| ድህነትን የሚያውቅ ሀብታም... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
ድህነትን የሚያውቅ ሀብታም ድሀን አይረሳም
ከባለቤታቸው ሞት በኋላ የአምስት ልጆች እናት ለሆኑት ለሚስተር ዎልተርማን እናት ህይወት ቀላል አልነበረችም፡፡ ቤተሰባቸው በድህነት ብዙ ተሰቃይቷል፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችንም አሳልፏል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የህጻንነት ዕድሜያቸውን በችግር ያሳለፉት ሚስተር ዎልተርማን ግን ድሀ ሆነው አልቀሩም፡፡ ሕይወትን ተጋፍጠው አሸንፈዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የ67 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኝህ ሰው በአመት ከ120 - 140 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚያንቀሳቅሱ እና ከ250 ሰራተኞች በላይ ያሏቸው የአምስት ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ኩባንያዎቹ ኩባንያው ጀርመን ውስጥ የሚያመርተውን በብዙ ሺ ቶን የሚቆጠር የተጣራና ያልተጣራ ብረት ወደ ቻይና፣ ሕንድና ቱርክ ይልካል፡፡ "ኤር ባስ" ለተባለው ታዋቂ የአውሮፕላን አምራች ድርጅትም በየወሩ 500 ቶን ያህል አልሙኒየም ብረታ ብረታ ያቀርባል፡፡ ይህንን ትልቅ ድርጅት የሚያስተዳድሩት ሚስተር ዎልተርማን የሚያገኙት ደመወዝ ከፍተኛ ነው፡፡ ሰውየው ከድህነት ወደ ሀብታምነት የተሸጋገሩ ቢሆንም "ድህነትን" አይረሱም፡፡ ለዚህም ይመስላል ድሀዎችንና አካል ጉዳተኞችን ባገኙ ቁጥር ከመርዳት የማይመለሱት፤ "የመጣሁበትን አልረሳም" ይላሉ ሚስተር ዎልተር፡፡ ሚስተር ዎልተርማን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከ11 ዓመት በፊት አዲስ አበባ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ጓደኛቸው እንዲጎበኙት በጋበዛቸው ጊዜ ነበር፡፡ አዲስ አበባ በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ አክሱም ሆቴል አርፈው የነበሩት እኝህ ጀርመናዊ አንድ ቀን ካረፉበት ሆቴል እንደወጡ ከሆቴሉ ፊት ለፊት በሚገኝ ቦታ ላይ ወደ ተቀመጠ አንድ ሊስትሮ ሄደው ጫማቸውን ማስጠረግ ጀመሩ፡፡ ትንሽም ቆይተውም ጫማቸውን የሚጠርግላቸው ታዳጊ ህፃን እንግሊዝኛ መናገር ይችል እንደሆነ ጠየቁት፡፡ እርሱም እንደማይችል ነገራቸው፡፡ የሊስትሮውን "ኖ" የሚል ምላሽ የሰሙት ሚስተር ዎልተርማን የጫማ ማስቀቢያ ሂሳብ ብቻ ከፍለው አልተለዩትም፡፡ ልጁን ወደ ጀርመን ት/ቤት ወስደው በማስመዝገብ በራሳቸው ወጪ ጀርመንኛና እንግሊዝኛ እንዲማር አደረጉት፡፡ ሚስተር ዎልተርማን በዚህ ብቻ አላቆሙም፡፡ ይህ ሄኖክ ኪሮስ የተባለ ታዳጊ ሕጻን 18 ዓመት ሲሞላው መንጃ ፈቃድ አውጥቶ የራሱ ታክሲ ባለቤት እንዲሆን አስችለውታል፡፡ ከትምህርት ቤት እስከ ታክሲ ግዢ ያለውን ሙሉ ወጪ የሸፈኑትም ራሳቸው ናቸው፡፡ ምስጋና ለዎልተርማን ይግባቸውና የቀድሞው ሊስትሮ ሄኖክ አሁን የተስተካከለ ህይወት መምራት ችሏል፡፡ ድሀን መርዳት የሚያስደስታቸው እኝህ ግለሰብ ባለፉት 11 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 3 ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ወደ አገሪቱ በመጡባቸው በነዚህ ጊዜያት ድሀዎችንና አካል ጉዳተኞችን ሳይረዱ አይመለሱም፡፡ ![]() ሚስተር ዎልተርማን ከአካል ጉዳተኞች ጋር ባለሀብቱ የፈጸሙት በጎ ተግባር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አክሱም ሆቴል ውስጥ ሙዚቃ የሚጫወት ታምራት የተባለ አይነ ስውር ወጣት ነበር፡፡ በሆቴሉ በሳምንት ሁለት ጊዜ ረቡዕና ቅዳሜ በሚያከናወነው የእራት ዝግጅት ላይ ተገኝቶ ሙዚቃ የሚጫወተውን አይነ ስውር የተመለከቱት ሚስተር ዎልተርማን ቀርበው አነጋገሩት ሚስተር ዎልተር አይነ ስውሩን ወጣት አነጋግረውት ብቻ አልቀሩም፡፡ ወጣቱ መፃፍና ማንበብ ይችል ዘንድ የብሬል ማሽን ገዝተው ሰጥተውታል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ቁጥርም ከአምስት ሺ እስከ አስር ሺ የሚደርስ ብር እንደሚሰጡትም ይናገራሉ፡፡ "ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያስተካክሉበት እድል ሲከፈትላቸው ማየት ያስደስተኛል" ይላሉ ሚስተር ዎልተር፡፡ "በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በርካታ አካል ጉዳተኞች ይታያሉ፡፡ ወደፊት እነኝህን አካል ጉዳተኞች ለመርዳት አቅደዋል?" ለሚለው ሲመልሱ "አዎ" በአሁኑ ሰዓት ዊልቸርና ክራንች የያዘ ኮንቴይነር እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ ኮንቴይነሩ ጅቡቲ ደርሷል፡፡ በያዝነው ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ ይደርሳል ብለን እናምናለን" በማለት ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡትን እርዳታ እንደሚቀጥሉበት ይናገራሉ፡፡ ችግረኞችን ከመርዳት በተጨማሪ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ይወዳሉ፡፡ ጀርመን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸው ግንኙነትም የጠበቀ ነው፡፡ በጀርመን አገር የሚገኝ የአንድ የብረት አምራች ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ከሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ እና እዚያው አገር ውስጥ አቢሲኒያ የተባለ ሬስቶራንት ባለቤት ከሆኑ ኢትዮጵያዊት ጋር ጥሩ ወዳጅነት መሰርተዋል፡፡ ሚስተር ዎልተርማን የሚያስተዳድሩት ኩባንያ በየዓመቱ ፓርቲ ያዘጋጃል፡፡ በዚህ ፓርቲ ላይ ደንበኞች የሚጋበዙ ሲሆን ኩባንያው መርከብ ተከራይቶ ደንበኞችን ለአምስትና ስድስት ሰዓት ያህል በባህር እያንሸራሸረ ያዝናናቸዋል፡፡ ጀርመናውያኑን ደንበኞች ለማንሸራሸር በተዘጋጀው መርከብ ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ተሰቅሎ የሚያይ ሰው በሁኔታው ሊገረም ይችላል፡፡ ሚስተር ዎልተርማን ግን አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይወዳሉና፡፡ ![]() ዐይነ ስውሩ ታምራት ሚስተር ዎልተርማን ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ወንድ ልጅ ባለመውለዳቸው ቅር ይላቸዋል፡፡ "ወንድ ልጅ ቢኖረኝ ኖሮ የእኔን ፈለግ ተከትሎ የኩባንያውን ቢዝነስ ሊያንቀሳቅስ ይችል ነበር፡፡ ሴቶቹ ልጆቼ ለስራው ብዙም ፍላጎት የላቸውም፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ልጆቼ አብረውኝ ይመጣሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |