Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Jan 08th
Home arrow Sections arrow የዓለም ማዕከላዊ ባንኮችና የሰሞኑ ሩጫቸው
የዓለም ማዕከላዊ ባንኮችና የሰሞኑ ሩጫቸው E-mail
Wednesday, 15 October 2008
በጋዜጣው ሪፖርተር

ዓለም በከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ እየታመሰች ትገኛለች፡፡  በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች የሕዝቡ የዕለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴ የሚከናወነው በብድር ተመርኩዞ ነው፡፡

ማንኛውም ሥራ ያለው ግለሰብ ቤት፣ መኪና መግዛት ቢፈልጉ ወይም ለጉብኝትና ለመዝናኛ የሚሆን ገንዘብ ሲሹ በቀላሉ ከየትኛውም ባንክ ተበድሮ የፍላጐቱን መፈፀም ይቻለው ነበር፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡

በዚህ አሰራር ሳቢያ ብዙዎቹ ባንኮች ገንዘብ አልባ ሆነው እንኳን የሚያበድሩት እስትንፋሳቸውን አቆይተው የሚውተረተሩበት የገንዘብ አቅም ማጣታቸውን ይፋ ያደረጉበት እና ዳር እስከ ዳር ሲታመሱ የሰነበቱበት ክስተት ተስተውሏል፡፡ ብዙዎቹም (የአሜሪካውን ኘሬዚዳንት ጨምሮ) በአጭር ጊዜ የሚቀረፍ ችግር እንዳልሆነ ሲናገሩ አስተውሏል፡፡

ትናንት ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ያሉ ማዕከላዊ ባንኮች ቀውሱ እንዲረጋጋና በባንክ አሠራር ስርዓቱም ላይ መተማመንን ለመፍጠር ይቻል ዘንድ የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን አትቷል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት የፋይናንስ ሚኒስትሮች በአባል አገሮች ውስጥ ለሚጠራቀም የባንክ ተቀማጭ ዋስትና በዓመት ከ2ዐ ሺህ እስከ 5ዐ ሺህ ዩሮ ለመመደብ ተስማምተዋል፡፡ አንዳንድ ትልልቅ የፋይናንስ ተቋሞች በተለይ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ለሚባሉትም ድጋፍ ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን አንዳንድ አገሮች እስከ መቶ ሺህ ዩሮ ለባንክ ዋስትና እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የጣልያንና የኦስትሪያ መንግሥታት ባለ 13 ነጥብ ረቂቅ እቅድ በማዘጋጀትና የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክን ለመደገፍ የተስማሙ ሲሆን በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ አቋም ወስደዋል፡፡ በሊኪውዲቲ፣ በባንኮች መካከል ለሚካሄድ ብድር ዋስትና እና አመኔታ ያጡ ባንኮችን መልሶ በካፒታል ማደራጀት በሚሉት አንኳር ነጥቦች ተስማምተዋል፡፡ ሮይተርስ የፈረንሳዩን ዕለታዊ ጋዜጣ ሌሞንድን ጠቅሶ እንደዘገበው "ጠቅላላው የአውሮፓ አገሮች 1.3 ትሪሊዮን ዩሮ ከተዘፈቁበት ቀውስ ሊገለገላቸው እንደሚችል አመልክቷል፡፡

የእንግሊዙ ማዕከላዊ ባንክ በባንኮች መካከል ለሚካሄድ ብድር 500 ቢሊዮን ፓውንድ የመደበ ሲሆን ለአስቀማጮች የቁጠባ ዋስትናቸው ከነበረበት የ35 ሺህ ፓውንድ መተማመኛ ወደ 5ዐ ሺህ ፓውንድ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የወለድ መጠኑን በ0.5 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

የግሪክ መንግሥት በበኩሉ የአስቀማጮችን ሒሳብ መታደግ ያስችለው ዘንድ የ2ዐ ሺህ ዩሮ ዋስትና አፅድቋል፡፡ የአየር ላንድ ማዕከላዊ ባንክ የ4ዐዐ ቢሊዮን ዩሮ ዋስትና ከመመደቡም በላይ በውጭ አገር ባለሃብቶች ባለቤትነት የማተዳደሩ ባንኾችም የዋስትናው አካል እንደሚሆኑ አሳውቋል፡፡ በጠቅላላወ በግሉ ሴክተር ለመንቀሳቀሱ ባንኮች ሙሉ ዋስትና ይሰጣል፡፡

በጀርመን መንግሥትም በሃይድሮ ሪል ስቴት፣ በንብረትና በሕዝብ ተቋማት እና አበዳሪዎች ለሚንቀሳቀሰው ገንዘብ የ68 ቢሊዮን ዩሮ የብድር ዋስትና ሰጥቷል፡፡

ወደ መካከለኛው ምስራቅ ስንመጣ ደግሞ ኳታር በ5.3 ቢሊዮን ዶላር የአገሪቱን ባንኮች በአክሲዮን ለመግዛት ወስናለች፡፡ የሲንጋፖር ማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ቀውሱን በሚመለከት መመሪያ ሲያወጣ የውጭ ምንዛሪ መጠኑን ከነበረበት በመቀየር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ተፈላጊነት ባገናዘበ መልኩ እንዲሰራበት አድርጐታል፡፡ አንድ የሲንጋፖር ዶላር መሳለመሳ ለግብይት ከሚውል ይልቅ ቀስ በቀስና በተመጠነ መልኩ ልውውጥ ማድረግ በሚያስችለው አካሄድ ቀይሮታል፡፡

ሕንድ ዝቅተኛውን የግዴታ ተቀማጭ መጠን በ7.5 በመቶ ወደታች በመቀነስ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ባንኮች ገንዘብ እንዲገባ የሚያስችል አሰራር ዘርግታለች፡፡

በየአቅጣጫው አብዛኞቹ የማዕከላዊ ባንኮች (ቀጥታ የገንዘብ ቀውሱ የሚመለከታቸው) የባንክ አሰራር ማሻሻያዎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሆላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ስዊድን፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አበር ኢምሬትስ እና አውስትራሊያ የመሳሰሉት አገሮች እርምጃ እየወሰዱ ከሚገኙ አገሮች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አሶሼትድ ኘሬስ በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቀው ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ በፊት ከመደበው የ7ዐዐ ቢሊዮን ዶላር ድጐማ በተጨማሪ የ25ዐ ቢሊዮን ዶላር ድጐማ መመደቡን ኘሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን የጃፓን መንግሥት በበኩሉ በፋይናንስ ቀውስ ሳቢያ ለተከሰተው የኢኮኖሚ መዋዥቅ ይረዳ ዘንድ የ1.7 ትሪሊዮን ዶላር እርዳታና ድጐማ ለማድረግ መፍቀዱ ተሰምቷል፡፡

አብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ የእስያ አገሮች ቀውሱን የሚቋቋሙበት ጫንቃ እንዳላቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ዤኑዋ ከትናንት በስትያ እንደዘገበው ቻይና በዓለም የተከሰተውን የገንዘብ ቀውስ በተመለከተ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት ትብብር እንደምታጠናክርና በቀውሱ መፈታትም እንደምትሠራ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

ሚ/ር ዩ ጃንግ፣ የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ገዢ እንዳሉት "ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጥረቱን በማጠናከር አስቸኳይ መፍትሔ ሊያመጣ ይገባል" ካሉ በኋላ የዓለም እድገትን ለመግታት እንደሚችል ጠቁመው የኢኮኖሚና የፋይናንስ መረጋጋትን ለማምጣት መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ቀናት ወዲህ መጠነኛ መረጋጋት እየተስተዋለ መሆኑን የአሶሼትድ ኘሬስ ዘገባ ቢጠቁምም የፋይናንስ ቀውሱ በአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ በመሆኑ በተዘዋዋሪ ተጐጂ የሚሆኑት ድሃ አገሮች በተለይ አፍሪካውያን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በየስብሰባውም ይህንኑ እየገለፁ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የዓለም መሪዎች ስብሰባ የአፍሪካ መሪዎች በየፊናቸው ለአፍሪካ የሚደረገው እርዳታና ትብብር በቀውሱ ሳቢያ ሊገታና ችግር ውስጥ ሊወድቅ እንደማይገባው አሳስበዋል፡፡
 
< Prev   Next >