Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow “የምንደራደረው በህወሓት ለማስገምገም...
“የምንደራደረው በህወሓት ለማስገምገም... Print E-mail
Wednesday, 23 January 2008
የአግአዚ ኦኘሬሽን ፊልም አዘጋጆች
“ህወሓትን ለማስደሰት አይደለም የሠራነው”
የኦኘሬሽን አግኣዚ ፊልም አዘጋጆች

በቅርቡ በያኔው ኰማንደር ሃየሎም አርአያ የሚመራ የህወሓት ጦር ጓድ በ1978 ዓ.ም. በመቀሌ እስር ቤት የደርግ እስረኞችን በ15 ደቂቃ ውስጥ ያስፈታበትን ታሪክ በመስራት ላይ ያሉ ባለሙያዎች ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በጥላሁን ታፈረ የሚመራው ቡድን ያዘጋጀው “ኦኘሬሽን አግኣዚ” በኢድናሞል ሲኒማ ተመርቋል፡፡ በሰሎሞን አስመላሽና በፍፁም አስመላሽ በሚመራው ቡድን የተዘጋጀው “አግአዚ ኦኘሬሽን” ደግሞ የካቲት 11 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ይመረቃል፡፡ የተወዛገቡበትን ምክንያትና ልዩነታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

የድርሰት አጀማመር

ከአግኣዚ ኦኘሬሽን (የካቲት 11 የሚመረቀው) ደራሲዎች አንዱ የሆነው ሃይለ አያልነህ እንደገለፀልን በ1994 ዓ.ም. አካባቢ መቀሌ ውስጥ በፍሪላንሰር ጋዜጠኝነት እየሠራ ባለበት ወቅት በክልሉ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ጋዜጣ ላይ እንዲፅፈው ከህወሓት ቢሮ ዶክመንት ተሰጠው፡፡ ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎችን ኢንተርቪው በማድረግ በተከታታይ በጋዜጣው ፃፈው፡፡ ከአንባቢዎችም ወደመፅሐፍና ፊልምነት እንዲለወጥ አስተያየት ተሰጠው፡፡ በዚያ ወቅት ተጨማሪ መረጃ ሲያፈላልልግ ከታሳሪዎች አንዱ ከነበረው ብርሃኑ አባዲ ጋር ተገናኝተው ለሁለት መፃፍ ጀመሩ፡፡ የመፅሐፋቸውን (አግኣዚ በሚል በትግርኛ የተፃፈ) ካሜራ ሬዲ  አዘጋጅተው በነበረበት ወቅት አቶ ፀጋዬ አለማየሁ (አሁን የተመረቀው ፊልም ኘሮዲዩሰር ናቸው) ፊልም መሥራት ስለሚፈልጉ አብረው እንዲሰሩ ጥያቄ አቀረቡላቸወ፡፡ ስክሪኘት አዘጋጅተው ሰጡ፡፡

የኦኘሬሽን አግኣዚ (የተመረቀው ፊልም) ደራሲ አቶ ኪዳኔ ይላቅ በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1984 ዓ.ም. ተመርቀው እንደወጡ በትግራይ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ተመድበው መሥራት በጀመሩበት ወቅት ፊልም እንዲሰራ ስለኦኘሬሽኑ እንዲያጠኑ ይታዘዛሉ፡፡ ወደ አዋሳ በመሄድም ከጀኔራል ሃየሎም አርአያ ጋር በአካል እንዲነጋገሩ በቢሮው ጥያቄ መሠረት ህወሓት ሄሊኮኘተር መድቦላቸው ከሄዱ በኋላ ከሃየሎም ጋር ለሦስት ወር ቃለመጠይቅ አድርገው መመለሳቸውን ይገልፃሉ፡፡ በኦኘሬሽኑ ውስጥም ተሳታፊ የነበሩ ኮማንደሮችን በማነጋገርና የመቀሌ ወህኒ ቤትንም በማጥናት ስክሪኘት ፃፉ፡፡ ስክሪኘቱን ለመሥራት ወደ ሜጋ ቢመሩም ፊልም የተሟሟቀበት ጊዜ ባለመሆኑ መጓተቱን ደራሲው ይገልፃሉ፡፡ ከትግራይ ባህልና ማስታወቂያ ተዛውረው በሜጋ ሲሰሩ ቆይተው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሲቀጠሩ በ1997 ዓ.ም. አቶ ፀጋዬ አለማየሁና አቶ ጥላሁን ታፈረ ፊልሙን መሥራት እንደሚፈልጉ አነጋገሯቸውና በህጋዊ መንገድ እንደሸጡላቸው አስረድተዋል፡፡

የውዝግብ መነሻ

የአግአዚ ኦኘሬሽን (ያልተመረቀው) ደራሲ ሃይለ አያልነህ እንደሚለው አቶ ፀጋዬ አለማየሁ ሌላ ስክሪኘት እንዳገኙ (የኪዳኔ ይላቅን ድርሰት መሆኑ ነው) ከሁለቱ ተወዳድሮ የተሻለውን መሥራት እንደሚፈልጉ ይገልፁላቸዋል፡፡ ኰሚቴዎች ተውጣጥተው የተሻለ የተባለውን የመምረጥ ሥራ ይከናወናል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ኃይለ እንደሚሉት ኰሚቴዎቹ ለዚያኛው ቡድን አዳልተዋል፡፡ “እውነተኛ ታሪኩን ሙሉ ለሙሉ የሚገልፀው የእኛ ድርሰት ነው የሚል ቅሬታ ብናሰማም ሰሚ አላገኘንም፡፡ ሰሚ ያጣውን ቅሬታ ይዘን ስንጓዝ ከሰሎሞን አስመላሽና ፍፁም አስመላሽ ጋር አብረን ልንሰራ ተስማማን” ያሉት አቶ ኃይለ፣ የውዝግቡ መነሻ የኰሚቴው ገለልተኛ አለመሆን በተለይም ለሁለቱ ወገን ደራሲዎች ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ፀጋዬ አለማየሁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኦኘሬሽን አግኣዚ ፊልም ዳይሬክተርና ኘሮዲዩሰር ጥላሁን ታፈረ እንደሚለው ኰሚቴው መረጣውን ያካሄደው በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ነው፡፡ ኰሚቴው የተውጣጣውም በሁለቱ ወገኖች እንደሆነ፣ በአንደኛው ወገን ራሱ ጥላሁን ታፈረና ኪሮስ ኃይለስላሴ በሌላኛው ወገን (በነኃይለ አቅራቢነት) ህቡር ገብረኪዳንና ሙሉጌታ ገሰሰ ሲሆኑ ስክሪኘቱ የማን እንደሆነ እንዳይታወቅ ስማቸው ተቀድዶ ለግምገማ መቅረቡን ያስረዳል፡፡ አቶ ጥላሁን እንደሚለው ታሪኩን የሚገልፅ፣ ለፊልም ሥራ የሚመች፣ በተቻለ መጠን ያልተጋነኑ ግን የፊልምን ሥራ የሚያጣፍጡ የፈጠራ ታሪኮች ያሉበት፣ ውሱን ገፀ ባህሪያት በውስጡ የያዘ በሚል መስፈርት ምርጫው ተካሄደና የኪዳኔ ይላቅ ተመረጠ፡፡ በዚያ ወቅት እነ ብርሃኑ አባዲና ኃይለ አያልነህ ቅሬታ አቀረቡ መግባባት ባለመቻላችን ተለያየን ሲል ገልጿል፡፡

የፊልም አጀመማር

የአግኣዚ ኦኘሬሽን አዘጋጆች ሰሎሞን አስመላሽና ፍፁም አስመላሽ እንደገለፁት ከነኃይለ አያልነህና ብርሃኑ አባዲ ጋር የተስማሙት እውነተኛውን ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ካላቸው ምኞች ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች ተጨማሪ ለህጋዊነት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አሟልተው ከአዕምሮአዊ ንብረት ፅህፈት ቤትና ከህወሓት ቢሮ የፈቃድ ወረቀት ይዘው ከውጭ ባለሙያዎችንና መሳሪያዎችን በማስመጣት ከ3 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት መንቀሳቀስ መጀመራቸውንና ህወሓት በተመሠረተበት ታሪካዊ ዕለት የካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም. ለማስመረቅ ተዘጋጅተው እየጠበቁ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡

አቶ ጥላሁን ታፈረ በበኩላቸው በ1997 ዓ.ም. ስክሪኘቱን ካገኙ በኋላ ከሚመለከተው አካል (እንደሱ ገለፃ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ባህልና ማስታወቂያ) የፈቃድ ወረቀት ተቀብሎ ወደ ሥራው ገባ፡፡ ከትግራይ ክልል መንግሥትም ፈቃድ መውሰዱን የሚገልፀው ጥላሁን ከህወሓት ባለሥልጣናት ግን የቃል ፈቃድ ከማግኘቱ በቀር የፅሁፍ ፈቃድ እንደሌለው ገልጿል፡፡

የውዝግቡ መካረር

በሸራተን ለማስመረቅ አስፈላጊውን ነገር ከጨረስኩ በኋላ በነሰለሞን አስመላሽና ፍፁም አስመላሽ በተፃፈ ደብዳቤ እንዳይመረቅ ተከለከልኩ የሚለው ጥላሁን ኢድናሞል ሲኒማ ጭምር ደብዳቤው ገብቶ ከብዙ መጉላላት በኋላ እንደተመረቀ ያስረዳል፡፡ እሱ እንደሚለው “እኛ ነን ህጋዊ እሱ አይደለም ብትተባበሩ እንከሳችኋለን” የሚሉበት ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡

እነ ሰለሞን አስመላሽ በበኩላቸው ሸራተን የሚሰሩ ሰዎች  “ማነው ህጋዊ” የሚል ጥያቄ ባቀረቡላቸው መሠረት ህጋዊ ሆነው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚያስረዳና የፓተንት ራይት ባለቤት መሆናቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ አስገቡ እንጂ እንከሳለን አላልንም ብለዋል፡፡ ሸራተንም ሆነ ኢድናሞል የሚተዳደሩበት የራሳቸው ህግ አላቸው፤ በመሆኑም የከለከሉት ውዝግብ ውስጥ ባለ ሥራ ጣልቃ መግባት አንፈልግም በሚል እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም ሲሉም ይገልፃሉ፡፡

ድርድር

በቅርቡ በኢትዮፒካሊንክ ውስጥአዋቂ የሬዲዮ ኘሮግራም (ኤፍ.ኤም. 98.1) “ተደራደሩ” የሚል ዘገባ ተሰራጭቷል፡፡ እነ ሰሎሞን አስመላሽ እንደሚያስረዱት ምንም የተደረገ ድርድር የለም፡፡ በእርግጥ በመቀሌ ብርሃኑ አባዲ /አንደኛው የእነሱ ደራሲ/ እና ጥላሁን ታፈረን የትግራይ ማስታወቂያ ቢሮና ህወሓት ኃላፊዎች አነጋግረዋቸዋል፡፡ “መነጋገር መደራደር አይደለም” ብለዋል እነ ሰለሞን፡፡

ጥላሁን ታፈረ በበኩሉ ጤናማ ያልሆነውና አፍራሽ ውዝግቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድርድር ላይ ደርሰናል በማለት ገልጿል፡፡

መሠረታዊ ልዩነት

እነ ሰሎሞን አስመላሽና ፍፁም አስመላሽ እንደሚያምኑት ታሪኩ የህወሓትና የትግራይ ህዝብ ታሪክ ነው፡፡ በመሆኑም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ገምግሞት “አዎ ትክክል” ነው ማለት አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ መገምገም አለበት፡፡ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት እውነተኛ ታሪክ እንጂ የሚሠሩት ቢዝነስ ላይ ስላላተኮሩ ብሎም ታሪኩ የህወሃት በመሆኑ ሊፈቅድና ህጋዊ ማስረጃ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የአንድን ሰው የህይወት ታሪክ ለመሥራት ባለታሪኩ ሊፈቅድ ይገባል የሚል አስረጅም አቅርበዋል፡፡

ጥላሁን እንደሚያምነው ደግሞ ታሪኩ በአንድ ወቅት በህወሓት ቢፈፀምም ታሪክነቱ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ማንም ሰው ታሪኩን ለመሥራት የህወሓትን ፈቃድ መጠየቅ ግዴታ አይደለም፡፡ እንደጥላሁን ገለፃ የሚሠራው ለቢዝነስ ነው፡፡ “በመሆኑም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ጥሩ የፊልም ጥበብ የታየበት ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ ህወሓት በሥራው ተደሰተም አልተደሰተም ለገበያ አቀርበዋለሁ፡፡ ምክንያቱም የሠራሁት ለገበያ እንጂ ህወሓትን ለማስደሰት አይደለም” ብሏል፡፡ በመሆኑም ከህወሓት ወረቀት መያዝ አስፈላጊ መሆኑን አያምንበትም፡፡

እነ ሰለሞን የሚያነሱት ሌላኛው መሠረታዊ ልዩነት ደግሞ የህጋዊነት ጉዳይ ነው፡፡ እኛ የታለንት ራይት ከአዕምሮአዊ ንብረት ፅህፈት ቤት፣ የህጋዊነት ደብዳቤ ከህወሓት ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ እኛ ባወጣነው ህጋዊነትና የፓተንት ራይት ማንም ሊሠራ አይገባም፡፡ ይህ ማለት ታሪኩን መከልከል ሳይሆን እኛ እየሰራንበት ባለው የፊልም አሠራር መንገድ የባለቤትነት መብት ያለን እኛ ነን የሚል ነጥብ አንስተዋል፡፡ ከመፅሃፋችን (አግኣዚ ማለት ነው) ላይ የተወሰደ አንግልም አለ የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡

ጥላሁን ታፈረ እንዳስረዳው፣ የአዕምሮአዊ ንብረት ፅህፈት ቤትን የምጠይቀው ፊልሙን ሠርቼ ከጨረስኩ በኋላ ይህንን ፊልም የሠራሁት እኔ ነኝ ብዬ እንጂ ሳልሠራ ልሰራ ነውና የባለቤትነት መብት ይሰጠኝ ማለት ህጋዊ ነው ብዬ ስላላመንኩ አልጠየኩም፡፡ አሁን ግን እጠይቃለሁ ብሏል፡፡ እሱ እንደሚለው ማንኛውም ሰው ፊልም የመሥራት መብቱን ተጠቅሞ እንደሚሠራው ሰርቻለሁ፤ በአዲሰ አበባ ባህልና ማስታወቂያም አስገምግሜ ይህ ሕገ መንግሥቱን የማይነካ ስለመሆኑ ማስረጃ አለኝ በማለት ያስረዳል፡፡ አንግሉ ተመሳሳይ ነው ለተባለው መፅሃፉ የታተመው እኔ የፊልም ስክሪኘቱን ከገዛሁት በኋላ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ወቅታዊ አቋም

እነሰለሞን አስመላሽም ሆኑ ጥላሁን ለመግባባትና በሠላማዊ መንገድ ለመቀጠል ፍላጐቱ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእነሰለሞን በኩል ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ እነሱ እንደነገሩን ለህወሓትና ለትግራይ ህዝብ የታሪኩን እውነተኛ ገላጭነት እስካላስገመገመ ድረስ አንደራደርም፤ የምንደራደረው ለማስገምገም ፈቃደኛ ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው የተዛባ ታሪክ ሳይሆን እውነተኛውን ታሪክ ይዞ ለመውጣት እንጂ ለቢዝነስ አንራወጥም የሚል ነው፡፡

ጥላሁን ታፈረ በበኩሉ ኤዲት ከተደረገ በኋላ የህወሓት ሰዎች እንዲገመግሙልኝ ቁጭ ብዬ የማይበት ምንም ምክንያት የለኝም፡፡ እኔ ገምግሜ ጥሩ ነው ያልኩትን ይዤ ወጥቻለሁ ብሏል፡፡

የሁለቱን ፊልሞች የታሪክ ገላጭነትና ኪነ ጥበባዊ ፋይዳ ሁለተኛው ፊልም (የነሰለሞን አስመላሽ አግኣዚ ኦኘሬሽን) ከተመረቀ በኋላ ተመልካች የሚፈርደው ይሆናል፡፡

በደመቀ ከበደ

 
< Prev   Next >