|
Wednesday, 23 January 2008 |
|
/ክቡር ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት” በሚል ወርክሾፕ እየተሳተፉ ነው፡፡ ውይይቱ እጅግ የተሟሟቀ ነው፡፡ ምሳ እየበሉም ውይይቱ አላቆመም/ - ክቡር ሚኒስትር መቸስ በምሳ ሰዓት አትጨቅጭቀኝ ካላሉኝና ፣ኢኮኖሚስት የሚመለከታቸውን ጠይቅ፣ ብለው ካልዘጉኝ፣ ኢሕአዴግ የማይገነዘበው ብዙ ነገር አለ፡፡ - ለምሳሌ ምን? - ክቡር ሚኒስትር የተሻለ ፖሊሲ ቢኖር ኖሮ የተመዘገበው ውጤት እጥፍ ድርብ ይሆን እንደነበር ይገነዘባል? - በፖሊሲ ላይ ችግር የለም፡፡ እንደ እናንተ አይነቱ ሰው ከማውራት ይልቅ አርፎ ቢሰራ ግን ውጤቱ እጥፍ ድርብ ይሆን እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ - ይኸው ነዋ ችግሩ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኸው ነዋ፤ ስትል አልገባኝም፡፡ - የፖሊሲ ስህተት የለም ነው የምትሉት? - አዎን ስህተት የለም፤ እንላለን፡፡ - ያሳዝናል” በጣም ያሳዝናል” - እስቲ የተሳሳተ ፖሊሲ ነው የምትለውን ንገረንና እኛም ስህተቱን አይተን እንዘን፡፡ - ለምሳሌ የእርሻ ማበረታቻን እንይ፡፡ አበባና ሌላ ኤክስፖርት ለሚያደርግ መንግሥት በባንክ ብድር ወዘተ. ለማበረታቻ ይሰጣል፡፡ በምግብ ራሳችን እንድንችል ለሚያደርግ እርሻ ግን ማበረታቻ አይሰጥም፡፡ ስንዴና ጤፍ ለሚያመርት ባለሃብት ማበረታቻ እንሰጣለን የሚል ፖሊሲ ለምን አይኖርም? - አቶ እከሌ የሚባል ባለሃብት ላይ አይደለም፤ ትኩረታችን አርሶ አደሩ ላይ ነው፡፡ - አርሶ አደሩም ይበረታታ፤ ግን ባለሃብቱም ቢበረታታ ምን አለበት? ምን ጉዳት አለ? - ይህ ጉዳት አለ ልልህ አልችልም፡፡ - ታዲያ ክቡር ሚኒስትር፣ ጉዳት ከሌለና ጥቅም ካለው ፖሊሲው ለምን አይሻሻልም? - እንዳልኩህ እኔ ኢኮኖሚው በቀጥታ የሚመለከተኝ ሚኒስትር አይደለሁም፡፡ ነገር ግን አልተሻሻለም፤ ብዬ አልወቅስም፡፡ - - ምክንያቱም ጥቅም ቢኖርበት መንግሥት ያሻሽለው ነበር፡፡ - ታዲያ ለምን አያሻሽለውም? - አንድ ችግር ቢኖርበት ነዋ፡፡ - የሚገርም መልስ ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ትክክለኛ መልስ ነው፡፡ መንግሥታችን ወይም ኢሕአዴግ በፖሊሲ ካላወጣው አንድ የታየው ችግር አለ ማለት ነው፡፡ - በሌላ ዓለም ተቀባይነት ያገኘ ፖሊሲም በአገራችን ተቀባይነት አጥቷል፡፡ - ምን ለምሳሌ? - ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር፣ በሌላ ዓለም ሁሉ አዲስ መኪና ሲመጣ ቀረጡ ዝቅ ያለ ነው፡፡ አሮጌ መኪና ላይ ቀረጡ ከፍ ያለ ነው፡፡ - አንተ አሁን ችግርህ አዲስ መኪና ለምን አላስገባሁም ነው፡፡ የእኛ ችግር የውጭ ምንዛሬ እንዳይባክን መጠንቀቅ ነው፡፡ ለአዲስ መኪና የውጭ ምንዛሬ ከምናባክን አሮጌ ይነዳ ነው፡፡ - የውጭ ምንዛሬ የሚያባክነውኮ አዲስ መኪና አይደለም፤ አሮጌ መኪና ነው የሚያባክነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እንዴት እባክህ? - አሮጌ መኪና ነዳጅ ይጨርሳል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ያባክናል፤ ማለት ነው፡፡ አሮጌ መኪና መለዋወጫ ይጠይቃል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ባከነ፤ ማለት ነው፡፡ አሮጌ መኪና ቶሎ ይጣላል የውጭ ምንዛሬ ባከነ፤ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊሲያችን የውጭ ምንዛሬ የሚያባክን እንጅ የሚቆጥብ አይደለም፡፡ አይመስልዎትም ክቡር ሚኒስትር? - ሊመስለኝ ይችላል፤ ግን ስህተት ነው ለማለት አልችልም፡፡ ለምን? - መንግሥታችን አንድ ነገር ባይታየው አያደርገውማ፡፡ - እንዴት ክቡር ሚኒስትር? - እኔ መንግሥት ሊታየው - ክቡር ሚኒስትር፣ ኢሕአዴግ ራሱ ታይቶትኮ ከአስር ዓመት በፊት ጅማ ባካሄደው ጉባኤ የተወሰነ የቴሌ ስራ ፕራይቬታይዝድ ይሆናል ብሎ በጉባኤው ወስኖ ነበር፡፡ - እናስ? - በኋላ ግን ስራ ላይ አልዋለም፡፡ ይውላል ማለት ነዋ፤ አትቸኩል፡፡ - እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ከአስር ዓመት በላይ ተግባር ላይ አልዋለም፣ኮ፡፡ - ለምን ነበር የወሰነው? - የአገሪቱን ዋና ስራ መንግሥት ይሸከመዋል፡፡ ግለሰብ ለትርፍ ሲስገበገብ ላይሰራው ይችላል፡፡ ከዋናው ስራ ውጭ ያለው ግን ግለሰብ ቢሳተፍበትም፣ ይጠናከራል፣ ውድድር አገልግሎት ያስብላል፡፡ ስለዚህ ይፈቀዳል ነበር ያለው፡፡ - ይህ ትክክለኛ አባባል ነው፤ ለምን ትቃወመዋለህ? - አልተቃወምኩትም ክቡር ሚኒስትር እደግፈዋለሁ፡፡ ተግባር ላይ ይዋል ነው የምለው፡፡ ለምን ተግባር ላይ አልዋለም ነው ጥያቄየ፡፡ - ተግባር ላይ አለመዋሉ አንድ ዓይነት ጥቅም ቢኖረው ነዋ” - ምን ዓይነት ጥቅም ክቡር ሚኒስትር? - እኔ ያልታየኝ ኢሕአዴግ ያየው ነገር ይኖራል፡፡ - አልገባኝም፡፡ - በተግባር አለማዋሉ ጥቅም ባይኖረው ኖሮ ይውል ነበር፡፡ ካልዋለ እኔ ያልታየኝ ጉዳይ ኢሕአዴግ ታይቶታል ማለት ነው፡፡ - በቃ ይኸው ነው መልስዎ ክቡር ሚኒስትር? - አዎን፡፡ አንድ ነገር ባይኖር ኢሕአዴግ ዝም አይልም፡፡ - ሲያወጣው አይታየውም ማለት ነው፤ ክቡር ሚኒስትር? - እንደ አዋጁ ነው፡፡ - የብሮድካስቲንግ ሕግ ብሎ መንግሥት ከስምንት ዓመት በፊት ያወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያን የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ማቋቋም ይችላሉ የሚል ነበር፡፡ - አዎን፡፡ - ግን ክቡር ሚኒስትር፣ እስካሁን ድረስ ቴሌቪዥን የግል አይፈቀድም፤ አዋጁ ስራ ላይ አልዋለም፡፡ - - ለምን? - ኢሕአዴግ አንድ ነገር ቢታየው ነዋ፡፡ ሲያወጣው ነበር ማለት ነው? - ሲያወጣው ጥቅሙ ታየው፣ አሁን ዝም ሲል ጉዳቱ ታየው፡፡ - ሆሆሆ”. ይች ናት ጨዋታ፡፡ - የከተማ ቦታ ለማግኘት በወጣው የመሬት ሊዝ አዋጅ ጨረታና ድርድር ተቀባይነት ያለው አሰራር ነበር፡፡ - አዎን በርካታ ባለሃብቶች በጨረታም በድርድርም ብዙ መሬት አግኝተው አልምተው የለም ወይ? - አልምተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡ በዚህ ልማት አገር ተጠቀመ ወይስ ተጎዳ? - ተጠቀመ እንጂ ምን ጥያቄ አለው፡፡ - አሁን ደግሞ የራሱን አዋጅ ራሱ ቀይሮ በድርድር መሬት አይሰጥም የሚል መመሪያ ወጥቷል፡፡ ትክክል ነኝ ክቡር ሚኒስትር? - ትክክል ነህ ወጥቷል፡፡ - ያለውን አዋጅ ራሱ ቀየረው ማለት ነው፡፡ ያውም እርስዎ ጠቃሚ አዋጅ ነበር ብለው ያመኑበትን፡፡ - አዎን፡፡ - ትክክለኛ ፖሊሲን በተሳሳተ ፖሊሲ መቀየር ትክክል ነው? - ይኸውልህ ኢሕአዴግ አንድ ነገር ቢታየው ነዋ” - ተሳስተናል፣ እንሳሳታለን፤ ነገር አይወጣችሁም ማለት ነው፡፡ - መቼና ምን ተሳሳትንና? - ተው ስንላችሁ ቴሌን አንዴ ለኖኪያ፣ አንዴ ለዜድ ቲ.ኢ እየሰጣችሁ ብልሽትሽቱን አወጣችሁት አይደለም፡፡ - ታዲያ ለተለያየ ድርጅት መስጠት ብልሀት እንጂ ስህተት አይደለም፡፡ - ብልህነቱ የት ላይ ነው ክቡር ሚኒስትር? - እንግሊዞች “እንቁላልህን ሁሉ በአንድ ቅርጫት አታስቀምጥ” ይላሉ፡፡ ቅርጫቱ ሲወድቅ ሁሉም እንቁላል ታጣለህ ማለታቸው ነው፡፡ - እና ይህ የኢሕአዴግ እምነት ነው፡፡ - እምነቱ ባይሆን ኖሮማ ለሁሉም ባልደረሳቸው ነበር፡፡ - ታዲያ ምነው አርኪሰንንም ኖኪያንም አስወጥቶ ለአንድ የቻይና ኩባንያ ብቻ ሰጠ፡፡ - አልገባኝም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር፣ ታዲያ ለምን አሁን “ሁሉንም እንቁላል በአንድ ቅርጫት ውስጥ አስቀምጠው” ነው ወይስ የቻይናውያን ተረት ከእንግሊዞቹ ለየት ያለ ነው፡፡ - አልገባኝም፣ አሁንም፡፡ - አሁን የኢትዮጵያ ቴሌ ስራ በቻይና አንድ ኩባንያ እጅ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለምን ለተለያዩ ድርጅቶች አይሰጥም? - ዘርዝሬ ልመልስልህ አልችልም ሙያዬ አይደለም፡፡ በርግጠኝነት ግን ለአንድ የቻይና ኩባንያ አሁን የያዘበትን ምክንያት አጠቃላይ መልስ ልሰጥህ እችላለሁ፡፡ - ምን የሚል መልስ፤ ክቡር ሚኒስትር? - አንድ ጠቃሚ ነገር ቢያይበት ነዋ” - በምሳ ሰዓት ጨቅጨቅኩዎ ፤ ክቡር ሚኒስትር? - ጥሩ ነው እንጂ ይልቅንስ ሳይታወቀኝ ብዙ በላሁ፡፡ /ከምሳ በኋላም ውይይቱ ቀጠለና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥተው የመዝጊያ ንግግርና መሪ ቃል ሰጡ፡፡ በምሳ ሰዓት አብረው የነበሩት ሰዎች በማታው የመዝጊያ ኮክቴል ግብዣ ላይም እያወሩ ነው/ - ክቡር ሚኒስትር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በሚገባ አዳምጠዋል? - ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አዳመጡ ወይ ብለህ ሚኒስትርን ትጠይቃለህ እንዴ? - እንዴት አልጠይቅም፤ ክቡር ሚኒስትር? - የሚኒስትር ዋናው ስራ እኮ ጠቅላይ ሚኒስትርን ማዳመጥ ነው፡፡ - ገባዎት ማለት ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር የማይገባው ሚኒስትርነት አይሾምም፡፡ - አንድ ጥቅም ቢያይበትስ ብዬ ነዋ፡፡ - አትቀልድ፡፡ - ይኸውልዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርስዎም ያሉት የነበረውን ሁሉ ተቃውመውታል፡፡ - ተቃወሙት እባክህ? - በርካታ ፖሊሲዎች አሉ፤ እንቀይራቸዋለን” ብለውኮ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ አላዳመጡም እንዴ? - አዳምጫለሁ በሚገባ ተረድቸዋለሁም፡፡ - እናስ እርስዎ አልተሳሳትኩም ሲሉኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳስተናል ብለዋል፡፡ - እና? - ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን እንደዛ አሉ? - አንድ የታያቸው ነገር ቢኖር ነዋ፡፡ - ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ምንድነው የሚገርመው? - እንደ እርስዎ ዓይነት ነው የኢኮኖሚና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆኖ መሾሙ ግራ ይገባኛል፡ - ጥሩ ሰው አይደለህም እያልከኝ ነው? - ጥሩ ሰው የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደውም እንደ ሰው እርስዎ ጥሩ ሰው ነዎት፡፡ - ታዲያ ችግሩ ምንድነው? - ክቡር ሚኒስትር፣ ችግሩማ ጥሩ ሰው መሆን ማለት ብቁ ሰው መሆን ማለት አይደለም፡፡ - እና እኔ ብቁ ሚኒስትር አይደለሁም፡፡ - እንደኔ ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እንዲህ ዓይነት ሚኒስትር አትፈልግም፡፡ - ታዲያ ከቦታየ አስነሳኛ፤ ከሚኒስትርነት አንስቼዋለሁ ብለህ አውጅ፡፡ - እኔ የማወጅ ስልጣን የለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የሚያደርጉት ይመስለኛል፡፡ - ለሳቸውም ለአገሬም ታማኝ አገልጋይ ነኝ፤ በዛ በኩል አታስብ፡፡ - ብቃት የሌለው ታማኝ ብለው ያወርዱዎታል፡፡ - እኔ ከሚኒስትርነት እንድነሳ ትፈልጋለህ? - አዎን በርስዎ ቦታ ሌላ ብቁ ሰው እንዲሾም እፈልጋለሁ፡፡ - ከልብ ነው የምትናገረው? - በጣም እጅግ ከልብ ነው፡፡ ቀረብ ብዬ ከሚኒስትር ጋር አውርቼ አላውቅም፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ - አሁን አዝነሃል፤ የኔን መውረድ ስትሰማ ትደሰታለህ? - መደሰት አለመደሰት ሳይሆን የምለው ነገር ግን ይኖረኛል፡፡ - ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር እገሌን አባረሩ፤ የሚል ዜና ብትሰማ ምን ትላለህ? - እርስዎ የሚሉትን እላለሁ፡፡ - ምን? - “አንድ ነገር ቢታያቸው ነዋ”“ |