Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Wednesday
Oct 15th
Home arrow Sections arrow ድምፁ የጠፋ ዜና
ድምፁ የጠፋ ዜና E-mail
Wednesday, 23 January 2008

/ቃለአብ አዳነ/

ከ2007 የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ አዲሱን የ2008 የአውሮፓውያን ዓመት እስከ አሁን እንዳለ ወጥሮ የያዘውን፣ ከኢትዮጵያ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በስተቀር፣ የመላው ዓለም የመገናኛ ብዙሃን የዕለት ተዕለት ብቻ ሳይሆን የየሰዓቱ ትኩስ ዜና የሆነውን የኬንያን የድህረ ምርጫ ሁከትና ውዝግብ የኛዎቹ ለምን በዝምታ ሴራ ዝም አሉት? ዘጉት? ጉዳዩን መታዘብ የማይሳናቸው፣ በጉዳዩ መገረም የማይበዛባቸው ኢትዮጵያውያን የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዚሁ ወዲውኑ ቀጥሎ ሊመጣ የሚገባው ሌላም ጥያቄ ነበር፡፡ የአለም የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃንን የዝምታ ሴራ እንደምን አድርገው ዘገቡት ወይም አዩት የሚል፡፡

የኋለኛው ጥያቄ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ የአገር ቤትም ሆነ የውጭ አገር ትንሹም ሆነ ትልቁ የህትመቱም ሆነ የኤሌክትሮኒክሱ ሚዲያ፣ (በመርህ ደረጃ) የሚዲያነቱን ህልውና፣ ሚዲያ መሆኑንን አሳልፎ ካልሰጠ በስተቀር የሚገዛበት ህግም ወግም አይደለም እንጂ “ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም” ወይም ከነጭራሹ አይሰማም የሚል አባባል አለ፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያን የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በኬንያ ጉዳይ ላይ የወሰዱትን “የዝምታ ሴራ” አቋም ሳይዘግቡት፣ ሳያነሱት፣ ከነጭራሹም ስለመኖሩም ሳያውቁት አለፍ ብለን ከመታዘባችን በፊት ራሳችንን እንደ ባለቤት ስለ”መጮሃችን”፣ ለመጮህ ስለመሞከራችን መጠየቅ፣ ተጠያቂም ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡

የመንግሥት ባልሆኑ፣ ከዚህም ጋር ድንገትም ይሁን በእቅድ ገጥሞ፣ ተገጣጥሞ የኤሌክትሮኒክስ ባልሆኑ የአገራችን የመገናኛ ብዙሃን (ጋዜጦች) አልፎ አልፎ የማነበው፣ ብዙዎቻችንም በግል የምንታዘበው፣ አንድ ጉዳይ በኬንያውና በኢትዮጵያው ድህረ ምርጫ ሂደት ውስጥ ያለውን የጎላ ልዩነት ነው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው ተቋም ነው፡፡ ሌላው የህዝቡ የራሱ የግንዛቤ፣ የባህል፣ በዚህም ላይ የተመሰረተው የተሳትፎና ዘብ የመቆም ወጉ ነው፡፡ ይህንን የመሰለው ከሌሎች መካከል ወሳኝ ጉዳይና ከቦታው ከስፍራው ተፈልጎ በቁርጥ ቀን ሲጠፋ ምን ያህል እንዳጎደለን ለማመሳከር ሌላ ክፉ ቀን መጠበቅና ማረጋገጥ የለብንም፡፡ እንደ ሕዝቡ ከዚያው አንድ ባህር የተቀዱት የመንግሥት እና ከመንግሥት ውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከየአቅጣጫው እያባባሱ ከድጡ ወደ ማጡ ያሸጋገሩትን ይህንን ጉዳይ ለማሳየት አንዲት ነገር ብቻ ባጭሩ ላንሳ፡፡

በዓለም ዙሪያ የሚደመጡትንና የሚታዩትን ታላላቅ የሚዲያ ኔትዎርኮች የኬንያን ምርጫ ዘገባ ይበልጥ “ካደመቁት” ጉዳዮች መካከል አንዱ የኬንያውያን የራሳቸው በሞባይል ስልኮቻቸው አንስተው የላኳቸው ምስሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሲ.ኤን.ኤን ዜናዎች ውስጥ ደግመን ደጋግመን ያየናቸው ግብዓቶች ከኬንያ የተላኩ የ”አይ ሪፖርት” ምስሎች ናቸው፡፡ በአገራችን ብዙዎች ሰዎች እጅ የምናያቸው የሞባይል (ቀፎ) ዓይነቶች አንድም ከተራ “ስልክ” በላይ እንዲያገለግሉ (በቴክኖሎጂው ሳይሆን) በባህሉ ስለተረገሙ ወይም ከተራና ከንቱ የማንነት መለኪያ በላይ እንዲፈይዱ ባለመሆናቸው አንድም የአገራችን ሰው ምርጫ 97ን ተከትሎ የተከሰቱትን የ”.እና”. ወሮች ሁከትና እልቂት በሞባይል ስልኩ ካሜራ አየሁ ብሎ “ሲያወራ” አላየንም፡፡

የኬንያ ጋዜጠኞችም ለወትሮው እጅግ በጣም ተፎካካሪ ሆነው በታወቁበት አገር የትግል አንድነታቸውን በመላው ዓለም ፊት አስመስክረዋል፤ አረጋግጠዋል፡፡ የዜና ግብዓት የሆነ ማቴሪያል ብቻ ሳይሆን መልዕክትና ርዕስ ተጋርተዋል፡፡ የጋራ የግንባር ገጽ፣ ርዕስ አንቀጽ አውጥተዋል፡፡ በአገራችን ግን ሁኔታው የተለየና ልዩ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ጦሱ አሁንም ድረስ እየቀጠለ ያለውን የቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኑኤ) እና የዶቼቬሌ (የአማርኛ ቋንቋ) ስርጭቶች መንግሥት ጥርስ ውስጥ የገቡበትን ጉዳይ በጥቂቱ አፍታቶ ማየት ይቻላል፡፡ ሁለቱም ለኢትዮጵያ አድማጮች የሚሰራጩት በተለይም የአማርኛ ስርጭቶች ምርጫውን ተከትሎ በመጣው ሁከትና ሞት ቀውጢ ወቅት አፍላ ጊዜ ውስጥ ያስተላለፉት በጥያቄና መልስ መልክ ይቀርብ የነበረ ዜና፣ ምናልባትም ብቸኛው የኢንፎርሜሽን ምንጫችን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የቮይስ ኦፍ አሜሪካ በተለይ ትኩስ ሀዘን ላይ ከተቀመጡ ልጇ ከተገደለባት እናት፣ ባለቤቷ/ባለቤቱን/ ቀብሮ ከተመለሰ/ባል/ሚስት፣ ከወላጆች መካከል አንዱ ተገድሎ ሌላው ከታሰረባት ልጇ ጋር ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ሲነጋገሩ እየሰማን በጉዳዩ ተደናግጠናል፡፡ ዜናው ከኢትዮጵያ የራዲዮ ጣቢያው ዘጋቢ በቀጥታ የማይዘገብበት ወይም የሰማነው አይነት ቃለምልልስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የሬዲዮ ጣቢያው ዘጋቢዎች/ወኪል ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ወይም በሌላው አማካኝነት የማይደረግበት ምክንያትም በጭራሽ አይጠፋንም፡፡ ምናልባትም ከዋሽንግተን ዲሲ አዲስ አበባ ወይም ሌላ ክልል/ ከተማ በስልክ ቃለምልልስ የሚደረግለትን ሰው የዜና ምንጭነትና ስልክ “ሹክ” ያለው አዲስ አበባ ከሚገኙ ጋዜጠኞች/ዘጋቢዎች መካከል አንዱ ወይም ሌላኛው ነው እንዳይባል፣ እውነትም አጉል እንዳይጠረጠር ሲሰጋ የዋሽንግተን ጋዜጠኞችም በዚህ ረገድ (ደግሞ ድንገት ልጆቹን ለአደጋ እንዳናጋልጣቸው ብለው) የተቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ከሩቅ መጠራጠራችን አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ መሰረት የሌለው ግምትና ጥርጣሬ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በኛ እና በኬንያ መካከል ያለውን ልዩነት አሳምሮ ያሳየናል፡፡

የኬንያን የፓርላማ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት፣ የምርጫውን ሂደት ተከትሎ የተከሰተውን ሁከትና እልቂት በተመለከተ የዝምታ ሴራ መትተው ፀጥ ረጭ ያሉት ያገራችን የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያው ምርጫ 97 አፍላና ከዚያ በኋላ በቀጠለው የተራዘመ ጊዜ ውስጥ “ተልዕኮ” አድርገው፣ በእቅድ ይዘው ይዘግቡባቸው ከነበሩት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሁለቱ ሬዲዮ ጣቢያዎች ነገር አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ እና የየክልሉ “ነዋሪዎች” የቪ ኦ ኤንና የዶቼቬሌን ኃላፊነትና ስነምግባር የጎደለው (ያሉትን) አሰራር ሲተቹ፣ ሲያወግዙ ተወያዮቹ በጉዳዩ ላይ ረዥምና ተከታታይ ውይይት ሲያደርጉ ሰምተናል፡፡ ከአገሪቱ በመላ የተሰባሰበ ነው የተባለ አቤቱታና ፊርማ ለተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጉዳዩ በሚመለከተው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀርቦ በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት አማካኝነት ለየአገሩ (የአሜሪካና የጀርመን) መንግሥታት እንዲተላለፍ ከአደራ ጋር ሲሰጥ አይተናል፤ ሰምተናል፡፡

በ131ዱ የቅንጅት አመራሮችና ጋዜጠኞች ላይ በተመሰረተው ከፍያለና ብርቱ ክስ ውስጥ ከአምስት የማያንሱ የቪ ኦ ኤ ጋዜጠኞች በተመሳሳይ ጉዳይ በሌሉበት መከሰሳቸውን ኋላም ላይ ክሱ ከተሰመረተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ከተጠቀሱት ጋዜጠኞች ላይ ማንሳቱን ሰምተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ተፋፍሞ እንደሚነገረው ደግሞ የዶቼቬሌ እና የቪ ኦ ኤ (የአማርኛና ኦሮምኛ) ስርጭቶች መሰማት የማይችሉ የሆኑበት ምክንያት መንግሥት የሚያፍን ሞገድ ስለሚለቅባቸው ነው የሚል ክስ እየቀረበ ነው፡፡ ይህንን ራሳቸው ሬዲዮ ጣቢያዎቹ በይፋ ገልፀውታል፡፡ አዲስ አበባ በምትገኘው ዘጋቢው አማካኝነትም ቢቢሲ (ፍሮም አወር ኦውን ኮረስፖንደንትስ በሚለው ፕሮግራሙ አማካኝነት) ተጨማሪ ምስክርነት ሰጥቶበታል፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎችም ተመሳሳይ ክስና ምስክርነት እየቀረበና እየተሰጠ ነው፡፡ በተለይም የቢቢሲዋ የኤሊዛቤት ብላንት (ከላይ የተጠቀሰው) ዘገባ ኢትዮጵያን ከሌሎች አፍሪካ አገሮች ልዩና አምሳያ የሌላት (ኤክሴፕሽን) አድርጎ ያቀረባት በዚህ ረገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት ቢቢሲ ይሁነኝ ተብሎ የሚደረግ ነው የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ግን የሚያስተባብለው “ጃሚንግ” ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች ቢቢሲን፣ ቮይስ ኦፍ አሜሪካን ወዘተ ወይም እነዚህን አገሮች ዒላማው አድርጎ የሚተላለፉትን የውጭ ሬዲዮ ፕሮግራሞች የሚያዳምጡት ከሾርት ዌብ ሬዲዮ ጋር ታግለው ጎርጉረው የድምፅ ጥራቱን መልዕክቱ መጣሁ ቀረሁ እያላቸው ሳይሆን በኤፍኤም ሬዲዮ ነው፡፡

እንደ “ጃሚንጉ” የኢትዮጵያ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን በኬንያ ምርጫ ላይ የወሰዱት የዝምታ ሴራ ወሬ ሊሆን ያልቻለበት ከነጭራሹም የማይታወቅ ቢሆን የማያስገርምበት ምክንያት በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለው “ልዩነታችን” ነው፡፡ የጉዳዩ ባለቤቶች መጮህ አለመቻል፣ ባለቤትነታችንን ራሱን መተዋችን ነው፡፡ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን የኛን የመገናኛ ብዙሃን የዝምታ ሴራ ለምን ሳይዘግቡት ቀሩ ብለን መጠየቅ የማንችልበት ስለዚህም ወደ መጀመሪያ የኛዎቹ ለምን የኬንያን የምርጫ ዜና ዘጉት ብለን መጀመሪያ እንጠይቅ ዘንድ የምንገደድበት ምክንያት ይኸው ጥፋትና ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን የሚባሉት ባጠቃላይ ሦስቱ በየራሳቸው የማቋቋሚያ አዋጅ ለየብቻ የተቋቋሙት 1) የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት 2) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና 3) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ናቸው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የተቋቋመበት ሕግ የመንግሥቱን ስራ ከሚያከናውኑት መስሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር በቅርቡ በተሻሻለበት አዋጅ በመሻሩ የዜና አገልግሎት ድርጅቱም እንደ (የመንግሥት) “ዋየር ሰርቪስ” እንኳን ፈርሷል፡፡ የሚኒስቴሩ መ/ቤት አንድ ሌላ መመሪያ (አካል) ሆኗል፡፡ እንደዛሬው ሳይሆን ኢ ዜ አም በሕግ ሳይፈርስ፣ የሌሎችም የ”ነጻ”ዎቹ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን የቦርድ አስተዳደር መልስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር መውደቁ ሳይቀር የሦስቱም እንደገና በ1987 ዓ.ም በአዲስ ሕግ የመቋቋም መነሻ ምክንያት “በመንግሥት ባለቤትነት ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በህብረተሰቡ መካከል ሀሳቦችና አመለካከቶች ሕገመንግሥቱ በደነገገው መሰረት በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ የተቋምና የአሰራር ነፃነት እንዲሁም የሕግ ጥበቃ እንዲኖረው ማድረግ ስለሚያስፈልግ” ነበር፡፡

የዚህ መሰረታዊ መነሻ ደግሞ በሕገመንግሥቱ “በመንግሥት ገንዘብ የመካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል” መባሉ ነው፡፡ ይህን የሚለው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29 ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንቀጽ 29 ማለት ደግሞ የዓለም አቀፋዊው የመብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ማለት ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ልዩነት አለ ቢባል አንቀጽ 29 የአንቀጽ 19 ትርጉም መሆኑ ነው፡፡ ትርጉሙ ውስጥ ሊታይ ከቻለው መጨመር መቀነስ በስተቀር ማለት ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ሕግ አካል በሆነው በአንቀጽ 19 እና በሕገመንግሥታዊው ድንጋጌ አንቀጽ 29 መካከል ያለው አንድ ግዙፍ ልዩነት የአንቀጽ 29 የአመለካከትና ሀሳቡን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት ድንጋጌ በንዑስ አንቀጽ (5) ያካተተው እንግዳና ባዶ ነገር ነው፡፡ በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ያደርጋል የሚለውን የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 29”5) ድንጋጌ ብዙዎች የዋሆች ያዩት በቀናነቱ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የመንግሥት ባለቤትነት በመገናኛ ብዙሃን የሚቀጥል መሆኑ በሕገመንግሥት ደረጃ የመቋቋምን አደገኛነት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድርጅት ሕገመንግሥቱ በደነገገው መሰረት የተቋምና የአሰራር ነፃነት እንዲሁም የሕግ ጥበቃ እንዲኖረው ለማድረግ እንደገና “በአዲስ መልክ” እንዲቋቋም በተደረገበት ሕግ የድርጅቱ ዓላማ ሆኖ በሕግ የተወሰነው ግልጽና እጅግ በጣም ግልጽ ነው፡፡ “የድርጅቱ ዓላማ በመገናኛ ብዙሃን በፕሬስና በሌሎች አግባብ ባላቸው ፖሊሲዎችና ሕጎች መሰረት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ስለሚፈጸሙ አበይትና ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም ትምህርታዊና አዝናኝ ዝግጅቶችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለሕዝብ ማቅረብ ይሆናል” ይላል፡፡ በመላው ዓለም ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣው፣ ሬዲዮው፣ ቴሌቪዥኑ የኬንያን ምርጫ ተከትሎ የተከሰተውን አለመረጋጋት ዋነኛና አውራ ዜናዎች አድርገውታል፡፡ የመላው አፍሪካም ትኩረት የኬንያ ዜና ነው፡፡ የጋናው ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነታቸው ቦታው ተገኝተው መላ አፈላልጋለሁ ብለው ሙከራ ያደረጉበት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ ኬንያን ብቻ ሳይሆን የበርካታ ጎረቤት አገሮችን ኢኮኖሚያዊ ደህንነት አናግቷል፡፡ ሌላው ቢቀር ““.በውጭ ሀገር በመፈፀም ላይ ያለ አበይትና ወቅታዊ” ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ዜናም ሆነ የዜና ትንታኔ ወይም ወቅታዊ ሪፖርት ይህን ጉዳይ የዜና ፋይዳ አልሰጠውም፡፡ ወቅታዊ ጉዳይ አላደረገውም፡፡

“የድርጅቱ ዓላማ በመገናኛ ብዙሃን በፕሬስና በሌሎች አግባብ ባላቸው ፖሊሲዎችና ሕጎች መሰረት”“. መሆኑን ከላይ ጠቅሻለሁ፡፡ የኬንያ ጉዳይ ድርጅቱ በሚያውቀው ከላይ በሚወርደው “ፖሊሲ” ውስጥ አይሸፈንም ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ማቅረብ የአገራችንን የመገናኛ ብዙሃን ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ “ዓላማ” ከዚህ ጋር አያይዞ መጠርጠርና መገመት የዋህነት በድንቁርና መወቀስን ሊያስከትል ይችል ይሆናል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየዓመቱ የሚቀርቡትን የነዚህን የመገናኛ ብዙሃን ሪፖርቶች ሪፖርቶችም ስለሚነገሩት የዜና እቅድ አቅጣጫ እንዲሁም የቁጥር “ኮታ” የማየት እድል ላጋጠመው ሰው ግን ከዚህም በላይ መጠርጠርና መገመት የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡

ይህን የመሰለ የተለየ ግምት ከመንገሱም የተነሳ የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ድንገትና “እግረ መንገዱን” ከሚሰማቸው ሌላ አማራጭ አጥቶ ከሚያዳምጣቸው በተጨማሪና በተለየ ሁኔታ ሌላና ይሁነኝ ብሎ የሚከታተላቸው የማይናቅ ቁጥር ያለው ተጨማሪ አድማጭ ያገኙ ይመስላል፡፡ የአድማጩን ቁጥር የጨመረው ደግሞ “እስቲ ሬዲዮ/ቴሌቪዥን ስለኬንያ ያወሩ ይሆን?”“ የሚለው “ጉጉት” ነው፡፡ ይህን ጉጉት ግን ቀደም ሲል የተገለጸውን “የራሳችን ችግር” ያልኩት፣ ድጋሚ ለማጠናከር ይሁነኝ የተባለ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የ”ሞኒታሪንግ” ባህልና ልምድ ሊከተለው ወይም ሊያግዘው ስለሚችሉ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የኬንያን ምርጫ ተከትሎ የተከሰተው ሁከት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዜና አለመሆኑን በብዙ ሰው ዘንድ ራሱን የቻለ “ዜና” መሆኑ ግን እውነት ነው፡፡

“የመገናኛ ብዙሃን ሕግ” የሚል አዲስ ስያሜ ተሰጥቶት ከ”መረጃ ነፃነት” ሕግ ጋር በአንድነት የቀረበው፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ አጀንዳ ሆኖ እስከ አሁን የቆየው የ1995 ዓመቱ ቅጅ አብዛኛው ዓይነተኛ ድንጋጌዎች ግን የተለያዩ ሕጎች አካል ሆነው የፀደቁት የኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግ ረቂቅ እንደገና በ2000 ዓ.ም ለ”ውይይት” ቀርቦ መነጋገሪያና አነጋጋሪ በሆነበት ወቅት፣ ራሳችን የ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ ከመጣው ጉዳትና ጠባሳ ገና ሳናገግም፣ ይልቁንም የቅንጅት አሁን ለደረሰበት ሁኔታ “መብቃቱ” ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ የቀሰቀሰው መሆኑ በሚታወቀበት ወቅት በዚህ ጽሁፍ ባነሳሁት ጉዳይ የተወሰደው የዝምታ ሴራ አቋም ቢያንስ ቢያንስ ለራሱ ለሚያውቅ ሰውም ሆነ አካል በብልጠትም ሆነ በጥበብ ላይ የተመሰረተ እርምጃ በጭራሽ አይደለም፡፡

 
< Prev   Next >