| የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ ለኢትዮጵያ... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
የመነጋገሪያ አጀንዳ ብቻም ሳይሆን የስጋትና የጭንቀት የአስቸኳይ እርምጃና የቢሊዮኖች ዶላር፣ ፓውንድና ዩሮ ድጎማ ጉዳይም ሆኗል፡፡ አሜሪካ 700 ቢሊዮን ዶላር እደጉማለሁ፤ ብላ በምክር ቤት ወሰነች፡፡ እንግሊዝም 50 ቢሊዮን ፓውንድ ድጎማ እጨምራለሁ፣ እያለች ናት፡፡ በርካታ ባንኮች ናሽናላይዝድ እየሆኑ ናቸው፡፡ ህዝቡ ባለባንኮቹ ባበላሹት ግብር ከፋዩ ለምን ይቀጣል እያለ ነው፡፡ አይስላንድ የወሰደችው ርምጃ የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማሲ ቀውስም አስከትሏል፡፡ እንግሊዝም ቁጭትዋን እየገለፀች ነው፡፡ እስያም በዚህ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጋ ነው፡፡ የእስያ ኢኮኖሚ ከአውሮፓና አሜሪካ ኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነውና፡፡ ይህ ሁኔታ የንብረት ዋጋ እንዲወድቅ አድርጓል፣ ብዙ ህዝብ ቤቱ ንብረቱ በባንክ እየተወሰደበት ነው፡፡ ባንኮችም የወረሱት ንብረት መሸጥ እያቃታቸው ነው፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎች የሚባሉት በርካታ ሠራተኞችን እየቀነሱ ነው፡፡ ስራ አጥነት በእጅጉ ተስፋፍቷል፡፡ መንግሥት ተቆጣጣሪ አካል እንጂ የንብረት ባለቤት ሊሆን አይገባም፤ የሚል ጽኑ እምነት የነበረው የምዕራባውያን ሰራዊት በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ካልገባና ካልደጎመ ቀውሱ ታይቶ ወደማይታወቅ አዘቅት ሊገባ እንደሚችል ሁሉም የሚናገረው ሃቅ ሆኗል፡፡ እኛስ ጋር እንዴት ነው? በዓለም ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ ለኢትዮጵያ ምን ትርጉም ይሰጣል? ምን ያህል ጫና ይፈጥርብናል? እስካሁን ድረስ ነክቶናል? ወይስ አልነካንም? ዋናው ጉዳያችን ይኸው ነው፡፡ ሊነገረን ይገባል፡፡ ግን መንግሥትም ኢኮኖሚስቶችም ስለዚህ ጉዳይ አይነግሩንም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ይህ በዓለም ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ በምናገኘው ብድርና እርዳታ ላይ ጫና የለውምን? ለራሳቸው ገንዘብ ካጠራቸውና ገንዘባቸውን ለራሳቸው ድጎማ ከተጠቀሙበት ወደ አፍሪካ ሊዘልቅ የሚችለውን የብድርና የእርዳታ መጠን አይቀንሰውምን? ይህ በዓለም እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ ለውጭ ገበያ በምናቀርበው መጠን ላይ ጫና አይኖረውምን? የመግዛት አቅማቸው ከተዳከመ የኤክስፖርት ውጤታችን አይቀንስምን? እርዳታውንም ኤክስፖርትም ከቀነሰ የውጭ ምንዛሬያችንን ቀንሶ ኤል. ሲ እና ሌላ ሌላ ለመክፈት አቅም አንሶን ወደ ሃገር ውስጥ በምናስገባቸው ዕቃዎች ላይ ጫና አይኖረውምን? ይህም ማለት እንዱስትሪያችን ኢኮኖሚያችን እርሻችን ወዘተ. ላይ ጫና እየፈጠረ አይደለምን? እዚህ የጠቃቀስናቸው ጉዳዮች በቀጥታ በገንዘብና በኢኮኖሚያችን ሊፈጠሩ (ወይም ላይፈጠሩ) የሚችሉ ጫናዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ጫናዎች ብቻ አይሆኑም፡፡ በአሉታ ይሁን በአዎንታ ሊታዩ የሚችሉ በፖሊሲዎቻችንና በህጎቻችን ላይ የሚንፀባረቁ ጫናዎችስ የሉም ወይ? መንግሥት የተበላሹ፣ የከሰሩ ባንኮች ሲደጎሙ ብቻ ሳይሆን፣ የመንግስት ቁጥጥር ሲጠናከርባቸው ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት በቁጥጥሩ ስር አስገብቶ ሲያካሂዳቸው በአሜሪካና በአውሮፓ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን መንግሥት የግል ባንኮችን ለመቆጣጠር የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች በፀጋ እንቀበላቸዋለን? "ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ" በሚለው ብሂል የሚካተቱ አዎንታዊ መመሪያዎች ናቸውን? የውጭ ባንክ ቢፈቅድ ኖሮ ይሄኔ ጣጣ ውስጥ እንገባ ነበር፤ በሚል ብያኔ አለመፍቀዱን በፀጋ የምንቀበለው ይሆን? ወይስ እንዴት አሉታዊ ጎን ብቻ አይተን አጠቃላይ የውጭ ባንክ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንርሳው የምንልበት ጉዳይ ነው? ያጋጠመን የኢኮኖሚ ቀውስ የፖሊሲዎቻችንን አዎንታዊ ገጽታ ወይስ አሉታዊ ገጽታ ያንፀባርቃል? ወይስ በአጠቃላይ ይህ የሃብታም አገሮች አጀንዳ ስለሆነ እኛን አይመለከተንም ብለን፣ ከቀውሱ የዳንነው ድሆች መሆናችን እየለፈፉን፣ "ድሃ መሆንስ ለካስ ጠቃሚ ነው" እያልን ራሳንን እናጽናና? ራሳችን የውስጥ ሃብት አለመፍጠራችንና ኢኮኖሚያችን ራሱን ችሎ አለመቆሙ፣ ሌሎች ያጠፉት ጥፋትም ቢሆን ልንቀጣ እንደምንችል ተምረን፣ የውስጥ ሃብት ፈጥረን መጠናከር እንዳለብን እንገነዘብበታለን? በብድርና በእርዳታ የሚገኝ የውጭ ገንዘብ የሚቀንስም የሚንርም ከሆነ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ምን ያህል የውጭ ኢንቨስትመንት መስክ እንዳለብንስ ያስተምረን ይሆን? ይህ ሁሉ ጥያቄ የምናነሳው በዓለም የተፈጠረው ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው ትርጉምና በኢትዮጵያ የሚፈጥረው ጫና የሚነገርን ስላጣን ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ፤ ይነገረን እንጂ" ይነገረን ስንል እንወያይበትና ተገቢ ትምህርት እናግኝበት ማለታችንም ነው፡፡ አሰራራችን፣ፖሊሲያችን፣ አወቃቀራችን ለማስተካከል የሚበጀን የትኛው ነው ብለን የሚጠቅመንን እንውሰድ፤ የሚጎዳን እናስወግድ፡፡ በዚህ አይነት አሳሳቢ የኢኮኖሚ ቀውስ በሚፍለቀለቅበት ወቅት "ዝምታ ወርቅ" አይሆንም፡፡ መንግስትም ባለሃብትም ህዝብም ሊማርበት ይገባልና" እንነጋገርበት" ይነገረን" |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |