Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow “በቢዝነስ መንገድ ብቻ ካሰብን አገሪቱን...
“በቢዝነስ መንገድ ብቻ ካሰብን አገሪቱን... E-mail
Wednesday, 23 January 2008

“በቢዝነስ መንገድ ብቻ ካሰብን አገሪቱን ትተናታል ማለት ነው”
አቶ ፀጋዬ ከበደ

አቶ ፀጋዬ ከበደ የኢትዮጵያ ኤዱኩዌሽን ሰፖርት አሶሴሽን ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ኤድኩዌሽናል ሪሶርስ ሴንተር ሲሰተም አናሊስት እና አቶ ዮናስ መንገሻ የኢትዮጵያ ኢዲኩዌሽን ሰፖርት አሶሴሽን ምክትል ሊቀመንበርና የሪሶርስ ሴንተሩ የሶፍትዌር ኢንጂነር ናቸው፡፡  በሙያቸው ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሶሴሽኑ ትምህርትን በምን መልኩ ይደግፋል?

አቶ ፀጋዬ፡- ኢትዮጵያን ኢዱኩዌሽን ሰፖርት አሶሴሽን የተቋቋመው የሌላው ኅብረተሰቡን በተለያዩ መስኮች ለማገልገል ነው፡፡ አንደኛው እቅዱ ኢትዮጵያን ኢዱኩዌሽን ሪሶርስ ሴንተር ይባላል፡፡ ለኅብረተሰቡ ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ ወይም አሥር ሲደመር አንድ፣ አስር ሲደመር ሁለት ከመሰናዶ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርትን በስፋት ማዳረስ ነው፡፡ በስፋት ለማዳረስ ትኩረት የተደረገው በትምህርት ጥራት ላይ ነው፡፡ በአገሪቱ 13 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተዋል፡፡ መከፈታቸው ጥሩ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ፣ የግድ መሳተፍ ስላለበት ከእኛ የሚጠበቀው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃን ማዳረስ ይሆናል፡፡

ቴክኖሎጂውም ሆነ ቴክኖሎጂውን የሚያውቅ ሰው አለ፡፡ እነዚህ ሁለቱን እያገናኘን ለኅብረተሰቡ ጥቅም መስጠት ይሆናል፡፡

አቶ ዮናስ፡- ጥራት ያለው የትምህርት ሪሶርስ ካለ ጥራት ያለው ትምህርት አለ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ናቸው፡፡ አንድ ሰው  ሥራ የሚፈለገውን መረጃ በሚፈለገው ጊዜ፣ ቦታና ሰዓት የሚያገኝ ከሆነ ሥራውን በጥራት ይሰራል፡፡ ኅብረተሰቡ የትምህርት ሪሶርሶችን በሚፈለገው መጠን ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህን የትምህርት ሪሶርስ ሰብስበን ለኅብረተሰቡ ከየት ማድረስ አለብን የሚለውን ተወያይተንበት የኢትዮጵያ ኢዱኬሽናል ሪሶርስ ማዕከልን ነደፍን፡፡ በአገሪቱ ያሉት ትምህርትና ምርምሮችን፣ መግለጫዎችን ይሰበስባል፡፡ ያቀናጃል፡፡ ያስቀምጣል፡፡ ለኅብረተሰቡም ይለቃል፡፡

ማዕከሉ እንደ አንድ የትምህርትና የምርምር ቦታ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ሰዎች ትምህርታዊና ምርምራዊ መረጃዎችን የሚያገኙበት፣ ምርምር የሚያደርጉበት፣ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተው የሚወያዩበት፣ ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ጋር የሃሳብ ልውውጥ የሚያደርጉበት ይሆናል፡፡

ሙከራ ማድረጊያም ይሆናል፡፡ አንድ ተማሪ ቤተ ሙከራ (ላቦራቶሪ) በሌለበት፣ ቤተሙከራ እንዳለ አድርጎ መሥራት የሚችልበት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከትምህርት ውጭ ደግሞ የኅብረተሰቡ ችግሮች መወያያም ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆኑ ትምህርት ቤቶች ቢስፋፉም የትምህርት ጥራት ከማነጋገር አልቦዘነም፡፡ በእናንተ ቴክኖሎጂ የትምህርት ጥራት እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?

አቶ ዮናስ፡- የትምህርት ጥራት ቀጥታ ግንኙነት ያለው ጥራት ካለው የትምህርት መረጃ ጋር ነው፡፡ የእኛ ቴክኖሎጂ ጥራት ያላቸው የትምህርት መረጃዎች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ በአገሪቱ የተሰበሰቡ እውቀቶች አሉ፡፡ እነዚህ እውቀቶች አንድ ላይ ሆነው ኅብረተሰቡ በጋራ እንዲጠቀም ማድረግ ነው፡፡ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን በጊዜና በቦታ ሳይወሰኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርትን ጥራት ተግባራዊ ለማድረግ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም፣ መሠረተ ልማት፣ ምሁራን፣ ቴክኖሎጂ ወዘተ. መሟላት አለባቸው፡፡ እነዚህን ማሟላት እንችላለን? የትምህርት ፖሊሲው እንደገና ወደ ኋላ ሊመለስ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ከዚህ ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

አቶ ፀጋዬ፡- የትምህርት ጥራት ለማምጣት ኅብረተሰቡ ራሴን መለወጥ አለብኝ የሚል እምነት ሊያሳድር ይገባል፡፡ መረጃዎችን እንዴት አግኝቼ አገሬን እንዴት ልጠቅም እችላለሁ ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡

ምሁራን በጣም ያስፈልጉናል፡፡ በአንድና በሁለት ሰው ጥራት እናመጣለን አይባልም፡፡ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ገጠሪቱ ኢትዮጵያ መታሰብ አለበት፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉት መረጃ በወረቀት ላይ የታተመ ኮፒ ይደርሳቸዋል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ በሲዲ ወይም በተለያየ መልክ ሊደርሳቸው ይችላል፡፡

ቴክኖሎጂውን በበጎ ዓይን አይተን ከሰራንበት ጥሩ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ በትክክል የማንጠቀምበት ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪካ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የምትገባው፡፡

የትምህርት ፖሊሲው ወደ ኋላ ቢመለስም እኛ ያዘጋጀነው ቴክኖሎጂ ችግር የለውም፡፡ ወደ ኋላ መመለስም ይቻላል፡፡ በሚፈለገው ሥርዓተ ትምህርት መሰረት መለወጥ ይቻላል፡፡ ዳይናሚክ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአሶሴሽናችሁ በምን መልኩ ነው ድጋፍ የሚያደርገው?

አቶ ፀጋዬ፡- በድረ ገጽ ለኅብረተሰቡ በሚፈለገው ቦታ መረጃ እንዲደርሰው ማድረግ ነው፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚመጣው መረጃ ለኅብረተሰቡ ይዳረሳል፡፡

ይሄ ሲስተም በሚሰራበት ሰዓት ብዙ ምሁራን ያስፈልጉናል፡፡ በተለያየ መንገድ የሚረዱን ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የፊዚክስ ትምህርትን ብንወስድ አንድ ወይም ሁለት ሰው አይደለም የሚያዘጋጀው፡፡ በሁለትና በሦስት ሰው ተዘጋጅቶ ለብዙ ሚሊዮን ሰው ሊዳረስ ይችላል፡፡ የእኛ እምነት ግን ይሄ አይደለም፡፡ አንድ መጽሐፍ የሚዘጋጀው ቢያንስ ቢያንስ በሁለት መቶ ሰው ነው፡፡ ፊዚክሱን በክፍል በክፍል ብንከፋፍለው መግቢያውን የሚያዘጋጁ አምስት ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡

አምስቱ ሰዎች መረጃ የሚሰጡት የግድ ቢሮ መጥተው አይደለም፡፡ እዚያው ባሉበት የተጠቃሚዎች ስምና ፓስወርዳቸወ (ዩዘር ኔምና ፓስወርድ) ስላለ በ”ኦን ላየን” ለዲፓርትመንቱ ይላካል፡፡ እያንዳንዱ ዲፓርትመንት ኃላፊነት አለበት፡፡ ሌላ ሰው እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ ሐብቶችን አበልጽጎ በጋራ መጠቀም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ምን ደረጃ ላይ ደርሳችኋል?

አቶ ፀጋዬ፡- በቅርቡ ሲስተሙን በመሰናዶ፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና በሙያ አካባቢ ለመልቀቅ ተዘጋጅተናል፡፡ አርባ ሺህ ላየን ኦፍ ኮደ ጽፈናል፡፡ የአገር ቅርስ እስከሆነ ድረስ እኛ ብቻ ሳንሆን ሁላችንም መሳተፍ ይኖርብናል፡፡

እኛ ቴክኖሎጂውን እናውቀዋለን፡፡ የሚያስፈልገው መረጃ ነው፡፡ ሕክምና ለማካሄድ ሐኪም ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊውን መረጃ ከኅብረተሰቡ ካገኘን ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ አይቸግርም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ፕሮጀክቶች ይታቀዳሉ፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ ሳይሆኑ መክነው ይቀራሉ፡፡ ይህም ፕሮጀክት ተመሳሳይ ዕድል እንዳያጋጥመው ምን ዋስትና አለው?

አቶ ፀጋዬ፡- ምርምሩን ስንሰራ መረጃውን የሰበሰብነው ከትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ሦስት ዓመት ተኩል ወስዶብናል፡፡ ስንጀምር ከወጣቱ ምን ይጠበቃል ከሚል ነው፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር የምንጋራቸው አሉ፡፡

ብዙ ምሁራን አሉ፡፡ እስከ ፕሮፌሰር ደረጃ አብረን እየሰራን ነው፡፡ የሥራው ፈጣሪ ብንሆንም የኅብረተሰቡ ጉዳይ ስለሆነ ለትርፍ ተብሎ አልተጀመረም፡፡ የተለያዩ ምሁራን ሰብስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምሁራኑ በሙያቸው ለማገልገል ፈቃደኞች ናቸው?

አቶ ፀጋዬ፡- በነፃ ለማገልገል ዝግጁ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም በቂ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች ገምግመውታል፡፡ ኅብረተሰቡ ያገለግላል፣ ጥሩ ዜጋ ሊያፈራ ይችላል ተብሎ እስከታመነበት ድረስ እንሄድበታለን፡፡

አቶ ዮናስ፡- ሐብቶችን ከዓለም መካፈል አልቻልንም፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖረን እንኳ መጠቀም አልቻልንም፡፡ የዓለም ሐብትን መጠቀም የቻሉት ያደጉት አገሮች ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ መካፈል የምንችለው ዕውቀትና መረጃ ነው፡፡ ዓለም አንድ መንደር ሆናለች በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ ዋናው መረጃ ነው፡፡ መረጃና ዕውቀት እንዳንካፈል የሚያደርገን እነርሱ የደረሱበት የቴክኖሎጂ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ስንደርስ እነሱ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ይጀምራሉ፡፡ ስለሆነም የእነሱን እውቀት ወደ እኛ ማፍሰስ (መካፈል) አልቻልንም፡፡

መካፈል አለብን፡፡ አንድ ኅብረተሰብ ዕውቀት አለው ማለት የሚሰራውን ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ያደጉት አገሮች በሄዱበት አቅጣጫ መሄድ አለብን፡፡ ይሄ ብዙ ጊዜ ሊፈጅብን ይችላል፡፡ ስለሆነም ቶሎ የሚያደርሰን አቋራጭ መቀየስ አለብን፡፡ አቋራጩ የትምህርት ሐብቶችን በጋራ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምሳሌነት ያነሳችሁት የፊዚክስ መጽሐፍ ለማዘጋጀት በርካታ ምሁራን መሳተፍ እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ አሁን በጥቂት የሰው ኃይል ውጤታማ ሥራ ከሚለው መርህ ጋር አይጋጭም?

አቶ ፀጋዬ፡- ይኼ የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ በተለይ ሚዲያው ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለት መቶ ሰዎችን ለማቀናጀት ችግር አይሆንም?

አቶ ፀጋዬ፡- ማቀናጀት ይቻላል፡፡ ትልቁ ሥራችን ኅብረተሰቡን ማሳወቅ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ማደግ ይፈልጋል፡፡ ካልተረዳዳ ግን ማደግ አይቻልም፡፡ ኅብረተሰቡ መነሳሳት አለበት፡፡

አንድ ሰው ክልል ላይ ሆኖ ምርምር መሥራት ይፈልጋል፡፡ ምርምር ለማካሄድ የግድ አዲስ አበባ መምጣት አለበት፡፡ አዲስ አበባ የሚመጣበት ምክንያት ቤተመጽሐፍትና የተለያዩ ተቋማት ስላሉ ነው፡፡  በዚህ ሲስተም ግን እዚያው ክልል ሆኖ ጊዜውን ሳያባክን፣ ከቤተሰቡ ሳይለይ፣ ሥራውን ሳይተው ምርምር ማካሄድ ይችላል፡፡

ስለ ሕክምና ሊመራመር ይፈለግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት ምርምር ከተደረገበት ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ በእኛው ሲስተም የተሰሩት ምርምሮች “ኦን ላየን” ይቀመጣሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከተቀመጡ የተሰሩና ያልተሰሩ ምርምሮች በቀላሉ ይለያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ተመራማሪዎች የተሰሩ የምርምር ውጤቶች “ኦን ላየን” ሲቀመጡ እንዳይዘረፉ የኮፒራይት መብት ይጠበቃል?

አቶ ፀጋዬ፡- መደባበቅ ለእኛ የሚጠቅመን አይደለም፡፡ በአገራችን ሐብት ላይ ነው የምንሰራው፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ያለ ትምህርት በተመሳሳይ አዳማ ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይኖራል፡፡ ተማሪው ምርምር ሊያካሂድ ይፈልጋል፡፡ መረጃው ስለማይኖረው የተሰራውን መልሶ ይሰራል፡፡ ይህ ድግግሞሽ እንዳይኖር ምርምሩን አንድ ማዕከላዊ ቦታ መቀመጥ አለበት፡፡ በአሁን አያያዝ በምን ርዕስ የት ምርምር እንደተካሄደ አይታወቅም፡፡

ሪፖርተር፡- የጀመራችሁት ሲስተም በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ መሠረተ ልማቱ አለ?

አቶ ፀጋዬ፡- ቴክኖሎጂው ጅምር ላይ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ጥናቶቻችን እንዳየነው ከሆነ ጥሩ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ዌብ ሳይት ኢንተርኔት ኮኔክሽን ስለሆነ ዕድሉ አለ፡፡ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለኅብረተሰቡ ሁሉ በአንድ ጊዜ ማዳረስ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ዕድሉ ባለበት ቦታ ላይ አሥር ሰው መለወጥ መቻል ቀላል አይደለም፡፡ በየሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም እያየን ነው፡፡ ጥሩ ጅምር አለ፡፡

እኛ የምናደርገው ኅብረተሰቡ እንዲገነዘብ ነው፡፡ እድገት ከታሰበ በምን ዓይነት መንገድ ማምለጥ እንዳለብን ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ በሁሉም ቦታ የለም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ኮኔክሽን አለ፡፡ ውስን ተማሪዎች መጠቀም ይችላሉ፡፡ ሌሎችም በግል የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ወደፊት እያደገ ራሱ ሲስተሙ ውስጥ ያስገባል፡፡
 
አቶ ዮናስ፡- የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲስፋፋ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ዩ.ኤን. ዲ. ፒ. የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽንም የሚያደርገው ጥረት አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ኢንተርኔት ኮኔክትድ ናቸው፡፡ ኢንተርኔት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ቢኖርም በአጭር  የሚቀረፍ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የእኛ ፕሮጀክት ከመሰናዶ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ደረጃ የምርምር ተቋማትን እንዲያቅፍ የተደረገው፡፡

ችግር ያለው በመሰናዶ ትምህርት ላይ ነው፡፡ በተለይ ገጠር ያሉ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች በሐርድ ኮፒ ወይም በወረቀት መልክ ተደርጎ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ የትምህርት መሣሪያዎች አቅራቢ፣ ከማተሚያ ቤቶችና ከሌሎችም ጋር በመስማማት እንዲደርስ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በቅድሚያ ግን እስኪ መረጃው ይኑረን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው በነፃ ነው የምናስተላልፈው ስትሉ እስከምን ድረስ ነው ነፃ የሚሆነው?

አቶ ፀጋዬ፡- እኛ እንደ ድልድይ አገልግለን ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ ካገኘና መልዕክቱ አጥጋቢ ከሆነ በኋላ ለሚመለከተው አካል ማስረከብ እንፈልጋለን፡፡ ሌላ ምርምር መሥራት ስላለብን ትምህርት ሚኒስቴር ወይም የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር እንዲወጡት ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱን በነፃ ለመስጠት እንዴት ወሰናችሁ?

አቶ ፀጋዬ፡- የኅሊና ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ ትልቁ እርካታ የኅብረተሰቡ መጠቀም ነው፡፡ ሕዝቡ ሲያድግ፣ ሲለወጥ አብረን እናድጋለን፣ አብረን እንለወጣለን፡፡ ፕላዝማ ላይ ለቢዝነስ በሚያመች መልኩ የሰሩ አሉ፡፡ በቢዝነስ መንገድ ብቻ ካሰብን አገሪቱ ትተናታል ማለት ነው፡፡

አቶ ዮናስ፡- ይህንን ስንሰራ የማንም የውጭ አገር ሰው አንፈልግም፡፡ የአገራችን ኅብረተሰብ ዕውቀቱ፣ ፍላጎቱ ካለው በተቻለ መጠን ከመንግስት የሚደጎምበት መንገድ ካለ ሲስተሙ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግስትን ማገዝ ክፍተትን መሙላት ነው ሥራቸው፡፡

ፈረንጆች ጥራት ያለው ትምህርት ሊሰሩልን አይችሉም፡፡ ልስራ ካሉም በገንዘብ ነው፡፡ መንግስት፣ ባለሃብትና በአገሬ ያገባኛል የሚል ሰው እንዲሄድበት ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ አዲስ ነው ብላችኋል፡፡ ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ለማመን እንዴት መሞከር አለብን?

አቶ ዮናስ፡- አዲሱን እቅድ እንደ ስትራቴጂም ሊታይ ይችላል፡፡ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ለኅብረተሰቡ አማራጭ ነው የሚሰጠው፡፡ ሙከራ  አያስፈልግም፡፡ አስፈላጊነቱ የታወቀ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው የለም ማለት አይደለም፡፡ ቴክኖሎጂው የምንጠቀመው ኦፕን ሶርስ በሆኑ ሶፍትዌሮች ኤችፒ፣ አፓቼ የተባሉ ዌብ ሰርቨሮች ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዋቶ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ጫናው ይመጣብናል፡፡ እኛ የምንለው አቅጣጫው (ሜተዱ) የለም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮምፒዩተርና የመሳሰሉት የተፈጠሩት ብዙ ሰዎች የሚሰሩትን በጥቂቶች ለመስራት ነው፡፡ የእናንተ ፕሮጀክት ደግሞ የሰው ኃይል እያበዛ ነው፤

አቶ ፀጋዬ፡- ቴክኖሎጂ የሚፈልገው ውሱን ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ማየት ያለብን ጉዳይ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል ነው? ባለሙያዎች ምን ያህል ናቸው? ምን ያህል ምሁራን አሉ? ጥራት ያለው ትምህርት እንዴት ሊተላለፍ ይችላል?

እያንዳንዱ ሰው ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ ያለበት ነገር አለ፡፡ ወደፊት ከዚህ በላaይ ሕዝብ ይኖራል፡፡ ከዚህ አንፃር ግራፉ ሲታይ በጣም ትንሽ ነው፡፡ የሚሳተፈው ብዙ ሰው አይደለም፡፡ ሁለት መቶ ሰዎች አንድ ፊዚክስ ላይ ቢሰሩ የሚጠቀሙት ግን ከ40ሺህ በላይ ይሆናሉ፡፡ እኛ የምንፈልገው ጥራት ያለው ነገር ለኅብረተሰቡ  ማስቀመጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶችን ያካታትታል?

አቶ ዮናስ፡- በትምህርት ሚኒስቴር የሚታወቁ የትምህርት ዓይነቶች ሁሉ ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ የምርምር ሥራዎችን ጭምር፡፡

 
< Prev   Next >