| ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ |
|
| Wednesday, 15 October 2008 | |
ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ? የመንግሥት ወይስ የፀረ መንግሥት? የኢሕአዴግ ወይስ የፀረ ኢሕአዴግ? የሚሉ ጥያቄዎች የሚያስነሱ አንዳንድ ተግባራት እየታዩ ናቸው፡፡ ሊተኮርባቸውና ሊስተካከሉ የሚገባም ይመስለናል፡፡ በቡታጅራ በመስቃን ወረዳ አለመረጋጋት ይታያል፡፡ አለመረጋጋቱን የሚፈጥረው ያለው ሁኔታ በጭራሽ አላስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የወረዳው ስም "መስቃን" ነው፡፡ በወረዳ ምክር ቤትም ተወስኗል፡፡ "መስቃን ዶቢ" መባል አለበት የሚል ወገን ሲነሳ በምክር ቤት ይወሰን ይባላል፡፡ እንደገናም በድምጽ ብልጫ "መስቃን" ወረዳ ይሁን ተባለ፡፡ ከዚህ ወዲያ መስቃን ዶቢ ካልተባለ እየተባለ ማሰር መፍታት አንደኛውን እንደገና መክፈት እንደገና መዝጋት ማስፈራራት አስፈላጊ ነወይ? ክልሉን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ ነው፡፡ መስቃን ይሁን ብሎ የወሰነው ይኸው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ነው፡፡ እንደገና መታየት ሲያስፈልግም በሕገ ደንቡ መሠረት ሶስት አራተኛው ጥያቄ እንዲያቀርብ ተደርጎ ይታያል፡፡ ሕግ አውጪ እያለ ሕግ አስፈፃሚ አካል እዚህ አጀንዳ ውስጥ ገብቶ አለመረጋጋት መፍጠሩ እውነት ለሕዝብ ድጋፍ ወይስ ሰላምና ልማትን ማደናቀፍ? እውነት የመንግሥት ወይስ ፀረ መንግሥት? እውነት የኢሕአዴግ ወይስ ፀረ ኢህአዴግ? በቅርቡ የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ሕገ ወጥ ናችሁ ላላቸው ተከራዮች እንዲወጡ ትዕዛዝ እየሰጠ በርካታ ቤተሰቦች ዘንድ አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በርግጥ ሕገ ወጥነት ይቀጥል አይባልም፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ቤት የያዙ ነዋሪዎች እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት አይባልም፡፡ ነገር ግን ወደ ሕግ መልሶ ሰላምና መረጋጋት ፈጥሮ መቀጠል የሚቻልበትን መንገድ በቅድሚያ እንደ አማራጭ ማየት ይገባል፡፡ ቁልፍ ገዝተው ቤት የያዙ፣ የሰሩትን ቤት እያከራዩ በኪራይ ቤቶች የተቀመጡ፣ (ባለስልጣኖች ጭምር) አገር ለቀው ሲሄዱ እንኳ ለሚፈልጉት "አውርሰው" ያስተላለፉ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ከነዋሪዎች እንደሚሰማው ከ60 ዓመት በላይ ከኖሩበት ውጡ ተብለዋል፡፡ ከአሁን በፊት ኪራይ ቤቶች ራሱ የተከራይ ተከራዮችን ውል ፈርሙ ብሎ ግማሹ ተመዝግቦ ግማሹ ሳይመዘገብ ቀርቷል፡፡ ለምን እንዳቋረጠው ባይገባንም በዚያ የተዛባ አሰራር የተፈጠረውን ክፍተት አስተካክሎ በዚያው መስመር ውል እንዲፈርሙ አድርጎ መቀጠል የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ በወቅቱ ግዳጃቸውን ያልፈፀሙትን ከቅጣት ጋር እንዲስተካከሉ ማድረግ ይቻላል፡፡ በቀላሉ ሊፈታ እየተቻለና መንግሥትም በቅጣት አስፈላጊ ገቢውን አግኝቶ ማስተካከል እየቻለ አላስፈላጊ ረብሻ፣ ጥላቻና አለመረጋጋት መፍጠር ጠቃሚ ነውን? ተግባሩስ ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ? የመንግሥት ወይስ የፀረ መንግሥት የኢሕአዴግ ወይስ የፀረ ኢሕአዴግ? በዓለም ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም በአገራችን ጨምሯል፡፡ ምናልባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ በዓለም ደረጃ ዋጋ ቢቀንስም፣ ካጋጠመን የገንዘብ እጥረት የተነሳ ድጎማውን ለሌላ ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ፣ ቁጠባ የወቅቱ አጀንዳ ስለሆነ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ኬሮሲን መጨመር ነበረበትን? ቤንዚን ቢጨምር ይሻላል ወይስ ዝቅተኛ ኑሮ ያለው ኅብረተሰብ የሚጠቀምበትን ኬሮሲን ላይም መጨመር፡፡ በኬሮሲን ላይ የተጣለው ጭማሪ ድሃውን ሕዝብ የሚጎዳ በመሆኑ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ተግባሩ ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ? የመንግሥት ወይስ የፀረ መንግሥት? የኢሕአዴግ ወይስ የፀረ ኢሕአዴግ? የፓርላማ አንድ ትልቁ ተግባር ሕግ ማውጣት ነው፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዴት እንደሚዋቀሩና ኃላፊነታቸው ምን እንደሚሆን መወሰን ነው፡፡ በውሳኔው መሰረት የመንግስት የሚኒስትሮችን ምክር ቤት ያደራጃል፤ የማደራጀት መብትም ተሰጥቶታልና፡፡ ከማደራጀት ውጭ ያለውን መብትና ስልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መስጠት ግን የፓርላማውን ሚናና ኃላፊነት ያደበዝዘዋል፡፡ ፓርላማውን ከመንግሥት አወቃቀርና ኃላፊነት ሚና ውጭ ያደርገዋልና፡፡ በሕገ መንግሥት አንፃር ሲታይና ፓርላማውም በኢሕአዴግ እጅ ስለሆነ የፈለገውን ማስወሰን ስለማያቅተው ይህ ሕግ ማውጣት ለምን አስፈለገ ያሰኛል፡፡ ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ? የመንግሥት ወይስ የፀረ መንግሥት? የኢሕአዴግ ወይስ የፀረ ኢሕአዴግ? የመንግሥት አካላት፣ ሕዝባዊ አካላት፣ የግል አካላት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ሁሉ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም መስራት አለባቸው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት አካላትም ሆኑ የሕዝብ ድርጅቶች ግን አገርንና ሕዝብን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲያጋጩ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ከፊፋ ጋር ማጋጨት፡፡ ይህ ነገር በቀናና በሕጋዊ መንገድ ማስተካከል ሲቻል ዝም ብለው እያዩ ችግሩ እንዲቀጥል ማድረግ ድጋፍ ወይስ ማደናቀፍ? በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ እንዲህ ናት፣ እንዲህ ሆነች፤ እንዲህ አደረገች፤ እየተባለች ትወቀሳለች፡፡ መከላከል የማትችለውን ያህል ከመከላከል ይልቅ ይበልጥ የሚያስወቅስ ሥራ ቃል አቀባይ በተባለው አካል ሲፈፀም ይታያል፡፡ በማን ስም? በኢትዮጵያ ስም" የመንግሥት ቃልና ንግግር መሳቂያ እየሆነ የሚታይበት፣ አንዱ ምክንያት በቃል አቀባዩ አቀራረብ ወይም ጭራሹኑን ባለማቅረብ ነው፡፡ ውጤቱም የሚሊዮኖች ኪሳራ ይሆናል፡፡ ይህ ታዲያ ድጋፍ ነው ወይስ ማደናቀፍ? የመንግሥት ወይስ የፀረ መንግሥት? የኢሕአዴግ ወይስ የፀረ ኢህአዴግ? በተደጋጋሚ የሚሰማውንና የሚነገረውን፣ "የኢሕአዴግ ጠላት ራሱ ኢሕአዴግ" መሆኑን የሚያረጋግጥ ድርጊት ይታያል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጠንካራ ተቃዋሚ ለማየት ባንታደልም ሁኔታውን መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ ለበጎ ነገር መጠቀም ነበረበት፡፡ ከሕዝብ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብና የሕዝብን ችግር ተረድቶ ለመፍታት አመቺ ሁኔታ አለ፤ ብሎ ማመን ነበረበት፡፡ ግን ሲጠቀምበትና ሁኔታዎች ሲስተካከሉ አይታዩም፡፡ ለምን አይታይም? የመንግሥት አካላት ወይም የኢሕአዴግ አካላት፣ በሕዝብ ስም፣ በመንግሥት ስም፣ በኢሕአዴግ ስም፣ ሕዝብና ኢሕአዴግን ወይም ሕዝብንና መንግሥትን የሚያጋጭ ሥራ ስለሚሰሩና "ተዉ" የሚል ስለጠፋ ነው፡፡ ስለሆነም ነው፤ ኢሕአዴግ ሁሌም ደፍሮ ራሱን ይፈትሽ፤ የሚለው አስተያየት ጎልቶ የሚሰማው፡፡ |
|
| Last Updated ( Wednesday, 15 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |