Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ስለውርስ አለመነጣጠል
ስለውርስ አለመነጣጠል E-mail
Sunday, 12 October 2008

ሁሉም የውርሱ ባለገንዘቦች ከተከፈላቸው በኋላ የንብረት ማጣራት ሂደቱ ያከትማል፡፡  ከዚህ ንብረት ማጣራት ማክተም በኋላ የሚቀር የውርስ ንብረት ይባላል፡፡ ይህ ንብረት የውርሱ አከፋፈል እስኪፈፀም ድረስ በወራሾቹ መካከል ውርሱ ሳይነጣጠል ይቆያል፡፡ የወራሾች የጋራ ባለሀብትነትና የባልና ሚስት ባለሀብትነት አንድ ዓይነት ትርጓሜ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም

 

•    ማንኛውም በባል ወይም በሚስት ያለ ንብረት የጋራ ንብረት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
•    የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ጋብቻው ፀንቶ እስከኖረ ድረስ የጋራ ንብረት ሆኖ ይቀጥላል፡፡
•    ባልና ሚስት በጋራ ንብረቶች ላይ እኩል መብት አላቸው፡፡ የወርስ ሐብትን በተመለከተ ግን፤
•    የወራሾች የጋራ ባለሐብትነት የሚኖረው ከውርስ ከመጣ ንብረት ብቻ ነው፡፡
•    ለረጅም ጊዜ በጋራ ባለሐብትነት ካልተስማሙ በቀር የጋራ ወራሾች ባለሀብትነት ፀንቶ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡
•    የጋራ ወራሾች ከውርሱ የተለያየ መብት ሊኖራቸው ይችላል፡፡
(አበረ አበበ፣ መሠረታዊ የውርስ ህግ ማብራሪያ፣ 2000)


ብልጣብልጥ አምባገነኖች

አምባገነኖች ሕዝብን ረግጠው ለመግዛት የሚያነሷቸው የተለያዩ ምክንያቶችና ዓላማዎች አሏቸው፡፡ ሲጠቀሱም ኃይል፣ ሥልጣን፣ ሀብት፣ ህብረተሰቡን ለነሱ በሚያመች መልክ መቀየርና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር በህዝቡ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ካጡ ከእነዚህ ከተጠቀሱት ፍላጐቶቻቸው መካከል አንዱንም ማሳካት እንደማይችሉ ነው፡፡ ስለሆነም በድርድር ጊዜ ለእነዚህ ግቦች መሳካት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አምባገነኖች በድርድር ጊዜ ምንም ዓይነት ቃል ቢገቡም ዓላማቸውን ለማሳካትና ዴሞክራቶችን በማዘናጋት ለማንበርከክ ሲሉ መሆኑ መታመን አለበት፡፡

(አሰፋ ኃይሌ እና ሌሎች፣ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ፣ 1998)

አትሌት ዋሚ ቢራቱ

ዋሚ በአገር፣ በአህጉርና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተካሄዱ ውድድሮች 51 የወርቅ፣ 44 የብርና 3ዐ የነሀስ ሜዳሊያዎችን ለመሸለም የበቁ አትሌት ናቸው፡፡  ዋሚ ቢራቱ "በሮም ኦሎምፒክ ተሳታፊ መሆን ብችል ኖሮ ቢያንስ የሁለት ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ልሆን እችል እንደነበር አልጠራጠርም" ይላሉ፡፡ "ሆኖም ግን ከውድድሩ ስድስት ቀናት በፊት በሰውነቴ ላይ በ19 ቦታዎች ብጉንጅ ወጣ፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ሮም ሳልሄድ ቀረሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን አሰልጣኞቼ በ5 ሺህ እና በ1ዐ ሺህ እንደዚሁም በማራቶን አሸናፊ መሆን እንደምችል፣ በወቅቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አሉ የሚባሉ ሯጮች የነበራቸውን ዝቅተኛ ሰዓት ግምት ውስጥ በማስገባት ተስፋ ጥለውብኝ ነበር" በማለት በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡
(ሰሎሞን ጥላሁን፣ ደማቆቹ፣ 2000)


ስልጣን

ወንድሜ፣ ራስ ወዳድነት በጭፍን የበላይ የመሆን መንስዔ ነው፡፡ የበላይነቱ ደግሞ ወገንተኝነት ይፈጥራል፡፡  ወገንተኝነትም ወደ አለመስማማት እና ጠብ የሚወስድ ስልጣን ይፈጥራል፡፡

ነፍስ ደግሞ በድንቁርና ሳይሆን በዕውቀት ኃይል እና በፍትሕ ነው የምታምነው፡፡ መሀይምነትንና ጭፍን ጭቆናን ለማስፋፋት መሳሪያ (ጐራዴ) የሚያቀርበውን ስልጣን ትቃወመዋለች፡፡ ያ ኃይል ባቢሎንን ያወደመ፣ የኢየሩሳሌምን መሰረት ያነቃነቀ እና ሮምን ያፈራረሰ ነው፡፡

(ተስፋሁን ምትኩ እና ሀብታሙ ተስፋዬ፣ የጥበብ መንገድ (ትርጉም"፣ 1998)


የሰብአዊ መብቶች ዋና ዋና ምድቦች

በርካታ ምሁራን ሰብዓዊ መብቶች በሦስት ምድቦች መከፈላቸው ላይ ይስማማሉ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ጥቂት ጊዜ በኋላ በወጣው ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ በሰብዓዊ መብቶች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት አልተደረገም ነበር፡፡  ሆኖም በተከታታይ ዓመታት የተወሰኑ መብቶች ምድቦችን የያዙ እራሳቸውን የቻሉ ሰነዶች ታውጀዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡

•    የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት፣
•    የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ስምምነት፣
•    የአካባቢ ደህንነት እና የልማት መብቶች ስምምነት፣

ሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉ ቢሆንም የተጠቀሱት ምድቦች የሚያገለግሉት ስለመብቶቹ ምንነት ለመረዳት አመቺ ስለሚሆኑ ብቻ ነው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ በእነዚህ የተለያዩ ምድቦች መካከል ግልጽ ድንበር የለም፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ተደጋጋፊና እርስ በርሳቸው የተቆራኙ ናቸው፡፡

(ሰብአዊ መብቶች ሕጎቹና አፈጻጸማቸው፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀ፣ 1999)


ስለ አንዲት የቆቅ ልጅ በወጥመድ መያዝ

አንዲት የቆቅ ልጅ የስንዴ እሸት ትርክክ ብሎ በስሎ በሚገኝበት እርሻ አጠገብ ወጥመድ ተጠምዶ አይታ እናቷን እናቴ ሆይ እሸት አምሮኝ ነበር፤ ከዚህ ማሳ ገብቼ እንዳልበላ ወጥመድ እንዳይዘኝ ሰጋሁ ምን ይሻለኛል? አለቻት፡፡

እናቷም ተይ ልጄ ይቅርብሽ ትያዣለሽ አይሆንም ብላ መከረቻት፡፡ ልጅቷ ግን ግድየለሽም አይዘኝም ትንሽ ተክ ተክ አርጌ ልውጣ አለችና ገብታ ስትበላ ያ ወጥመድ እናቷ እንደፈራችው እግሯን ጥርቅም አድርጎ ያዛት፡፡

መቼም መከራ በመጣ ጊዜ በመጀመሪያ የሚታሰቡት ወላጆች ስለሆኑ፤ ያች የናቷን ምክር አልሰማ ያለች ልጅ እናቴ ኸረ ተያዝኩልሽ አለቻት፡፡ እሷም ምነው ልጄ አስቀድሜ ነግሬሽ አልነበረምን፤ አሁን ታዲያ ምን ላደርግሽ እችላለሁ? ስትል መለሰችላት፡፡

-    እማምዬ እባክሽን ፍቺልኝ፤
-    በምን እጄ?
-    ታዲያ እንዴት ልሁን፤ ምን ይበጀኝ? የኔ እናት፤
-    
በዚህ ጊዜ እናት ለልጅዋ ምን ጊዜም ምክር ዐዋቂ ናትና ዝም ብለሽ የሞትሽ መስለሽ ተኚ፤ ባለወጥመዱ ሲመጣ ሞታለች ብሎ ፈትቶ ይለቅሻል፤ በዚያ ጊዜ ታመልጫለሽ አለቻት፡፡

ያ ባለወጥመዱ ሰው ሰብሉን ጎብኝቶ መጣና ቢመለከት ዝልፍልፍ ብላ ተኝታ ዐይኗን አጨልማ አገኛት፡፡ እሱም የሞተች መሰለውና አዬ ጉድ ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበረ፤ ነገር ግን በክታለች እያለ አዘነ፡፡

ጓደኛው ከበላዩ ሰብል ይጠብቅ ነበርና ወንድም ብሎ ተጣርቶ ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበር፤ ነገር ግን በክታ አገኘኋት አለና ነገረው፡፡ ባልንጀራውም እስቲ ወደ ላይ አጉናት አለው፡፡ እሱም እያት አለና ወደ ሰማይ ወርወር በያደርጋት ተር ብላ ከጫካው ጥልቅ አለች ይባላል፡፡

(ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል፤ ባለን እንወቅበት፣ 1961)


"የጥቅምት አበባ"

ልክ ወርሃ ጥቅምት ሲብት የታዋቂው አርቲስት ንዋይ ደበበ ጥዑመ ዜማ "የጥቅምት አበባ" የሚለው በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያና በሌሎችም እንደሚለቀቅ ልብ ያልኩት ቁም ነገር ነው፡፡

ጥቅምት የመፀው (የአበባ) ጊዜ ነው፡፡ ነፋሻና ብርዳማም ነው፡፡ ከናፍር እስከ መሰንጠቅ ያደርሳል፡፡ ይሄኔ፣ የአንጋፋው ተጫዋች ጥላሁን ገሠሠ "የቀጩን መድኃኒት ላኪ ለከንፈሬ . . . . " የሚለው ቅላፄ ትዝ የማይለው የለም፡፡

"በጥቅምት አንድ አጥንት" ይባልስ የለ"" የንዋይን ዜማ ተከትሎ ጥቂት የምለው አለ፡፡ ከተቀሩት ወራት ሁሉ ከጥቅምት ብዙ የቃላት ዕርባታ መመሥረት ይቻላል፡፡ ይሄም ጥቅም፣ ጥሞ፣ ምጥ፣ ቅምጥ፣ ምት፣ ጥጥ፣ ጥምጥም፣ ቅትት . . . የተሰኙ ናቸው፡፡ ከወርሃ ህዳር - ዳር የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ሁለት ፍች አለው፡፡ አንደኛው ጫፍ ወይም ጠርዝ ማለት ነው፡፡ ሌላው ዳር ሲል ልጅህን ትዳር አስይዘው/አስይዛት ማለት ይሆናል፡፡ ከወርሃ መጋቢት "ጋቢ" እና "ጋት" የሚለው ይወጣዋል፡፡ "መጋቢ" የሚል ቃል አለው፡፡ በጦሩ ክፍል የማዕረግ ስም ነው፡፡ መጋቢ የ" አለቃ ይሏል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን "መጋቢት" የምንላቸው እንስት አሉ፡፡ ዋና ተግባራቸው የመገበርያ ስንዴውን ለሥርዓተ ቁርባን ማዘጋጀት ነው፡፡

(መገርሣ ዓለሙ፣ የካ ክፍለ ከተማ)


ፈረቃ

ሞትና ሰውነት ሁሌም ይነቃሉ
ነፍስና ነፋስ ግን ወቅት ይጠብቃሉ፡፡
ሁሌ ህያው መሆን አከተመ በቃ
የኛ ህያውነት ሆኗል በፈረቃ፡፡

(በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000)


ገ     ራ     ገ    ር
ቡና ቤቱ ዝንጀሮዎችን በአስተናጋጅነት ቀጠረ


አንድ የጃፓን ቡና ቤት ሁለት የሰለጠኑ ዝንጀሮዎችን ደንበኞቹን እንዲያስተናግዱለት መቅጠሩን ሜትሮ ዘግቧል፡፡

ከቶኪዮ በስተሰሜን የሚገኘው ካያቡኪያ መጠጥ ቤት ሁለቱን ዝንጀሮዎች የቀጠረው የተለመዱትን የሰው አስተናጋጆች እንዲያግዙለት ነው፡፡

ተገልጋዮች ለሁለቱ የዝንጀሮ አስተናጋጆች የሚሰጡት ቲኘ የተቀቀለ ባቄላ ሲሆን ከሁለቱ ትልቁ የ12 ዓመቱ ያት ቻን ሲሆን ለደንበኞች የመጠጥ ትዕዛዝ ተቀብሎ በጠረጴዛቸው ላይ ያኖራል፡፡ ትንሹ ፋኩ ቻን ትዕዛዝ መቀበል ባይችልም ለደንበኞች ትኩስ ፎጣ ያቀብላል፡፡

የመጠጥ ቤቱ ባለቤት የ63 ዓመቱ ካኦሩ ኦትሱካ ቀደም ብሎ ዝንጀሮዎቹን ለቤት እንስሳነት እየተጠቀሙባቸው የነበረ ቢሆንም በቡና ቤቱ ውስጥ የሚያደርገውን ተግባር ሲቀዱ ካስተዋለ በኋላ ግን አስተናጋጅ ሆነው እንዲሰሩ ወስነዋል፡፡

ኦትሱካ በአሁኑ ሰዓት የወደፊት ተተኪ አስተናጋጅ እንደሚሆኑ ተስፋ ያደረጉባቸውን ሦስት የዝንጀሮ ልጆችን እያሰለጠኑ ነው፡፡


የእርግዝና መከላከያ ተጠቃሚዋ በአንዴ ሦስት ልጆችን ተገላገለች

በእንግሊዝ ሀምኘሻዬር ግዛት የምትኖር የእርግዝና መከላከያ እየተጠቀመች ባለበት ሰዓት በማርገዟ ከ2ዐዐ ሚሊዮን ሰዎች በአንዱ ላይ ብቻ የሚከሰተው እንዳጋጠማት ዴይሊ ሚረር ዘግቧል፡፡

የ22 ዓመቷ ክርስቲ ሃሌ ከእጮኛዋ ቶቢ ዊልሰን ጋብሪኤላ፣ ሊሊና አሊሻ የተባሉ ልጆችን ተገላግላለች፡፡

ሦስትያ ልጆች በሆስፒታል ኢንኩቤተር ውስጥ ጥንካሬ እያገኙ ያሉ ሲሆን አባታቸው የ28 ዓመቱ ቶቢ "ልጅ የመውለድ እቅድ አልነበረንም፡፡ ክርስቲ የእርግዝና መከላከያ እየተጠቀመች ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህን ትንንሽ ግን አስደሳች ህፃናት በማግኘታችንበአስቸኳይ ህብረት ለመፍጠር የተዘጋጀን ቤተሰቦች ሆነናል" ብሏል፡፡

ህፃናቱ ከመወለጃ ቀናቸው 13 ሳምንታት በፊት በመወለዳቸው እስከ መጪው ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ በኢንኩቤተር እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡

ቶቢ ሚስቱ ክርስቲ እርጉዝ መሆኗ ሲነገራት መደንገጧን አስታውሶ ይህ ድንጋጤ በምርመራ ውጤቷ ሦስት ልጆችን እንደምትወልድ ሲነገራት ከደነገጠችው ድንጋጤ እንደማይነፃፀር ያብራራል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ለበጎ እንደተፈጠረ በአፅንኦት ያስረዳል፡፡


አይጥዋ እባቡን ገደለች


ለመርዛማ እባብ ምግብነት የተወረወረች አንዲት ትንሽ አይጥ የተገላቢጦሽ እባቡን እንደገደለችው አኘል ዴይሊ ዘግቧል፡፡

በታይዋን ናንቱ ከተማ የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ አባላት 35 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለውን አደገኛ እባብ ከያዙት በኋላ በአይጥ የሽቦ ሳጥን ውስጥ ያስቀመጡት ለደህንነት ሲሉ ነበር፡፡ የቡድኑ ቃል አቀባይ "ከምሳ ስንመለስ ያገኘነው ምግብ ያልናትን አይጥ እንጂ አደገኛውን እባብ አልነበረም" ብሏል፡፡ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ አባላቱ አይጧ ለእባብ አዳኝዋ የሰጠችው የተተናኳሽነት ምላሽ በጣም አስደምሟቸዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ሲቀጥሉ "አይጧ እባቡን በተከታታይ ስትነክሰውና ስትቧጭረው ነበር" ሲሉ ያክላሉ፡፡

ከ3ዐ ደቂቃ አሰልቺ ትግል በኋላ እባቡ ሲሞት በአይጧ ላይ አንድም የቡጭሪያ ምልክት አልነበረም፡፡ የብርጌዱ ተጠሪ ላን ሴንግክዊ "ምናልባትም ስንይዘው እባቡ መርዙን አስቀድሞ ተጠቅሞበት ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ገራም አዳኝ ይሆን ይሆናል" ብለዋል፡፡


 
< Prev   Next >