| አሁንም ተጨማሪ እርምጃ |
|
| Sunday, 19 October 2008 | |
|
በናታን ዳዊት
በአገሪቱ በተከሰተው የዋጋ ንረት 57 በመቶ የሚሆነው እድገት የሚታየው ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ወይም አቅርቦት ላይ በመሆኑ ከነዳጅ ይልቅ ስንዴን መደጎሙ ወቅታዊና አንገብጋቢ ስለመሆኑም አፍታተው ተናግረዋል፡፡ በእርግጥ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገርና የምግብ እህልን ወይም ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ገበያ ለማረጋጋት ሲባል መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ወይም እየወስደ ያለው እርምጃ ለውጥ ስለማምጣቱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የምንችልበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ የነዳጅ ድጎማ ስለተነሳና ለነዳጅ ይደረግ የነበረው ድጎማ ስንዴን ለመደጎም መዋሉ አሁን እየታየና እያደገ የመጣውን የዋጋ ንረትና የሸማቾችን አቅም እየተፈታተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ያረጋጋዋል ብሎ አፍን ሞልቶ ለመነጋገር ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ የተወሰዱ እርምጃዎች ያመጡት ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል የማይችለውም ለውጥ ባለመምጣታቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንድንገባ ስለሚያደርገን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የዋጋ ንረቱ ያለመቋረጥ ሲጓዝ በየዕለቱ ከሸማቹ አቅም በላይ የሆኑ ዋጋዎች ሲወጡ መንግሥት ብዙ እርምጃዎች ወስጃለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ለምሳሌ አያንዳንዱ ነጋዴ የሚሸጠውን ምርት ዋጋ እንዲለጥፍ ማስገደድ፣ የባንክ የወለድ መጠንን መገደብ በጅንአድ በኩል ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ ማከፋፈል የሸማቾች ማህበር በየቀየው ማቋቋም ወዘተ. የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ስንዴ በርካሽ አስገብቶ ገበያ ውስጥ ማስገባትም እንዲሁ መንግሥት እየወሰደ ካለው እርምጃ ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ ነገር ግን ገበያውን ስንመለከት ከአንድ ስንዴ በስተቀር (እሱም አንፃራዊ ነው) ቀነሰ የሚባል ነገር የለም፡፡ ባይሆን ሸማቹ ሳይማረር እየገዛ ያለው ምርት ቢኖር ወይም ብዙም ጭማሪ ሳያሳይ ረዥም ጊዜ የቆየው ዘይት ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ተመክሮ የነዳጅ ድጎማውን አንስቶ ስንዴን መደጎም እየባሰበት የመጣውን የዋጋ ንረት ያቀዘቅዘዋል ወይም ሸማቹ እፎይ ብሎ ይኖራል ለማለት የሚያስችለው አልሆነም፡፡ እዚህ ላይ ግን በድጎማ ገባ የተባለው ስንዴ ለውጥ አላመጣም ማለት አይችልም፡፡ በዚህ ተግባሩ መንግሥት ምስጋና ማጣት የለበትም የሚል እምነት ሊኖር ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጭራሽ የነዳጅ ድጎማው መነሳትና አዲሱ የነዳጅ ዋጋ ተግባራዊ ሲሆን ወትሮም ዋጋቸው አልቀመስ ያሉ ምርቶች የነዳጅ ጭማሪውን ሰበብ አድርገው ተጨማሪ የዋጋ እድገት እያሳዩ ነው፡፡ የትራንስፖርት ዋጋም በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአብዛኛው የከታማ ነዋሪ ለማብሰያ የሚጠቀምበት ላምባ ታይቶ በማይታወቅ የጭማሪ መጠን መሰቀሉም ያላቸውን አብቃቅቶ ይጠቀም የነበረውን ሸማች ኪስ የባሰ እያሳሳና የኑሮ ውድነቱ የበለጠ እንዲሰማው እያደረገው ስለመገኘቱ የችግሩ ሰለባ የሆነ ሁሉ ራሱን በምሳሌነት እንዲያቀርብ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በቢሊዮን ብሮች ይደጎም የነበረው ነዳጅ ትቶ በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠርን ድጎማን የሚጠይቀውን ስንዴ በመደጎም ብቻ አሁን ያለውን ስር እየሰደደ ያለ የኑሮ ውድነት እና ዘወትር ሸማች የሆነውን ኅብረተሰብ ቀዳዳ ወይም ክፍተት ይሸፍናል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ይህንን ስጋትና ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አሁንም ተጨማሪ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህም የሚታየው እስከዛሬ የታዩት የዋጋ ንረቶች ሲረጋጉ ሸማቾችም ይህ ነገር ቀነሰልን ብለው ሲያምኑ ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |