Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Jan 08th
Home arrow Sections arrow የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ሲቃኝ
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ሲቃኝ E-mail
Sunday, 26 October 2008
በሚኒሊክ ተካልኝ (ባለሙያ)

ይህ ፅሁፍ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበታል የሚባለውን "የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ትምህርት ፖሊሲ" ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በተለይ ደግሞ ያለበትን ወቅታዊ ችግር ለመጠቀምና በዘርፉ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግ ለሚፈልጉ ወገኖች "ፍንጭ" ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

በቀጥታ ወደ ፖሊሲው ችግሮች ከማለፌ በፊት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በኢትዮጵያ የነበረበትን ቦታ እና ፖሊሲው ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ አጠር አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት በኢትዮጵያ የነበረው ቦታ፡-

ልጅ ሆነን በከተማችን አዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች በግለሰቦች የሚሰሩ የቴክኒክ ድርጅቶች (ጋራዦች፣ የብረታ ብረት እና የእንጨት ሥራዎች. . .) አልፎ አልፎ ማየት የተለመደ ነበር፡፡ የእነዚህም ድርጅቶች ቦለቤቶች ጣሊያኖች፣ በጣሊያኖቹ ድርጅቶች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ጥቂት ሐበሾች አብዛኞቹ ደግሞ ኤርትራዊያን፣ የትግራይ ተወላጆች እና ጥቂት የሌላ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች ነበሩ ብል ጥቂት ጊዜ ወደ ኋላ በመዞር ሊረጋገጥ የሚችል እውነታ ነው፡፡

በእኛ አባቶችና አያቶች ዘመን እጅግ ወደ ኋላ እንሂድ ብንል ዘርፉ በወቅቱ በነበሩ ገዢወች ጭምር የሚጠላ እና እንደ ነውር የማቆጠር ሥራ መሆኑ ብዙ ፀሃፍቶች ያስቀመጡት ምስክርነት ተቀምጦ ይገኛል፡፡ አናፂ፣ ግምበኛ፣ ሸማኔ፣ ባለ እጅ . . . ወዘተ የሚባሉ ሙያዎች በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚሰጣቸው ቦታ ዝቅ ያለ ብቻ ሳይሆን እንደ ነውር የሚቆጠሩ ሥራዎችም ጭምር ነበሩ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡

በአንፃሩ ደግሞ "White Collars" በተለምደ "የቢሮ ሠራተኛ" መሆን የአዋቂነትና የሥልጣኔ መለኪያነት ተደርጐ ይስተዋል ነበር፡፡

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ትምህርት ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ፡-  

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለት ይቻላል በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት በመላው የሐገሪቱ ክልሎች ሳይቀር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአዲሰ መልክ ተገንብተው የታዩት በዚህ በኢሕአዴግ መንግሥት ነው፡፡ በርግጥ በደርግና በአፄው ጊዜም በአዲስ አበባ እና በጥቂት የሐገሪቱ አካባቢ አልነበረም ማለት ሳይሆን እነዚያ ገዢዎች የመንግሥታቸውን የቢሮክራሲ ሥራ ሊሰሩላቸው የሚችሉትን ሰዎች ለማግኘት የመረጡት የትምህርት ፖሊሲ በተለምዶ "የቀለም ትምህርት" ብለው የሚጠሩትን ፔን ኤንድ ሀንድ ዜጐችን ለማፍራት የታሰበ ነበር፡፡

በየትኛውም ሐገር ባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ክፍፍል መኖሩ ብዙ የሚያጨቃጭቅ ነገር ባይሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገሮች በሥራ ክፍፍሉ በመሀከለኛ ወይንም ባለባቸው የባለ ሙያ ችግር የሰለጠኑ እጆችን ማግኛ ምንጩ ይሄኛው የትምህርት ፖሊሲ ነው ብል "ጥራዝ ነጠቅ" የሚያስብል አይሆንም፡፡

እስኪ አንድ ምሳሌ በማቅረብ ከላይ የጠቀስኩትን ጉዳይ ለማብራራት ልሞክር፡፡ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ባለው የሕዝቦቿ ሁኔታ 85 በመቶ የሚሆነው ገበሬ ነው ሲባል ይህ ገበሬ ደግሞ እጅግ ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም የሚሠራና የአካዳሚክ እውቀቱን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ  ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን አንበልና ዛሬ ድንገት ብትጀምር ያ ገበሬ ከጐጆው ሲወጣ ከቤቱ በራፍ ላይ ለምሳሌ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ ጀነሬተር የውሃ ፓምፕ እና የመሳሰሉትነ  ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች አገኘ፡፡ ማግኘቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ እንዴት መጠቀም ይችላል ብለንም ስናስብ ትራክተር መሾፈር፣ ኮመባይነር ኦፕሬት ማድረግ እና መጠገን ማስተማር ሊኖርብን ግድ ይላል፡፡ ይህ ግን በአንድ መዐልት ይሆናል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው፡፡ . . . እናሳ ኢትዮጵያ ምን ታደርግ? በዚህ ጥያቄ ትክክለኛው ምላሽ ትራክተር ወይንም ኮምባይነር ዲዛይን የሚያደርግ አውቶሞቲቭ ኢንጂነር ሳይሆን እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኦፕሬት ማድረግ ብሎም መጠገን የሚቻሉ እጅግ ብዙ ዜጐችን ነው፡፡

በተጨባጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቅ ክፍተት በገበሬውና በተቀረው በ15 በመቶ ሕዝብ መካከል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዘመናዊት ኢትዮጵያን ያለ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፖሊሲ ማሰብ ቅዥት ይሆናል፡፡

የኔ ዋናው ጉዳይ ግን በፖሊሲው አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ነገር ግን ፖሊሲው በትክክል ተግባራዊ እንዳይሆንና ውጤታማነቱም የተገመተውን ያህል እንዳያድግ እንቅፋት በሆኑት ምክንያቶች ላይ ሲሆን እነዚህን ደግሞ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት ላይ ይበልጥ በማተኮር እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

1ኛ. የተቋማቱ የአቅም ውሱንነት

አንደ አዲስ በኢሕአዴግ ዘመን ተገነቡ የሚባሉት የመንግሥት የሙያ ተቋማት SDC (skill Development Center) ተብለው የሚጠሩት በብዛት የሚገኙት ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞች ሲሆን እነዚህ ተቋማት በያዟቸው ወርክ ሾፕ ውስጥ የሚገኙ ማሽኖች እና የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶች ተቋማቱ ሲመሠረቱ አዲስ የነበሩ ይሁን እንጂ በእንዝህላልነትና በባለሙያዎች ብቃት ማነስ ምክንያት ከነበራቸው ይዞታ አንፃረ ጥሩ ሁኔታ ላይ የማይገኙ ማሽኖች፣ የትምህርት መገልገያዎች እና የእጅ መሳሪያዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በግል የተቋቋሙትን የወሰድን እንደሆነም አብዛኛዎቹ (በከተማችን አዲስ አበባም ጭምር ያሉ) ሲቋቋሙ ጀምሮ በመማሪያ ቁሳቁሶችና በወርክ ሾፕ ግንባታቸው ዓይን የሚገቡ ባለመኞቸው በነሱ ላይ ችግሩ ይበልጥ ገዝፎ ይስተዋላል፡፡  

በሌላ መልኩ ተማሪዎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ማለትም (10ቲ1..፣ (10ቲ2) እንዲሁም (10ቲ3) ለማሰልጠን በሐገር አቀፍ ደረጃ የተቀረፀ "Curriculum Guide" አለ፡፡ በዚህ መሠረት ተማሪዎች እንዲሰለጠኑ ቢፈለግም ለስልጠናው ምለዕነት ወሳኝ የሆኑት መገልገያዎች በተቋማቱ ውስጥ ከነ ጭራሹ አለመኖራቸው ችግር ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡

በአንፃሩ በክልል ከሚገኙትና በመንግሥት ከተቋቋሙት ቲቪቲ ተቋማት እንደ ሞዴል ሊጠቀሱ የሚችሉ አንድ ወይንም ሁለት በጥቂት ክልሎች ይገኛሉ፡፡ (ማይጨው ቲቪቲ ኮሌጅን) እንደ አብነት መጥቀስ አስፈላጊም ጭምር ይሆናል፡፡ እነዚህን መሰል ተቋማት በሁሉም የሐገሪቱ ክልሎች በተለይ ለገበሬው ቅርብ በሆኑት የወረዳ ከተሞች ውስጥ ሊኖሩት እንደሚገባ መንግሥት ማወቅ የኖርበታል፡፡ ተቋማቱን ፍፁም የተሟሉ ለማድረግ ወጪው ለመንግሥት የሚቀመስ ባይሆንም የአካባቢው ሕብረተሰብ በተለይም የግል ባለሃብቱ ጉድለቶችን እንዲሸፍኑ የየክልሉ መንግሥታት የራሳቸውን ጥረት ካሁኑ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡

2. በተቋማቱ ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኞች ብቃት ማነስ

ኢትዮጵያ ባላት ረዥም ታሪክ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት መምህራን (በዲግሪ ደረጃ) ማሰልጠኛ ሥራ የጀመረው አሁንም በዚሁ በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ይሄውም ቀድሞ "ናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ" ቀጥሎም "ናዝሬት የቴክኒክ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ" አሁን ደግሞ "አዳማ ዩኒቨርሲቲ" ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እራሱን "The  center of excellence in Technical and vocational education' በማለት መጥራት የጀመረው ዩኒቨርሲቲ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ነበር፡፡ በእውነት ከተነጋገርን እውን ይህ ስም ይገባሃልን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ የሚገኘው ከዚህ ግዙፍ ተቋም የወጡ (ምሑራን እንበላቸው?!)  ምሁራን ናቸው፡፡

ናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ በ1986 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) በዲግሪና በዲፕሎማ መርሐ ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ (ሀ) ብሎ ስራ ሲጀምር በግቢው ውስጥ የሚገኙት ወርክ ሾፖችና በውስጡ ያሉት የትምህርት መሳሪያዎች፣ አንዲሁም ማሽነሪዎች፣ መፃህፍት ቤት፣ የተማሪዎች ዶርሚተር፣ የመምህራን መኖሪያ ቪላዎች በውጭ ሲመለከቱቸው የማማራቸውንና ዘመናዊ የመሆናቸውን ያህል ኮሌጁ በቅቱ አሰልጣኝ (Instructor) ብሎ በውስጡ አቅፏቸው የነበሩ ምሁራን ብቃትም (ሀ) ተብሎ የተፈተሸበት ጊዜም ነበር፡፡ ረይሄንን በድፍረት ስፅፍ ከዚሁ ኮሌጅ የተመረቁ ተማሪዎችን እማኝ አድርጌም ለመጥቀስና ኃላፊነት የጐደለው ሂስ ተደርጐም እንዳይወሰድብኝ ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ሪ

የመጀመሪያዎቹም ባለ ዲግሪ የቴክኒክ መምህራን የተመረቁት ከ4 ዓመት በኋላ በ1989 (እ.ኤ.አ) ሲሆን እነዚህ መምህራንም በመንግሥት ወደተከፈቱት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው አንዲያሰለጥኑ የመንግሥት እቅድ ቢሆንም አብዛኞቹ በግልና በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት በመግባት ኑሯቸውን እየገፉ ይገኛሉ፡፡ (ይህ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው) በመሆኑም መንግሥት ወደ ከፈታቸው ተቋማት በመሄድ ያሰለጠኑ የነበሩት እነዚሁ ችግር ምክንያት በቀድሞው ናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኒክ መምሕራንን እጥረት ለመቅረፍ ኮሌጁ ሲከፈት በዲፕሎማ ደረጃ አንድ ዲፓርትመንት ይኸውም "Industrial Education" የሚባል ተከፍቶ ተማሪዎችን ማሰልጠን የጀመረ ቢሆንም ሰልጣኞቹ የሰለጠኑበት ዘርፍ ጠቅለል ባለ መልኩ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ለማሰልጠን የታሰበ ነበር፡፡ እነዚህ መምህራንም በመላው ሃገሪቱ ያሉትን ተቋማት በመቀላቀል የማሰልጠን ሥራ ቢጀምሩም ይህ ነው ተብሎ ለብቻው የሰለጠኑበት ዘርፍ ባለመኖሩ የመዘበራረቅና የመምታታት ችግር ተፈጥሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ከነዚህ ሠልጣኞች በፊት ለተመሳሳይ ተግባር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቲ.ቲ.ኢ (Technical Teachers Education) ዲፓርትመንት የቴክኒክ መምህራንን አሰለጥናለሁ ትበል እንጂ አብዛኞቹ መምህራን በአንዳንድ ኮምፕሬሄንሲቭ ሃይ ስኩል በተጓዳኝ ከሚሰጠው የቴክኒክ (የይስሙላ) ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች በመሄድ የስፖርት፣ የሒሳብ፣ የሳይንስ . . . መምህራን በመሆን እድሜያቸውን የፈጁ ቢሆኑም እና ከነበረው የአሰልጣኞች እጥረት የተነሳ በኢሕአዴግ መንግሥት ወደተቋቋሙት አዳዲስ የወረዳ ሲ.ዲ.ሲዎች በማስገባት ስልጠናውን አንዲሰጡ ቢደረግም ውጤታማ ነበሩ ለማለት የሚያስችል አልሆነም፡፡

የቀድሞ ናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን ቲ.ቲ.ኢ ዲፓርትመንት ጠቅልሎ ከወሰደም በኋላ ኮሌጁ ቀርፆት የነበረውን ካሪኩለም ተግባራዊ ለማድረግ ሲቸገርና በመምህራን የማሰልጠን ብቃት ላይ ከጅምሩ ዎች አመፅ ሲናጥ የነበረ መሆኑን ስናስተውለ በየቲ.ቪ.ቲ ተቋማቱ አሁን የሚገኙት አሰልጣኞች
ችግር መነሻው ከዚሁ ኮሌጅ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ረበዚህ አጋጣሚ የአሁኑን አዳማ ዩኒቨርሲቲ ብቃት እንዲህ ነው ብዬ ማለት ባለመቻሌ ይቅርታ እየጠየኩኝ ሌሎች ፀሃፍትን ለመጋበዝ እወዳለሁ፡፡ሪ

በመሠረቱ የማንኛውም የቴክኒክ ክሕሎት ቀጣይነት ባለው የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ስልጠናዎች ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያድግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ1994 (እ.ኤ.አ) ከነበረው አገር አቀፍ የአሰልጣኞች ስልጠና ወዲህ በአዲስ አበባና በጥቂት ክልሎች ከሚገኙት ሰልጣኞች በስተቀር ይሄንን ዓይነት እድል በተለይ ሰፊ የቆዳ ሽፋንና አብላጫው የቲ.ቪ.ቲ ተቋማት በሚገኝበት በኦሮሚያ ክልል በአሰልጣኞቹና በካሪኩለም ጋይድ አሰልጥን ተብለው በተቀመጡት ነጥቦች መካከል የተፈጠረው ስኪል ጋፕ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቲ.ቪ.ቲ ፖሊሲ በጂቲዜድ ድጋፍ እራሱን ከፈተሸና አዲስ ካሪኩለም ከመቅረፁ አንጻር በአሰልጣኞች ከህሎት ዙሪያ ያለው ችግር ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡

ሌላው ለዚህ የአሰልጣኞች ብቃት ማነስ እንደ ምክንያት የቆጠረው አብዛኞቹ አሰልጣኞች በኮሌጅ ወይንም በአሁኑ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው መምህር ለመሆን የማይፈልጉና ይልቁንም የትምህርት ማስረጃቸውን ይዘው ከወጡም በኋላ በተለያዩ ከማስተማር ስራ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ስራዎች የመስራት ፍላጎት ላይ ማዘንበላቸው ነው፡፡ ይሄንን እድል በማጣት ጥቂቶች በቲ.ቪ.ቲ ተቋማት ገብተው ሥራ ቢጀምሩም ከነዚህም ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው አሰልጣኞች 'Chalk & Talk' ከመሆን ያልዘለሉ እጆቻቸው የተግባር ስራን በመስራት እንዲቆሽሽ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ በአንፃሩ አንጸባራቂ የሚባልም ለውጥ ያመጡና የራሳቸውን ስራ በሙያቸው ቢፈጥሩም ለተማሪዎች ሞዴል የሚሆኑ ወጣት የቴክኒክ መምህራን አልፎ አልፎ አያጋጥሙም ማለት አይደለም፡፡

የቲ.ቪ.ቲ አሰልጣኞች ብቃት ማነስ ከኢትዮጵያ ገበሬ ጉያ የሚወጡትን ሰልጣኞች ብቃት ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል እና ውጤቱም ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት እያደረገች ላለው ግብግብ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ግልፅ ቢሆንም ሰሚ ካለ ችግሩን ለመቅረፍ ግን ጊዜው የረፈደ ነው የሚባል አለመሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

3. ሕብረተሰቡ ለዘርፉ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ

እስኪ አሁን ልጆቻቸውን ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወደሚልኩ ወላጆች አስተሳሰብና አመለካከት እንምጣ፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ (የኢ.ኤ.ዲ.ሪ) የትምህርት ፖሊሲ ኢሕአዴግ በተግባር ላይ ማዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ "ተቃዋሚ ፖለቲከኞች" ሲተችና ሲንቋሸሽ እንደነበረ (እስከ ምርጫ 97 ድረስ) ለኢሕአዴግም ሆነ ለሌላው እውነት ነው፡፡ ኢሕአዴግም ይሄንን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ "እውነት ነው፡፡ ኢሕአዴግም ይሄንን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ "እውነት ይመሰክራል" በሚለው እምነቱ የፖሊሲው (ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ ጠቀሜታ የተቀጣበትን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ከሕዝቡ ሊያጠፋና በምትኩ ሕዝቡ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ለቴክኒካና ሙያ ተቋማት ተማሪዎች በተለይ ደግሞ የሕብረተሰቡን ችግር ፈቺዎችና አዲስ ሃብት ፈጣሪዎች መሆን እንደ ፖሊዎ ክትባት የቤት ለቤት አልያም የሰው ለሰው ጸረ-ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሀቅን መሰረት በማድረግ ተግባራዊ ባለማድረጉ እስካሁን የብዙ ወላጆች አመለካከት ለዘርፉ ጥሩ ነው የሚባል አይደለም፡፡ አብላጫው ቁጥር የሚይዘው ወላጅ ልጁ የመሰናዶ ትምህርት ማለፊያ ፈተናውን ከወደቀ እና ወደ ቲ.ቪቲ ተቋማት መግባት እንደሚችል እንኳን ቢረዳ "ልጄ ዩኒቨርሲቲ ካልገባ ምኑን ሰው ይሆናል?" የሚል ፀለምተኛ አስተሳሰብ የያዙ በመሆናቸው የሰልጣኙ ስነ ልቦናም ከወላጆቹ ተፅዕኖ ውጪ ይሆናል ማለት ኢ-ሳይንሳዊነት ነው፡፡ በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ሌላው ትልቁ የሕብረተሰባችን ችግር ያለው ከዚህ በፊት በተለምዶ "የልምድ ቴክኒሻኖች" ተብለው ለሚጠሩት ወገኖች ትልቅ ዋጋ የሚሰጥና "የቴክኒክ ክሕሎት ከማሰልጠኛ ተቋማት መቅሰም ከንድፈ-ሀሳብ የሚዘል አይደለም" በሚል የቂል አባዜ ጥንወት ተጨማሪ እንቅፋት ሆኗል፡፡

በርግጥ ይሄንን የአስተሳሰብ ችግር ለመቋቋም ብሎም ለማጥፋት በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተማሪዎቻቸውን ክህሎት ሊያሳዩ የሚችሉበት እና ለሕብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበትን መድረክ በተጠናከረ መልኩ በተደጋጋሚ በመፍጠር (ለምሳሌ የተቋማት ሾው፣ የተማሪዎች ኤግዚቢሽን...) እና ለሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝነት ያለው ፖሊሲ መሆኑን በማሳወቅ እና በማስተማር መታገል የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አናሳ ክልሎች...?!

4. ተማሪዎቹ ስልጠናውን የመቀበል አቅማቸው አነስተኛ መሆን

አቅም የሚለውን ነገር ለመግለፅ የምሞክረው ተማሪው ወደ ተቋማቱ ይዞ የሚመጣው በተመለከተ ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም የቲ.ቪ.ቲ ሰልጣኝ ማለት ይቻላል ወደ መሰናዶ ትምህርት የሚያስገባውን ፈተና ማለፍ ያቃታቸው በመሆናቸው በአብዛኛው በተቋማቱ ውስጥ ገብተው የሚሰጣቸውን ስልጠና በቶሎ ለመቀበል ብሎም ተግባራዊ ለማድረግ ሲሳናቸው ይሰተዋላል፡፡ ተማሪዎች በተፈጥሮ ካላቸው ዝንባሌ እና ተሰጥኦ ይልቅ ፈተናን በመውደቅ ወደ ቲ.ቪ.ቲ ተቋማት እንዲገቡ መደረጉ በራሱ "መንግሥት የራሱን ፖሊሲ ወዴት እየመራው ነው?" የማያስብል ይመስላል፡፡ የተማሪዎችን ፍላጎትና ተሰጥኦ ባገናዘበ መልኩ ወደ ተቋማቱ በማስገባት የተለያዩ የፈጠራ ችሎታቸውን ተጠቅመው ውጤታማ በመሆን የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ መቀየር ሲቻል እስካሁን ሳይቻል ቀርቷል፡፡

5. በክረምት የሚሰጠው የስራ ላይ ስልጠና /Apparentship/ ይስሙላነት

ይህ የክረምት የሥራ ላይ ስልጠና በመሰረቱ ተማሪው ወደተለያዩ ድርጅቶች በመሄድ በተቋማቱ ያገኘውን መሰረታዊ ትምህርት በተግባር በማዋል ችሎታውን አዳብሮ ትምህርቱንም ሲያጠናቅቅ ብቃት ያለው ሰራተኛ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይሁንና ተቋማቱ ለተማሪዎቻቸው ድርጅቶችን ሲያፈላልጉ በጥናት ላይ ባለመደገፋቸውና ሰልጣኞቹን እዚያው ድርጅቶቹ ድረስ በመሄድ ያለባቸውን ችግርና ሂደቱን ስለማይከታተሉ በየክረምቱ የሚከወነው የተማሪዎች የሥራ ላይ ስልጠና እምብዛም ውጤታማ ሲሆን አይታይም፡፡ ይሄንን ችግር በተመለከተ አብዛኞቹ ሰልጣኞች የሚሰጡት አስተያየት "የድርጅቶቹ ባለቤቶች እኛ ሥራ እንድንለማመድ ሳይሆን እቃ እንድናቀብል ነው የሚፈልጉት" የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄንን ጉዳይ እንዲከታተል በሁሉም የመንግሥት ቲ.ቪ.ቲ ተቋማት ላይ ቢሮ ተከፍቶ ቮኬሽናል ጋይዳንስ ኤንድ ካውንስሊንግ ኦፊስ ቢኖርም በቢሮው ውስጥ የተቀመጡት ሰዎች ሹመትን እንደ "መብት" እንጂ "ሐላፊነት" መሆኑን በቅጡ የተረዱ ባለመሆናቸው ችግሩን እያወቁት ዝምታን ይመርጣሉ፡፡

ይህ የክረምት የሥራ ላይ ስልጠና እራሱን የቻለ መመዘኛ ቢኖረውም ባለድርጅቶቹ የየድርጅቶቹ ኃላፊዎች በነሲብ የሚሞሉት እንጂ ትክክለኛ ምዘና አለመሆኑ በራሱ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን መገመት አያዳግትም፡፡

ማጠቃለያ፡-

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች እና ምናልባትም እኔ ለጊዜው አነስተኛ ናቸው ብዬ የተውኳቸው ተደራርበው ሰልጣኞቹ ከተቋማቱ ከወጡ በኋላ ሥራ ፈላጊ እንጂ ስራ ፈጣሪ ሲሆኑ ባለመታየታቸው ሕብረተሰቡና ሰልጣኞቹ ለፖሊሲው ጤናማ አመላካከት እንዲያድርባቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በድህነት ላይ የሚደረገውን ርብርብ በጥቂቱም ቢሆን ወደ ኋላ ሊጎትት የሚቻል መሆኑ ለመንግሥት ግልፅ ይመስለኛል፡፡

መንግሥት በአዲስ አደረጃጀት (የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ) የሚል ቢያቋቁምም ወደ ገበሬው ወርደን ስንመለከት የስም ለውጥ ከመሆን ውጪ የተለየ ሥራ ሲሰራ አይታይም፡፡ ሌላው እጅግ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር በአብዛኛው በመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት (TVET Principal) አብዛኞቹ የፖለቲካ ሹመኞች እንጂ ከሙያው ጋር ንክኪ የሌላቸው በመሆናቸው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት እድገት በኢትዮጵያ ዘገምተኛ እንዲሆንና ወደፊትም የለውጥ እንቅፋት መሆናቸው የማይቀር መሆኑን የፌዴራል ኤጀንሲውም ሆነ ሌላ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ሊያስብበትና መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
Last Updated ( Sunday, 26 October 2008 )
 
< Prev   Next >