Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ስለ ሣሪስ
ስለ ሣሪስ E-mail
Sunday, 12 October 2008

ጌታቸው አየለ

በአሁኑ ጊዜ አዋሽ ወይን ጠጅ አክሲዮን ማህበር ተብሎ የሚጠራው ድርጅት በደርግ ሥርዓት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ኬ. አሌክሣንድራኪስና ኩባንያው የወይን ጠጅ ፋብሪካ ወይንም ሣሪስ ይባል እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ይህ የወይን ጠጅ ፋብሪካ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለው መጋቢት 17 ቀን 1967 ዓ.ም በኩባንያው አድራሻ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ብሔራዊ ሐብት ልማት ሚኒስቴር በቁጥር ሰአ14/1-5 በተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡

 

ኬ. አሌክሣንድራኪስና ኩባንያው የወይን ጠጅ ፋብሪካ ሥራ የጀመረው አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ራስ አበበ አረጋይ መንገድ በሚገኝ ቅጥር ግቢ ከዛሬ 48 ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ1961 ነበር፡፡ ኩባንያውን ያቋቋሙት ሚኒስተር ኮስታ አሌክሣንድራኪስ የተባሉ የግሪክ ዜጋ እና ሚስተር ጂዮዜፔ ጋላንቱ የሚባሉ ኢጣሊያዊ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ሜይ 21 ቀን 1966 ሚስተር ጂዮዜፔ ጋላንቲ የነበራቸውን የአክሲዮን ድርሻ ለሚስተር ኤ.ሚሆስ ለሚባሉት ሌላ ግሪካዊ አዛውረውላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የወይን ጠጅ ምርት ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱ ኬ. አሌክሣንድራኪስና ኩባንያው የወይን ጠጅ ፋብሪካ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሚወስደው ጄኔራል ስሙትስ መንገድ ከድልድዩ በስተቀኝ በኩል የሚገኘውን አዲስ ሕንጻ አሠርተው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የወይን ጠጅ ፋብሪካ አቋቁመዋል፡፡ ፋብሪካው ሥራውን በሚገባ በማከናወን ላይ እንዳለ በደርግ ሥርዓት ከአዋጅ ውጭ በደብዳቤ የተወሰደ መሆኑ ከዚህ በላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶችን ለመመለስ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 110/1987 የተደነገገውን መሠረት በማድረግ የፋብሪካው የቀድሞ ባለንብረቶች ያላግባብ የተወሰደባቸው የወይን ጠጅ ፋብሪካ እንዲመለስላቸው ነሐሴ 1987 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ማመልከቻ አቀረቡ፡፡ የኤጀንሲው ሥራ አመራር ቦርድ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ድርጅቱ ከአዋጅ ውጭ የተወሰደ መሆኑን በማረጋገጥ የካቲት 22 ቀን 1992 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ንብረቱ እንዲመለስላቸው ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህ ውሳኔ እንደተዘረዘረው ባለሃብቶቹ ንብረቱን ለመረከብ ድርጅቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ፋብሪካውን ለማስፋፋት በመንግሥት ወጪ የተደረገውን ኢንቨስትመንት እንዲከፍሉና ድርጅቱን እንዲረከቡ ወይንም በተወረሰባቸው ንብረት ግምት ላይ ተመስርቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሰጣቸው፣ በዚህ ካልተስማሙ ፋብሪካው ተሸጦ ድርሻቸው በካሣ መልክ ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚል ነው፡፡

በዚሁ መሠረት የድርጅቱ ጠቅላላ ሃብት፣ ከቀድሞ ባለሃብቶች የተወረሰው ንብረት ግምት፣ በመንግሥት በኩል ፋብሪካውን ለማስፋፋት የተደረገው ወጪ ዝርዝር በኤጀንሲው ኤክስፐርቶች ከተሠራ በኋላ ታህሳስ 1992 ዓ.ም የዋጋ ትመናው ሪፖርት አንድ ኮፒ ለቀድሞ ባለሃብቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዋጋ ትመና ላይ ተመሥርቶ የወይን ጠጅ ፋብሪካው ካፒታል እያንዳንዱ ዋጋው 1000 (አንድ ሺህ) የሆነ በጠቅላላ በ30580 አክሲዮን ተከፋፍሎ በአክሲዮን ማህበር መልክ እንዲቋቋም ሲደረግ የቀድሞ ባለንብረቶች 7415 የአክሲዮን ድርሻ ወይንም 23ኀ የባለቤትነት መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ቀሪው የአክሲዮን ብዛት የመንግሥት ኢንቨስትመንት ድርሻ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለቀድሞ ባለንብረቶች ለተወሰደባቸው ንብረት የተሰጠው ግምት እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም ይሄንኑ መነሻ በማድረግ የሚፈለገውን ገንዘብ ለመንግሥት ከፍለው ፋብሪካውን ለመረከብ ተስማሙ፡፡ ለመንግሥት ሊከፍሉ የሚገባቸውን ድርሻ በሁለት ከፍሎ በማየት በአንድ በኩል አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉትን የቋሚ ንብረቶች Fixed Assets    ዋጋ፣ በሌላ በኩል ተንቀሳቃሽ ንብረቶችንና ጥሬ እቃዎች በፕሮሰስ ላይ የሚገኙ ምርቶች ወዘተ Raw Materials & Stock on Process etc ለይቶ በማስቀመጥ መጀመሪያ የቋሚ ንብረቶች ዋጋ እንዲከፈል፣ ቀጥሎ የተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በሚመለከት ብዛቱ/መጠኑ ስለሚለዋወጥ በርክክብ ዕለት በሚደረገው ቆጠራ Stock Inventory ላይ ተመስርቶ ለመንግሥት የሚከፈለውን ጠቅላላ ገንዘብ ገቢ በማድረግ ፋብሪካውን እንዲረከቡ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ክፍያውም በከፊል በባንክ ብድር ጭምር ለመሸፈን በታቀደው መሠረት የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲው ለንግድ ባንኮች ፋብሪካው ከአዋጅ ውጭ መወሰዱ ስለተረጋገጠ፣ የቀድሞ ባለሃብቶች ኬ. አሌክሣንድራኪስና ኩባንያው መንግሥት ፋብሪካውን ለማስፋፋት ያደረገውን ኢንቨስትመንት ወጪ ከፍለው ለመረከብ እንዲችሉ የፋብሪካውን ንብረት በማስያዝ ብድር መውሰድ ይችላሉ የሚል የድጋፍ ደብዳቤ ሰኔ 2 ቀን 1997 ዓ.ም ተሰጥቷቸዋል፡፡

የቀድሞ ባለንብረቶች በመንግሥት በኩል ፋብሪካውን ለማስፋፋት የተደረገውን ወጪ ተሳስበው ለመክፈል እና ፋብሪካውን ለመረከብ በተዘጋጁበት ወቅት በመንግሥት በኩል ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲው በተሰጠው አዲስ መመሪያ ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶችን የመመለሱ ሂደት እንዲቆም በመታዘዙ በወቅቱ ፋብሪካውን የመመለሱ ተግባር ለመፈጸም እና ለማረካከብ ሳይቻል ቀረ፡፡

በመካከሉ እገዳው እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ ፋብሪካው በርካታ ተጨማሪ የማምረቻ መሣሪያዎች እና የተሽከርካሪዎች ግዢ በመፈጸሙ እገዳው በ1998 ዓ.ም ሲነሳ በርክክቡ ስርዓት ለመነጋገርና ብድሩ ከቆመበት ለመቀጠል ስለሚቻልበት ሁኔታ ባለጉዳዮቹ ጥያቄ ሲያቀርቡ ኤጀንሲው በፋብሪካው በኩል የተደረጉትን ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ዝርዝርና የሂሳብ መግለጫ ከፋብሪካው እስኪላክለት ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2005 በጽሑፍ አስታወቀ፡፡

ሆኖም ፋብሪካው እንዲልክ የተጠየቀውን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ዝርዝር እስኪያዘጋጅ ጊዜ በመውሰዱ የቀድሞ ባለንብረቶች ለርክክቡ የሚያስፈልጉ ሌሎች ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ለወደፊቱ የሚያስፈልገውን የሥራ ዕቅድ በማጠናቀቅ ላይ ይገኙ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶች ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት መስከረም 4 ቀን 1999 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ አዳዲስ ጥያቄዎችን በማንሳቱ ምክንያት ከአዋጅ ውጭ የተወሰደው የወይን ጠጅ ፋብሪካ እንዲመለስ ቦርዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን ቆየ፡፡ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ካቀረባቸው አዲስ ጥያቄ መካከል ዋና ዋናዎቹ ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡  

ሀ) ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ የመመስረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ
ለ) አመልካቾች ለተወረሰው ንብረት ካሣ ተቀብላችኋል የሚል ነበር፡፡

በመሠረቱ የመመስረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ በድርጅቱ ጽ/ቤት እንጂ እያንዳንዱ ባለአክሲዮን እጅ የሚቀመጡ ስላይደሉ ከ48 ዓመት በኋላ ፈልጎ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሆኖም በቀድሞ ባለንብረቶች በተደረገ ከፍተኛ ጥረት ግልባጩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመገኘቱ ቀጥሎም ከብዙ ፍለጋ በኋላ ኦርጅናሉ ሰነድ ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በመገኘቱ ይሄው ተሟልቶ ለኤጀንሲው ቀርቧል፡፡  

ሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተ ከአዋጅ ውጭ ለተወሰደው የወይን ጠጅ ፋብሪካ ለባለንብረቶች ካሣ ያልተከፈለ መሆኑን የሚመለከተው የመንግሥት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ለኤጀንሲው በጽሑፍ አረጋግጧል፡፡

ስለዚህ የወይን ጠጅ ፋብሪካው ለቀድሞ ባለንብረቶች እንዲመለስ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ የሚሻርበት ምክንያት እንደሌለ ግለጽ ነው፡፡ በመሆኑም ከአዋጅ ውጭ የተወሰዱ ንብረቶች ለትክክለኛ ባለሃብቶች እንዲመለስ የኢፌዲሪ መንግሥት በፈቀደው መሠረት የኬ. አሌክሣንድራኪስ እና ኩባንያው ንብረት የነበረው የወይን ጠጅ ፋብሪካ ያለተጨማሪ መዘግየት እንዲመለስላቸው ከፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ቦርድ ፍትሐዊ ውሳኔ ይጠብቃሉ፡፡
 
< Prev   Next >