| በጋዛ የሀይል ምንጭ መቋረጥ ቀውስ ፈጥሯል |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
በጋዛ ካለፈው እሁድ ጀምሮ የሀይል ምንጭ መቋረጡን ተከተሎ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን አሶሺየትድ ፕሬስ ከጋዛ ያሰራጨው ዘገባ አመለከተ፡፡ እስራኤል የሀማስ አባላት የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለማግኘት የፈጠሩት ችግር መሆኑን ገልፃለች፡፡ እስራኤል ከጋዛ የሚሰነዘረውን የሀማስ የሮኬት ጥቃት ለማስቆም በሚል የጋዛን የሀይል ምንጭ እንደዘጋች የጋዛ ባለስልጣናት ገልፀዋል፡፡ በዚህም በጋዛ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ በአካባቢው ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩን የጋዛ ባለሥልጣናት ገልፀዋል፡፡ የሀማስ ቴሌቪዥን ዘጋቢ “እኛ እየተገደልን ነው፣ እየተራብን ነው” ሲል በንዴት እስራኤልን ኮንኗል፡፡ የጋዛ የሀይል ስርጭት ባለሥልጣን ተጠሪ ካና አቢድ የጋዛ ብቸኛ ኤሌክትሪክ ሀይል ምንጭ ተቋም ካለፈው እሁድ ጀምሮ መዘጋቱንና ከተማዋ በጨለማ መዋጧን ገልፀዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሞያ ሀሳኒን በከተማዋ የሀይል መቋረጥ የጤንነት ቀውስ እንደሚፈጥር አስጠንቅቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ “የማዋለጃ ክፍልና የልብ ቀዶ ህክምና ክፍል ላይ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቋረጥ ተገደዋል” ሲሉ አማረዋል፡፡ የከተማዋ የዳቦ አቅራቢዎች በበኩላቸው በሀይል መቋረጡ ምክንያት ስራቸውን ማቆማቸውን ገልፀዋል፡፡ በጋዛ የሚገኙ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች በዋነኝነት ትኩስ “ፒታ” ዳቦ ተመጋቢ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስልማን የተባለ የጋዛ ነዋሪ “ከጋዛ ረጅም መንገድ ተጉዤ ለቤተሰቦቼ ለሁለት ቀን ብቻ የሚቆይ ምግብ እገዛለሁ ምክንያቱም የኤሌክትሪክ ሀይል ስለሌለ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ አይቻልም” በማለት ችግሩን ገል”ል፡፡ በሌላ በኩል የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው ጋዛ ሰባ በመቶ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ከእስራኤል እንደምታገኝና ይህም አለመቋረጡን ገልፀዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ እስራኤል ለጋዛ የምታቀርበው የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡንና በዚህም ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል፡፡ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ሻሎም ድሮር በበኩላቸው የሀይል አቅርቦቱ የተቀነሰው ከጋዛ የሚሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ለማስቆም መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ የሀይል አቅርቦት ቅነሳ ከመካሄዱ ከሁለት ቀን በፊት ሀምሳ ሶስት የሮኬት ጥቃት ከጋዛ መሰንዘሩንና ከቅነሳው ወዲህ እሁድ ብቻ አምስት የሮኬት ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸዋል፡፡ በማያያዝም “ይህ ግን በቂ አይደለም” ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ሚኒስትር ዳሮር ከጋዛ ወደ እስራኤል መሸጋገር እንደማይቻልም አያይዘው አስታውቀዋል፡፡ ይህም የሀማስን ጥቃት ለመከላከል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሚኒስትሩ “የሀይል አቅርቦት ቅነሳውን ብናቆምና በጋዛና በእስራኤል መካከል ያለውን መተላለፊያ ብንከፍት ከሀማስ የሮኬት ጥቃት ይደርስብናል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ “የሀማስ ዋነኛ ችግር የእስራኤልን ህጋዊነት አለመቀበልና እስራኤልን የማጥፋት አላማ በመያዙ ነው” በማለት “እኛ ደግሞ እንዲያጠፉን በር አንከፍትላቸውም” በማለት ሚኒስትሩ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡ የሀማስ ባለሥልጣናት በጋዛ ከአምስት ሰዎች በላይ በሀይል እጥረት ምክንያት ሆስፒታል ውስጥ መሞታቸውን ገልፀዋል፡፡ የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩላቸው የሀማስን ውንጀላ አስተባብለዋል፡፡ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እስራኤል ከጋዛ የሚሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ለማስቆም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በጋዛና በእስራኤል መካከል የሚገኙትን መተላለፊያዎች መዝጋቷንና የነዳጅ፣ የምግብና የመድሃኒት አቅርቦት ማቋረጧን ዘግበዋል፡፡ የጋዛ ነዋሪዎች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ሀይል መቋረጥ ምክንያት የምግብ ማስቀመጫ ማጣታቸውንና የትኩስ ምግብ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን በመጥቀስ አማርረዋል፡፡ የፍልስጤም መሪ መሀመድ አባስ እስራኤል የዘጋችውን መተላለፊያ እንድትከፍት ያለፈው እሁድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ቃል አቀባያቸው ገል”ል፡፡ መሀመድ አባስ ዌስት ባንክን ብቻ በህጋዊ ሁኔታ እየመሩ መሆኑና የጋዛ አስተዳደር በሀማስ እጅ መውደቁ ይታወቃል፡፡ ፍልስጤማውያን መሀመድ አባስ በአሜሪካ አደራዳሪነት ከእስራኤል ጋር የጀመሩትን የሰላም ድርድር በማቋረጥ እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል፡፡ በግብፅ የአባስ አመራር ተጠሪ ናቢል ሻታ በቅርቡ እስራኤልና የአባስ መንግሥት በሚያደርጉት ድርድር ላይ የጋዛ ጉዳይ እንደሚነሳ ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ ናቢል ሻታ “ነገር ግን በጋዛ ምክንያት አባስ ከእስራኤል ጋር የተጀመረውን የሰላም ድርድር ወደኋላ እንዲመለስ አይፈልጉም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በሶርያ ደማስቆ በእስር የሚገኙት የሀማስ መሪ ከሀልድ ማሻል ያለፈው እሁድ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መሀመድ አባስ ከሀማስ ጋር ያላቸውን ልዩነት በመተው ለጋዛ ነዋሪዎች እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማሻል ከአልጄዚራ ቴሌቬዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “በየደቂቃው ለሚሞቱት የጋዛ ነዋሪዎች ነብስ የአረብ መሪዎች ተጠያቂ ናችሁ” ሲሉ ኮንነዋል፡፡ በፍልስጤማውያን መካከል አንድነት እንዲኖር ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የእስራኤል በጋዛ ላይ የነዳጅ አቅርቦት ማዕቀብ መጣሏን አውግዘዋል፡፡ ኦክስፋም የተባለው ድርጅት የእስራኤል ማዕቀብ “ውጤት የአልባና ህገወጥ” ሲል አጣጥሏል፡፡ ድርጅቱ የእስራኤል እርምጃ የሮኬት ጥቃቱን ከማስቆም ይልቅ ያባብሳል በማለት ገል”ል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል እርምጃ መሆኑን ኦክስፋም ገል”ል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ እስራኤል ዜጎቿን ከሮኬት ጥቃት የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳላት ነገር ግን በጋዛ ላይ የተወሰደው እርምጃ አጥፊዎችን በመለየት የተካሄደ አለመሆኑን አሳውቋል፡፡ የአለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ሚካኤል ሜርሳየር በጋዛ ጥቂት የመድሀኒት ክምችት መኖሩንና በቅርቡ ተጨማሪ የመድሃኒት አቅርቦት ካልተገኘ ከፍተኛ ችግር እንደሚከሰት አሳስበዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |