Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Jan 08th
Home arrow Sections arrow ዋጋቸውን የማይመጥኑ አገልግሎት ሰጪዎች
ዋጋቸውን የማይመጥኑ አገልግሎት ሰጪዎች E-mail
Sunday, 02 November 2008

በናታን ዳዊት

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ብዙ እንከኖችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በተለይ በከተማ አካባቢ የምንኖር ሰዎች ውሏችን ውጭ ከሆነ በተለያዩ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎች ገንዘባችንን ከፍለን የምናገኘው መስተንግዶ ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ያሳየናል፡፡

በተለያዩ መዝናኛ ሥፍራዎች ለምንፈልገው አገልግሎት የምንጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑ ሳያንስ ክፍያውና የሚሰጠንን አገልግሎት አይመጣጠንም፡፡ ምግብ አብስለው በሚያቀርቡ የመዝናኛ ሥፍራዎች የምግብ ጥራት ደረጃና መጠን ሳይቀር ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡

የአንዳንዶቹ ወጥ ቤት የጥራት ደረጃቸውም ሆነ ምግብ የሚያበስሉትን ሰዎች ልብስ ስንመለከት የመመገብ ሃሞታችንን ፈጽሞ ሊያጠፋው ይችላል፡፡

ከታች እስከ ላይ የለበሱት ልብስ ጽዳት፣ የሚያበስሉበት እቃ ንጽህና ምግብ የሚያዘጋጁበት ሥፍራ ጭምር መቆሸሽ እነዚህን ሰዎች የሚቆጣጠረው ማነው? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በግል ከሦስት ቀናት በፊት የገጠመኝን አንድ ነገር ላካፍላችሁ፡፡ ቦሌ ድልድይ እየተባለ ከሚጠራውና ታክሲዎች እንደመነሻና መድረሻ ከሚጠቀሙበት መናኸሪያ ፊት ለፊት ከሚገኝና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ሬስቶራንትና ካፌ ውስጥ ምሣ ልበላ ገባሁ፡፡

ምሣ ስላልበላሁ ምሣ አልኩ እንጂ ሰዓቱ ወደ 12 ተቃርቦ ነበር፡፡ ወደ መመገቢያ ክፍሉ ስገባ የሥራ ባልደረቦቼን አየሁና ከእነርሱ ጋር ጠረጴዛ ተጋራሁ፡፡

በጣም ርቦኝ ስለነበር አስተናጋጁን ጠርቼ የሚበላ ነገር እንዳላቸው ጠየቅሁት፡፡ ሜኑ ሳይሰጠኝ ያሉትን ምግቦች በቃሉ ዘረዘረልኝ፡፡ እኔም አንዱን ነግሬው ያዘዝኩት ምግብ እስኪመጣ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ወግ ቀጠልኩ፡፡

የታዘዘው ምግብ ትዕግስት አስጨራሽ ከሆነ ቆይታ በኋላ መጣ፡፡ የመጣው ምግብ ግን በትክክል “ጥብስ ፍርፍር” የሚል ስያሜ የሚያሰጠው አልነበረም፡፡ ያለማጋነን “የጾም ፍርፍር” ሊባል ይችላል፡፡ ሠሃኑን ከሞላው ከዚህ ምግብ ውስጥ በትክክል ቆጥሬ ያገኘሁት ስድስት፣ በስስት የተከተፉ የሥጋ አንኳሮችን ብቻ ነበር፡፡

በነገሩ ተበሳጭቼ “ይሄ ነገር ጥብስ ፍርፍር ነው ወይ?” ብዬ አስተናጋጁን ጠርቼ ጠየቅኩ፡፡ የተሰጠኝ መልስ “አዎ” የሚል ነበር፡፡

“ይህ ጥብስ ፍርፍር አይደለም፡፡ አስተካክሎ ይምጣልኝ፡፡ ስጋ የሌለው ጥብስ ፍርፍር የለም ብዬ በትክክል አሰርቶ እንዲያመጣልኝ መለስኩት፡፡

ከአፍታ ቆይታ በኋላ “ይኸው ተስተካክሏል አለኝ” ተስተካክሏል ያሰኘው በላዩ ላይ ቀይ ወጥ ፈሶበት መምጣቱ ነበር፡፡ ይበልጥ ብናደድም እርቦኝ ስለነበር አንድ ሁለት ጎርሼ አላስኬድ ሲለኝ ተውኩት፡፡

አስተናጋጁን ጠርቼ ሂሳብ ጠየቅኩት፡፡ “አይበሉም እንዴ?” ቢልም መልስ ሳልሰጥ ዋጋውን እንዲነግረኝ ለመንኩት፡፡ “አስራ ስምንት ብር ብቻ” የተባልኩትን ከፍዬ የቤቱን ኃላፊ እንዲያገናኘኝ ጠየቅኩት፡፡ በቅርብ ርቀት ከሚገኝ የካሸሪ ቦታ ላይ የተቀመጠን ሰው ጠቆመኝ፡፡

ወደዚያው ሄጄ የቤቱ ኃላፊ ስለመሆኑ ስጠይቀው አለመሆኑንና ለጊዜው ኃላፊ የሌለው መሆኑን ገለፀልኝ፡፡ ምን ገጥሞኝ እንደሆነም ስለጠየቀኝ የሆነውን ሁሉ ነገርኩት፡፡

የገጠመኝን ሁሉ ብዘረዝርም ጆሮ ዳባ አይነት ምላሽ አተረፍኩ፡፡ “ምንም ነገር ማድረግ አንችልም” ተባልኩና ረሃቤ ላይ ብስጭት ጨምሬለት ወጣሁ፡፡

አንድ ጥብስ ፍርፍር 18 ብር በሚሸጥበት ቤት የሚሰጠው መስተንግዶና የሚጠየቀው ክፍያ የሚጣጣም አይደለም፡፡

ምግቡም ቢሆን በትክክል ጥራቱን ያልጠበቀና በሽንኩርትና ቲማቲም ቁርጥራጭ የተሞላ በመሆኑ ያቀረብኩትን አቤቱታ ሊቀበል የሚችል ኃላፊና ለእርምት ዝግጁ የሆነ አስተናጋጅ አላገኘሁም፡፡ እንዲህ አይነት የምግብ አቀራረብና አዘገጃጀት ይዘው የአገልግሎት ተጠቃሚውን ሊያዳምጡ የሚችሉ ኃላፊዎች የሌሉባቸውና የመሳሰሉት ችግሮች ያሉባቸው ተመሳሳይ ሬስቶራንቶች በከተማችን ሞልተዋል፡፡

ይህ ደግሞ አንድ አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋመ ድርጅት ፈጽሞ ሊጠበቅ የማይገባ ጉዳይ ቢሆንም የየዕለት ገጠመኛችን ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡ ውጫቸውን በተብለጭላጭ መብራቶች አሽቆጥቁጠው መመገቢያ ጠረጴዛና ወንበሮቻቸው ግን ደንበኞቻቸውን የሚያስከፉና የሚሰጣችውንም አስተያየት ለማረም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳቢያ አገልግሎት ፈልጎ የሚመጣውን ደንበኛ ስሜት እየጎዱና ተዉ የሚላቸው አካል እየጠፋ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

እንዲህ አይነት መገልገያ ተቋም የሚከፍቱ ሰዎች ድርጅታቸውን ለመቆጣጠር ባይችሉ በኃላፊነት የሚያስተዳድር ሠራተኛ መቅጠር እንዳለባቸው የሚያውቁ ቢሆንም በምንቸገረኝነት የሚሰሩት ሥራ የራሳቸውንም ቢዝነስ እንደሚጎዳ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ሸማቹ ኀብረተሰብም ቢሆን ዋጋውን የሚመጥን አገልግሎት የማይሰጡ መሰል ተቋማትን ደንበኝነቱን በማቋረጥ ጭምር አስተማሪ ቅጣት ሊጥልባቸው ይገባል እላለሁ፡፡

 
< Prev   Next >