Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow አርባ ዓመታት-በአንድ ሆቴል
አርባ ዓመታት-በአንድ ሆቴል E-mail
Wednesday, 23 January 2008

አርባ ዓመት በሥራ ዓለምም ይሁን በህይወት የካበተ ልምድ የሚያገኙበት ነው፡፡ ለአቶ ኡሊ ኡትቻ ደግሞ ይህ ቁጥር በአንድ ቀጣሪ፣ በአንድ የሙያ ዘርፍ ያሳለፏቸውን ዓመታት የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ ኡሊ ተወልደው ያደጉት በላንጋኖ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነታቸው የዛሬ 46 ዓመት የተከፈተው ሆቴል በአቅራቢያው ቀዳሚው ነበርና ከትምህርት ቤት መልስ በሆቴሉ አካባቢ መገኘት ለዚያ አካባቢ ልጆች እንደተለመደው እሳቸውም በቀለ ሞላ ሆቴል ይውሉ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ በመራቁ ሳቢያ ትምህርታቸው ሲቋረጥ በለጋነታቸው ሆቴሉን በፅዳት ሠራተኝነት ተቀላቀሉ፡፡

<>

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ በላንጋኖ በቀለ ሞላ ሆቴሎች፣ ለሆቴሉ ዋና አስተናጋጅ (ተቆጣጣሪ) በሆቴሉ ለረጅም ዓመታት የሰሩ ሰው ባገኝ ለማነጋገር እንደምፈልግ ስገልፅ ፈቃደኛ ሆነው የመጡት አቶ ኡሊ በቆይታዬ ከዕድሜያቸው በማይመጣጠን ቅልጥፍናና ትህትና ያስተናገዱኝ ሰው ነበሩ፡፡

አቶ ኡሊ ላንጋኖ በበቀለ ሞላ ሆቴሎች የተቀጠሩት በ1961 ዓ.ም ነው፡፡ በፅዳት ሠራተኛነት ጀምረው ወደ ወጥ ቤት ተዛወሩ፡፡ በወጥ ቤቱ በረዳት ምግብ አብሳይነት የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ አስተናጋጅነት ተሸጋገሩ፡፡

በአስተናጋጅነቱ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ስላቸው ለማስታወስ መቸገራቸውን በሚገልፅ ቃና “ኡ”. እዚሁ ላይ ነው ያረጀሁት ማለት እችላለሁ” ነበር ያሉኝ፡፡

አርባ ዓመት በቆዩበት የሆቴል ሥራ በላንጋኖ ጀምረው አርባ ምንጭ፣ አዋሳ፣ ሞያሌ፣ ባሌ፣ ሻሸመኔ፣ ናዝሬት፣ ዝዋይ፣ መቂ ያሉት የሆቴሉን ቅርንጫፎች አዳርሰው ወደ ላንጋኖ ተመልሰዋል፡፡ ላንጋኖ ተመልሰው ከመጡ ደግሞ 10 ዓመታት አልፏቸዋል፡፡

የትኛው የሆቴሉን ቅርንጫፍ፣ የትኛውን የሥራዎን ጊዜ ጥሩ አድርገው ያስቡታል? ለሚለው ጥያቄ አቶ ኡሊ ሲመልሱ “ከላንጋኖ የበለጠ የለም፡፡ ጥሩ የእንግዳ፣ የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባቸው አርባ ምንጭና ናዝሬት ናቸው፡፡ በውጪ ዜጐች እንግድነት አርባ ምንጭና ላንጋኖ በሀገር ውስጥ እንግዳና ጥሩ ገቢ በማስገባት ናዝሬት ጥሩ ናቸው” ይላሉ፡፡

ኑሯቸው በላንጋኖ ሆቴል ቅጥር ግቢ ሲሆን ልጆቻቸው ግን ትልልቆቹ ናዝሬት፣ ታዳጊዎቹ አርሲ ነጌሌ እንደሚኖሩ አቶ ኡሊ ነግረውናል፡፡

አስተናጋጅነት ከሰዎች የተለያየ ባህርይ አንፃር አስቸጋሪ አይሆንም ለሚለው ጥያቄ “ከልምድ አንፃር ምንም አያስቸግረኝም፡፡ ትልቁ ነገር ሰውን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆን ነው፡፡ ሆቴሉ ብዙ ሆቴሎች ባልተስፋፉበት የተቋቋመ ስለሆነ እንግዶች እንደቤታቸው ያዩታል፣ ብዙዎቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቤተሰብጋ እየመጡ ያዩት፣ የሚያውቁት ናቸው፡፡ እኛም እንደቤታቸው እንዲሰማቸው ተቀብለን በሥርዓት እናስተናግዳቸዋለን” ብለዋል፡፡

በቀለ ሞላ ሆቴሎች ሲሠሩ የተማሩት በትህትናና በፈገግታ እንግዶቻቸውን እንደቤተሰብ መያዝ እንዳለባቸው ነው፡፡ እንደ አቶ ኡሊ ገለፃ በዘመኑ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት የሚማሩት ወጣቶች ባላቸው ዕውቀት ልምድ ሊጨምሩበትና ለእንግዶች ማድረግ የሚገባቸውን ልምድ ካላቸው ሊማሩ ይገባል፡፡

አቶ ኡሊ በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይመጡ የነበሩ (በህፃንነታቸው) ትልልቆች ሆነው ከሀገር ውጪ የወጡ ሳይቀሩ መጥተው “በዚህ ዓመተ ምህረት እናውቅሀለን” እንደሚሏቸው፣ ይህም በመልካም መስተንግዶ የመሸኘታቸው ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ተገልጋዮች ከላንጋኖ ሆቴል ሠራተኞች ጋር ያላቸው ቤተሰባዊነት መጠን ገፍቶ አንዳንዶች ልጆቻቸውን ክረምቱን በሆቴሉ ተቀምጠው እንዲያሳልፉ በአደራ ሰጥተው እስከመሄድ እንደሚደርሱ አቶ ኡሊ አጫውተውናል፡፡

አቶ ኡሊና ሌሎች ቀደም ሲል የነበሩት አስተናጋጆች የሚመጡትንና ከእነርሱ በኋላ የተቀጠሩትን ሁሉ ያለማምዳሉ፣ ያሰለጥናሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት እንግዶች በማይበዙባቸው ቀናት ነው፡፡ ሆኖም አቶ ኡሊ ሙያ ከዘመን ጋር የሚያድግ በመሆኑ ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ አስፈላጊ መሆኑን ያምኑበታል፡፡

“እንግዶች ከሚበሉትና ከሚጠጡት በላይ አቀባበል ያስደስታቸዋል” የሚሉት አቶ ኡሊ በልጅነታቸው አፄ ኃ/ሥላሴ ደጋግመው ሲመጡ የማስተናገዱን ዕድል ባያገኙም የማየት ዕድል ግን እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡

አቶ ኡሊ ላንጋኖ እንደሚሉት ላንጋኖ እንዳሁኑ የሁሉም ሰው መዝናኛ ከመሆኑ በፊት በተለይ በአፄውና በደርግ ዘመን ሊዝናኑ የሚመጡት ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ሕዝቡ አሁን ተምሮ፣ ገንዘብ አግኝቶ እንደልብ መምጣት ሳይጀምር በተለይ በአፄው ዘመን ነጮች እና የመኳንንት ቤተሰቦች ይስተናገዱ ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያምና ባለስልጣናቱም ይመጡ ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን የሚመጡ ባለስልጣናት ደግሞ አጀብ የማይወዱ፣ ማንነታቸውም እንዲታወቅ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ ሠራተኞቹ ባለስልጣናቱን ስለሚያውቋቸው ይለዩዋቸዋል አንዳንዴም ከሆቴሉ አስተዳዳሪዎች እንደሚመጡ ይነገራቸዋል፡፡

ከሐሙስ እስከ እሑድ ባለው ጊዜ የሥራ ቀን፣ እንግዶች የሚበዙበት በመሆኑ አቶ ኡሊና ሌሎችም ሠራተኞች መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የቀሩትን ቀናት በሽፍት ይሠራሉ፡፡ በበዓላት የሚሠሩ ሲሆን በትርፍ ጊዜና በበዓላት ክፍያዎች አሏቸው፡፡ ሆኖም እንደለቅሶ ያሉ ማኅበራዊ ህይወቶች በሥራው ባህሪ አለመታሰባቸው ቅር ቢላቸውም 40 ዓመት የሠሩበት በቀለ ሞላ ሆቴሎች ድርጅት የቤት ያህል መሆኑንና ለዓመታት ያቆያቸውም ይኸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

አቶ ኡሊ በወጣት የሆቴሉ ሠራተኞችና በነባሮቹ መካከል ልዩነት እንዳለ ሲገልፁ የእነርሱን ትህትናና ታዛዥነት ሲያዩ ወጣቶቹ “ባርነት” እንደሚሉት፣ ተግተው በመሥራቱም በኩል ያን ያህል እንዳልሆኑ ይገልፃሉ፡፡ በከተሞች አካባቢ የሚታዩ አስተናጋጆች ችግርም እንግዶችን አለማክበርና ሥራቸው በአግባቡ አለማከናወን መሆኑ ያሳዝናቸዋል፡፡ “ጥሩ ቢሠሩ ለራሳቸው ነው፡፡ ዕድገት ሊያገኙ ከእንግዶች ጋርም መልካም ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል” ይላሉ፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ

 
< Prev   Next >