| ሥነ ጠቢቡ ሲገለጥ |
|
| Wednesday, 15 October 2008 | |
|
በሔኖክ ያሬድ
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ከ40 ዓመት በፊት "የጠፈር ባይተዋር" ብሎ ከገጠመው የተወሰደ አንድ አርኬ (አንጓ) ነው፡፡ በዘመናዊ የሥዕል ጥበባት ታሪክ ውስጥ ፊት በር ላይ የሚቀመጠው ሠዓሊ ወ ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ፋና ወጊ እንደሆነ ስምምነት አለ፡፡ ለዚህም ከሚጠቀሱት አንዱ እሸቱ ጥሩነህ "ገብረ ክርስቶስ ደስታ አጭር ትውስታና ጨረፍታዊ ዕይታ" በሚለው ሐተታ ጥበቡ እንደገለጸው፤ የዘመናዊ ሥዕል ጥበብ ጉዞ ከነበረበት ወይም ታጥሮና ተወስኖ፤ ፈዞና ደንዝዞ ከቆመበት መስቀልያ መንገድና ብዥታ መሃል አውጥቶ፣ ወደ ፈለገው አቅጣጫ እንዲጓዝ፣ የአራቱንም ማዕዘን መንገድ ቀድሞ የከፈተና ፈር ቀዶ ያመላከተ፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥዕልን ከነባሩ ትውፊታዊ ኪነ ንድፍና ኪነ ቅብ አሳሳልና አቀባብ ጋር እንዲመሳጠር የዓለም አቀፉ ጥበብ ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥዕል እንቅስቃሴ ጋር እንዲቀናጅና እንዲስተጋበር ማድረግ ያስቻለ ነው፡፡ በ1924 ዓ.ም ጥቅምት 15 ቀን የተወለደው ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ የጐልማሳነቱን ዕድሜ ሳያገባድድ፣ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም በአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ውስጥ በ49 ዓመቱ አጋማሽ ላይ ነበር ያረፈው፡፡ በሥዕል ዓለም ከ1953 እስከ 1973 ዓ.ም አሳልፏል፡፡ ስለ ሥዕላዊ ቋንቋው ሠዓሊ እሸቱ ሲገልጽ፣ የማንኛውም ሠዓሊ ሥዕላዊ ቋንቋ ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ያለው በሠዓልያኑ የአሣሣል ዘይቤ፣ የጥበብ ፍልስፍና እና በሚከሰቱት ጥበባዊ ምስሎች ላይ ነው፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ መስመራዊ ኪነ ንድፎችን መሣል ይወዳል፡፡ ፈጣን፣ ግልጽ፣ ጠንካራና ያልተንዛዙ ቁጥብ መስመሮችን ይጠቀማል፤ በብዕርና በብዕር ጥቁር ቀለም የሣለው የታዋቂው ደራሲና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ምስል ለዚህ ምስክር ነው ብሏል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ዘርፈ ብዙ ሠዓሊ ነበር፡፡ ይህ የሥዕላዊ ቋንቋውንና የቁስ ጥበባት (Art media) አጠቃቀሙን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ በኪነ ቅቦቹ የሚዳስሳቸው ርእሰ ጉዳዮችና ሐሳቦች የሚያስቀራቸው ወይም የሚዳስሳቸው ምስሎች እጅግ የበዙ ናቸው፡፡ የሀገራዊው የጥበብ ግንዛቤ አናሳ መሆን ያስቸገረውን ያህል በሌላ በኩል አንዳንድ የአውሮፓ ምሁራን ኢትዮጵያዊነቱንና አፍሪካዊነቱን በመጥቀስ፣ ለምን እንደ ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ የጥበብ አሣሣል አትሥልም? ለምንስ አውሮፓዊ አቀራረብ ይኖርሃል? በማለት፤ ልክ አቻምየለህ ደበላ እንዳስቀመጠው ዘመናዊው የአውሮፓ ጥበብ ከሩቅ ምሥራቅ እና ከአፍሪካ ያልወሰደውን ያህል፣ ኢትዮጵያውያን ወይም አፍሪካውያን፣ ከአውሮፓ መውሰዳችሁ ምንድነው ችግሩ? እንዳለው፤ ቀደም ሲል ገብረ ክርስቶስ ደስታም እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ "ለውጠኸዋል በመባል አልፎ አልፎ እወቀስበታለሁ". ያለንን ባህላዊ ኪነ ጥበብ መጠበቅና ማቆየት ማስፈለጉን አልክድም፤ ነገር ግን ሁሉም የነበረውን፣ ያለውን ጠብቆ ለማቆየት ብቻ መሰለፍ የለበትም፤ እንደሌላው የሙያ ዘርፍ ሁሉ ለኪነ ጥበብም መሥራትና አስተዋዋቂ ያስፈልጋል፡፡ እኔም አንድ ኢትዮጵያዊ በዘመናዊ መንገድ በሥነ ጥበብ ምን ያህል ለመራመድ እንደምንችል ለማሳወቅ በመሥራት ላይ እገኛለሁ" ሥነ ጠቢቡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በትምህርት ዓለም እያለ በመጀመሪያዎቹ የፈጠራና የፍለጋ ጊዜው በ1963 (1955/56 ዓ.ም) ከሠራቸው ሥዕላት ውስጥ መጠቀስ የሚገባው ሥራ ቢኖር፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ነው፡፡ "ኤሎሄ" ወይም "ጎልጎታ" ተብሎም ይታወቃል፡፡ ይህንን ሥዕል ለምን እንደሠራው አንዳንድ መሠረታዊ ግምቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሐታቲው እሸቱ ይገልጻል፡፡ ገብረ ክርስቶስ የአለቃ ደስታ ነገዎ፤ ያውም በጣም የሚወዱትና የሚሳሱለት ልጃቸው ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እምነት ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ጋር በወጉ እንዲያውቅ አስተምረው አሳድገውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ብለውም ስም ሲያወጡለት ምክንያት ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ሥዕል ሲሥል፤ እንደማንኛውም አማኝ ክርስቲያን ብቻ አይደለም ብለን መከራከር እንችላለን፡፡ ወደ ኋላ በወጣትነት እድሜው ከደረሰበት አካላዊ ሕመም አኳያ፣ አንድም ለእምነትና ለፈውስ፤ አንድም ለጥበብና ለፈጠራ ኃይል መነሻ እንዲሆነው፤ ምክንያት አግኝቶ ሥሎታል የሚል አጠቃላይ ግምት በደምሳሳው ይኖረናል፡፡ በሠዓሊ እሸቱ አገላለጽ ይህ የገብረ ክርስቶስ ደስታ የሥነ ሥቅለት ሥዕላዊ ድርሰት፤ ቅርፅና ይዘት በሁለት አንጻራዊ ሁኔታ ላይ የተቃኘ ነው፡፡ በቅርጹ ዘመናዊ አቀራረብ ሊኖረው፤ በይዘቱ ከሞላ ጐደል በመጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ፤ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ርእስ ነው፡፡ በቅርጻዊ አቀራረቡ ሲታይ በወርቃማና ብርማ የብርሃን ድባብ ውስጥ፤ በጥቁር ቀለማት፤ ዓምዳዊና አግድማዊ ወይም መስቀልያ በተሰመሩ ወፍራምና ቀጭን መስመሮች የተሞላ ነው፡፡ በመሆኑም የተመልካችን ዓይን በሰሌዳው ሙሉ ያለረፍት እንዲሮጥ ያደርጉታል፡፡ መስመሮቹ በደጀንነት ተደጋግመው በመኖራቸውም ጥልቀትን በሰሌዳው ላይ ከመፍጠራቸውም በላይ፤ መስኮታዊ ትዕይንት አላቸው፡፡ ተመልካች እረፍት የሚያገኘው አብዛኛውን የሰሌዳ ክፍል በተቆጣጠረው፤ ግን ትንሽ ቀይ ሕብረ ቀለም ነው፡፡ ይህ ብቸኛ፤ የቀይ ሕብረ ቀለም መስቀልያ አቀባብና አቀማመጥ፤ ሥዕላዊ ድርሰቱን አትኩረን እንድናይ ይጋብዘናል፡፡ በይዘታዊ አቀራረቡ ፍጹም ንዑዳዊ እውነታዎችንና ተምሳሌትነትን፤ በክርስቶስ የሥነ ሥቅለት ሥዕል፤ ገብረ ክርስቶስ ሲሥል የመስዋዕትነትን፣ የቤዛነትን፣ የሕያውነትንና የዘላለማዊነትን፤ እንዲሁም የነጻነትንና የሰላምን ምንነት ባጭሩ በሕብረ ቀለማት የቃኘበትና የተቀኘበት ነው፡፡ መስቀሉ እውነታዊ ነው፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ ግን ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ሥዕሉ እስከተሠራበት እስከዚያን ጊዜ ድረስ ብዙ ሠዓሊዎች አካሉን ወይም ስጋውን አልፎም እውነታዊ ምስሉን ከነስቃዩ ይሥላሉ እንጂ፤ እንደ ገብረ ክርስቶስ ክቡር ደሙን በቀይ ሕብረ ቀለም ብቻ ተምሳሌት አድርገው እና ወስነው የሠሩ የሉም፡፡ ይህን በሚመለከት የጀርመን አገር ጓደኛው ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡፡ "ሠዓሊ ተብሎ የጎልጎታን ተራራ ያልወጣ ትልቁን ትራጀዲ ያላየ የለም፤ ግን የገብረ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ለብቻው ነው፤ ቀለም ተናጋሪ ነው፤ የሚታየው ንጹሑ ብቻ ነው፤ ግራና ቀኝ የነበሩት ፈያት ቦታ የላቸውም ተዘንግተዋል፡፡ ወይም ሠዓሊው ሊያያቸው አልፈለገም፤ ይገርማል፤ ጥበብ ከንጹሕነት ከጽርየት ከርቀት ብቻ እንጂ ከሌላ ጋር ግንኙነት የሌላት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡" ይህ በጋራ የምካፈለው ሐሳብ ነው፡፡ በሰፊው ፍኖተ ኢትዮጵያ (የኢትዮጵያ መንገድ) ላይ በጥበብ ዐውድ ፀሐይ ሆኖ የፀኸየው ገብረ ክርስቶስ ጥበበ አብስትራክትን (ረቂቅ ሥዕልን) በመግለጥ ረገድ ተጠቃሽም፣ ታዋቂም (እሙር) ነው፡፡ እርሱ እንዳለውም "ሥዕል የዓይን ሙዚቃ ነው፤ ይኸውም የቀለሞች ኅብረትና ዝምድና አካሄድንና አመራር ማሳየቱን ለመግለጽ ነው፡፡" ገብረ ክርስቶስ ደስታ የ"ክራር ተጫዋቿ" በሚለው ምስሉ ሥዕላዊ ሙዚቃ ከሀገራዊ ርእሰ ጉዳይ ጋር አያይዞ በጥበባዊ ክህሎቱ ገልጦታል፡፡ በሠዓሊ እሸቱ አደማደምም በእርግጥም ገብረ ክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ጥበብ ታሪክ ውስጥ የጥበበ አብስትራክት (abstract art) ግንባር ቀደምና ፋና ወጊ ሠዓሊ ነበር፤ አሁንም ድረስ ነው፡፡ አሁን በጠቢቡ ስም የቆመው ተክለ መዘክር ገብረ ክርስቶስ ያረፈበትን 28ኛ ዓመት ዘንድሮ በመጋቢት ያስበው ይሆን? 28 ዓመት በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ (የዘመን ቀመር) የዐውደ ፀሐይ (Solar cycle) ልኬት ነው፡፡ በ28ኛው ዓመቱም የቤተ መዘክር ጎጆ ተቀልሶለታል፡፡ "የጠፈር ላይ ባይተዋር" ብሎ በገጠመው ግጥሙ አንድ ጥግ "በፀሐይ ላይ ቤቴን ጐጆ እቀልሳለሁ" ያለው ሳይሰምር አልቀረም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |