| "አለቅን"" |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
ከ2001 አንድ ወር ቀንሰናል፡፡ ሁለት ሺህ ባየንበት ለ2001 ሥጋት አድሮብን ቆይተናል፡፡ ደላላው 2001 እንደ 2000 ዓ.ም. ዙሩ የሚከር፣ ኑሮው የሚከብድ ከሆነ ይለፈን ብሎ ነበር፡፡ ሁለት ሺህ አንድ አገባቡ፣ አጀማመሩ ስላላማረን ይለፈን ብለን በአንድ ድምፅ ማመልከት ነበረብን፡፡
የንግግር መጀመሪያም መሆን ነበረበት፡፡ ብዙም ሳንጓዝ 2001 ከባድ እንደሚሆን ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ ብሔራዊ ሜትሮዎሎጂም በዚህ በኩል ሳይደግፈን አይቀርም፡፡ ለ2000 የተመደበልን ዝናብ በቂ አይደለም፡፡ ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚመጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙን ከሆነ ያልሞሉ ወንዞች እንደነበሩ ነው፡፡ ወንዞች ያልሞሉበት ክረምት ቢኖር የ2000 ክረምት ነው፡፡ ዙሩ ከባድ መሆኑን ከሁሉም ይበልጥ ግልፅ ያደረገልን የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው፡፡ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል ይሉኛል ደንበኞቼ፡፡ እኛ ጋ ደግሞ ችግር ተፈጥሯል፡፡ ምግብ ስላጠረን በድጎማ ስንዴ ይገዛል፡፡ ለስንዴ ድጎማ ሲባል የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንዳስፈለገ ሲነገር ሰምተናል፡፡ አምበርብር የማስታወስ ችሎታው ዝቅተኛ ነው ካላላችሁ፣ በ2000 ለነዳጅ የሚደረገው ድጎማ ቀጣይነት እንዳለው በአደባባይ ሲነገር አዳምጧል፡፡ የኑሮ ውድነቱን፣ የዋጋ ንረቱን ለማቀዝቀዝ የነዳጅ ድጎማው ይቀጥላል ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ቃል ተቀይሯል፡፡ የተናገርኩት ከሚጠፋ የወለድኩት ይጥፋ ይባል ነበር ድሮ፡፡ ደንበኞቼ ከየአቅጣጫው እየደወሉ "አለቅን" ይሉኛል፡፡ "ገና ምን አይታችሁ" እላችኋለሁ፡፡ አምበርብር ፈሪ ነውና ፍርሃት ከለቀቀበት ቆይቷል፡፡ በ2001 ከ2000 ጠንከር እንደሚል አንዳንድ ምልክቶች ከወዲሁ እየታዩ ነው፡፡ የውኃ እጥረት ስላለ የመብራት ፈረቃው የማይቀር ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው የምግብ ዋጋን የበለጠ እንደሚያንረው ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲያውም አንዱ ደንበኛዬ "ከትራንስፖርት በስተቀር ውጭ ምንም ነገር አልጠቀምም" ብለውኛል፡፡ እሳቸው ያደረጉት ይሆናል፡፡ ሌላው ግን ስንቱ ይህንን ለማድረግ ይመቸዋል? የሆቴሎች፣ ከሬስቶራንቶችና የሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ዋጋቸውን በምን ያህል መቶኛ ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ለኑሮ የምትመች፣ ሁሉም በአቅሙ የሚኖርባት እንዳልተባለች፣ ከእንግዲህ ግን አቅም ያለው እንጂ ሌላው የሚሰደድባት ልትሆን ነው፡፡ የፈሩት ይደርሳል እንዲሉ የፈራነው ሁሉ እየመጣ ነው፡፡ መሪዎቻችን አዝመራው ጥሩ እንደሆነ ሲተነብዩ በጥያቄና መልስ አዳምጠናል፡፡ እንዳፋቸው እንዲያደርግልን ተመኝተናል፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ተግባራዊ የሚሆን አይመስልም፡፡ ከዓመታት ወዲህ የወጣው ገበያችን ቀጥሏል፡፡ በየቀኑ መጨመር እንጂ መቀነስ ትቷል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ገበያው ባለሙያ ነኝ የሚለውም ሊገልፀው፣ መፍትሄ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ባለሥልጣኖችም ደስ ያላቸውን ይናገራሉ እንጂ የኢትዮጵያ ኑሮ ውድነት መንስዔና መፍትሄ ሊያውቁት አልቻሉም፡፡ ገበያው ያለምንም ተቆጣጣሪ እየተወሳሰበ ነው፡፡ በደህና ጊዜ መኪና ያስያዝኩት ደንበኛዬ "ተሸንፌያለሁ" አለኝ፡፡ "ባለመኪናው አንተ መሸነፍክን ካመንክ ሌላውማ ከመስመር ሙሉ በሙሉ ወጥተዋል ማለት ነው" አልኩት፡፡ በ1999፣ በ2000 ፈር የለቀቀው ገበያ፣ ሥርዓት ያጣው ኑሮ፣ በ2001 በተባባሰ መልኩ ቀጥሏል፡፡ አብዛኛዎቹ የምግብ ሸቀጦች ጭማሪያቸው የሚደረስበት አልሆነም፡፡ ይጨምራሉ ሳይሆን ይወረወራሉ ነው መባል ያለበት፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም ይሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲነጋገሩበት የሚያስፈልገው አዝማሚያው ስላላማረን 2001 እንዲያልፈን ነው፡፡ እኛ ዜጎችም በአንድነት 2001 አዝማሚያው ስላላማረን "ይለፈን" ማለት አለብን፡፡ ዕድገቱ ቀርቶብን ካለንበት እንቆይ ብንል ይሻላል፡፡ ማደግ ይህን ያህል ሸምቀቆን የሚያጠብቅ ከሆነ ይቅርብን፡፡ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ይተላለፍልን፡፡ ዘመናዊነቱም፣ መልካም አስተዳደር መጥቷል የተባለውም ለጊዜው ቀርተውብን ላልተወሰነ ጊዜ ቢተላለፍልን፡፡ መልካም አስተዳደር ኑሮን ምቹ ሲያደርግ እንጂ ሲያባብስ አልሰማንም፡፡ መልካም አስተዳደር መብራት፣ ውኃ ሲያመጣ እንጂ ሲነሣ አናውቅም፡፡ እኛ መስመሩ ከጠፋን ወደመስመሩ እስክንመለስ ምክር ቤቶቹ እርምጃ እንዲወስዱልን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጁልን እንጠይቃለን፡፡ በተፈጠረው የኑሮ ውድነት ምክንያት እኔና ባሻዬ "አንድ ሁለት" ማለት አቁመናል፡፡ አንድ ሁለት የሚባለው ሁሉ ጠጁ፣ ቢራው፣ ድራፍቱ . . . ዋጋው በሚያስደነግጥ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ እኔና ባሻዬ ማውጋት የምንችለው እየተጓዝን ነው፡፡ ከወደ ውኃው ቀርቶ ሻይ ቡና መባባልም አልተቻለም፡፡ የሻይ ቡናውም ዋጋ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ ኑሮ እንዲህ እያየነው ከእጃችን አምልጧል፡፡ የገቢ ምንጭ የሚሰፋበት መንገድ ሲጠፋ፣ ፍላጎትን መገደብ ሆኗል፡፡ ከመብላት ወዳለመብላት፣ ከመጠጣት ወዳለመጠጣት፡፡ እንዲህም እየሆነ "ኑሮ ሰመረ" ብለው ከበሮ የሚደልቁልን እንዳሉ እንታዘባለን፡፡ እነሱ ስለጠገቡ እኛ የጠገብን አስመስለው መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ በከተማው ያለው ጥቂቱ ነዋሪ እንጂ አብዛኛው ከተሜና ገጠሬው (ገበሬው) የዋጋ ንረቱን፣ የኑሮ ውድነቱ ብዙም ተፅእኖ አላደረጉበትም ሲባል ያመናል፡፡ ከእኛ ወዲያ መስካሪ፣ ከእኛ ወዲያ ተጠቂ ያለ ይመስል፡፡ በእርግጥ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ ተፅእኖ ያላደረሱባቸው ጥቂት ሰዎች አይጠፉም፡፡ እነዚህ ደግሞ ብዙ ጉድጓድ ያላቸው ናቸው፡፡ የገቢ ምንጫቸው በሺዎችና በሚሊዮኖች የሆነ፣ አደግን የሚሉት ቅርብ የሆኑ፣ እውነትም የኑሮ ውድነቱም ይሁን የዋጋ ንረቱ ላይሰማቸው ይችላል፡፡ ዱሮም እኮ የቸገረው ነው እርጉዝ የሚያገባው፡፡ ያልቸገረው በቸገረው ቁስል ላይ እንጨት ቢሰድ፣ ለእርሱ ምንም አይደለም፡፡ ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ እንደሚወስድ ሁሉ ኑሮም ቀስ በቀስ እያሸነፈን ነው፡፡ ላለመሸነፍ ምን መደረግ እንዳለበት መምከር አለብን፡፡ የእኛን ኑሮ የሚኖሩ ይመስል በእኛ ስም መግለጫ የሚሰጡት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንጠይቅ፡፡ ያልበላቸውን ለማከክ ለሚዳዱም ከተቻለ ተግሳጽ፣ ተግሳጽ ካልተቻለ ምክር ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡ ከመከላከል አልፈን ወደ ማጥቃት እንገባለን ብለን አናስብም፡፡ ምክንያቱም መሸነፋችን እውነት ሆኗል፡፡ በግብግቡ አልተሸነፍኩም፣ ኑሮን በጥሩ ሁኔታ እመራለሁ የሚሉ ካሉ ከላይኞቹ የሚመደቡት ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን ግን ተሸንፈናል፡፡ እጅ ሰጥተን የተማረክንም አንጠፋም፡፡ የሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የሚመጣው የዋጋ ማሻቀብ የተወሳሰበውን ኑሯችንን ምን ያህል እንደሚያባብሰው መገመት ይቻላል፡፡ እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ፤ ምቱ ኃይለኛ፣ ዙሩ ከራራ ነው፡፡ ምንም መጣ ምን የሚያርፈው እኛ ላይ ነው፡፡ ነዳጅ ቢጨምር አበሳችንን የምንቆጥረው መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያለን ነን፡፡ እንደ አሁኑ አያያዝ ከሆነ ጫናው በሙሉ እኛ ላይ ያርፋል፡፡ የዋጋ ንረቱን ቀንበር በላያችን ላይ ተሸክመነዋል፡፡ ጭነቱ የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ እንዳልሆነ ከልምዳችን እናውቀዋለን፡፡ አምበርብር የተሰማውን የጨነቀውን ሁሉ ሲጠቁም ቆይቷል፡፡ የ2000 የዋጋ ንረት በ2001 እንደሚደገም ለመተንበይ ነቢይ መሆን አያስፈልግም ነበር፡፡ "አካሄዱን"፣ "አቅጣጫውን" አይተን ለመገመት አልቸገረንም፡፡ አሁን አሁን 2000ን በስንት ጣዕሙ ማለት የጀመሩ ደንበኞች አጋጥመውኛል፡፡ በ2001 ጥቃቱ ዘርፈ ብዙ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ የዝናብ እጥረቱ የሚያመጣው ተፅእኖ ከተወሳሰበው የዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ ፍዳችንን እንደሚያስቆጥረን ግልፅ ነው፡፡ መሄጃ ያለው ሸሽቶ ያመልጣል፣ መሄጃ የሌለው ግን የችግሩ ተሸካሚ ይሆናል፡፡ የተሻለን መጠበቅ አቁመን፣ የሚመጣውን የኑሮ ጫና ለመቋቋም እናቅድ፡፡ ከወዲሁ ጫናውን ለመቋቋም የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ካልጀመርን ፈተናው ከባድ ይሆናል፡፡ ፈርቼ እንዳላስፈራራችሁ ብዬ ነው እንጂ ሥጋቴ ጨምሯል፡፡ ለማንኛውም ተዘጋጁ፡፡ ደህና ሁኑ፡፡ ሰላም" |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |