Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የአርጎባ ጋብቻ ባህላዊ ገጽታዎች
የአርጎባ ጋብቻ ባህላዊ ገጽታዎች E-mail
Sunday, 12 October 2008

Image
ተስፋዬ ኃይሉ
በሔኖክ ያሬድ

የሰው ልጅ የሕይወት ዑደት በመባል የሚታወቀው ልደት፣ እድገት፣ ጋብቻና ሞት ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የመሸጋገሪያ፤ ጋብቻ የመቀላቀያ ሥነ ሥርዓት  ሲከናወንላቸው፣ ሞት ደግሞ የመለያያ ሥነ ሥርዓት ይፈጸምበታል፡፡ በአርጎባ ብሔረሰብ ከሚታዩት ባህላዊ ክንውኖች አንዱ የመቀላቀያ ሥርዓት የሚከወንበት ጋብቻ ነው፡፡

 

በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኘው የአርጎባ ብሔረሰብ የጋብቻ ባህል አስመልክተው በመስክ ያጠኑት ነፍስ ሔር አቶ ተስፋዬ ኃይሉ እንዳመለከቱት፣ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በሚፈጸምበት ጊዜ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ልምዶች፣ ወጎች፣ ፋይዳዎች፣ እሴቶች ወዘተ". ይገለጹበታል፡፡ የተጋቢዎቹ እርስ በርስ፣ የቤተ ዘመዶቻቸው፣ ግንኙነት የሚወሰንበት ይሆናል፡፡ ባህላዊ ገጽታዎች የሚንጸባረቁበትና ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚመሠረቱት በጋብቻ ምርጫ፣ በሠርግና በመልስ ሥነ ሥርዓቶች አማካይነት ነው፡፡

"የሶሽዮ ካልቸራል ጥናት በአርጎባ ብሔረሰብ" በሚለው የአቶ ተስፋዬ ጥናት መሰረት፣ በአርጎባ ባህል መሠረት ወንድና ሴት ልጅ እስከሚጋቡ ድረስ ከወላጆቻቸው ጋር አብረው ይቆያሉ፡፡ ሴት 10-15 ዓመት፣ ወንድ ደግሞ ከ18-20 ዓመት ሲሆናቸው ጋብቻ የሚፈጽሙት በቤተሰብ አማካይነት ነው፡፡ የወንድ አባት ለጋብቻ ተመጣጣኝ ነው ብሎ የገመተውን ሰው ልጅ ጥሩነቷንና አባቷም የግቢ ሰው መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ልጅህን ለልጄ እንድትሰጠኝ ብሎ ብቻውን እቤቱ ድረስ ሄዶ ይጠይቀዋል፡፡

የልጅቷ አባት ከሚስቱም ሆነ ከራሱ እናትና አባት፣ እህቶችና ወንድሞች  ጋር ስለ ጋብቻው ጥያቄ ይማከርና ይወስናል፡፡ የልጁ አባትም በቀጠሮው ቀን ምን መከርክ ብሎ የልጅቷን አባት ሲጠይቀው መስማማቱን ከገለጸለት ሽማግሌዎች ይመርጥና ከሴቷ አባት ተነጋግረው የፊቂሃ/ፍጥምጥም/ ቀን ይወስናሉ፡፡

በዚህም ቀን የልጁ አባት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ቃዲ፣ ቤተሰብ ወዘተ". በሚገኝበት ከአባቷ ቤት እንደገቡ ቆመው "አሰላማሌኩም" ካሉ በኋላ የሴት ወገን "በአጸፋው ወአሊኩም ሰላም" ብለው ይመልሳሉ፡፡ በመቀጠልም የወንድ ወገን "አላህ የሰጣችሁን ልጃችሁን፣ አላህ ለሰጠን ልጃችን ስጡልን ብለን መጥተናል" ብለው ይጠይቃሉ፡፡ የሴት ወገንም መልሶ "አላህ የሰጠንን ልጃችንን፣ አላህ ለሰጣችሁ ልጃችሁ ሰጥተናል" ካሉ በኋላ ይዘይራሉ፡፡ እጅ ለእጅ ይሳሳማሉ፣ ሥነ ሥርዓት ላይ የኔካሁ/ የሰማኒያ ውል/ ይፈጸማል፡፡ ከዚህ በኋላ የወንድ ልጅ አባት በልጅቷ ፀጉር ላይ የሚሰካ ወለባ፣ ቅቤ፣ በአንገት ላይ የሚንጠለጠል የተበሳ ብር፣ የወገቧ መታጠቂያ መቀነት /ጃዊ/፣ በአንገቷ የሚደረጉ አምስት ቀጫጭን ቀለበቶች ያደርጋል፡፡ ይህም ልጅቷ ለመታጨቷ ምልክት ነው፡፡

