Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Jan 08th
Home arrow Sections arrow የአራዳው ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት...
የአራዳው ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት... E-mail
Sunday, 19 October 2008

የአራዳው ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት ቢውል

መስከረም 21 ቀን ስለ ሁዳ ሪል እስቴት የግንባታ ውል ማለፍ የጻፋችሁትን ሳነብ በመጋቢት 28 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ጋዜጣችሁ የአዲስ አበባ ከተማ "በ27 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው ቤተ መጻህፍት ማሰሪያ የሚውል ቦታ እስካሁን አልተገኘም" በሚል የጻፋችሁት ትዝ አለኝ፡፡

 

ቀድሞውንም በማዘጋጃ ቤቱ አጠገብ የተንጣለለውን ሰፊ መሬት በጥንቃቄ አቅዶ ቁልፍ ለሆኑ ህዝባዊ አገልግሎቶች ማዋል ሲገባ በችኮላ ለግል ኢንቨስተር መሰጠቱ ተገቢ አልነበረም፡፡ ደግነቱ እስካሁንም ምንም የረባ ግንባታ ስላልተካሄደበት በአጋጣሚው ተጠቅሞ ውሳኔውን ማረምና ለተሻለ ተግባር ላይ ማዋሉ ይመረጣል፡፡

ስለ ዋና ከተማችን እድገትና ስለህዝብ አገልግሎት በሃቅ ለሚያስብ፣ ከታሪካዊነቱም ሆነ ከማእከላዊ አቀማመጡ አንጻር፣ ለመዲናችን ዋነኛ መጻህፍት ቤት ትክክለኛ መናኸሪያ በማነጽ ረገድ፣ ከዚህ በፒያሳ እምብርት ላይ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጎን ከሚገኘው ቦታ የተሻለ አማራጭ የሚኖር አይመስለኝም፡፡

አሁን የያዙት ባለሃብት እስከዛሬ ሳይጠቀሙበት መቆየቱ ራሱ ቦታውን ይህን ያህል እንደማይፈልጉት ያመለክታል፡፡ ያም ሆኖ በእውን ለልማት መሬት ካስፈለጋቸው አዲስ አበባችን ሰፊ ናትና ለሳቸው ብዙ አማራጮችን መስጠት ይቻላል፡፡ እሳቸውም ዓላማቸው የአገሪቱ ልማትና የህዝቡ እድገትም እስከሆነ ድረስ የግድ ይህንን ይዞታ ብቻ ካልወሰድኩ ይላሉ ብዬ አላስብም፡፡ ቦታው ላይ የብዙሃኑ ህዝብ መገልገያ የሆነ ቋሚ ቅርስ ቢሰራበት የሚደሰቱ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም ለዝግጅቱ አስተዋጽኦ ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ እገምታለሁ፡፡ በዚህ መልክ ለህዝብ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት ተገቢው ንጣፍ ወይም ማካካሻ ተደርጎ ቀድሞውንም የህዝብ መናኸሪያ የነበረው አራዳ ተመልሶ ለብዙሃኑ ህዝብ አገልግሎት እንዲውል ቢደረግ ጠቀሜታው የላቀ ይሆናል እላለሁ፡፡ አዲሱ የከተማው አስተዳደርም ጉዳዩን በጥሞና አስተውሎ ይህንኑ በጎ ዓላማ እንደሚከተል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

(ይበይን ተግባሩ፣ ከቂርቆስ)

ግድቦቻችን አለመሙላታቸው ያሳዝናል

ወደ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በ2ዐዐዐ ክረምት የገባው ውሀ ሊሞላቸው እንዳልቻለ በረቡዕ ዕትማችሁ ያቀረባችሁትን አንብቤ አዝኛለሁ፡፡ እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ እንዲሉ ግድቦቹ አለመሙላታቸው በዜናችሁ እንደጠቀሳችሁት በፍጥነት ወደፈረቃ እንድንገባ የማያስገድድ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ከነዳጅ ዋጋ እና ከእህል ዋጋ መናር ናላው በዞረበት በዚህ ወቅት እንደገና መብራት ሌላ ዙር የዋጋ ንረት ይዞበት ሲመጣ እንዴት አያሳዝን ትላላችሁ፡፡

(ትርንጎ ጀማል፣ ከአዲስ አበባ በስልክ የተሰጠ አስተያየት)


ሀቁን ለመሸፋፈን መሞከር ያስፈራል

ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 5 ቀን 2ዐዐ1 እትም መጀመሪያ ገጽ "መንግሥት 6.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መራባቸውን አመነ" በሚል ርዕፋ የተጻፈውን ዜና እውነቱን ለመሸፋፈንና ሀቁን ላለመቀበል መንግሥት ሲያደርገው የነበረው ሙከራ ሁሉ ውጤት አልባ እንደሆነበት ያስመሰክራል፡፡ "የተራበው የሕዝብ ቁጥር 6.4 ሚሊየን አይደለም፡፡ ይህ መያዶች ለጥቅማቸው ሲሉ የፈጠሩት መሠረተ ቢስ የሆነ የሀሰት ወሬ ነው" እያለ ነበር፤ እሱ ብቻ በሚያዝበት ሚዲያ ሲወተውት የነበረው፡፡ ሀቁን ግን የፈጠራ ወሬ የሚነዛው መንግሥት እንጂ መያዶች አለመሆናቸውን በራሱ አንደበት አምኗል፡፡

ለወደፊቱ መንግሥት ተአማኒነት የማይንሱበትን ሐቀኛ መረጃዎች ለሕዝቡ ቢያደርስ ሊደመጥ ይችላልና ቢታሰብበት፡፡

(በለጠ አበበ፣ ከፒያሳ)


ኮንዶሚኒየሞችን የሚያስተዳድር ጽህፈት ቤት ቢቋቋም

በሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 25 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. እትም "ይድረስ ለሪፖርተር" አምድ ላይ በኮንዶሚኒየም አጠቃቀም ግለኝነት ቢወገድ በሚል በቦሌ ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቁጥር 1 ነዋሪዎች የተፃፈው ፅሁፍ ህገ ወጥ እና ስነምግባር የጎደላቸው ነዋሪዎች ከሚፈፅሙት ድርጊቶች የተወሰኑትን ችግሮች ብቻ ያንፀባረቀ ቢሆንም ችግሩን ለማስወገድ የሚመለከታቸው አካላት በዝምታ ማለፋቸው ሊታወቅ የሚገባ ስለሆነ ፀሐፊዎቹም ሆነ ጋዜጣችሁን እያደነቅኩ እንደኔ በነዋሪዎች እና በመንግሥት ፋይናንስ የሚደረግ ኮንዶሚኒየሞችን የሚያስተዳድር ጽህፈት ቤት ቢቋቋም ለማህበረሰቡ ግድ የሌላቸው እና ህገ ወጥ ግለሰቦችን ለሕግ ለማቅረብ እንዲሁም የአካባቢውን ደህንነት ከነዋሪዎች ተፅእኖ ነፃ በሆኑ የጥበቃ አባላት ለማስጠበቅ ይረዳል እላለሁ፡፡

(ሠናይት፣ ከቦሌ ገርጂ ኮንዶሚኒየም)


የጅማ ፀጥታ ያሳስባል

ጋዜጣችሁን ከሚከታተት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡  ብዙ ጊዜ ልፅፍላችሁ ብዕሬን እያነሳሁ መልሼአለሁ፡፡ ዛሬ ግን አንዳንድ ነገር ስለጅማ ከተማ የፀጥታ ችግር ለመፃፍ ያስገደደኝን ነገር ለመፃፍ ወደድኩኝ፡፡

መቼም ከአዲስ አበባ ሆኖ ስለ ጅማ ሲወራ ብዙ ነገር ሩቅ ላለው ሰው (ተመልካች) ጥሩ ይመስለዋል፡፡ ሌላ ሌላውን ትቼ ስለ ከተማዋ ፀጥታ ችግር ግን ብዙ ማለት ቢቻልም ከብዙ በጥቂቱ መግለፅ ይቻላል፡፡

የከተማዋ የሰላም ሁኔታ ግን እጅግ ከቀን ወደ ቀን አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ቀን ቀን በከተማዋ የገበያ አካባቢ ሌቦች የህዝቡን ሞባይልና ከገጠር የሚመጣውን ነዋሪ ገንዘብ ሲዘርፉ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡

ሴቶች ተማሪዎች በከተማዋ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ለመከታተል እጅግ ተቸግረዋል፡፡ ማንም ሴት ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አትችልም፡፡ ወደ ጅማ መሰናዶ ትምህርት ቤት፣ ወደ ኪያ ሜድ ኮሌጅ፣ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የምትሄድ ሴት ተማሪ ወዮላት፤ በራሷ ላይ የፈረደች መሆን አለባት፡፡

ወጣት ወንዶች ተማሪዎችም ቢሆኑ ከመንደራቸው ርቀው ሄደው ለመማር ተመሳሳይ ችግር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ከቆጥ መንደር ወደ መንቲና መንደር ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት መሄድ እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ህዝቡ ይህንን ለማን አቤት ይበል? ግራ ተጋብቷል፡፡ ፖሊስ የሰላም ዘብ ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም ግን የጅማ ከተማ ፖሊስ ለሰሙ ቢሮ አለው እንጂ በተግባር ለህዝቡ የሰላም አለኝታነቱን ሊያስመሰክር አልቻለም፡፡

ሌላው በከተማዋ የተደራጁ ሌቦች ሌሊት ሌሊት ከተማዋን በማመስ ወርቅ ቤቶችን ሲዘርፉ፣ ቀን ቀን ተማሪዎች መግቢያና መውጪያ አጥተው ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ፤ ቤተሰብ አቤት የሚልበት አጥቶ መንግሥት የት ነው ያለው እያለ ሲማፅን ማን ይድረስለት፡፡ ጅማ የሌባ ከተማ ሆናለች፡፡ ህዝቡ ሰላም ናፍቆታል፡፡ ወላጆች ከነልጆቻችን በሰላም ወጥተን በሰላም መግባት እየናፈቀን ነው፡፡ እውነት ለከተማ ነዋሪ ደህንነትና ሰላም የሚያስብ የመንግሥት አካል ካለ አንድ ይበለን፡፡ ካለበለዚያ ግን ዛሬ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት የጅማ ከተማ ጩልሌዎች ነገ ወደ መሐል ሀገር ስላለመግባታቸው ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት ግን ልትታደጉን ከቻላችሁ ታደጉን እያልን ድምፃችንን እናሰማለን፡፡

(ከጅማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል)
 
< Prev   Next >