| ዐፄ ምኒልክና ፖስታ - 50ኛ ... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
የኢትዮጵያ ቴሌግራፍና ፖስታ እንደ ሮፓ መንግሥት ደንብ ከኡኒዮን ፖስታ እንዲገባ አስታውቅሃለሁ፡፡ ሌሎቹ መንግሥቶች እንደሚከፍሉት ገንዘብ እኛም ባመት ባመት እንደደንቡ ለኡኒዮን ፖስታል እንሰጣለን፡፡" ጥር 22 ቀን 1900 ዓ.ም. ፀፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ሚኒስትር ለነበሩት ክሎቢኮብስኪ ኢትዮጵያ የዓለም ፖስታ ኅብረት አባል እንድትሆን የላኩት ደብዳቤ ነበር፡፡ በ1901 ዓ.ም. ጥቅምት 21 ቀን ማኅበሩም ተቀበላት፤ አባልነቷ ዘንድሮ 100 ዓመት ሞላው፡፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ይህንኑ መቶኛ ዓመት በዓሉን መስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ከዓለም ፖስታ ቀን ጋር በአንድነት አክብሮታል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ፖስታ ኅብረት አባል የሆነችው በ1901 ሲሆን ሥራው የተጀመረው ግን በ1886 ዓ.ም. ግድም ነው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ በ1885 ዓ.ም. የካቲት 10 ቀን ከፖስታ ማኅበር ለመግባት ደብዳቤ ቢጽፉ "መጀመሪያ የፖስታ ሥራ ማካሄዱን ይጀምሩ" የሚል መልስ ማግኘታቸውን፣ በ1886 ዓ.ም. በጥቅምት ወር፣ በፈረንሳይ (ፓሪስ) በመልካቸው የተቀረፀ ቴምብር አሳትመው ገበያ ላይ በማዋል ሥራ መጀመራቸውን በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በየዓመቱ መስከረም 29 ቀን (ኦክቶበር 9 ቀን) በመላው ዓለም የሚከበረው የዓለም ፖስታ ቀን ዘንድሮ የተከበረው ለ134ኛ ጊዜ ነው፡፡ በዓሉ በመላው ዓለም በሚገኙ የፖስታ አስተዳደሮች መከበር የጀመረው በ1962 ዓ.ም. በኅብረቱ የቶኪዮ ጉባዔ "የወጣቶችን ደብዳቤ የመጻፍ ባህል እናዳብር" በሚል ውሳኔ የተጀመረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ዘንድሮ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር የሐዋሳዋ ሐና ታሪኩ 1ኛ፣ የአዲስ አበባዋ ቃል ኪዳን አሰፋና የባሕር ዳሯ ቃል ኪዳን ወልደ አማኑኤል ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ተሸልመዋል፡፡ በዓለም ፖስታ ቀንና የኢትዮጵያ አባልነት አንድ መቶኛ ዓመት በዓል ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግደይ ገብረ ዮሐንስ ባደረጉት ንግግር፣ የፖስታ አገልግሎት ሁለመናው ያበቃለታል፣ ይዳከማል ተብሎ ቢገመትም በአሁኑ ጊዜ የፖስታ አገልግሎት ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ መሆኑ እየታየና ኢንተርኔትና ኢሜይል ሊተኩት እንደማይችሉ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የዓለም ፖስታ ኅብረት ዳይሬክተር ሚስተር ኤድዋርድ ዲያን "የፖስታው ዘርፍ በጠቃሚነቱ ወደፊት መግፋቱን ይቀጥላል" በሚል መሪ ሐሳብ ባስተላለፉት መልእክት የፖስታ አገልግሎት ከቀድሞው በበለጠ አስፈላጊነቱ እየታየ መሆኑና ኢሜል እና ኢንተርኔት ሊተኩት እንዳልቻሉና ከዚህ ባሻገር ጥሩ አጋጣሚዎች እንዲፈጠሩለት አስተዋጽዖ አድርገውለታል ብለዋል፡፡ ዓመታዊው የፖስታ ቀን ከኢትዮጵያ አባልነት 100ኛ ዓመት ጋር የገጠመ ቢሆንም ከደብዳቤ አፃፃፍ ሀገር አቀፍ ውድድር ባሻገር ነባሩን የኢትዮጵያ ፖስታ ታሪክና ዐፄ ምኒልክን ከስም ጥሪ ባለፈ በምልዐት ሳይገልጽ ታልፏል፡፡ ከአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደተደመጠው 1ዐዐኛ ዓመት ታላቅ በዓል በመሆኑ በትጋታቸው አባል ያደረጓትን ዐፄ ምኒልክና ጥንታዊ ፖስታን የሚያመለክት የመታሰቢያ ቴምብር ሊወጣለት ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ ከ1964 ዓ.ም. እስከ 2001 ዓ.ም. በተካሄዱት 37 ዓለም አቀፍ የወጣቶች የደብዳቤ አጻጻፍ ውድድር የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ባደረጉት ተሳትፎ በ1965 ዓ.ም. ታዳጊ ወጣት ድባብ ወርዶፋ፣ በ1967 ዓ.ም. ታዳጊ ወጣት ፍቅሬ ገብረ ክርስቶስ፣ ሁለቱም ሦስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያ፣ በ1968 ዓ.ም. "የዐውደ ዓመቱ ትዝታና የንባብ እርካታ" በሚል ርእስ በተካሄደው ውድድር አዜብ ገ/ክርስቶስ 1ኛ ሆና የወርቅ፣ በ1983 ዓ.ም. ቢንያም ብርሃኑ 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ፣ በ1997 ዓ.ም. ደግሞ "ወጣቱ ትውልድ ድህነትን ለመቀነስ እንዴት እንደሚችል እጽፍላችኋለሁ" በሚል ርእስ በተካሄደው 33ኛው ውድድር ታዳጊ ወጣት አንዋር ያሲን አሸንፎ ወርቅ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ቀጣዩ 38ኛው የደብዳቤ አጻጻፍ ውድድር ዕድሜያቸው እስከ 15 ዓመት የሚደርሱ ታዳጊ ወጣቶች እንዲወዳደሩ ኅብረቱ የጋበዘ ሲሆን፣ የተዘጋጀው ርእስም "የምጽፍልህ"ሽ) እንዴት ጤናማ የሥራ አካባቢ ለጥሩ ሕይወት እንደሚያበቃ ለመግለጽ ነው" የሚል ነው፡፡ ደብዳቤዎች ለዓለም አቀፉ ተቋም ቢሮ መድረስ የሚገባቸው ከሚያዚያ 22 በፊት መሆኑ ታውቋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ሕፃናቱ በውድድሩ ተሳታፊ በመሆን ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ድርጅቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ |
|
| Last Updated ( Monday, 13 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |