Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Saturday
Oct 11th
Home arrow Sections arrow ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አገር እናድርጋት!
ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አገር እናድርጋት! E-mail
Wednesday, 23 January 2008
ኢንቨስትመንት በሌለበት ከድህነት መላቀቅ ብሎ ነገር የለም፡፡ ስራ አጥነት የሚወገደው ኢንቨስትመንት ሲኖር ነው፡፡ የተሻለ ገቢ ሊኖር የሚችለው የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴና ትርፋማነት ሲኖር ነው፡፡ የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴና ትርፋማነት ደግሞ ካለ ኢንቨስትመንት ሊሳካ አይችልም፡፡

Imageመንግሥት ብቻውን አገር ሊያለማ አይችልም፡፡ ይችላል ካልንም ዘለቄታዊ ልማት አይሆንም፡፡ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር እየተናጋ የሚከርም ልማት ይሆናል፡፡ የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሚና ግን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ስለሆነም በሕግና በስነ ሥርዓት የሚሰሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በብዛት አግኝተን መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንዲኖር እንዴት እናድርግ የሚለው ጉዳይ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

የዚህ ዋናው ቁም ነገር ደግሞ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳድሮና ብቁ ተፎካካሪ ሆኖ መገኘት ነው፡፡

ከሁሉም በፊት ሊፈተሽ የሚገባው የኢንቨስትመንት ሕግና ፖሊሲ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ሕግና ፖሊሲያችን ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ነው ወይ፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን ጅቡቲ ከመሄድና ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ኢትዮጵያ ትሻላለች የሚሉበት የተሻለ ሕግና ፖሊሲ አለን ወይ፣ የሚለውን ማየት ትተን እንግዳ ተቀባይና ጨዋ ሕዝብ ስለሆንን ይመጣሉ ማለቱን እንርሳው፡፡ እንኳን ኢንቨስተርና ቱሪስትም ከነሃብታችንና ከነጨዋታችን ከኢትዮጵያ ይልቅ ኬንያና ታንዛኒያን ይመርጣሉ፡፡

የሚጠየቁት ጥያቄዎች የታወቁ ናቸው፡፡ መሬት፣ ባንክ፣ ግብር፣ ቀረጥ፣ መሠረተ ልማት የመሳሰሉት ነገሮች ከሕግ አኳያ እንዴት ይታያሉ? የሚለውን አይተውና መርምረው ነው የሚመጡት፡፡

የኢንቨስትመንት ሕጎቻችን በየጊዜው ተሻሽለዋል፡፡ ኢሕአዴግ ያወጣው የኢንቨስትመንት ሕግ ራሱ በተለያዩ ጊዜያት ተሻሽሏል፡፡ ግን አሁንም በቂ አይደለም፡፡ አሁንም ተወዳዳሪና ተፎካካሪ አይደለም፡፡ በቂ እስካልሆነ ድረስ መከለስ ያስፈልጋል፡፡ በተገቢው ፍጥነት፣ ትኩረት ተፈትሾ፣ ተሻሽሎ ተወዳዳሪ ሆኖ ሊቀርብ ይገባዋል፡፡

ከሕግና ከፖሊሲ በተጨማሪም አሰራራችንና ቢሮክራሲያዊ ቁጥጥራችን ልዩ ትኩረትና መሻሻል ያስፈልገዋል፡፡ ፍትሕና ውሳኔ እስኪሰጥ፣ አለቃ እስኪፈርምና ከውጭ አገር እስኪመለስ ሆቴል ተከራይቶ ገንዘቡንና ጊዜውን የሚያባክን ባለሀብት የለም፡፡ ከላይ እስከታች ገንዘብ እየበተነ የሚውል ባለሃብትም የለም፡፡ ይህ ባለበት አገር ሃብትና ገንዘቤን የማፈሰው ለምንድነው? እያለ መበርገጉ አይቀርም፡፡ በተለይ ጊዜ የማባከን ጉዳይና የጉቦ ጉዳይ በእጅጉ ፀረ ልማት ሆኗልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የኢንፎርሜሽን፣ የፕሮሞሽንና የማስተዋወቂያ ጉዳይም ከኢንቨስትመንት ጋር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ኢንቨስተር ኢንፎርሜሽን ይፈልጋል፡፡ ኢንፎርሜሽን ግን አያገኝም፡፡ ምን ምን የተዘጋጀ ነገር እንዳለ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ በየትኛው ዘርፍ ቢሰማራ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ፕሮሞሽንና ኢንፎርሜሽን ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ይህ አላቸው? ለዚህ የተዘጋጁ ዌብሳይቶች አሉን? ስለኢንቨስትመንት ሲታሰብ ይህም ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ ለኢንቨስትመንት መንግሥት የሚያበረክተው ድጋፍና ጥበቃ ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡

ሁለት የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በምሳሌነት እንመልከት የመድሃኒት ፋብሪካዎችና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፡፡ መድሃኒትና ጨርቃ ጨርቅ ለማምረት ባለሀብት ከባንክ ይበደራል፣ መሬት ይገዛል (እሺ በሊዝ"፣ ማሽነሪ ያስገባል፣ ኢንሹራንስ ይገባል፡፡ ገና ስራ ከመጀመሩ በፊት ወለድ ክፈል ይባላል፡፡ ይህንን ሁሉ መከራ አይቶ ማምረት ሲጀምር ግን በኮንትሮባንድ የገባ ዕቃ ይወዳደረዋል፡፡ የዚህ ርካሽ ነው የእሱ ውድ ነው፤ እየተባለ ገበያ ያጣል፡፡ አያተርፍም፣ ይከስራል፡፡

ይህ ምን የሚሉት ኢንቨስትመንት ነው? ዘርፉ እጅግ በጣም ጠቃሚ ዘርፍ ነው፡፡ ትርፉ እጅግ በጣም ጠቃሚ ትርፍ ነው፡፡ ኪሳራ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መንግሥት ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ወይስ "ስራህ ያውጣህ" ብሎ ነው የሚተወው?

ሌላው የኢንቨስትመንት ትኩረት ደግሞ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ባለሀብቶች ተቀናጅተው በ"ጆይንት ቬንቸር" የሚሰሩበት ሁኔታ ነው፡፡ የሩቅ ምስራቅ አገሮች የበለፀጉት አንዱ ምክንያት ዜጎቻቸው የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡና አብረው ኩባንያዎች እያቋቋሙ እንዲሰሩ በማድረግ ነው፡፡ እንዲያውም የውጭ ባለሃብት ካመጣችሁ የናንተን (የዜጎችን) ድርሻ እኔ እሰራዋለሁ፤ እያለ መንግሥት ያበረታታቸዋል፡፡

በእኛ አገርስ እንዴት ነው? መንግሥት ኢትዮጵያውያንና የውጭ ባለሀብቶች በጋራ እንዲሰሩ ምን ማበረታች ያደርጋል? ምን ዋስትና ይሰጣል? ምን ጥበቃ አለው?

በኢንቨስተሩም ዙሪያ ሊሰሩ የሚችላቸውና የሚገቡ ነገሮች እጅግ በርካታ ስለሆኑ እዚህ ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ በጥቅሉ ለኢንቨስተሮች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነው የምንለው፡፡ የኢንቨስትመንት ባለሃብቶች በጋራ ሆነውም ሆነ በተናጠል፣ ከውጭ ይምጡ የአገር ውስጥ፣ በከፍተኛ ደረጃ ለልማት እገዛ ለሚያደርግ ኢትዮጵያውያን ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የአለም ባንክ ገንዘብ ጣጣ አለው፡፡ የአይ.ኤም.ኤፍ ገንዘብ ጣጣ አለው፡፡ ከዛና ከዚህ የሚመጣው እርዳታና ብድር ውልና ፊርማው መዓት ነው፡፡ "በአለበዚያ" የታጀበም ነው፡፡

አስተማማኝ የልማት ዋስትና ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ልዩ ትኩረት አመቺ ሕግና ፖሊሲ ቀልጣፋ ቢሮክራሲና አበረታች አሰራር ይደረግበት፡፡ ተወዳዳሪና ተፎካካሪም ሆነው ለመቀጠል የበቁ ይሁኑ!

Last Updated ( Thursday, 24 January 2008 )
 
< Prev   Next >