| እንደ ጦጣ የሚያስብ ሮቦት ተሠራ |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከቶኪዮ እንደዘገበው እንደ ጃፓኖቹ ሮቦቶች የሚንቀሳቀስ ግን እንደ አሜሪካ አካባቢ (ፓስፊክ) ጦጣ የሚያስብ ሮቦት ተሠርቷል፡፡ የጃፓንና የአሜሪካ አጥኝዎች እንደገለጹት በፓስፊክ አካባቢ የሚገኙ ጦጣዎችን ያክል ማሰብ የሚችልና ለሰው ልጅ ህልውና የተቃረበ ሮቦት ፈጥረዋል፡፡ በምዕራባዊቷ የጃፓን ከተማ ኩዮቶ በሚገኝ ላቦራቶሪ የተሰራው ሮቦት 155 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን እንደ ቅርብ ወዳጅ አትኩረው ማየት የሚችሉ ጥቋቁር አይኖች አሉት፡፡ የጃፓን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በመግለጫው እንዳመለከተው “የጦጣ ጭንቅላት ያክል እንዲያስብ የሚያደርገውን የሮቦት እንቅስቃሴ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ጃፓን እንደተሸጋገረ ከዳታው ተገንዝበናል” ብሏል፡፡ መግለጫው አክሎ እንዳመለከተው በዓለም ለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው ጋር የተቀራረበ ህልውና ያለውን ሮቦት ከጃፓን ለመሥራት ያግዘናል ብሏል፡፡ ናሳ በጠፈር ዙሪያ የኢንተርኔት ጨዋታ አዘጋጀ የአሜሪካ የጠፈር ጥናት ተቋም (ናሳ) በጠፈር ዙሪያ የኢንተርኔት ጌም አዘጋጅቷል፡፡ የኢንተርኔት ጌሙ የናሳን የኢንጅነሪንግ የሳይንስ ተልዕኮ መሠረት በማድረግ የተሠራ በመሆኑ ለተማሪዎች ስለጠፈር ሰፋ ያለ ግንዛቤ ይፈጥራል ተብሎለታል፡፡ ለዚህ ይረዳው ዘንድ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች ፕሌት ፎርሙን በማሻሻል ረገድ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ናሳ እንደሚለው ጌሙ ጠፈርን በማሰስ ረገድ በሚደረገው ጥረት ቀጣይ ሳይንቲስቶችን ከተማሪዎች ለማፍለቅ ይረዳል፡፡ “ጥራቱ የተረጋገጠለት የጌም ፅንሰ ሃሳብ የናሳ ትምህርታዊ ክንውን ዋና መሣሪያ ነው” በማለት ናሳ ትብብርና ድጋፍ ከድርጅቶች ጠይቋል፡፡ ከማንበብም በላይ በጥቂት ጊዜና ዝቅተኛ ወጪ የጠለቀ የጠፈር ዕውቀት ለማስጨበጥ ጌም መሰራቱን እንደፈለገ ናሳ አስረድቷል፡፡ ለዚህ ማስረጃነት ያሳተመው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂን፣ ሂሳብና ኢንጅነሪንግ በጥልቀት ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ጌሙን እንዳቀረበ ገልጾ እንደ አሜሪካ ጦር ኃይል ያሉ ድርጅቶች የኢንተርኔት ጌሞችን ለማስተማሪያነት መጠቀማቸውን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ ጄኔራል ሞተርስ በሃድሮጅን የሚሰሩ መኪኖች ሊያቀርብ ነው በዓለማችን በመኪና አምራችነት ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ የሚገኘው ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ አንድ መቶ ያህል የፊውል ሴል ተሽከርካሪዎችን በዓመቱ መጨረሻ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡ አሽከርካሪዎች መኪናዎቹን የመሞከር እድል እንዳያመልጣቸው ያሳሰበው ኩባንያው መኪኖቹ የሚቀርቡት በቼቭሮሌት ኢኩኖክስ ኤስ ዩ ቪ መሠረት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ መኪናዎቹ ለባለስልጣናት፣ ለፖሊሶች፣ ለወታደሮችና ተሰሚነት ላላቸው ግለሰቦች ቢዘጋጁም ማንኛውም ተራ ግለሰብ በኢንተርኔት የማመልከት መብት እንዳለውም አክሎ ገልጿል፡፡ በኩባንያው የምርምርና ዕድገት እንዲሁም ስትራቴጅክ ፕላን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ላሪ በርንስ “ከደንበኞቻችን አስተያየት እየተቀበልን ነው፣ ይህም የፊውል ሴል ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ገበያ ለማውጣትና ገበያውን እንድናውቅ ይረዳል” ብለዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በቻይናና በጃፓን እንደሚሰራጩ የታወቀ ሲሆን አገራቱም ከነዳጅና አየር ብክለት አንጻር ምርጫቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ የእንግሊዝ ሞተር ኢንዱስትሪ አማካሪ የሆኑት ዴሪክ ቻርተር ለቢቢሲ እንደገለጹት የወደፊቱን የተሽከርካሪዎች ከብክለት ጠንቅ መሆን ለመከላከል ለወጣው ፕሮግራም ጠቀሜታቸው የጎላ ይሆናል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ጥቅማቸው የጎላ ቢሆንም ዋጋቸው ዋጋቸው ሊሆን እንደሚችል እየተናገሩ ነው፡፡ ሞባይል በምሽት መጠቀም ለራስ ሕመም ያጋልጣል
ጥናቱን ዋቢ በማድረግ የቢቢሲ ዘገባ እንዳመለከተው ሰላማዊ እንቅልፍን የሚያዛባ ሲሆን ሰውነት ዘና ለማለት የሚረዳውን አቅም በማዳከምም ለሰውነት መዛል ምክንያት እንደሚሆን ተረጋግጧል፡፡ ከስዊድኑ ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩትና ከአሜሪካው ዋይኒ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን የተደረገው ይኸው ጥናት በሞባይል አምራቾች ፎረም በተመደበለት በጀት መሰረት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 45 ያሉ 35 ወንዶችና 36 ሴቶች ነው፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው ከፊሎቹ ሞባይል ከተጠቀሙ በኋላ ወደ እንቅልፍ ለመግባት የጊዜ ተመጣጣኝነት የተስተዋለባቸው ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ ከአጥኝዎቹ አንዱ የሆኑት ቤንጅት አንቴዝ እንደገለጹት ሞባይል መጠቀም የእንቅልፍንና የጭንቀትን መጠን በሚቆጣጠረው የአዕምሮ ክፍል ጫና ያሳድራል፡፡ የሰውነት የውስጥ ሁኔታ የሚቆጣጠረውን ሆርሞን የማመንጨት አቅምንም ሊያዛባ ይችላል፡፡ አጥኝ ቡድኑ እንደጠቆመው በምሽት ወቅት ሞባይል ከመጠቀም ይልቅ በኬብል ስልክ (የቤት ስልክ) መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው ብሏል፡፡ አቡዳቢ ለአየር ብክለት 15 ቢሊዮን ዶላር መደበች እየተስፋፋ የመጣውን የአየር መዛባት ለመቆጣጠርና ቴክኖሎጂዎች ከብክለት ምንጭነት የፀዱ እንዲሆኑ ለማድረግ የአቡዳቢ መንግሥት 15 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ዘገባው እንደሚያስረዳው የተመደበው የአምስት ዓመት በጀት ሲሆን እስካሁን በመንግሥት ደረጃ ለዚህ ተግባር ከተመደበ ገንዘብ ትልቁ ወጭ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም በዓለም ላይ ለሚገነባው ታላቁ የሃይድሮጅን ኃይል ግንባታ የሚውል ይሆናል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ የአቡዳቢ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ከመደበው ወጭ በተጨማሪ ለ50 ሺህ ሕዝቦች መኖሪያ የሚሆን የፀዳ ከተማ ለመመስረትና ምንም ዓይነት የግሪን ሃውስ ጋዞች የማይኖርበትና መኪና የማይዘዋወርበት ለማድረግም አቅዷል፡፡ የ15 ቢሊዮን ዶላር በጀቱ “ማሳዳር ኢንሺየቲቭ” የተሰኘው የሀገሪቱ ድርጅት ከብክለት የፀዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከሚገበያዩና ከብክለት ጋር በተያያዘ ከሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩበትም ተገልጿል፡፡ የማሳዳር ሥራ አስኪያጅ “የኃይል አቅርቦት የሁሉም አገር ፍላጎት በመሆኑ እየተስፋፋ ነው፡፡ ይህም ለአየር ንብረት መዛባት ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ የወደፊቱን የመመልከቻ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ አክለውም “ይህን እውነታ በመረዳታችን ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት አገራችን የምታደርገው ጥረት ይቀጥላል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገራችን ዕድገትና ስልጣኔ ቀጣይነት ይረዳል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |