Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow አንዳንዶቹ ትናንት በሩጫ ወደ ፓርቲው (ቅንጅት) ዘ
አንዳንዶቹ ትናንት በሩጫ ወደ ፓርቲው (ቅንጅት) ዘ Print E-mail
Sunday, 06 January 2008

አንዳንዶቹ ትናንት በሩጫ ወደ ፓርቲው (ቅንጅት) ዘለው የገቡ ስለሆኑ መስዋዕትነቱ ከብዷቸው ይሆናል

አቶ አባይነህ ብርሃኑ
በኢንጂነር ኃይሉ ውክልና የቅንጅት ሊቀመንበር

አቶ አባይነህ ብርሃኑ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ውክልና የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው በጊዜያዊነት ተሹመዋል፡፡ በቅንጅት ወቅታዊ ውዝግብ፣ መከፋፈልና የኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የዕገዳ እርምጃና የውክልና መስጠት በመሳሰሉ ዙሪያዎች አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ውክልናና መሾም በተያያዘ ከፓርቲው ህገ ደንብ አሰራር ውጭ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡

አቶ አባይነህ፡- የሚቃወሙ ሰዎች የሚያወሩት ወሬ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የአንድ ፓርቲ ወይም ድርጅት መሪው ወደ ውጭ በሚወጣበት ጊዜ ሥራውን ተክቶ ሊሰራ ይችላል ብሎ በሚያምንበት ሰው መወከል የተለመደ አሰራር ነው፡፡ በኛ በፓርቲያችን ህገ ደንብ አንቀፅ 24/1 [      ] መሠረት ሥራውን ለማቀላጠፍ ወቅታዊ ሥራ ለማንቀሳቀስ ይችላል ተብሎ የሚታመን ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አንድ ሰው መወከል የተለመደና በዛ መሠረት እየተሰራ ነው፡፡ ስለዚህ በህግ የሚደገፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አንቀፅ ፕሬዚዳንቱ ላዕላይ ምከር ቤት ሳያውቅ በራሱ ፈቃድ የመወከል የመሾም መብት አይሰጠውም ይባላል?

አቶ አባይነህ፡- ይሄ እኮ ጊዜያዊ ውክልና ነው፡፡ እስኪመለስ ድረስ ሥራውን እንዲሰራለት የሚያደርግ ውክልና ነው፡፡ ይህ ሹመት አይደለም፡፡ በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ የሥራ አስፈፃሚውን ቢሆን በላዕላይ ምክር ቤት አስመርጦ የሚያስብበት ሁኔታ ነው ያለውና ከእሱ ይሁንታ ውጭ ብዙ ሥራ አይሰራም፡፡ ይሄ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ግን ይሄ ቋሚ የሆነ ሹመት ሳይሆን ፕሬዚዳንቱ እስኪመጡ ድረስ ሥራው ወቅቱን ጠብቆ እንዲሠራ ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ ያንን ሥራ ሊሰራ ይችላል ብሎ ያመነበትን ሰው መወከል ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት የተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኦዲት ሥራ ለመሥራት አቅዳችኋል ይባላል፡፡ የውጭ አገር ድጋፍ ሰጪ ቻርተሮች የላኩት ገንዘብ ይታወቃል?

አቶ አባይነህ፡- በትክክል ይታወቃል፡፡ ከአገር ውስጥ የሚሰበሰብና ከውጭ የሚገባ ድጋፍ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊትም ኦዲት እያደረግን ቆይተናል፣ አሁንም አዲት ይደረጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቋሚ ኦዲተሮች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ነው ኦዲት የሚያደርጉት? ገንዘብ ብቻ ነው ኦዲት የሚደረገው?

አቶ አባይነህ፡- ዶክመንቶችን አይተው የመጀመሪያ ደረጃ ኦዲት ያደርጋሉ፡፡ የኦዲቲንግ ሥራ ያሰባስባሉ፡፡ ኦዲቲንግ በመሠረቱ ቁጥር ብቻ አይደለም፡፡ አስተዳደርም ኦዲት ይደረጋል፡፡ ይህንን በተለይ ጠቅላላ ኦዲት እንደሚደረግ ከታወቀ ለጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ማቅረብ ስላለባቸው ኦዲት መደረግ አለበት፡፡ ኦዲት አስደርገው አሰርተው ያንን የሚያምኑበትን ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡  በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ እንጠራለን ብለን ስለምናስብ ኦዲት ለማስደረግ አስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ቻፕተሮች ድጋፍ የሚታወቅ ከሆነ ሊገልፁልኝ ይችላሉ?

አቶ አባይነህ፡- እኔ አላውቀውም፡፡

ሪፖርተር፡- ፕ/ር መስፍን ከእስር ከተፈቱ በኋለ ድምፃቸውን አጥፍተው አሁን በቅንጅት ክፍፍል ከተፈጠረ በኋላ አስተያየት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የእነ ወ/ሪት ብርቱካን ቡድን ትክክለኛነትም እየተናገሩ ነው፡፡ ይሄ እናንተን አይጎዳም?

አቶ አባይነህ፡- ይሄ የግል መብታቸው ነው፡፡ እሳቸው አንዱን ወገን ስለደገፉ፣ ሌላውን ስላልደገፉ ወይም ዝም ስላሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ የሚመጣው በፓርቲው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ለጋዜጣ ፍጆታ ከሆነ የፈለጉትን ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጋዜጦችም በመጠቀም አፈነዳለሁ፣ እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንዲህ እፈጥራለሁ፣ ብዙ ሚስጢር አለኝ አወጣዋለሁ... እያሉ እንደሚያወሩ እሰማለሁ፡፡ ምንም የሚያውቁት ምስጢር የለም፣ የሚያፈነዱትም ነገር የለም፡፡ ይሄ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ስብሰብ ነው፡፡ እኛ ሌላ ተልዕኮ የለንም፡፡ በሰላማዊ መንገድ የምናንቀሳቅሰው ፓርቲ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በገዛ ገንዘባችንና ጉልበታችን ለሀገር ይጠቅማል ብለን የምንሰራው ሥራ ነው፡፡ ይሄ ለፕ/ር መስፍን ተብሎ የሚሰራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የሆነውን ያልሆነው በማውራት የሚደሰቱ ከሆነ ፕ/ር መስፍን ማውራት ይችላሉ፡፡ ግን በፓርቲው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የሚያመጡ አይደሉም፡፡ ከወሬ አያልፍም፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚችል እዚህ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ የሚሰራ ሰው ብቻ ነው፡፡ ምንም እያደረጉ አይደለም፡፡ ስለዚህ በወሬ ምንም የሚሰራ ሥራ የለም፡፡ የሚመጣ ለውጥም የለም፡፡ ደገፍኳችሁ ለሚሉዋቸው ሰዎችም ቅንጣት ያህል የሚጠቅሟቸው ነገር የለም፡፡ እኛንም በመስደብ የሚያጠፉት ጊዜ ሊቆጫቸው ይገባ ነበር፡፡ ነገሩን ብንተወው ይሻላል፡፡ እሳቸው ለሚሰድቡን ሁሉ አፀፋ እንስጥ ብንል ሰውም ይታዘበናል፤ እሳቸው ግን መሳደብ ይችላሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ግን ምንም ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ የእሳቸውን ስድብ ፈርቶ ስልጣን የሚሰጣቸውም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ ሰው ጆሮ ይሰጣቸዋል ይባላልና በእናንተ ቡድን ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ አይኖርም?

አቶ አባይነህ፡- በፍፁም አይኖርም፡፡ ፕ/ር መስፍንን አብዛኛው ሰው ያውቃቸዋል፡፡ የፈለጉትን ነገር በመናገር እንጂ፣ ሰርተው ውጤት በማሳየት የሚታወቁበት ነገር የለም፡፡ እውነቱ ይሄ ነው፡፡ ምናልባት ኢሰመጉ በማቋቋም ካልሆነ በስተቀር በዚሁ በኛ ፓርቲ ውስጥ የሚያወሩትን ያህል ምንም የሰሩት ነገር የለም፡፡ ለረዥም ጊዜ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ከቀጠልንበት ጊዜ ጀምረው፣ እሳቸው አንድ ቀን ጋዜጣ ላይ አንጃግራንጃ ስለአወሩ ይህን ያህል ስሜታችንም አይጎዳም፤ ሰውም ደግሞ በዚህ ይታዘባቸዋል እንጂ ረይቅርታ አድርግልኝሪ ምንም አያመጡም፡፡ እሳቸውን የማያውቅ ማን አለ? በእሳቸውስ የሚታለል ማን ነው? ይታወቃሉ..

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ሁላችሁም በየፊናችሁ፣ ..ቅንጅት አንድ ነው..፣ ..የዓላማ ልዩነት የለም.. ትላላችሁ፡፡ በተግባር ግን ይህ እንዳልሆነ እያየን ነው፣

አቶ አባይነህ፡- አሁንም ቢሆን በቅንጅት መካከል መከፋፈል አለ ብዬ አላስብም፡፡ እኔ ቅንጅት የምለው ጠቅላላ ፓርቲውን ነው፡፡ ግለሰቦችን አይደለም፡፡ ግለሰቦች እንደአሰላለፋችን የተለያየ ስሜት አለን፡፡ ይህ ፓርቲ ብዙ የደከምንበት ፓርቲ በመሆኑ እንኳንስ በህይወት እያለን ከሞትን በኋላ ቢሆንም ጠንክሮ እንዲቀጥል የምንመኘው መሆኑ ምንም ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ትናንት በሩጫ ወደዚህ ፓርቲ ዘለው የገቡ ሰዎች ስለሆኑ መስዋዕትነቱ ከብዷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ወደ ፓርቲው ከገቡ ዓመት ሳይሞላ እስር ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም በኋላ ወጣን፤ አሁንም ቢሆን የተመቻቸ ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ሥራ ለመሥራት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ፀንቶ አቋሙን አጠናክሮ ሥራ መሥራት ካልተቻለ ምክንያት ፈጥሮ ከፓርቲው ለመለየት ሰበብ ፍለጋ ሊኖር ይችላል፡፡

አሁን እንደዚህ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የዓላማ ልዩነት ቢሆን ግን ጠረጴዛ ላይ በመወያየት ጥያቄዎችም መልሶችም ይኖሩ ነበር፡፣ ግን አሁንም የዓላማ ልዩነት የለም ነው የምለው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ..ቅንጅት አንድ ነው.. እያለ፣ አትከፋፈሉ እያለ ነው ያለው፡፡ በአመራር ውስጥ ያለው መቃረን እንኳ ተገቢ አይደለም፡፡ እያለ ልቡ እየቆሰለ ነው፡፡ ሕዝቡን መካስ አለብን፣ ብለን በቁርጠኝነት የምንታገለው ለዚህ ነው፡፡ ቀላል መስዋዕትነት አይደለም የተከፈለው፡፡ ይሄ ሕዝብ እኛን ከመረጠበት ጊዜ ጀምሮ መስዋዕት እየከፈለ ነው፡፡ ያለው ስለዚህ ..ይህ ፓርቲ የሕዝብ ፓርቲ ነው.. ብለን ስለምናምን ከግል ፍላጎታችን በላይ ነው የምናየው፡፡ ከግል ፍላጎታቸው በላይ አርቀው የማያስቡ ሰዎች ግን እንደዚህ ያለ ስሜት ቢኖራቸው አይደንቀኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ፍላጎት ሲሉ የስልጣን ጥማት ለማለት ነው?

አቶ አባይነህ፡- የስልጣን ጥማት ይሁን የሌላ ሰዎቹ ራሳቸው መመለስ ያለባቸው ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ አብረን መሥራት እንፈልጋለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ገና ከአውሮፕላን ሲወርዱ መከፋፈል እንዳለና፣ እንደውም በጣም የሚያሳዝነው በዚህ በቅንጅቱ ፅ/ቤት ገብተን የምንሰራ ሰዎች ..መኢአድን ከቅንጅት ገንጥለው ሊወጡ ነው..፣ ለዚህ ተጨባጭ ምክንያት አለኝ ብላ ወ/ሪት ብርቱካን ከተናገረች ጊዜ ጀምሮ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ እዚህ እንኳ መጥታ ምን እየተሰራ እንደሆነ ሳታይ ገና ከአውሮፕላን እንደወረደችው ነው ይህንን አስተያየት የሰጠችው፡፡ ከዚያም በኋላ ፓርላማ የገቡም፣ ያልገቡ፤ የታሰሩም ሆነ ያልታሰሩም በቅንጅት ስም የተመረጡ ስብሰባ አድርገን እንወያይ ነበር፡፡ ወ/ት ብርቱካን መጥታ ይህንን ህጋዊ አይደለም ብላ ወጥታ በተናገረችበት ጊዜ የገጠማት ተቃውሞ ቀላል አልነበረም፡፡ አንቺ ራስሽ የት ነበርሽ? እኛ እንኳን ቢያንስ በመቶ ሺዎች ሰው ተመርጠን ነው እዚህ ያለነው፣ አንቺ ማነሽ? ሲሉዋት ጥላ ወጣች፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ ከዚህ ውጭ አይደሉም፡፡ ከጽ/ቤቱ ውጭ ነው በየቤቱ ሲሰባሰቡ የነበሩት፡፡ እና አድራጎታቸው ትክክል አለመሆኑ ታውቆ ታግዳችኋል ሲባሉ ..ህገወጥ እገዳ.. ነው ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- እገዳው ህጋዊ ነው ይላሉ?

አቶ አባይነህ፡- እገዳው በህግ ነው፡፡ ከህገደንብ ውጭ ሆነው የሚያስቸግሩ ሰዎች በሚኖሩበት ጊዜ ፕሬዚዳንቱ አግደው ለበላይ ኮሚቴ ያሳውቃሉ ነው የሚለው፡፡ ያንን ነው ያደረጉት፡፡ በገለልተኛ ሁኔታ ይጣራ፣ ሁኔታው ግን ይሄን ይሄን አጥፍተዋል ብለው ሃያ ነጥቦችን ያቀረቧቸው በሙሉ እነዚህ ሰዎች ከህገደንብ ውጭ የሚያደርጉትን ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፡፡ ይሄ ለጠቅላላ ጉባኤም ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንጂነር ኃይሉ በዚህ እርምጃቸው ላይ ህገ ደንቡን የተከተለ እንደሆነ አንቀፅ እንዲጠቅሱ በጋዜጠኛ ተጠይቀው ..ህግ ተሸክሜ አልዞርም.. ብለዋል፤ ላዕላይ  ምክር ቤት ነው መወሰን የሚችለው ወይስ እሳቸው?

አቶ አባይነህ፡- ፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ላዕላይ ምክር ቤትን ማሳወቅ ይችላሉ፡፡ ላዕላይ ኮሚቴ ውሳኔው የተሟላ አይደለም፣ ችግር አለበት ካለ ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርቡታል፡፡ ጉዳዩ ተጣርቶ ይፀድቃል ወይም ይሻራል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ውሳኔው ገና አልፀደቀም ማለት ነው?

አቶ አባይነህ፡- እስከዚያ ድረስ ሰዎቹ ታግደው ይቆያሉ እንጂ ፀደቀ ማለት አይቻልም፡፡ ገና የሚጣራ ነው፡፡ የስነስርዓት ኮሚቴው ያጣራዋል፡፡ አጠፉ የተባሉትን ጠርቶ ይጠይቃቸዋል፡፡ እኛ አሁን እንዳንድ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡ ጥፋቱ ውስጥ የሌሉበት የተወሰኑ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ ለድምፅ ብልጫ ብለው ችግር የፈጠሩ ሰዎች መኖራቸውን አውቀናል፡፡ ይሄን ሁሉ ካገናዘቡ በኋላ እርምጃ የሚወሰድበት ይኖራል፣ ነፃ የሆነ ደግሞ ነፃ የሚወጣበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

አቶ ኃይሉ በወቅቱ የተናገረው እንደዚህ ቃሉን በማያስታውስበት ጊዜ ጋዜጠኛው በጠየቀበት ..አንቀፅ ልጠቅስልህ አልችልም ግን ህገደንቡ አለ.. ነው ያለው፡፡ ይህ እንግዲህ ፀጉር ተሰንጥቆ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለምዶ ስንሰራበት የቆየ ነው አላሉም?

አቶ አባይነህ፡- አይደለም፡፡ በተለምዶ የሚባል ነገር የለም፡፡ ግን እየተሰራበት የቆየ ህግ ነው፡፡ በህገ ደንባችን አንቀፅ 42/1 ረላይ ብታነብሪ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ፕሬዚዳንቱ እርምጃ ወስዶ ለሚቀጥለው ዕርከን ሪፖርት ያደርጋል ነው የሚለው፡፡ ይሄ ማለት ለምሳሌ ላዕላይ ኮሚቴ የለም፣ መወሰን አይችልም፡፡ ረግማሾቹ ወጥተዋል፡፡ ወደ 60 አባላት ነው ያሉት ከእነዚህ ውስጥ 30ና ከዚያ በላይ የሚገኝ አይመስለኝምሪ፡፡ ይሄ ከሆነ ላዕላይ ኮሚቴ ከሌለ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠብቃሉ፡፡ ቢሆን ግን በላዕላይ ኮሚቴ ነገሩ ያልቃል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅንጅት የተፈጠረውን መከፋፈል ማጥበብ አለመቻሉ የቅንጅትን ከፍተኛ አመራር ብቃት ጥያቄ ውስጥ አይከትም? አብራችሁ የማትሰሩበት ምክንያት ምንድንነው?

አቶ አባይነህ፡- ሊሆን ይችላል፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ የብቃት ችግር አስመልክቶ ደጋግመው ይናገሩት የነበረው የብቃት እንበለው የምን እንበለው አላውቅም፡፡ 1ኛ/ በላዕላይ ምክር ቤት ተወስኖ ነው፣ ይህንን ይህንን ያደረግነው ሲሉ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ፡፡ አንድም ቦታ ከመውጣታችን በፊት (ምልአተ ጉባኤ ባለመኖሩ) አንድም ቀን ቃለ ጉባኤ ይዘን፣ አጀንዳ ይዘን ተወያይተን ወስነን የተፈረመ ነገር የለም፡፡ ይሄ በሌለበት ጊዜ ላዕላይ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ በወሰነው መሠረት ነው የምናደርገው፣ እየተባለ እየተደጋገመ ይወራ ስለነበር (ይህንን ብርቱካን ከተመለሰች በኋላ ነው ያነሳሁላት) የት ቦታ መቼ ነው ቃለጉባኤ ኑሮሽ፣ ይሄ ይሄ ተወስኖልኝ ነው ፕሬዚዳንቱን ጥየ የመጣሁት፣ ተፈቅዶልኝ ይህንን ስሰራ ነው የምትይው፣ የት ነው ያለው ማቅረብ ትችያለሽ? ነው ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል በሚል ነው? ብየ ስጠይቃት ልትመልስልኝ አልቻለችም፡፡ እነዚህ ሰዎች በሚዲያ ላይ ጋዜጠኞች በሚጠይቋቸው ጊዜ አንዱ ከሌላው ያልተሻለ የውሸት ክምር ነው ሲናገሩ የነበሩ፡፡ ሰዎቹ ከውጭ ከመጡ በኋላ አብረውን ለመሥራት ያልቻሉበት ምክንያት ይሄ ውሸት ስለሚጋለጥ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በምንም ምክንያት ከእኛ ጋር አብረው የማይሰሩበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ ምንም የተለየ ተልዕኮ እንደሌለንም ያውቃሉ፡፡ ቀደም ብለንም ለዚህ ለቅንጅት መፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረግን ሰዎች መሆናችንን ያውቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በቅንጅት በተፈጠረው የስራ አስፈፃሚዎች ለሁለት መሰንጠቅ  ከነወ/ሪት ብርቱካን ያለው ቁጥር ይበልጣል የሚባል ነገር አለ?

አቶ አባይነህ፡- ይሄ መሠረት የሌለው ነው፡፡ ቢሆንም እንኳን የሚጠቅም ነገር አይደለም፡፡ አንድ ላይ ሁነን እንኳ ኮረም አንሞላም፣ እንኳንስ ተከፋፍለን፡፡ ይሄ ወቅቱም የደረሰ ጉዳይ ስለሆነ የትኛው ቁጥር ይበዛል የሚያጨቃጭቀን ጉዳይ አይደለም፡፡ ግን አብዛኛው ሰው ከኢ/ር ኃይሉ ጋር እንደሆነ ላረጋግጥልህ እፈልጋለሁ፡፡ ዋናው እነሱ ህጋዊ ሆነው ፓርቲው የሚቀበላቸው እስከሆነ ድረስ በህጋዊ ይመረጣሉ፡፡ የእኛ ሰዎች ትክክል ከሆኑ ደግሞ እኛ እንመረጣለን፡፡ ወይም ደግሞ ከእነሱም ከእኛም የሚመረጥ ይሆናል፡፡ ወይም አዳዲሶችን መርጦ እናንተ ሁላችሁንም አታስፈልጉም፤ ልንባል እንችላለን፡፡ በዛን ጊዜ በደስታ ተሰናብተን ወደየቤታችን አጨብጭበን እንገባለን፡፡ ይህ ጊዜው ሩቅ አይሆንም፡፡

በየማነ ናግሽ

 

 
< Prev