| ቀለብ የመስጠት ግዴታን ያለመወጣት... |
|
| Sunday, 12 October 2008 | |
|
ቀለብ የመስጠት ግዴታን ያለመወጣት በወንጀል ያስቀጣል
በህጉ እንደተመለከተው ሁሉም ሰው ቀለብ የመቀበል መብት፣ የመጠየቅ መብት እና ቀለብ የመስጠት ግዴታ የለበትም፡፡ በህጉ ተለይተው የተመለከቱ ሰዎች ናቸው ቀለብ ለመቀበል መብት የሚኖራቸው፡፡ በአንፃሩ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸውም ሰዎችም እንዲሁ በቤተሰብ ህጉ ተመልክተዋል፡፡ ቀለብ ለመጠየቅ መብት የሚኖረው ሰው በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 201 መሠረት ሠርቶ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነ ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለው እና በችግር ላይ የወደቀ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም አይነት ገቢ ያለው ሰው ቀለብ የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ህግ አንቀጽ 198 እንደተመለከተው ቀለብ የመስጠት ግዴታ በቀጥታ ወላጆች እና ተወላጆች እንዲሁም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች እንዲሁም በወንድማማቾች እና እህትማማቾች መካከል ነው፡፡ ለፍርድ ቤት በሚቀርቡ አቤቱታዎች መሰረት የቀለቡ መጠን የሁለቱም ሁኔታ ተገናዝቦ ሲሆን፣ ቀለብ ጠያቂው ያለበትን ችግር ወይም ለኑሮ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ወጪ እንዲሁም የቀለብ ሰጪው ቀለብ የመስጠት አቅም በአንድነት በማገናዘብ እንደሆነ አንቀጽ 202 በግልጽ ያመለክታል፡፡ ይህን ሁኔታ ፍርድ ቤት አገናዝቦ ቀለብ ሲወስን በገንዘብ ነው፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ግዴታውን የሚወጣው በፍርድ ቤት ለቀለብ ተቀባዩ እንዲሰጥ የታዘዘውን ገንዘብ በመስጠት ነው፡፡ በተግባር የሚታየው ግን ፍርድ ቤት የወሰነው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ወገን ለመፈጸም ፈቃደኛ ያለመሆኑን ነው፡፡ ከላይ ቀለብ የመስጠት ግዴታ በህግ የተመለከተ እና የግድ ሊፈጸም (ሁኔታዎች ከተሟሉ) የሚገባው ሲሆን ግዴታውን ባለመፈጸም የቀለብ ተቀባይ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ መገመት አያዳግትም፡፡ ቀለብን በተመለከተ አግባብነት ያላቸው የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ ውስጥ ቀለብ የመቀበል መብቱን ለማግኘት ሰርቶ ገቢ ለማግኘት የማይችል እና ችግር ላይ የወደቀ መሆኑ ከመረመረ የእድሜ ሁኔታን ከግምት ውስጥ እንዲገባ አላደረገም፡፡ ምን አልባት አሥራ ስምንት ዓመት የሞላው/ት ልጅ በመደበኛ ደረጃ የኖረ ለራሱ ገቢ ሊያገኝ የማይችል እና ችግር ላይ የወደቀ መሆኑን እድሜ ነው ተብሎ ላይገመት ስለሚችል እና በተግባር ጥገኝነት የሚኖር በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ የቀለብ ጥያቄ የሚነሳው አባት እና እናት ሲለያዩ በአባትና በልጅ መካከል ሲሆን ፍርድ ቤት የወሰነውን ቀለብ ለማስፈጸም የልጅ እናት ወይም የሕጻኑ ወኪሎች ሲቸገሩ ይታያል፡፡ በተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 658 (1) (2) ቀለብ መስጠት በሕግ ወይም በውል ግዴታ ያለበት ሰው ያለ በቂ ምክንያት ግዴታውን ካልተወጣ (ሊያሟላ የሚገባው የገንዘብ ግዴታ ካልተወጣ) አቤቱታ ሲቀርብ በመቀጫ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡ በሕግ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ማለት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 ላይ የተዘረዘሩት በቀጥታ ወላጆች እንዲሁም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች ወንድማማቾች እህትማማቾች መካከል ሲሆን፣ መብቱ የተገኘው የቤተሰብ ህጉ በግልጽ እነዚህ ቀለብ ለመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው በመደንገጉ ነው፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሰዎች በቤተሰብ ሕግ መዘርዘሩ ቀለብ ጠያቂው በቀጥታ ጥያቄውን ግዴታው ላለባቸው ወንድሞቹ ወይም እህቶቹ ወይም ወላጆች ወይም ባል ወይም ሚስት ማቅረብ የሚችል ሲሆን ፍቃደኛ ካልሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 65 መሠረት ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ቀለብ የግድ የፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ ሲፈቀድ እንዳልሆነ ለማሳየት የተፈቀደ መብት መሆኑን ለማሳየት በህግ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው በግል ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ቀለብ ለመስጠት ውል የተዋዋለ ሰው ግዴታውን ባይወጣ ውሉ ከሚያስከትለው የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ገንዘቡን እንዲያገኝ በውሉ የተመለከተውን የቀለብ ገንዘብ በተጨማሪ የወንጀል ክስ ሊቀርብበት እንደሚችል አንቀጽ 65 በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 65/1 እና 2 ለመረዳት የሚቻለው በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ወይም በሌላ አግባብነት ባለው ህግ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ግዴታውን ባይወጣ የፍትሐ ብሔር ክስ መሠረት ሳያስፈልግ ግዴታውን ባለመወጣቱ ብቻ በቀጥታ የወንጀል ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በህግ በቀጥታ ግዴታ ባይጣልበትም እንኳ በውል ቀለብ እሰጣለሁ በማለት ከጋብቻ ውጭ ላስረገዛት ሴት ወይም አብሯት ለኖረ ሴት ወይም ለተወለደ ልጅ አንድ ህጻን ካሉት በርካታ መብቶች አንዱ ለእድገቱ መሠረታዊ እና አስፈላጊ የሆኑ ፍላጎቶችን እንዲሟሉ የሚያስገድድ ሲሆን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ አርፎባቸው ሳይፈጽሙ ወይም አባት ለልጅ ቀለብ ለመስጠት በውል ተስማምቶ ሳይፈጸም ከቀረ በተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 658 መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡ በፍርድ ቤት የተወሰኑ እና በውል የተፈረሙ ቀለብ የመስጠት ግዴታዎች ያሉ እና በየጊዜው የሚከናወኑ ቢሆንም አፈጻጸሙ በተለይ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ቀለብ ጠያቂዎች ውጣ ውረድ በጉዳዩ እንዳይቀጥሉበት ተስፋ እያስቆረጠባቸው ይገኛል፡፡ ይህን የወንጀል አንቀጽ በውል ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገኙ ቀለብ የመቀበል መብትን ለማስፈጸም ብቃት ያሉት ሲሆን ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ወገን ግዴታውን ባለመወጣቱ የወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ሲያውቀው በፈቃደኝነት ቀለብ ለመስጠት እንዲነሳሳ የማድረግ ጠቀሜታ አለው፡፡ የቀለብ የመስጠት ግዴታ ቀላል ቁጥር የሌላቸው እናቶች ሕጻናት ችግር ሲሆን፣ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ያስቀመጠ የተጠያቂነት መፍትሄ ችግሩን ለማቃለል እና ለወደፊትም እንዲቀንስ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 658/2/ ሌላ ጠቀሜታ ለሴቶች እና ለቀለብ ተቀባዮች አለው፡፡ በሕግ ወይም በውል ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ቀለብ ሰጪ ቀለብ ለመስጠት ላስረገዛት ሴት ወይም ከጋብቻ ውጭ አብሯት ለኖረ ሴት ወይም ከጋብቻ ውጭ ለወለደው ልጅ ግዴታ ካለበት ይህን ግዴታ ካልተወጣ የወንጀል ተጠያቂነቱ አይቀርለትም፡፡ ይህ አንቀጽ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ላይ አንዲት ሴት ከጋብቻ ውጭ አብራው ከምትኖረው ወንድ የፀነሰች ከሆነ አና በዚሁ እርግዝናዋ ጊዜ አብሯት ይኖር ከነበረው ወንድ ቀለብ መጠየቅ በህግ የማትችል ከሆነ እና አብሯት የሚኖረው ሰው በእርግዝናዋ ወቅት ቀለብ ለመስጠት ውል ከገባ ይህን የገባውን ግዴታ እንዲፈጸም ይገደዳል፡፡ ለመፈጸም ፍቃደኛ ካልሆነ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |