Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "እየሠራን ለሌሎች ምሣሌ...
"እየሠራን ለሌሎች ምሣሌ... E-mail
Sunday, 12 October 2008

Image"እየሠራን ለሌሎች ምሣሌ መሆን እንፈልጋለን"
በዳዊት ታዬ

ዶ/ር አከዛ ጣእመ በአሜሪካን ከ17 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሜላት አባተም ከ10 ዓመታት በላይ ኖረው አሁን አንድ ልጃቸውን ይዘው ወደአገራቸው ተመልሰዋል፡፡

 

በህክምና ሞያ በአሜሪካን ለበርካታ ዓመታት ተምረዋል፤ አገልግለዋል የህክምና ሙያ በአሜሪካን አገር ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ቢሆንም ዶ/ር አከዛ የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ ሳያጓጓቸው ወደአገራቸው ተመልሰው መስራት መምረጣቸውን ይገልፃሉ፡፡

ወደአገር ቤት በመመለሳቸው ብዙ ጓደኞቻቸው ይህንን ያህል ተምረህ ስፔሻላይዝድ አድርገህና ደህና ገንዘብ እያገኘህ አሜሪካ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝልህን ሞያ ትተህ እንዴት ጥለህ ትሄዳለህ ብለው ወደ አገር መመለሳቸውን የሚቃወሙ ሰዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ "ነገር ግን ከአገሬ ስወጣም ሆነ በትምህርት ላይ እያለሁ ወደአገሬ ተመልሼ መጥቼ የአገሬን ሕዝብ አገለግላለሁ የሚል እምነት ነበረኝ" ይላሉ፡፡

ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ጥሩ እንዲማሩና ውጤት እንዲያመጡ በብርቱ የረዳቸው ይኸው አገራቸው ገብተው ወገናቸውን አገለግላለሁ የሚለው እምነታቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ይህንንም እምነት ይዘው ቅዱስ ያሬድ ጠቅላላ ሆስፒታልን ሲሳይ ሽመልስ ከተባለ ወዳጃቸው ጋር በመሆን በጋራ ለማቋቋም አስችሏቸዋል፡፡

የዶ/ር አከዛ ባለቤት ወ/ሮ ሜላት በአሜሪካ ቆይታቸው በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ወስደው በአራት የተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ወደአገራቸው እንዴት እንደተመለሱ ሲገልፁ "ወደአገሬ ለመመለስ እኔም ፍላጐት ነበረኝ ግን የባለቤቴ ምኞትና አገሩ ገብቶ የመሥራት ጉጉት በቶሎ እንድመጣና በተማርኩት ትምህርት ባለቤቴንም ወገኔንም እንዳግዝ አድርጐኛል፡፡" ይላሉ፡፡

ዶ/ር አከዛ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆስፒታል ለመክፈት የወሰኑት ከ7 ዓመታት በፊት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ሆስፒታል ወደማቋቋሙ ከመግባታቸው በፊት ቅዱስ ያሬድ በሚል መጠሪያ አንድ ክሊኒክ አቋቁመው በመመላለስ ይሰሩበት ነበር፡፡ ክሊኒኩ ለሆስፒታሉ መሠረት የሚሆን ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ወደ አገር ቤት ከመጡ አንድ ዓመት የሆናቸው ቢሆንም በሲኤምሲ አካባቢ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ያሉትን ሆስፒታል የሚያስፈልገውን መሣሪያ ግዥና ተከላ ለማካሄድ የወሰደባቸው በወራት የሚቆጠር ጊዜ እንደነበርም ከገለፃቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ለሆስፒታል የሚሆነውን ህንፃ ያገኙት በኪራይ ነው፡፡ ይህ የተከራዩት ህንፃ ለሆስፒታል ተብሎ የተገነባ በመሆኑ ብዙም ችግር አላጋጠማቸውም፡፡ በጥቅሉ እስካሁን ድረስ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገውበታል፡፡

እንደ ዶ/ር አከዛ ገለፃ ይህ ሆስፒታል 80 አልጋዎች ይኖሩታል፡፡ አዳዲስ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥም እንደሆነና ለዓመታት ያለፉበትን ትምህርትና በአሜሪካን አገር ለህክምና ያካበቱትን ትምህርት በሚከፍቱት ሆስፒታል ውስጥ ሆነው ወገናቸውን ለማገልገል ማዋላቸው ደግሞ ትልቅ እርካታ የሚፈጥርላቸው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ሆስፒታሉ ሥራ ሲጀምር 100 የሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ውስጥ በትርፍ ጊዜ የሚሠሩትን ጨምሮ 20 የሚደርሱ ዶክተሮች ይኖሩታል፡፡  ከዚህም ሌላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ ይህ ማስፋፊያ ሥራም የሠራተኞቹን ቁጥር 200 ያደርሰዋል፡፡

ሆስፒታሉ ለየት ከሚልባቸውና አዲስ አገልግሎት ናቸው ተብለው ከሚታመንባቸው ውስጥ የኩላሊት ዝውውር ህክምና አንዱ ነው፡፡

እንደ ዶ/ር አከዛ ገለፃ "እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት በአፍሪካ ውስጥ የሚሰጠው በደቡብ አፍሪካና በኬንያ ውስጥ ብቻ ነው"፡፡

ይህንን አገልግሎት ለማስጀመርም ከአንድ የህንድ ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን እየሠሩም መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ አሜሪካን አገር ከሚገኝና አራት ሺህ ዶክተሮች ካሉት ግዙፍ ሆስፒታል ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት በመደረጉም በአገራችን ህክምና ውስጥ አዳዲስ ነገሮችን ለማስተዋወቅ የሚረዳንን ሥራ እንድንሠራ ያደርገናል ይላሉ፡፡

አዳዲስ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ "በተለይ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እዚህ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ጥሩ ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ አዲስ አሠራር ይጀመራል፡፡ ይህም አዲስ አሠራር ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ በየወሩ ሃያ አምስት ዶላር ለሆስፒታሉ ይከፍላል፡፡ በዚህ ክፍያ መሠረትም እዚህ ያለው ቤተሰብ ሙሉ ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ ይችላል፡፡ ይህ አሠራር የኢንሹራንስ ህክምና እንደማለት ይቆጠራል" ያሉት ዶ/ር አከዛ ይህንን አሠራር ቀደም ብሎ በክሊኒካቸው የጀመሩትና ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በአሠራሩ ተደስተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉም ነው፡፡

ይህ አሠራር ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ቤተሰቡን በቀላሉ ከማገዝ ባለፈ ለአገሪቱም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል ያምናሉ፡፡

ሆስፒታላቸው የክፍያ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችልም ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ዶ/ር አከዛ በሰጡት መልስ "ዋናው አላማችን ገንዘብ አይደለም፡፡ ገንዘብ ብፈልግ ዛሬ እዚህ አልመጣም፡፡ በአሜሪካን አገር በአራት የተለያዩ ግዛቶች በፈለኩበት ሰዓት የምሠራበት ፈቃድ አለኝ፡፡ በህክምና እዚያ የሚከፈለው ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ስመጣ ወገኔን ለማገልገልና ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ነው" ብለዋል፡፡

"ነገር ግን ይህንን ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ ቀጣይነት ሊኖርህ ይገባል፡፡ አገልግሎታችንን በአግባቡ ለማካሄድ የሚያስፈለገውን ገንዘብ ማግኘት ከተቻለ በቂ ነው፡፡" ይላሉ፡፡

"እኛ ጋር ሊታከም የሚመጣ ታካሚ አቅሙ ሳይፈቅድለት ታካሚው እንዲመለስ አንፈልግም፡፡ ሁሉንም ሊያስተናግድ የሚችል ዋጋ ይኖራል፡፡ ከተማ ውስጥ ለህክምና አገልግሎት ከሚከፈለው ዋጋ ያንስ ይሆናል እንጂ አይበልጥም፡፡"

በሥራቸው ብዙ ነገር ሊያጋጥም እንደሚችል  የሚናገሩት ዶ/ር አከዛ እኛ አገር ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ የሠራተኛውን የሥራ ባህሪ ለየት ያለ እንዳደረገው ጠቁመው "ስራ ማክበር በኛ ባህል ገና ስር የሰደደ አይደለም፡፡ ትንሽ የሥራ ዲስፒሊን ላይ ችግር ይገጥምሃል፡፡ ትንሽ ያስቸግራል ቢሮክራሲም አለው፡፡" ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ሜላትም ለሆስፒታሉ የሚሆኑ ባለሙያዎችን ለመቅጠር በተደረገ ጥረት ብዙ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህንንና ሌሎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ተቋቁሞ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠትና ውጭ ያዩትን ልምድ በአሜሪካን በሞያቸው በሰሩባቸው ቦታዎች ያካበቷቸውን ጥሩ ልምዶች እዚህ በመተግበር አንድ ለውጥ እንደሚያመጡ ያምናሉ፡፡ በዚህ ሆስፒታል እርሳቸው የሆስፒታሉ አስተዳዳሪ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ዶ/ር አከዛ ደግሞ ሜዲካል ዳይሬክተር፡፡

"በመንግሥት በኩል እንደሚመስለኝና እንደማየው ከላይ ነገሮችን ለማስተካከል በጐ ነገር አለ፡፡ ታች ስትሄድ ግን ያለአግባብ ብዙ ነገሮች ይጓተታሉ፡፡ ይወሳሰባሉ፡፡ ለምሣሌ ኒዎርክ ሄደህ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ምን እንደሚያስፈልግህ ዌብሳይታቸው ላይ ገብተህ ማሟላት ያለብህን ነገር ታያለህ እሱን እስካሟላህ ድረስ ተጨማሪ ነገሮች አያስፈልጉህም፡፡ እዚህ አገር ግን ይህንን ለማድረግ ምንድነው የሚያስፈልገኝ ስትል በግልፅ አይነገርህም፡፡" ያሉት ዶ/ር አከዛ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር መለወጥ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

"እዚህ አገር አንተ ስትሄድ የሚሰጥህ መረጃና እኔ ስሄድ የሚሰጠኝ መረጃ የተለየ ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ የሚሰጥ መረጃ የተለያየ ነው፡፡ አሠራሩ ወጥ አለመሆኑ ለእድገት እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ያለንበት የየራሳችን አሠራር ዘመናዊ በማድረግ አገልግሎት መስጠት ይኖርብናል፡፡"

"ዲያስፖራን በሚመለከት ላቀረብነውም ጥያቄ ሁሉም ሰው አገሩ መመለስ ይፈልጋል፡፡ አንድ መንገድ ላይ የምታገኘው ኢትዮጵያዊ ዛሬ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ ቢደርስህ ምን ታደርጋለህ ብትለው ወዲያው ሊናገር የሚችለው ወደአገሬ እመለሳለሁ የሚለውን ነው፡፡" ይላሉ፡፡  

"ሁሉም መመለስ ይፈልጋል፡፡ አንዳንዱ ምን ይዥ እገባለሁ ይላል፣ አንዳንዱ ደግሞ ትምህርትም ገንዘብም ይዞ ወደ አገር ቤት መመለስ ጨለማ የሚሆንበት አለ፡፡ ወደ አገር ቤት መመለስ ከባድ ነው መሥራት አትችልም የሚል ወሬ ይሰማል፡፡ እኛ እንግዲህ እየሠራን ለሌሎች ምሣሌ ለመሆን ነው የምንፈልገው፡፡"

"አገራችን ነው፡፡ ችግር አለ እንቅፋት አለ፡፡ ግን ያንን ችግር መቅረፍ የምንችለው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን፡፡" በማለት መጥተናል፡፡ ሌሎች አዲስ ስራዎችን መስርት ለሚፈልጉ እየመጡ ቢሞክሩት ውጤት እንደሚያመጡ ይመክራሉ፡፡

"በእኛ ሆስፒታል ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች እንዲመጡ እናደርጋለን እንዲያዩት እንፈልጋለን፡፡ ትንሽ ጊዜም ቢሆን እየመጣችሁ ስሩ ከወደዳችሁት ሙሉ ለሙሉ እዚሁ ሆናችሁ ትሠራላችሁ እያልን ነው፡፡" ያሉት ዶክተሩ በእነሱ ግፊት የመጡም እንዳሉ አሳውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለ28 ዓመታት ውጭ የነበረ አንድ ዶ/ር እንዲመጣ አድርገው እዚህ ያለውን ሁኔታ አይተው ከሌሎች ሠዎች ጋር ሆነው ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው ለመምጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የወይዘሮ ሜላት አስተያየትም ከባለቤታቸው ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ነገር ግን ወደዚህ መመለስ "በእርግጥ በጣም ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፡፡ ይላሉ ነገር ግን ከመጣሁ በኋላ ግን ወድጀዋለሁ፡፡ በተለይ ልጅ ላለው ሰው በሴትነቴም በእናትነቴም የምመክረው አሜሪካ ውስጥ ልጅ ማሳደግ ከባድ ነው፡፡ እዚህ ደግሞ የተሻለ ነገር ታያለህ የምታጣው ነገር ቢኖርም በአገሬ መስራቴ እርካታን ይፈጥርልኛል፡፡ ስለዚህ መመለሳችን ለዚህም ጠቅሞናል፡፡ በኑሮህ ላይም ደስታ ይጨምራል፡፡ ባይ ናቸው፡፡

ዲያስፖራን በተመለከተ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባና ይገባል የሚሉት ዶ/ር አከዛ እና ወ/ሮ ሜላት ዲያስፖራው እስኪለመድ ድረስ የተቻለውን እርዳታ ቢያደርግ እንደሚመረጥ ዲያስፖራው ሲመጣ ከሌላው የተለየ ጥቅም ይሰጠው ጠቃሚ ሥራዎችን እንዲሠራ ቢሮክራሲው ሊቀልለት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ሳይሆን ለዲስፖራው ደግሞ የማስተላልፈው ደግሞ መጥታችሁ እዩት ነው፡፡
Last Updated ( Monday, 13 October 2008 )
 
< Prev   Next >