| የቁንጅና ውድድር ድሮና ዘንድሮ |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
ሪፖርተር፡- በውድድሩ እንዴት ሊሳተፉ ቻሉ? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ወላጆቼ ሳያውቁ ተደብቄ ራሴ ለብቻዬ ያደረግኩት ነገር ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ስለሁኔታው የሰሙት በሬዲዮ ሲነገር ነው፡፡ በዚያ ውድድር ቁመት፣ ቁንጅና፣ አንደበተ ርቱነት፣ ግብረገብነትና እውቀት የመመዘኛ መስፈርቶች ነበሩ፡፡ ሁለተኛ ወጥቼ ተደስቼ ወደ ቤቴ ስመለስ የጠበቀኝ ሁኔታ በተቃራኒው ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ቤት አላስገባም ብለው አባረሩኝ፡፡ በቁንጅና ውድድሩ ላይ መሳተፌን እንደ ውርደትና እንደ ነውር ነበር የቆጠሩት፡፡ ውድድሩ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚካሄድ ነበር፡፡ የውድድሩ ዳኝነት ላይ የቲፎዞ ነገርም ነበር፡፡ እኔ ነበርኩ አንደኛ መውጣት የነበረብኝ ለማለት አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- ዋንኛ መመዘኛዎቹ ምን ነበሩ? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የቆዳ ቀለም ላይ ብዙ ትኩረት አልተደረገም ነበር፡፡ እንዲያውም ቀይና ቀይ ዳማ ለሆኑ ነበር ያደሉት፡፡ ሊመረጡ የሚገባቸው ብዙ ጠያይም ቆነጃጅት ነበሩ፡፡ በዳኝነት የተሳተፉት ብዙዎቹ ቢሞቱም አንዱ ግን በሕይወት አሉ፡፡ ቁመት፣ ቅጥነትና የእግር ውበት ትኩረት ይሰጣቸው ነበር፡፡ በዋና ልብስም ታይተናል፡፡ አቋቋምና አረማመድም ይታይ ነበር፡፡ ጠይምነት የኢትዮጵያዊያን፣ የአፍሪካዊያንም መገለጫ ቀለም በመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጠይምነት ጥሩ ዋጋ መሰጠቱ ትልቅ ልውጥ ነው ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር፡፡ ሪፖርተር፡- የቁንጅና ውደድር ሂደቱ ምን ያህል ጊዜ ወስዷል? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ከስድስት ወር በላይ ወስዷል፡፡ ለብሰን የቀረብነው አንድ አይነት ልብስ አልነበረም፡፡ እያንዳንዳችን የሚያምርብንን ልብስ ለመምረጥ፣ አረማመድ አቋቋም ለማስተማር ጊዜ ወስዶ ነበር፡፡ በትክክል ባላስታውሰውም ከስድስት ወር የሚያንስ አልነበረም፡፡ በአበሻ ልብስ፣ ፓሪ ሞድ (በዘመናዊና) በዋና ልብስ ነበር የታየነው፡፡ አነጋገርና አመላካከታችንን ለመመዘን የቀረቡ ጥያቄዎች ቁንጅና ውድድሩ ላይ ለምን መሳተፍ እንደፈለግን የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ እኔ የተጠየኩት በውድድሩ ላይ የተሳተፍሽው በቁንጅናሽ ተማምነሽ ነው ወይ? የሚል ነበር፡፡ ብዙ ያልወጡ ቆነጃጅት እንዲወጡ ለማነሳሳት እንጂ ከኔ ወዲያ ብዬ አይደለም በማለት መልስ ሰጥቻለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- መዋቢያዎቻችሁ ምን ምን ነበሩ? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ኩላ ኩል ሜካፕ አናበዛም፣ ክልክልም ነበር፡፡ በተፈጥሮ ፀጉር እንጂ ዊግ ማድረግም አይቻልም ነበር፡፡ መቀንደብም የነበረ አይመስለኝም፡፡ እኔ አልተቀነደብኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ከውድድር ውጭ እንዲሁም ቢሆን ብዙ የሚቀነደብ ሴት መኖሩን አላስታውስም፡፡ የቅንድብ ብዛት ራሱ ውበት ስለሆነ በኩል ብዙ ለማስመሰል ይሞከር ነበር፡፡ ጥፍር መሰራትና ቀለም፤ አሁን ያለው ሌላ ሌላ ነገር ሁሉ በእኛ እድሜ የነበረ ነው፡፡ እንዲያውም አዲስ የመጣ የለም፡፡ የነበረው ራሱ እየተደገመ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሽልማቱ ምን ነበር? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አንደኛ ለወጣችው ቤቢ ፊያት መኪናና ነፃ የጉብኝት የውጭ አገር ትኬት፤ ለሁለተኛ የልብስ ስፌት መኪናና የውጭ አገር ነፃ የጉብኝት ትኬት፡፡ ለሦስተኛ የተሰጠውን አላስታውስም፡፡ ነገር ግን ሶሰታችንም የወርቅ ሜዳሊያና ሰዓት ከጃንሆይ ተቀብለናል፡፡ በነበረብኝ የቤተሰብ ችግር፣ ከቤት በመባረሬ የውጭ አገር ጉብኝቱን አልሄድኩም፡፡ ከቤተሰቦቼ የታረቅኩት ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የቁንጅና ውድድር ላይ አልተሳተፍኩም፡፡ ሪፖርተር፡- የቀድሞና የአሁኖቹን የቁንጅና ውድድሮች አነፃፅረው ያውቃሉ? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አዎ" ትልቅ ለውጥ ነው ያለው፡፡ በእኛ ጊዜ የቁንጅና ውድድር በወላጆች የሚታየውእንደ ትልቅ ነውር ነበር፡፡ እንዴት ልጄ ወገቧ በሜትር ተለካ ተደፈርኩ ይባላል፡፡ ያ ዛሬ ቀርቶ ወላጆች አምነውና ተቀብለውት ነው ልጆቻቸው በውድድር የሚሳተፉት፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን ጥሩ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የእገሌ ልጅ የቁንጅና ውድድር ላይ ቀረበች ከተባለ ተረባራቢው ይበዛል፡፡ ምናልባትም ወላጆች ያን ይጠሉት ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር የውበትና የመኳኳሉን ስመለከት የአሁኑ ልጆች በአጠቃላይ መኳኳል ያበዛሉ፡፡ ልጅነት፣ ወጣትነት በራሱ ቁንጅና ነው፡፡ የአስራ 18 እና 20 ዓመት ልጅ ሜካፕ አያስፈልጋትም፡፡ በዚህ እድሜ መታየት ያለበት የተፈጥሮ ውበት ነው፡፡ እድሜ ሲገፋና ቆዳ መሸብሰብ ሲጀምር ነው ሜካፕ የሚያስፈልገው፡፡ የማያስፈልገው ቆዳ ላይ ሜካፕ መጠፍጠፍ አያምርም፡፡ ሪፖርተር፡- በእርስዎ ጊዜ የተወዳዳሪዎች አቀራረብ እንዴት ነበር? ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አሁን ላይ ያለመበሰል ነገር ይታያል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምናልባትም ጊዜ በባህል ላይ ያመጣው ተጽዕኖ ይሆናል ብለን ልንቀበለው እንችላለን፡፡ እኛ ሁሉን ረጋ ባለ መንፈስ ነበር የምናደርገው፡፡ ቁንጅና መታየት ያለበት ከባህል ጋር ነው፡፡ """""""""////""""""" ኪዳን ገብረ እግዚአብሔር በ2000 ዓ.ም ወይዘሪት ሚሌኒየም ንግሥት ኢትዮጵያ ሆና ተመርጣለች፡፡ ቁመቷ ሜትር ከሰማኒያ አንድ ሲሆን ክብደቷ ሀምሳ ስምንት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እንዴት ልትወዳደሪ ቻልሽ? ኪዳን፡- ለስምንት ወራት በሞዴልነት ሠርቻለሁ፡፡ ቀደም ሲል 1996 ዓ.ም ደግሞ መቀሌ ውስጥ የወ/ት መቀሌ የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ በዚያ ውድድር የመጨረሻዎቹ ምርጥ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የመጣሁት ለሥራ ነበር፡፡ ከስራ ጎን ለጎን ሞዴሊንግ መማር ጀመርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወ/ት ሚሌኒየም ንግሥት ኢትዮጵያን ያሸነፍኩት፡፡ የወ/ት ሚሌኒየም ንግሥት ኢትዮጵያ አዘጋጅ ውጭ አገር ስለነበር የሚኖረው ውድድር መኖሩን እንደሰማሁ ፎቶግራፎቼን በኢንተርኔት ልኬ ተመዘገብኩ፡፡ ለሁለት ወራት ስልጠና ተሰጥቶን ለውድድር ቀረብን፡፡ ሪፖርተር፡- እንደምታሸንፊ አስበሽ ነበር? ኪዳን፡- ብዙ ቆነጃጅት የነበሩ ቢሆንም የውድድሩ መመዘኛ አለም አቀፍ ስለነበር፤ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን መወከል የሚችል ተወዳዳሪ የሚመረጥበት ስለነበር ልበ ሙሉ ነበርኩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አለም አቀፍ መስፈርት የሚሆነው ቅጠነት፣ ቁመት፣ ጎላ ያላ አይንና የተፈጥሮ ፀጉር ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ተፈጥሮአዊ መሆን አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፍሽበት የቁንጅና ውድድር እንዴት ነበር? ኪዳን፡- ያን ጊዜ ሞዴሊንግ አልተማርኩም፡፡ መድረክ ላይ እንዴት መራመድ እንዳለብኝ አልተማርኩም፡፡ ብዙም ልበ ሙሉ አልነበርኩም፡፡ አወዳዳሪዎቹም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አልነበሩም፡፡ አንደኛ ለመውጣት ግን ጉጉቱ ነበረኝ፡፡ ተማሪ ስለነበርኩ ለመወዳደር የቻልኩትም በሰዎች ግፊት ነበር፡፡ ከመቶ ሀያ ተወዳዳሪዎች የመጨረሻ ምርጥ ሀያዎች ውስጥ መግባት ችዬ ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- አገር ውስጥ ባደረግሻቸው ሁለት ውድድር፣ ያየሽው ዳኝነት ምን ይመስላል? ኪዳን፡- ዓለም አቀፍ ልምድ የሌላቸው ዳኞች ስለቁንጅና በትክክል ያውቃሉ ብዬ አላስብም፡፡ ቁንጅና ለነሱ የሚታይ ነገር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ቁንጅና ስብዕናንና እውቀትን ማጠቃለል ይኖርበታል፡፡ አለም አቀፍ ልምድ ያላቸውና የሌላቸው ዳኞች የሚሰጡት ውሳኔ ይለያያል፡፡ በወ/ት ሚሌኒየም ንግሥት ኢትዮጵያ ውድድር በሁለት ወር አዘጋጁ የአመጋገብ ሥርዓታችንን፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ቀረቤታ፣ አለባበሳችንንና የተለያዩ ነገሮችን ለማጥናት የሞከረበት ሁኔታ አለ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰራር የተወዳዳሪዎችን ስብዕናና ፀባይ ከግምት ውስጥ ለማስገባት ይረዳል፡፡ ውጫዊ ውብት፣ ልበ ሙሉነት፣ ስብእናና እውቀት እኩል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- የራስሽን ውበት እንዴት ትገልጭዋለሽ? ኪዳን፡- ሰው ብዙ ጊዜ የሚመለከተው ውጫዊውን ገፅታ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ቀና አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ለአገሬ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንቀሳቀሳለሁ፡፡ በማገኘው አጋጣሚ አገሬን ለማስተዋወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም ለተለያዩ ውድድሮች ጃፓንና ቻይና ሄጄ በነበረበት ወቅት አገሬን ያስተዋውቁልኛል ያልኳቸውን ነገሮች በሲዲ ቀርጨ በማባዛት ከተለያዩ አገራት ለነበሩ ተወዳዳሪዎች በመስጠት አገሬን በተወሰነ መልኩ ለማስተዋወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- የተሳተፍሽባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዴት ነበሩ? ኪዳን፡- ወ/ት ሚሌኒየም ንግሥት ኢትዮጵያን ካሸነፍኩ በኋላ ጃፓን ላይ በተካሄደው ሚስ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ተካፈልኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ለሚስ ቱሪዝም ኢንተርናሽናል ቻይና ሔድኩ፡፡ ጃፓን የተደረገው ውድድር ከቻይናው ጋር ሲነፃፀር ሰፊ አልነበረም፡፡ በመጨረሻም አሥር ምርጥ ቆነጃጅት ተመረጡ፡፡ ከነሱ ውስጥ መግባት አልቻልኩም ነበር፡፡ ሀሳቤ ግን ጥሩ ውጤት አመጣለሁ ብዬ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ሦስት ተወዳዳሪዎች ብቻ ነበርን የተሳተፍነው፡፡ አሸናፊ የሆነችው ሜክሲካዊ ነበረች፡፡ የቻይናው ውድድር አህጉርን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ነበር፡፡ ከአፍሪካ አሥራ ሁለት የምንሆን ተወዳዳሪዎች ተካፍለን ነበር፡፡ በዚያ ምርጥ አፍሪካዊ ሞዴል ተብያለሁ፡፡ አንደኛ የወጣችው ከፔሩ የመጣች ተወዳዳሪ ነበረች፡፡ ከዚህ በኋላ በአገር ውስጥ የቁንጅና ውድድር መሳተፍ አልችለም፡፡ በዚህ ዓመት ፊሊፒንስና ቻይና ላይ በሚደረጉ የቁንጅና ውድድሮች እሳተፋለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ውበትን እንዴት ነው የምትገልጭው? ኪዳን፡- ሴቶቻችን በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ደስ የሚል ነው፡፡ በፀጉርም ሆነ በአለባበስ የተለያዩ ስታይሎችን ይከተላሉ፡፡ በዚህም ሴቶቻችን በውበት ላይ ውበት ሆነው ቆንጆ ይሆናሉ፡፡ አለባበስ ላይ በተለይም አጫጭርና የተቆራረጡ ልብሶችን መልበስ እየተዘወተረ በመምጣቱ ኢትዮጵያዊነትን የመልቀቅና የመተው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ የባህል ልብሳችንን መልበስም ከዋጋ አንፃር ቀላል አይደለም ውድ ነው፡፡ |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |