለም፡፡ ረይህሪ የተበታተነው ድምጽ ወደ ተባበረና ከፍ ያለ የህዝብ ጩኸት ልንለውጠው ይገባል" የሚለው የፓርቲው መግለጫ፣ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነትና ይሉኝታ ተተብትቦና በየጎጆው አንገቱን ደፍቶ የሚያነባውን ተቃዋሚዎች ሊጮሁለት እንደሚገባ ይጠይቃል፡፡ "ተቃዋሚዎች በመንግሥት ላይ ጠንካራ ግፊት ለማሳረፍ ከዚህ የባሰ ቀውጢ ቀን ባንጠብቅ መልካም ነው" ይላል የፓርቲወ መግለጫ፡፡   

ፓርቲው ባወጣው በዚሁ የአቋም መግለጫ፣ የተነሳው የነዳጅ ድጎማ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ፣ በሶማሊያ እየተጠቃ ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲወጣና በጀቱም ለነዳጅ ድጎማው እንዲውል፣ የመንግሥት የሥራ ማስኬጃ በጀት በግማሽ እንዲቀነስ ለብሔራዊ ግንባታ ፕሮጀክት የተያዘው በጀት ለጊዜው እንዲታጠፍ፣ አገሪቱ ባልተጠበቀ ሰዓት አደጋ ላይ እንዳትወድቅ የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች ያሰባሰበ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲጠራና የኢትዮጵያ ህዝብም ለሚጠራው ሰላማዊ የተቃውሞ እርምጃ በንቃት እንዲዘጋጅ ይጠይቃል፡፡

የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው የነዳጅ ድጎማ መነሳት የኑሮ ውድነቱ መሸከም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ያደርሰዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ "የነዳጅ ዋጋ በዓለም በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት ምን ተገኝቶ ነው ድጎማው የሚነሳው?" በማለት የጠየቁት አቶ ቡልቻ፣ "መንግሥት በህዝቡ ላይ እንዲህ አይነት ወንጀል የመፈጸም መብት አለው ወይ?" ይላሉ፡፡ መነሳቱ ብቻ ሳይሆን አነሳሱም ድንገተኛና "አርቢትረሪ" ብለውታል፡፡ ድጎማ የሚነሳው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርቦ መሆን እንደነበረበት ገልፀው፣ በቅርቡ ጉዳዩን በፓርላማ ለማንሳት ማሰባቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢዴአፓ-መድህን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ ፓርቲያቸው ገና አቋም እንዳልያዘበት ገልፀው፣ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡ "እርምጃው ግልጽነትና ታማኝነት ይጎድለዋል" የሚሉት አቶ ሙሼ በሶስት ምክንያቶች የድጎማው መነሳት አሳማኝ አይደለም ይላሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ድጎማው ወደ እህል ምርቶች ሄዷል የሚል፣ ምን ዓይነት እህል ላይ እንደሆነ? በስንዴ ላይ የተደረገው የድጎማ በጀትስ ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ ሌላው ከ9 ወር በፊት በነዳጅ ላይ የተደረገው ድጎማ በኬሮሲን ላይ ብቻ እንደነበር ገልፀው፣ አሁንስ የተነሳው ድጎማ ይሄ ብቻ ነው? ቤንዚን ላይስ፣ የድጎማ መነሳት የተደረገው መቼ በነበረው የነዳጅ ዋጋ መሰረት ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች አንስተው፣ "ግልጽነት የለውም" ይላሉ፡፡ እንዲሁም፣ ወደ ስንዴ ተዛውሯል የተባለው፣ የነዳጅና የእህል ድጎማዎች ምን አገናኛቸው? በማለት አባባሉ ተአማኒነት  እንደሚጎድለው አስረድተዋል፡፡

አቶ ሙሼ ድጎማው ተነሳ የተባለበት ምክንያት በፍፁም አሳማኝ እንዳልሆነ ሲናገሩ፣ "ጉዳዩ የጋራ ችግር ነው፡፡ በመንግሥትም በህዝብም ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ አሳማኝ በሆነ ምክንያትና የህዝቡን ስነልቦና በማይጎዳ መሆን ይችል ነበር" ብለዋል፡፡ እንደውም፣ ድጎማው በዓለም አቀፍ ተቋማት ምንም ተቃውሞ እንዳልተደረገበት ገልፀው፣ እርምጃው የዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ያስገባ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

"የኑሮ ውድነት የመቀነስ ጥረት ማጠናከር እየተገባ፣ ህዝቡ ቀውስ ውስጥ እያለ ሌላ ችግር መጨመር ተገቢ አይደለም" የሚሉት አቶ ሙሼ፣ "የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ መንግሥት ዋጋ መጨመሩ አሳፋሪ ነው" ብለዋል፡፡ "የኢኮኖሚ ቀውስ መፈታት የሚችለው በጋራ ብቻ ነው" የሚሉት አቶ ሙሼ፣ የደጎማው መነሳት ግልጽነት በጎደለው አሰራር በመሆኑ በመንግሥትና በህዝብ መግባባትና መተማመን ያሳጣል ብለዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ሙሼ፣ ጉዳዩ ለፓርላማ ቀርቦ መንግሥት ዝርዝርና ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥበት እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡን አስተያየት፣ ስለ ነዳጅ ዋጋ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታና በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ለየቅል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

"የዓለም የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት፣ በኢትዮጵያ ግን በተለይ ነጭ ጋዝ በሊትር በሶስት ብር እንዲጨምር የተደረገበት ምክንያት አልገባኝም" ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ሁኔታው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ድንገተኛ የመንግሥት እርምጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ንረትም ሆነ በዓለም አቀፍ ያለው የነዳጅ ዋጋ ሁኔታ ግምት ያላስገባ መሆኑን አስገርሟቸዋል፡፡ "በሌላ አገር ቢሆን እኮ አሁን ህዝቡ ሆ" ብሎ ይወጣ ነበር" ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዓመጽ መነሳሳት ያልለመደ በመሆኑ አንገቱን ይድፋ እንጂ እጅግ ያሳስበናል ብለዋል፡፡

እርምጃው በተለይ የእህል ምርት ዋጋ አልቀመስ ያለው ድሃ የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ የባሰ የሚያናጋ መሆኑን በማስረዳት፣ "መንግሥት ቅድሚያ እሰጠዋለሁ የሚለውና ጠዋትና ማታ የሚያወራበት የረሃብ ቅነሳ ፕሮግራም ጋር የሚፃረር ነው" በማለት መንግስትን ወቅሰዋል፡፡ ፓርቲያቸው ሁኔታው ገምግሞ አቋም እንደሚይዝበትም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የነዳጅ ድጎማ መነሳት ምክንያት አብዛኛው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል በትራንስፖርትና በፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ስጋት ላይ የወደቀ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የተከሰተውና እስካሁንም መፍትሄ ያልተገኘለት የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ያንሰራፋ መሆኑን ይታወቃል፡፡

ኅብረተሰቡ ከዋጋ ንረቱና ከምግብ እጥረት ቀውሶች ባልተለቀቀበት በአሁኑ ወቅት ለነዳጅ ይደረግ የነበረው የድጎማ በጀት በድንገት መነሳት፣ ችግሮችን ይበልጥ ሊያባብስ እንደሚችል የሚገልፁ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ በሚገኝበት ወቅት መንግሥት የወሰደው ይህ ያልተጠበቀ እርምጃ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች ድጎማው የተነሳበት ምክንያት አሳማኝ አለመሆኑና አሰራሩ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ አግባብ እንዳልሆነ መንግሥትን እየወቀሱ ይገኛሉ፡፡
 
< Prev   Next >