Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የተፈራው ደረሰ!!፡-
የተፈራው ደረሰ!!፡- E-mail
Sunday, 12 October 2008

አዋጅ ቁጥር 603
በአዲስ ሕብረት

ሦስተኛው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ አመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ የመስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም አጀንዳ የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳይ "የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ መርምሮ ማጽደቅ" ነበር፡፡ በዚያው በምክር ቤቱ ከሞላ ጎደል ሁልጊዜም በተለመደ አሰራር መሰራት ከላይ በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት አጀንዳ ራሱ ወዲያውኑና እዚያው ስለ "መርምሮ ማጽደቅ" መናገሩ እራሱን የቻለ አንድ ችግር ነው፡፡ የአገሪቱን የሕግ አወጣጥ ስርዓት በዝግታ የመሞከር (ዴሊበሬሽን) "ፍጥነት" ለአላስፈላጊና ምንም ዓይነት ምክንያት ላልተሰጠው ጥድፊያ መዳረግ ነው፡፡

 

የመስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም የምክር ቤቱ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ያስተናገዳቸው የአምስት የረቂቅ አዋጆች ጉዳይ ሲሆን ከመጀመሪያው "የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ መርምሮ ማጽደቅ" ከሚለው በስተቀር የሌሎቹ አራት ረቂቅ አዋጆች አጀንዳ የተቀረጸው "መርምሮ ወደሚመለከተው ኮሚቴ መምራት" ተብሎ ነው፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ የአፍሪካ ኢነርጂ ኮሚሽንን፣ የአፍሪካ ጥቅማ ጥቅሞችና ልዩ መብቶች ጠቅላላ ኮንቬንሽን ተጨማሪ ፕሮቶኮልን፣ የአፍሪካ ማዳበሪያ ልማት ማዕከል ማቋቋሚያ ኮንቬንሽን ለማቋቋም በአፍሪካ አገራት መካከል የአፍሪካ ቴክኒክ ትብብር መርሃ ግብርን መመስረት ኮንቬንሽን እነዚህን ሁሉ ለማጽደቅ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች "ተመርምረው ወደሚመለከተው ኮሚቴ" ተመሩ፡፡ የመጀመሪያው አጀንዳ ግን በቀረበበት የመጀመሪያ ቀን ወዲያውኑ ፀደቀ፡፡ አንደኛው "ተራ"ው ችግር ይህ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሌሎች በርካታ ችግሮችም አሉ፡፡

ከነዚህ መካከል አንዱና አስፈፃሚው አካል ሳያሰልስ በየአመቱ ብቻ ሳይሆን በዚያም መካከል የማያበራ ጥያቄ የማሻሻያ ረቂቅ ሕግ እያቀረበ አፅድቁልን የሚልበት ዋነኛው መደበኛ አድርጎ የያዘው ጉዳይ የራሱ የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ይህ አሁን ይሻሻል ተብሎ ማሻሻያ የቀረበበት ሕግ አሁን መስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም እንደገና ሲሻሻል ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እነሆ ከአስር ጊዜ በላይ ነው፡፡

አገራችን ዋናው ዓይተኛውና ሁነኛው የፖሊሲ ይዘት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ደጋግማ በመንግሥት አማካኝነት ቃል ለምድር ለሰማይ የገባችበት ሌላው ጉዳይ የማስፈጸም ብቃትን ማጎልበት ማጥራትና ማስላት ነው፡፡ አስፈፃሚውን አካል ግን በአንድ ፓርቲ የሥልጣን ዘመን ውስጥ ሲሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አለዚያም ጥቂት ርቀት ሊያስኬድ የሚችል አኳኋን አደራጅቶ ወደመደበኛው ስራዋ መግባት አልቻለችም፡፡ ዋናውን የማስፈጸም ስራ የሚሰራውን አስፈፃሚ አካል መልክና መዋቅር ደጋግሞ እየሞከሩ መፈተሽ ዋነኛውን ስራ የተካው ዋናው ሥራ ሆኗል፡፡ ከዚህም የተነሳ በየአመቱ ብቻ ሳይሆን በዚያም መካከል "የአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል" የሚለውን የመንግሥት/የአስፈጻሚውን አካል ማስታወቂያ ማየት መከታተል የማይችሉት እግር በእግር ቆጥረው የማይዘልቁት ከባድ ተግባር ሆኗል፡፡

ችግሩ "የሪከርድ"ና ወይም የእስታቲስቲክስ ጉዳይ ብቻ ሆኖ ግን ሊቀር አልቻለም፡፡ ለራሱ ለአስፈፃሚው አካል ለያንዳንዱ የመንግሥት የአስተዳደር መስሪያ ቤትም የሚያስቸግርና የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ ለእቅደች ያስቸግራል፣ በእቅድ ላይ ይባረቃል፣ የበጀት ዲሲፕሊንን ይፈታተናል፣ በሰው ኃይል አጠቃቀም ላይ ብኩንነት ያስከትላል፣ ለሰራተኛው የስራ ዋስትና፤ ለአሰሪው የእቅድ እርግጠኝነትን ለሌላ  "የተፈጥሮ ኃይል" የ"እግዚአብሄር ቁጣ" ይዳረጋል፡፡

"ንጉሥ" ለሚባለው ደንበኛና ተገልጋይ ሕዝብም ያንኑ ያህል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የመንግሥት መዋቅር፣ አደረጃጀት አሰራር አላስተማምን እንደሚለው ዝናባችን አንጋጠው የሚያዩት፣ የሚለማመኑት ከዚያም በላይ እንደ አሜሪካው የ"ዳውጆንስ አቬሬጅ" በየቀኑ የሚጠያየቁት ሆኗል፡፡

አንድ መለስተኛ ሌላ "ተራ" ነገር ልጨምር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ4ኛው ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የመስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም አጀንዳ ተራ ቁጥር አንድ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ መርምሮ ማጽደቅ የሚል በአንድ ግማሽ ቀን ቀርቦ የሚፀድቅ ስራ ሆኖ የቀረበው ከሁሉም በላይ ሁሉንም እውነት እውነቱን በሙሉ እንዲናገር ሆኖ አይደለም፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም አደረጃጀትን በሚመለከት የኢፌዴሪ "አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል ስለተዘጋጀው አዋጅ ረቂቅ የቀረበ አጭር መግለጫ" በዚህ ጽሁፍ ዋናውና አደገኛው ጉዳይ አድርጎ የሚቀርበውን ዓቢይና መሰረታዊ ነገር አደባባይ ያወጣው "በተጨማሪም"". ብሎ፣ የሌላው ነገር ተቀጽላ የመናጆ ወይም የ"ግዳጅ" ዕቃ አድርጎ ነው፡፡ ዋናውና መሰረታዊው ጉዳይ ግን ለሁሉምና ከምንም በላይ እሱ ነው፡፡

"የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው" ደንብ በማውጣት ነባር አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ ወይም ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን እንዲኖረው ለማስቻል በረሚሻሻለውሪ አዋጅ ክፍል አራት ስር አዲስ አንቀጽ 34 ተጨምሯል፡፡ ይህም ያስፈለገው በመካሄድ ላይ ያለው መሰረታዊ የተቋማዊ ለውጥ ሂደት የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከልን ስለሚጠይቅ በየጊዜው የአዋጅ ማሻሻያ ማቅረብ ሳያስፈልግ የሚፈለገውን ማስተካከያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በማጽደቅ በተቻለ ፍጥነት ወደትግበራ ለመግባት እንዲቻል ሲባል ነው" የሚል ሕገመንግሥታዊ አደጋ የሚያስከትል "ተልካሻ" ምክንያት ያለው ታላቅ ጉዳይ የቀረበው ራሱን የቻለ አጀንዳ ሆኖ ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም አደረጃጀት ውስጥ ተሸፍኖ ቢያንስ ቢያንስ የሱ ተቀጽላ ሆኖ ነው፡፡

"የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ቁጥር 471/1998 ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ" የሚለውና ከዚያ በላይ ምንም የማይናገረው ተጨማሪ ማብራሪያም ሆነ የፖሊሲ መግለጫ የሌለው መስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም የፀደቀው ማሻሻያ አዋጅ የአንድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ይባል የነበረ የመንግሥት መስሪያ ቤትነት ከፍ አድርጎ ለማደራጀት ብቻ የወጣ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይና ከሁሉም ይበልጥ "የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት ነባር አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ፣ እንዲከፋፈል ወይም ተጠሪነቱ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ስልጣን" ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሰጠነው በራሱ በተሻሻለው አዋጅ መግቢያ ያልተጠየቀ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ቦታ ያልተሰጠው የዚህ ምክንያት "በመካሄድ ላይ ያለው መሰረታዊ የተቋማዊ ለውጥ ሂደት የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከከልን ስለሚጠይቅ"". ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ "በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከልን" የሚጠይቀው የመሰረታዊ የተቋማዊ ለውጥ ሂደትና የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት "".በየጊዜው የአዋጅ ማሻሻያ ማቅረብ ሳያስፈልግ የሚፈልገውን ማስተካከያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በማጽደቅ በተቻለ ፍጥነት ወደትግበራ ለመግባት "እንዲቻል ሲባል" ጭምር ነው፡፡ አንዱ በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከል ይጠይቀዋል፡፡ ሌላው በተቻለ ፍጥነት ወደ ትግበራ መግባት ይቻል ዘንድ ከ"ለብለብ" በላይ ሌላ ተጨማሪ ምርመራና ቁጥጥር አያስፈልገውም፡፡

መሰረታዊና ሕገመንግሥታዊ መርህ አተረማምሶ የሚያስከትለው አደጋ እንዳለ ሆኖ የዚህ የተሻሻለ ሕግ ገጽታ ቢያንስ ቢያንስ እንዳማረበት ትንሽ መራመድ ይችል የነበረው ዋነኛውን ማሻሻያ እርሱ ራሱ አድርጎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም አደረጃጀት ለውጥ ያው እንደተፈለገው በሚኒስትሮች ምክር ቤት "አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት"" ወደሚኒስቴር መ/ቤትነት ቢለውጠው ነበር፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት ስልጣኔ "የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት" ሥራ እኔ እሰራ ዘንድ በዚህ ሕግ ሥልጣን ይሰጠኝ ማለቱ ምን ችግር አለው? ለምን አደገኛ ነው ተባለ? የሚለው ጥያቄን የአገር ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም እስከ ዛሬ ድረስ አገሪቷን አጋጥመዋት ከነበሩት ችግሮች ጋር ሲነፃፀር በ1997 ዓ.ም ተደረገ ከተባለው ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ ቀጥሎ ይህ አምሳያ የሌለው አካሄድ የአገር አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለምን እና እንዴት?

የመጀመሪያውና በአንጻራዊነት መለስተኛው ችግር እና አደጋ የራሱን የመንግሥትን የአስፈጻሚውን አካል አልሳካልህ፣ አልሆንልህ ባይነትና ፍርጃ በሕግ መመረቅ መሆኑ ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ቢፒ አር እየተባለ ከአስር ጊዜ በላይ የአስፈጻሚው አካላት ስልጣንና ተግባር እየፈረሰ እንደገና ተገነባ እየተባለ ነገሩ ሁሉ "የእንቧይ ካብ" ሆኖ ቆይቷል፡፡ አስፈጻሚው አካል አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከ1987 ዓ.ም ጊዜ ጀምሮ እንኳን በየአመቱና በዚያ መካከል ሁሉ "ሳስበው ሳስበው ደከመኝና ተውኩት" ቢልም የሚቆጣጠረውና ለምን ብሎ የሚጠይቀው መጥፋቱ አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ እንደገና "በመካሄድ ላይ ያለው መሰረታዊ የተቋማዊ ለውጥ ሂደት የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በጥልቀት መፈተሽና ማስተካከልን ስለሚጠይቅ" የሚል ምክንያት ተሰጠ፡፡ ስለዚህም "በየጊዜው የአዋጅ ማሻሻያ ሳያስፈልግ የሚፈለገውን ማስተካከያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በማጽደቅ በተቻለ ፍጥነት ወደ ትግበራ ለመግባት እንዲቻል ሲባል" የተወካዮች ምክር ቤት ራሱ በውክልና ያገኘውን ሕግ የማውጣት ሥልጣን አሳልፎ ሊያስረክብ እጅ ሰጥቶና ተማርኮ ሊገብር ይገባል ተባለ፡፡ ይህም እሺ ተባለ፡፡ አዋጁም በአንድ ቀን ጀምበር በጥቂት የስራ ሰዓታት ውስጥ ፀደቀ፡፡ ይህ ከሁሉም አስቀድሞ የአስፈጻሚውን አካል የተደጋጋሚ አልሳካ ያለ ሙከራ በሕግ ማጽደቅ ነው፡፡

ትልቁና ዋነኛው ችግር ግን ይህ አይደለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዚህ አገሪቷ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ፍጡርና ተጠሪ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የማውጣት ስልጣን በቀጥታ ከሕገመንግሥቱ አንቀጽ 77/13 የሚመነጭ ሳይሆን "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሰረት" በእያንዳንዱ ሁኔታና ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የተወካዮች ምክር ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የማውጣት "የነጻ እርምጃ" ፈቃድ ሊሰጠው አይችልም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊፈጥር አይችልም፡፡

ይህንን ጥቂት ዘርዘር አድርጎ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ ሉዓላዊነት መነሻና መሰረት የሕዝብ ሉዓላዊነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት መግለጫም ሕገመንግሥቱ ነው፡፡ ሉዓላዊነቱ የሚገለጸው በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን (የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነውና) ከሕዝብ በውክልና የተገኘ የተሰጠ ነው፡፡ ምክር ቤቱ የሕዝብን የውክልና ሥልጣን ሳይጥስ አሁን እንዳደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤትን አድራጊ ፈጣሪ ሊያደርገው አይችልም፡፡

አንድ አጭርና ምናልባትም ከላይ ከላይ ሲያዩት ሊያስደነግጥ የሚችል ምሳሌ ላቅርብ፡፡ ሁሉም በአንድ አምላክ የሚያምኑ ሃይማኖቶች በእግዚአብሄር ከሀሌ ኩሉ ሥልጣን ላይ ያላቸው የፀና አቋም የታወቀና አንድ ዓይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በፊትም ማንም ያልቀደመው ከዚያ በኋላም ማንም የማይከተለው፣ የማይተካው አሀዱ አምላክ ነው፡፡ ለሥልጣኑ ወሰን ገደብ የለውም፡፡ ይህን የመሰለ ፍፁም ስልጣን ያለው አምላክ ራሱ እግዚአብሔርም ቢሆን ፈጽሞ የማይችለው ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር ሌላ እግዚአብሄር መፍጠር አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ሌላ ተጨማሪ እግዚአብሄር መፍጠር የማይችለው ከኔ በስተቀር ሌላ አምላክ አታምልክ ከኔ ሌላ ሌላ አምላክ የለም የሚል መሰረታዊና እርሱ ራሱ የማይሽረው መሰረታዊ ህግ ስላለው ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት ግን ከሕዝብም ከእግዚአብሄርም በላይ ሆኖ ሌላ የተወካዮች ምክር ቤት መፍጠር እችላለሁ አለ፡፡ ራሱን ሳያጠፋ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ሳያፈርስ ግን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን ሥልጣን መስጠት አይችልም፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ከሚዘረጋበት የተፈቀደ ክልል አለማውጣቱን መቆጣጠር ሕግ ከማውጣት እኩል መሰረታዊ ተግባሩ መሆኑን ማረጋገጥ ሲገባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውና በራሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት በሚወጣው ነጋሪት ጋዜጣ ደንቦች "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሰረት" መሆኑን በዚህ መሰረት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠው ውስን ውክልና ከመስመር አለመውጣቱን መቆጣጠር በተገባው ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸው ደንቦች ሁሉ "የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 471/1998 አንቀጽ 5" እና በሌላ አንድ ሥልጣን መስጫ አዋጅ መሰረት የወጡ አይደሉም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የማውጣት ሥልጣን ያለው መሆኑን ለማረጋገጥና ሥልጣን ያለው መሆኑን ለማረጋገጥና በዚህም መሰረት ሕግ ተብሎ የሚጠራ የሚፀና ደንብ ለማውጣት የሚያስፈልገው የይለፍ ቃል (ፖስወርድ) የሕገመንግስቱ አንቀጽ 77 (13) ወይም አዋጅ ቁጥር 471/98 አንቀጽ 5 ወይም ሁለቱም ብቻ አይደለም፡፡ በያንዳንዱ ጉዳይ የሕዝብ ተወካዮች የሰጠው  የውክልና ሥልጣን መኖሩን መጥራትና ማረጋገጥ አለበት፡፡ ብዙዎች ደንቦች ያወጡት ግን ያለዚህ ነው፡፡ እነዚህ ያሉት ችግሮች ያለ ጠያቂ በቀሩበት ወቅት ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱን የ2001 የሕግ ማውጣት መርሀ ግብር ስንሰማ በተለይም

የመንግሥት አመራርና አገልግሎትን ለማሻሻል በተለይ ደግሞ ከሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ተግባራዊነት ጋር በማዛመድ የተለያዩ የመንግሥት አደረጃጀት ለውጦች በሚያስፈልጉበት ጊዜ መንግሥት የተቀላጠፈ አሰራር እንዲከተል ማድረግ ይችል ዘንድ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል"

ሲሉ ጉዳዩ ከሩቅ ሸትቶን የደነገጥነውና ሰሚና ሃይ ባይ ቢኖር ብለን ያስጠነቀቅነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በእርግጠኝነት ከታወቀው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ካመላከተው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ተለዋጭ የአደረጃጀት ለውጥ በተጨማሪ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አደረጃጀትን መቀየር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ መስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም ተነግሮናል፡፡

"እድሜ (ሥልጣኑን አሳልፎ ለሰጠው) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ ከዚህ በኋላ የተወካዮች ምክር ቤትን መሰብሰብ ሳያስፈልግ የማስታወቂያ ሚኒስቴርን እንዳሻው ማደራጀት በማደራጀት ሂደት ውስጥም በሌላ አቢይና ዓይነተኛ ሕግ ያልነበር ሥልጣን መስጠት ይቻላል፡፡

ብዙዎች ይህንን ጽሁፍ ሲያነቡ የፀሐፊውን ስጋት ሲሰሙ ምን ልዩነት አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ ያው ነው ማለታቸው አይቀርም፡፡ እኔ ግን ወርቁ ቢጠፋ ለምን ሚዛኑ ይጥፋ ባይ ነኝ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ የኢትዮጵያ "እግዚአብሄር ሌላ እግዚአብሄር ፈጠረ"፤ ከኔ በስተቀር ሌላ አምላክ አታምልክ ከኔ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም ሕግ ተሻረ፡፡
 
< Prev   Next >