Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "በአሁኑ ወቅት ቀጣሪዎች ልምድና...
"በአሁኑ ወቅት ቀጣሪዎች ልምድና... E-mail
Wednesday, 15 October 2008

Image"በአሁኑ ወቅት ቀጣሪዎች ልምድና ችሎታ ያላቸውን ሠራተኞች ይፈልጋሉ"

አቶ መሳይ ክፍሌ የኢንፎማይንድ ሶሉዩሽንስ ምልመላ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽንስ በስሩ በያዛቸው ታለንት ሰርች፣ ኢትዮ ጆብስ ድረ ገጽ እና ሂዩማን ሪሶርስ ትሬኒንግ ኤንድ ኮንስልታንሲ ድርጅቶች ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪዎችን ያገናኛል፤ ሠራተኞችን መልምሎ ለቀጣሪዎች ያቀርባል፣ የሰው ሀይል ስልጠናና የማማከር አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ኃይሌ ሙሉ ዳይሬክተሩን አነጋግሯቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ጆብስ እንዴት ተመሰረተ? ዓላማውስ ምንድነው?

አቶ መሳይ፡
- መጀመሪያ ላይ የተመሠረተው ታለንት ሰርች የተሰኘው የሠራተኞች ምልመላ ድርጅት ነው፡፡ ዓላማውም ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪዎችን ማገናኘት ነው፡፡ ታለንት ሰርች የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1998 ሲሆን የሥራ ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አሰራሩን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሲስተም ለመቀየር ኢትዮ ጆብስን አቋቋምን፡፡ በሀርድ ኮፒ ይመጡልን የነበሩትን ሲቪዎች ወደ ኢንተርኔት እንዲገቡ የተደረጉት ኢትዮ ጆብስ እ.ኤ.አ በ2004 ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ ኢትዮ ጆብስ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት የመጀመሪያው የሥራ ፈላጊዎች ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሥራ ፈላጊዎች በድረ ገጹ ተመዝግበው የራሳቸው ሆሞ ፔጅ ኖሯቸው ሲቪያቸውን የሚያስቀምጡበት ነው፡፡ በድረ ገጹ ያሰፈሩትን ሲቪም በፈለጉበት ሰዓት ማሻሻል ይችላሉ፡፡ ሁለተኛው ክፍል የኢትዮ ጆብስ ቀጣሪዎች ድረ ገጽ ነው፡፡ ሶስት ዓይነት የቀጣሪዎች አመዘጋገብ አለ፡፡ ዓመታዊ ምዝገባ የሚያደርጉ፣ በየስድስት ወር የሚመዘገቡና ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚመዘገቡ ቀጣሪዎች አሉን፡፡ እነዚህ ቀጣሪዎች የእኛን ድረ ገጽ ተጠቅመው የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጡ ሥራ ፈላጊዎች በእኛ ድረ ገጽ አማካይነት ማመልከቻቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ኢትዮ ጆብስ በቀጣሪዎቹና በተቀጣሪዎቹ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው፡፡

በኢትዮ ጆብስ ላይ ሲቪውን ያስቀመጠ ማንኛውም ሰው ቀጣሪዎቹ ላወጡት ክፍት የሥራ ቦታ ማመልከት ይችላል፡፡ ቀጣሪዎቹ ደግሞ የቀረበላቸውን ሲቪ መርጠው የፈለጉትን ሰው ይመለምላሉ፡፡ እኛ ብዙውን ጊዜ የምንሰጠው የቴክኒክ ድጋፍ ነው፡፡ አመልካቾቹን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው፣ ሲቪዎችን እንዴት መከፋፈል እንዳለባቸውና የመሳሰሉትን የቴክኒክ ድጋፎች ለቀጣሪዎች በመስጠት የምልመላ ሥራውን እናቀልላቸዋለን፡፡ ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ካምፓኒ ለመቀጠር ያመለከተ አንድ ሰው ቢኖር እና ከሁለት ዓመት በኋላ ቀጣሪዎቹ የአመልካቹን ሲቪ ቢፈልጉ የተሻሻለውን ማግኘት ይችላሉ፡፡

በኢትዮ ጆብስ ላይ የሚጠቀሙ ከመቶ በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው የግል ካምፓኒዎቹም በአሁኑ ጊዜ ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በታለንት ሰርች የምታከናውኑት ሥራ ምንድነው?

አቶ መሳይ፡-
ቀጣሪዎች ከተቀጣሪዎች የሚፈልጉትን መስፈርት ለእኛ ይሰጡናል፡፡ ይህን ይህን እንፈልጋለን ብለው ዝቅተኛ መስፈርቱን ይሰጡናል፡፡ እኛም ኢትዮ ጆብስን ተጠቅመን ክፍት የሥራ ቦታውን ለሥራ ፈላጊዎች እናሳውቃለን፡፡ ቀጣሪውን ድርጅት ወክሎም ታለንት ሰርች ምልመላውን ይሰራል፡፡ ዝቅተኛ መስፈርቱን ሊያሟሉ የሚችሉትን አመልካቾች ታለንት ሰርች ወስዶ ለቀጣሪው ድርጅት ይልካል፡፡ ይህንን ስናደርግ ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟሉትን ሰዎች ጠርተን የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ እናካሂዳለን፡፡

ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ የአመልካቾችን ብቃት ለማወቅ ይረዳናል፡፡ ከመስፈርቱ ጋር ይሄዳሉ? አቅማቸው ከገፉት ሲቪ ጋር ይመሳሰላል? የሚለውን እንድንገመግም ያግዘናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲቪው ላይ ጥሩ የፃፈ ሰው እንደፃፈው ላይገኝ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ሲቪው ብዙ ባይናገርም በቃለ ምልልሱ ሊያስደምምህ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ የምታካሂዱት የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ ለሥራ ፈላጊዎቹ ይጠቅማቸዋል?

አቶ መሳይ፡
- የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ ዋና ዓላማው ቀጣሪዎች የሚፈልጓቸውን ተፎካካሪ አመልካቾች መለየት ነው፡፡ ዝቅተኛ መስፈርቱን አሟልተው ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውን አመልካቾች በሙሉ ወደ ቀጣሪዎቹ እንልካቸዋለን፡፡ ከአመልካቾቹ ሲቪ በተጨማሪ በቃለ መጠይቅ የተመለከትነውን ጠንካራና ደካማ ጐን ገልጸን አስተያየታችንን እናስቀምጣለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሥራ ፈላጊዎቹ ለቃለ መጠይቅ ሲሄዱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ይሰጣቸዋል፡፡ ብዙ የሥራ ልምድ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ለቃለ መጠይቅ ሲጠሩ እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከአለባበስ ጀምሮ ራሳቸውን እንዴት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ትምህርታዊ ምክር እንሰጣቸዋለን፡፡ የአመልካቾቹን ደካማና ጠንካራ ጐን በመግለጽ ለዋናው ቃለ መጠይቅ ሲጠሩ በምን መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ምክር እንለግሳቸዋለን፡፡ አመልካቾች ያልሰሩትን ሳይሆን የሰሩትን ነገር እንዴት መግለጽ እንዳለባቸው እንነግራቸዋለን፡፡ ይህም አመልከቾች ስህተታቸውን አርመውና ጠንካራ ጐናቸውን ይዘው ለዋናው ቃለ መጠይቅ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል፡፡ በራስ መተማመናቸውንም ይጨምርላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ታለንት ሰርች መጀመሪያ ላይ ሥራውን ሲጀምር የገጠሙት ችግሮች ነበሩ? ችግሮቹ አሁንም አሉ?

አቶ መሳይ፡-
መጀመሪያ ላይ ሲታይ የነበረው ችግር አሁንም ድረስ በተወሰነ ደረጃ ይታያል፡፡ አመልካቾች በሲቪ አፃፃፍ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ አመልካቾች የሥራ ልምዱ ቢኖራቸውም ራሳቸውን እንዴት መግለጽ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ኮሙዩኒኬሽን ላይ ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን ለውጦች ይታያሉ፡፡ ቢዝነሱ እየተለመደ እና እያደገ መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል የኢንፎማይንድ ሶሊዩሽንስ ደንበኞች በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከትላልቅ መንግሥታዊ ያልሆኑ ደንበኞች ጀምሮ እስከ ትንንሽ ፒ.ኤል.ሲዎች ድረስ ከእኛ ጋር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የቢዝነስ አካሄድ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ በዘመድ እና በትውውቅ የምትሰራበት አይደለም፡፡ ቀጣሪዎች ብቃትና ችሎታ ያለው ተቀጣሪ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነሱ የሚፈልጉትን እያቀረብን እንገኛለን፡፡ በዚህም ምክንያት ቀጣሪዎቹ እና ሥራ ፈላጊዎቹ በድርጅታችን ያላቸው እምነት ጨምሯል፡፡ ቀጣሪዎቹ በበኩላቸው ከእኛ የሚገኘውን ሪሶርስ በአግባቡ አይጠቀሙም ነበር፡፡ ድርጅቱ አዲስ እንደመሆኑም መጠን ሰው የተሳሳተ ግምት ነበረው፡፡ ቀደም ሲል ታለንት ሰርች የሚፈልገውን ሰው ነው ለቀጣሪዎች የሚልከው የሚል አመለካከት ነበር፡፡ እኛ ግን ቀድሞም ሆነ አሁን ለቀጣሪው ድርጅት በአግባቡ ሊሰራ የሚችልና ጠቃሚ የሆነን ሥራ ፈላጊ ነው የምንመለምለው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተዓማኒነትን መገንባት ለቀጣሪው ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጠቃሚ መሆኑን እናምንበታለን፡፡
 
ሪፖርተር፡- ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽንስ ቀጣሪና ተቀጣሪዎቹን በማገናኘቱ የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው?

አቶ መሳይ፡-
ታለንት ሰርች መልምሎ ለቀጣሪዎች የላካቸው ሰዎች ከተቀጠሩ ቀጣሪዎቹ ሰርቪስ ቻርጅ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ከተቀጣሪዎቹ ግን ምንም ዓይነት ክፍያ አንጠይቅም፡፡ ኢትዮ ጆብስን ስንመለከት ደግሞ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በየዓመቱ፣ በየስድስት ወሩ እና ለአንድ ጊዜ ተመዝግበው ተመዝገባው በድረ ገጹ የሥራ ማስታወቂያ የሚያወጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶችም በድረ ገጹ ለሚያገኙት አገልግሎት ክፍያ ያከናውናሉ፡፡ በውጭው ዓለም ቀጣሪዎችም ተቀጣሪዎችም የሚከፍሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ወስጥ ግን የአገሪቱ ህግ የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ ህጉ ቢፈቅድ እንኳን አሰራሩን ሊያበላሸው ስለሚችል ከተቀጣሪዎች ገንዘብ መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ተቀጣሪው ገንዘብ ሲከፍል አድሎ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አሁን ባለው አሰራር ገንዘብ መክፈል የሚችል ሳይሆን ብቃትና ልምድ ያለው ተቀጣሪ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- ታለንት ሰርች ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎችን አስቀጥሯል?

አቶ መሳይ፡-
ትክክለኛ ቁጥሩን ለማወቅ ድርጅቱ ከተቋቋመ ጀምሮ የተመዘገቡ ዳታዎችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊዎችን ሥራ አስይዟል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያለውን አሰራር ብንመለከት እንኳን ድርጅታችን ቀጣሪዎች ለሚፈልጓቸው ሥራ ፈላጊዎች በየቀኑ ቃለ መጠይቅ ያካሂዳል፡፡

በየቀኑ ቃለ መጠይቅ አጠናቅረን ሪፖርት እንጽፍና ለጠየቁን ድርጅቶች እንልካለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካሪየር ኤክስፖ አዘጋጅተን ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪዎችን እናገናኛለን፡፡ በዚህ ሂደትም በጣም ብዙ ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ያገኛሉ፡፡ ካሪየር ኤክስፖ የተጀመረው እ"ኤ አ በ2002 ሲሆን ዝግጅቱ የሚካሄደውም በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በካሪየር ኤክስፖው ሥራ ፈላጊዎቹንና ቀጣሪዎቹን እንዴት ነው የምታገና"ቸው?

አቶ መሳይ፡
- የኤክስፖው ዓላማ ካምፓኒዎች ለወደፊቱ ባለሙያ እንቀጥርበታለን ብለው በያዙት ክፍት ቦታ ላይ ሥራ ፈላጊዎችን በማምጣት እንዲቀጠሩ ማድረግ ነው፡፡ ቀጣሪዎቹ የሚፈልጓቸውን ተቀጣሪዎች ዝርዝር በካታሎግ አዘጋጅተው ለሕዝቡ ይሰራጫሉ፡፡ ሥራ ፈላጊው ደግሞ በካታሎግ የሰፈረውን ዝርዝር ተመልክቶ ቀጣሪው ድርጅት የሚጠይቀውን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ከሆነ የትምህርትና የሥራ ማስረጃውን ይዞ ወደ ካምፓኒው በመሄድ ማመልከት የሚችልበት እድል ይፈጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛዎቹ የእናንተ ደንበኞች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፤

አቶ መሳይ፡-
ከመንግሥታዊ ድርጅቶችም ጋር አልፎ አልፎ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ግን ከመንግሥት ድርጅቶች የሚመጣው ጥያቄ እንደ ኤን.ጂ.ኦዎች ብዙ አይደለም፡፡ አንደኛ የመንግሥት ድርጅቶች የቅጥር አካሄድ በራሱ የሚገድበው ነገር አለ፡፡  የደመወዝ ስኬልን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ የቅጥር ሂደቱን በጥንቃቄ መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር አብረን እየሰራን ነው፡፡ ውይይቶች አካሂደናል፡፡ የእኛን ድርጅት እንደአማራጭ የቅጥር መመልመያ እንዲጠቀሙበት ተነጋግረናል፡፡ የእኛ ድርጅት ብቸኛው የሥራ ፈላጊዎች መመልመያ ነው እያልን አይደለም፡፡ እንደ አማራጭ እንዲያዩት ነው የምንፈልገው፡፡ ይህን መሰል ውይይት ካደረግን በኋላ የተወሰኑ መንግሥታዊ ድርጅቶች የእኛ ደንበኞች ሆነዋል፡፡ በተለይ በካሪየር ኤክስፖ ላይ የመንግሥታዊ ድርጅቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣሪ ድርጅቶችን ወክላችሁ ለሥራ ፈላጊዎች የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ ስታደርጉ ትኩረት ሰጥታችሁ የምታዩት መስፈርት ምንድነው?

አቶ መሳይ፡-
ጥሩ መሆን ያለበት የመጀመሪያው ነገር ሲቪ ነው፡፡ ሌሎቹ ሁሉ ተከታይ ናቸው፡፡ ሲቪህ አንተን የሚወክል ትልቅ ነገር ነው የሲቪ አፃፃፍህ ጥሩ ከሆነ በቀላሉ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ትሄዳለህ፡፡ ሲቪህን በደንብ ከፃፍክ ቀጣዩ ሥራ ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡ ራስህን መግለጽ ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ሲቪ የፃፉ ሰዎች እንደሲቪያቸው አይሆንም፡፡ ሥራ ፈላጊዎች የሌላቸውን ነገር ይጽፋሉ ማለት ሳይሆን ፊት ለፊት ቀርበው ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ መረበሽና መደናገጥ ይታይባቸዋል፡፡ እንደ ሲቪው ራሳቸውን መግለጽ አይችሉም፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ቃለ መጠይቅ መኖሩ ሥራ ፈላጊዎች እንደዚህ ዓይነት ችግራቸውን እንዲቀርፉ ይረዳቸዋል፡፡ በቃለ መጠይቁ ላይ የተመለከትነውን ደካማ ጐን እንዲያሻሽሉና ጠንካራ ጐናቸውን ደግሞ ይዘው እንዲቀጥሉ እንመክራቸዋለን፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ዳታ ቤዝ ውስጥ የነበሩት ሲቪዎች 30 ሺ ገደማ ብቻ ነበሩ አሁን ግን ከ70 ሺ በላይ ሲቪ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ድረ ገጹ እየታወቀና እየተለመደ መምጣቱን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዜብራ ጆብስ ዶት ኮም ፕሮግራማችሁ ምንድነው ለመሥራት ያቀዳችሁት?

አቶ መሳይ፡-
ዜብራ ጆብስ ዶት ኮም መቀመጫው ዩናይትድስቴትስ ከሆነ ዳንያ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር የተመሰረተ ፕሮግራም ነው፡፡ በዜብራ ጆብስ ዶት ኮም እና በዳንያ መካከል ስምምነቱ የተፈረመው ባለፈው ዓመት ሲሆን ሥራውን በቅርቡ ይጀምራል፡፡

ዜብራ ጆብስ ዶት ኮም አፍሪካውያን ሥራ ፈላጊዎችን እና ቀጣሪዎችን የሚያገናኝ ነው፡፡ አፍሪካውያን ዲያስፖራዎች በተለይ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ የሚል እምነት አለን፡፡ ዳንያ ኢንተርናሽናል ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሥራ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ በቴክኖሎጂም ድጋፍ ያደርግልናል፡፡ የዜብራ ጆብስ ዶት ኮም ዋና ቢሮ የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥም ሌላ ቢሮ ለማቋቋም አስበናል፡፡ አውሮፓ ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ ዲያስፖራ ወደ አፍሪካ መጥቶ የሚሰራበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽንስ ስንት ቋሚ ሠራተኞች አሉት? የሠራተኞቹ የሥራ ግንኙነትስ ምን ይመስላል?

አቶ መሳይ፡-
በአሁኑ ሰዓት 23 ቋሚ ሠራተኞች አሉ፡፡ ሁሉም የኢንፎማይንድ ሶሊዩሽንስ ሠራተኞች የቡድን ሥራቸውና የሥራ ግንኙነታችን ጥሩ ነው፡፡ በየቀኑ ከተለያዩ ሰዎች ጋር እንገናኛለን፡፡ ተናደው የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ተደስተው የሚመጡ አሉ፡፡ ሁሉንም ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀብለን አነጋግረንና፡፡ ከደንበኞች ጋር ተግባብተን ነው የምንለያየው፡፡

ሪፖርተር፡- በሂዩማን ሪሶርስ ዲፓርትመንት የምትሰሩትስ ሥራ ምንድነው?

አቶ መሳይ፡-
የሂዩማን ሪሶርሱ ዲፓርትመንት የሰው ሀይል ስልጠናና የማማከር ሥራ ነው የሚሰራው፡፡ ካምፓኒዎች ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን ሠራተኞቻቸውን መርጠው ለእኛ ይልኩልናል እኛም ሰልጣኞች ሊያውቁ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንሰጣለን፡፡ ካምፓኒዎቹ በሠራተኞቻቸው ላይ ያለውን ክፍተት ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ የሠራተኞቹ ችግር የፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ክህሎት ወይም የኮሚዩኒኬሽን ክህሎታቸው ከሆነ በእነዚህ ክህሎት ላይ ስልጠና እንድንሰጥላቸው ይጠይቁናል፡፡ የምንሰጠው ስልጠና እንደየካምፓኒው ፍላጐት ይለያያል፡፡ በየካምፓኒዎቹ የሚፈለገውን ስልጠናና የምክር አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሥራውን በቢሮው ባሉ ሰዎች መሸፈን የማይቻል ከሆነ ደግሞ ዝርዝራቸው አስቀድሞ የተያዙ ባለሙያዎች አሉን ከእነሱ ጋር በመሆን አገልግሎቱን እንሰጣለን፡፡

በማማከር ሥራውም ካምፓኒዎች ጨረታ በሚያወጡበት ጊዜ ተወዳድረን በደመወዝ ጥናት በሠራተኞች ተነሳሽነት እና ካምፓኒዎች በሚፈልጓቸው የተለያዩ ፓኬጆች ላይ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
Last Updated ( Wednesday, 15 October 2008 )
 
< Prev   Next >