የታጨችው ልጅ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ከሆነች አሥራ አምስት ዓመት እስኪሞላት ድረስ ከወላጆቿ ዘንድ ትቀመጣለች፣ በዚህም ጊዜ በኢድ ወቅት ለልጅቷ አንደኛው ሙዜ ልብስ፣ ጫማና የተለያዩ ስጦታዎች ወስዶ ይሰጣታል፡፡ በአረፋ ወቅት ደግሞ የበግ ሙክት ለቤተሰቦቿ ከሰጠ በኋላ እራሱ አርዶ ይጋብዝና ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ እነዚህን ለኢድና ለአረፋ በዓል ጊዜ ሙዜ ለስጦታ የሚወስዳቸውን ወጪዎች የሚሸፍነው የልጁ ቤተሰብ ነው፡፡

የፋቂሃ/ የፍጥምጥም/ ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ የሴት ልጅ አባት ቢከዳ በሽማግሌ ጉዳዩ ታይቶ እንዲቀጣ ይደረጋል፡፡ የወንድ ልጅ አባት ሲያፈርስ ደግሞ የሰጠሁትን እቃ ላኩልኝ ብሎ ሽማግሌዎችን ሲልክ፣ በሴት በኩል ቀደም ሲል የሰጣቸውን አጣጥበው ይልኩለታል፡፡

አንዲት የታጨች ሴት ልጅን የጠለፈ ወይም በኃይል አስገድዶ የደፈረ ሰው በባህላዊ ሕግ መሰረት ይጠየቃል፣ ይቀጣል፡፡ በዚህ መሰረት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሀገር ሽማግሌዎች ይሰበሰቡና ጉዳዩን አጣርተው ጥፋት የፈጸመውን ሰው የእርሻ በሬ አርደው ይበሉበታል፡፡ ይህም አንድ የቅጣት ዓይነት ሲሆን፣ በደል የደረሰባትንም ግለሰብ የሚያስደስት በመሆኑ በበዳይና በተበዳይ መካከል እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል፡፡

በሽማግሌዎች አማካይነት በተወሰነው መሰረት የሰርጉ ቀን ሲደርስ በሴትም ሆነ በወንድ በኩል ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ሀብት ያለው ሰው ቅቤ፣ ከብትና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ገዝቶ የድግስ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ለዚህም ቤተ ዘመድ ቤተ ሰብና ጎረቤት ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

ሰርጉ ስምንት ቀን ሲቀረው ልጅቷ የእጆቿንና የእግሮቿን ጣቶች ጥፍሮች ወተት እያስነኩ የጎረቤት አሮጊቶች ይቆርጧታል፡፡ ይህም የሚደረገው ሙሽራይቱን ከልጃገረድነት ወደ ሴትነት መሸጋገሯን ለማሳወቅ ሲሆን ስትቆረጥም ጣቶቿን ወተት የሚያስነኩት እርጥብ እንድትሆን በማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሆዷ እንዲጠራ ተብሎ ኮሶ ትጠጣለች፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ወንዱም የእግሮቹን ጥፍር የሚቆረጥ ሲሆን ኮሶም ይጠጣል፡፡

ሙሽራይቱ ለሠርጓ ሶስት ቀን ሲቀራትም ወትሮ ከምትሰራው የፀጉር አሰራር ለየት ባለ መልኩ በቀጭኑ በብሔረሰቡ አጠራር መሰረት ለጥቄት የሚባለውን ትሰራና እስከ ሰርጉ ቀን ድረስ ፀጉሯን በአዝጋኖ ትሞቃለች፤ የሠርጓ እለትም የወይባ ቅጠል ይቀቀልና ገላዋን በቅጠሉና በውኃው ከታጠበች በኋላ አዝጋሮ ትሞቃለች፡፡ በመቀጠልም ሙሽሪቱን ጥሩ መዓዛ፣ ጠረንና ውበት እንዲኖራት ለማድረግ በሶስት ደረጃ የሚከፈል የጭሳ ጭስ አሟሟቅ ዘዴ ይከናወናል፡፡ አንደኛው ማንሻ ተብሎ የሚጠራውና አዝጋሮ፣ ሉባንጃ፣ ነድና በሽቶ የታሸ ምጥንን የሚይዘው የመጨረሻ የሚባለውን ሉባንጃ፣ ጭቃ ብርጉድና ነድ ሞቃ ሽቶ ትቀባለች፡፡

በዚህ ዓይነት ከሞቀች በኋላ ስትቀዘቅዝ በቅደም ተከተል ለሠርጉ የተዘጋጀውን ልብስ ትለብሳለች፤ ጌጣ ጌጧንም ታደርጋለች፡፡ በብሔረሰቡ፣ ጎንደሬ በመባል የሚታወቀውን ጥልፍ ያለበትን የባህል ቀሚስ ትለብሳለች፣ የአንገት ጌጦችን፣ ኤንዳ፣ ቸንቸልና አሸንክታብ፣ የእጅ ጌጥ፣ የእጅ አምባር፣ የእጅ አዛብ፣ የእግር አምባር፣ የእግር አልቦ፣ የእግር ቻቸቴ፣ የጆሮ ጭልጭሌ ታደርጋለች፡፡ እንዲሁም ለፀጉሯ ስስ ጥቁር ማሰሪያ አብራ መቅለሚያና ኩታ ተከናንባ በመቀመጥ ሙዜዎቿና አጃቢዎቿ ክብብ አድርገው ሲያጫውቷት ይውላሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ወንድሞቿና ዘመዶቿ ጥይት ይተኩሳሉ ወይም በእልልታና በጭብጨባ ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እናቷም ቡና አፍልታ፣ ዱአ /ፀሎት/ ይደረጋል፡፡ ለጉፍታ መጫኛ ተብሎ ለዘመድና ለወዳጅ ማሩ፣ ቅቤው፣ ሥጋው፣ እንጀራው፣ ዳቦው ቀርቦ ይበላል፤ ይጠጣል፡፡

ሙሽራውም በበኩሉ በሠርጉ እለት አጃቢዎቹ ጋር በመሆን በአንደኛው ሚዜ ቤት ከተጋበዙ በኋላ ወደ ሙሽራይቱ ቤት ለመሄድ ሙሽራው ይለብሳል፡፡ አለባበሱም ሱሪው ተነፋነፍ፣ ከነጭ ጨርቅ መብሩቅ የተሰራ እጅ ጠባብ ጥብቆ ያደርጋል፡፡ ከላይ ባለ ገበር ኮት ከደረበ በኋላ ከላይ ሽርፍን ኩታ ጣል ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ከቆዳ የተሰራ የሙሽሮች ጫማ አድርጎ በእጁ ዘንግ ወይም የጉማሬ አለንጋ ይይዛል፡፡

የወንዱ ወገን ሽማግሌ የሙሽራይቱን አባት ጌጡ ተሟላልህ ወይ ብሎ ሲጠይቀው ተሟልቶ ከቀረበ ከአዎንታ ይመልሳል፣ ካልተሟላ ደግሞ የወንድ አባት እስከ አሥር ቀናት ድረስ ለማሟላት ቃል ገብቶ ዋስ ይጠራል፡፡

ይህ ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ሠርገኞችና እንግዶች በየተመደበላቸው ቦታ ተቀምጠው ምግብና መጠጥ ይስተናገዳሉ፡፡ ሽማግሌዎች በመስጊድ፣ ሙሽራው ከነአጃቢዎቹ ከጎረቤት ቤት ውስጥ፣ ሙሽራይቱ ደግሞ በአባቷ ቤት ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ ለሠርገኞቹ የቀረበው ምግብና መጠጥ ከተበላና ከተጠጣ በኋላ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ለመሄድ በሚዘጋጁበት ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን፣ ከተቀመጠችበት ቤት እርሷን የአክስቷ ልጅ አዝሎ ያወጣትና ጉዞ ይጀምራሉ፡፡

ሠርገኛው ከሙሽራው ቤት በሚደርስበት ጊዜም "አዛይ መጣ፣ አዛይ መጣ" እየተባለ ይዘፈናል፣ ይጨፈራል፡፡ ሙሽራይቱ ጫጉላ ቤት ስትገባ ለእርሱ ደግሞ አልጋ ይዘረጋለታል፡፡ ከወንዱ ሙሽራ ቤት የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ለአጃቢዎችና ለታዳሚዎች ይቀርባል፡፡

በዚህ ጊዜ ሙዜዎቹ ሙሽራውን ደብቀው ሙሽራይቱ ወደአለችበት ቤት ወስደው ከጠባቂዋ ሴት ተረክበው ለእርሱ ይሰጡትና በሩን ዘግተው ይወጣሉ፡፡ ሙሽራውም ክብረ ንጽሕናዋን ከገሠሠ በኋላ ከውጭ ሲጠባበቁ የቆዩት አንደኛው ሙዜና የሙሽራይቱ ጠባቂ ድምጽ ሲሰሙ በሩን ከፍተው ይገቡና ሙዜው ለሙሽራው፣ ሴትየዋ ደግሞ ለሙሽራይቱ በኩባያ ማርና ቅቤ በጥብጠው ያጠጧታል፡፡ ከዚህ በኋላ የምሥራቹን ይዘው ሴትየዋ እልል እያለች፣ ወንዱ ሙዜ ደግሞ እየፎከረ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ወደሚገኝበትና ወደተሰበሰበበት ቦታ ይገባሉ፡፡ በዚህም ወቅት የሙሽራይቱ አባት እንደአቅሙ ዝና የሚያገኝበትን በሬ፣ ላም ወይም ሌላ ነገር ለሙሽራው ስጦታ ያበረክታል፡፡ የሙሽራይቱ እናትም እንደዚሁ ሙሉ ኩታ ሸልሜአለሁ ትላለች፡፡ ወንድሞችና እህቶችም እንደዚሁ የተለያዩ ሽልማቶችን እንደየአቅማቸው ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ ጨዋታውና ጭፈራው ይቀጥላል፡፡    

 በብሔረሰቡ ባህል መሠረት ሙሽራው ልጅቷን ለሠርጉ እለት ይዞ ስለሚሄድ ቤተሰቦቹ ሊነጋ ሲል ለሙሽሮቹና ለሙዜዎቹ የአልጋ መውረጃ ተብሎ በድብቅ ገንፎ ወይም ሌላ የተለያየ ምግብ ይሰጣቸውና ይበላሉ፡፡

ሙሽራው፣ ሙዜዎቹና አጃቢዎች በሴቷ ቤት ለአራት ቀናት ሲበሉ፣ ሲጠጡና ሲጫወቱ ይቆያሉ፡፡ በሁለተኛው ቀን ምሳ ከተበላ በኋላ ሙሽራይቱን ከጫጉላ ቤት አንደኛው ሙዜ ተሸክሞ ወደጨዋታው ቦታ ያወጣትና ከአጃቢዎች ጋር ትተያያለች፡፡ በዚሁ ዕለት ከወንዱ ቤት ተጭኖ የመጣው ዱቄት፣ ቅቤና ማር ሙዜዎች የሴቷ ቤተሰብና ቤተዘመድ ባሉበት ይታያል፡፡ ይህም የሚደረገው የጭነቱን ብዛትና የአጃቢውን ቁጥር ለማነጻጸርና ለዝና ሲባል ነው፡፡ የመጣው ዱቄትም እየተቦካና እየተዘጋጀ ከብቱም እየታረደ ቅቤና ማሩም እየተቀዳ ወደ ወንዱ ቤት እስከሚሄዱ ድረስ አጃቢዎቹ እየበሉና እየጠጡ ሙሽሮቹን እያጫወቱ ይሰነብታሉ፡፡

በሶስተኛው ቀን አንደኛው ሙዜ አጃቢዎቹን አስከትሎ ሸንኮራ እያደለና ሽቶ እየቀባ አለንጋ ይዞ ሴት ወንዱን እየገረፈ "ደመቅ በይ በዚህ ጊዜ" ሲል ደመቅ በይ የተባለችው ሴት ከሆነች "ደመቅሁ ለባሌ ለእገሌ" ስትል፣ ተጠያቂዋ ልጃገረድ ከሆነች "ደመቅሁ ወደፊት ለማገባው ባሌ" ትላለች፤ የተገረፈውና ደመቅ በል የተባለው ወንድና ባለትዳር ከሆነ "ደመቅሁ ለሚስቴ ለእከሌ" ሲል፣ ያላገባው ደግሞ "ደመቅሁ ወደፊት ለማገባት ሴት" ይላል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ከሙሽሮቹ አንስቶ እስከ ምግብ አዘጋጆቹ ድረስ ያሉት የሠርጉ ተካፋዮች ተሳታፊ በመሆን በጨዋታውም ደስታቸውን በመሣቅና በጭብጨባ ይገልጻሉ፡፡

በአራተኛው ቀን ሙሽራው ለሙሽራይቱ ይዞ የመጣው ጥሎሽ/ ቤኒንና ካች የሚባል ቀሚስ፣ ሽቶ፣ ፎጣ፣ ሻሽ፣ ጫማ፣ ጥላ፣ መስታወት/ የገላና የልብስ ሳሙና ለእናቷ ቀሚስና መቅለሚያ፤ እንዲሁም ለአባቷ ሸሚዝ፣ ሽርጥና ጥምጣም የልጅቷ ዘመድ አዝማድ በተሰበሰቡበት ወጥቶ ይታያል፡፡ ከዚህ በኋላ አጃቢዎቿ የማሽላና የጤፍ እንጀራ አነባበሮ፣ ዶሮ ወጥ ከነእንቁላሉ፣ መቃሊሞ፣ አሊጣጦ፣ ጠመሸኛ ተጋብዘው ለእያንዳንዳቸው ሙልሙል ዳቦ ይታደላቸውና ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

ሙሽራውና ሙዜዎቹ ግን ለአሥራ ሁለት ቀናት በሴቷ ቤት እየታረደና እየተጋገረ ሲበሉና ሲጠጡ ይቆያሉ፡፡ በአሥራ አንደኛው ቀን የምግብ አዘጋጆችንና የሙሽራዋን ቤተሰብ ልብስ ሰብስበው ይዘው ወደወንዝ በመውሰድ ያጥቡና ይመጣሉ፡፡ በነጋታው ለአጃቢዎቹ የተደረገላቸው የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ለሙሽራውና ለሙዜዎቹ ተፈጽሞላቸው ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

ሙሽራው ወደ ቤቱ ተመልሶ በሄደ በሶስተኛው ቀን በሴቷ ቤተሰብ ተደግሶ መልስ ይጠራል፡፡ በመልስ ጊዜ የሚደረገው ዝግጅት በሠርጉ እንደነበረው ባህላዊ የምግብ ዓይነትና አቀራረብ ተዘጋጅቶ ሙሽሮቹ ከአጃቢዎቻቸው ጋር በመሆን ለአራት ቀናት ሲበሉ፣ ሲጠጡና ሲጫወቱ ይቆያሉ፡፡ በአራተኛው ቀን ለሙሽራውና ለአጃቢዎቹ አሸኛኘት ሲደረግላቸው ሙሽራይቱ ግን ከቤተሰቦቿ ጋር ትቀመጣለች፡፡

በዚህም ጊዜ ሙሽራው እየተደበቀ ልጅቷን ለተወሰነ ጊዜ ካያት በኋላ ልውሰዳት ብሎ ሽማግሌ ልኮ ቤተሰቦቿን ይጠይቃል፡፡ እናትና አባቷም በዚህ ቀን ይውሰዳት ብለው ይመልሳሉ፡፡ ቀኑም ሲደርስ አንደኛው ሙዜ ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ቤት ይሄድና ሙሽራይቱን፣ ሙዜዎቿንና አጃቢዎቿን ይዞ በአህያ ዱቄት፣ ዳቦ፣ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቅቤና ማር ጭኖ፣ ሙክት በግ እየነዳ ወደሙሽራው ቤት ይመለሳል፡፡ ከልጅቷ ቤተሰቦች ቤት የመጣው ዱቄት ተጋግሮ፣ የበጉም ሙክት ታርዶ ይዘጋጅና ጎረቤት ተጠርቶ የመታወቂያ ግብዣ ይደረጋል፡፡ ሥነ ሥርዓቱም እጅ መታጠቢያ በመባል ይታወቃል፡፡

የሙሽራይቱና የሙሽራው ሙዜዎችና አጃቢዎች ለአራት ቀናት ቆይተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ የልጁ አባት ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የእርሻ መሬት፣ በሬ፣ ላም፣ አህያ፣ ጉድጓድ እህል፣ የቤት ዕቃ ሲሰጣቸው የልጅቷ እናትና አባት ደግሞ የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን ይሰጧቸውና ጎጆ ወጥተው በራሳቸው መኖር ይጀምራሉ፡፡

በአርጎባ ባህል መሠረት ከጋብቻ በፊትና በኋላ ወንዱም ሆነ ሴቷ የሚለዩበት የተለያዩ ምልክቶችን ያደርጋሉ፡፡ ያላገባች በፀጉሯ ላይ ምንም ነገር የማታደርግ ሲሆን፣ ካገባች በኋላ ግን በፀጉሯ ላይ ጉፍታ እንዲሁም በግራ እጇ ላይ ሁለት አምባሮችን ታደርጋለች፡፡ አንድ ወይም ሶስት ወይም ከዚያ በላይ አምባር አይደረግም፡፡ ያላገባ ወንድም ፀጉሩን የማይቆረጥ እንዲሁም በአንገቱና በግራ እጁ ላይ ጨሌ የሚያስር ሲሆን ካገባ በኋላ ግን ፀጉሩን ይቆረጣል፡፡  
Last Updated ( Monday, 13 October 2008 )
 
< Prev   Next >