| አልኮልና እርግዝና |
|
| Sunday, 02 November 2008 | |
|
በእርግዝና ወቅት በመጠኑ አልኮል መጠጣት በፅንስ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንደማያስከትል፣ ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የወጣ አንድ ጥናትን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ጥናቱ እናቶቻቸው በእርግዝና ጊዜአቸው መጠነኛ አልኮል መጠጦችን ይወስዱ በነበሩ አሥራ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ህፃናት (የሦስት ዓመት) ላይ ነው የተደረገው፡፡ በሌላ በኩል በጤና ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ብዙ ተቋማት ነፍሰጡር እናቶች ወይም ለመፀነስ ጥረት እያደረጉ ያሉ ሴቶች ፈፅሞ አልኮል እንዳይወስዱ ያስጠነቅቃሉ፡፡ በተመሳሳይ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጥናት ይፋ መሆንን ተከትሎ ኤክስፐርቶች ጥናቱ ምናልባትም ሴቶችን በተለይም ለነፍሰጡሮች ትክክለኛ ያልሆነ ዋስትና እየሰጠ እንዳይሆን ስጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጥናቱ እንደሚያመለክተው፣ ነፍሰጡር ሴቶች መጠጣት ያለባቸው በሳምንት አንድ ወይም ሁለት መለኪያ አልኮል መጠጥ ብቻ ነው፡፡ መስከርም የለባቸውም፡፡ ከፍተኛ የአልኮል መጠን በእርግዝና ላይ የሚያስከትለው ችግር በተለያየ መልኩ በግልፅ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶች አልኮል እንዳይወስዱ የሚከለክሉ ፖሊሲዎችን ለማውጣት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ባለበት ወቅት የዚህ ዓይነቱ ጥናት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ እንደሚችል የጥናቱ መሪ ዶክተር ያቮን ኬሊ ተናግረዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ የአልኮል መጠን መውሰድ በአብዛኛው የማህፀን ፅንስን መድከም ያለመቻልን፣ ያለጊዜ መውለድ ወይም በሽል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚወለዱ ጥቂት ህፃናት በእድገታቸውና በአእምሮአቸው አድማስ ላይ አልኮሉ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪዎች ነፍሰጡር ሴቶች ዘጠነኛ ወራቸው ከገባ በኋላ ምን ያህል አልኮል ይወስዱ እንደነበር የጠየቁ ሲሆን አንዳንዶቹ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት መለኪያ አልኮል መጠጦችን እንደሚወስዱ ሲናገሩ በሳምንት ሦስትና ስድስት መለኪያ የአልኮል መጠጦችን ይወስዱ እንደነበር የተናገሩ ሴቶቹም አሉ፡፡ ከተጠየቁት ሴቶች በመነሳት በሳምንት ሰባት መለኪያ የአልኮል መጠጥ በአንድ ሳምንት ውስጥ መውሰድ ወይም በአንድ አጋጣሚ ስድስት መለኪያ የአልኮል መጠጥ መውሰድ አደገኛ መሆኑን አጥኚዎቹ አመልክተዋል፡፡ 63 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ሙሉ ለሙሉ የአልኮል መጠጦችን እንደማይወስዱ፣ 28 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመጠኑ አልኮል መጠጦችን እንደሚወስዱ፣ 6 በመቶ የሚሆኑት መደበኛ አልኮል ወሳጆች መሆናቸውንና 2 በመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ መጠን አልኮል እንደሚወስዱ ጥናቱ አስታውቋል፡፡ በጥናቱ በተካተቱት የሦስት ዓመት ህፃናት ላይ ባህሪያቸውንና ነገሮችን የመረዳት ችሎታቸውን በሚመለከት በተደረገው ጥናት እናቶቻቸው በእርግዝና ወቅት መጠነኛ አልኮል ይወስዱ የነበሩ 40 በመቶ የሚሆኑ ወንድ ልጆች የባህሪ መዛባት እድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እናቶቻቸው በእርግዝና ወቅት መጠነኛ አልኮል ይወስዱ የነበሩ ህፃናት የቃላት ትርጓሜ የማወቅ ችሎታቸው፣ ቀለም፣ ቅርፅ፣ ፊደልና ቁጥር የመለየት ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የነፍሰጡሮች መጠነኛ አልኮል መውሰድ በፅንስ ላይ አደጋ እንደማያስከትል የሚያትተውንና በኢንተርናሽናል ጆርናል ኦፍ ኢፒዲሞሎጂ ላይ የታተመው ጥናትን በሚመለከት የጥናቱ ግኝት ነፍሰጡር ሴቶችን በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይመራቸው ስጋት እንዳላቸው የእንግሊዝ ሜዲካል ማህበር የበላይ ዶ/ር ቬቪየን ናታንሰን ተናግረዋል፡፡ “ጥናታችን የደረሰበት በእርግዝና ወቅት መጠነኛ አልኮል በልጆች ባህሪና ነገሮችን የመረዳት ችሎታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የለውም፡፡ ለዚህ በከፊል ምክንያቱ መጠነኛ አልኮል የሚወስዱ እናቶች ፈፅሞ ከማይወስዱት ማህበራዊ ትስስራቸው የተሻለ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በእርግዝናቸው ወቅት መጠነኛ አልኮል የሚወስዱ እናቶች በጣም ዘና ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለልጆቻቸው ባህሪና ነገሮችን የመረዳት ችሎታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው” በማለት ተናግረዋል የጥናቱ መሪ ዶክተር ያቮን ኬሊ፡፡ በተቃራኒው የእንግሊዟ ሜዲካል ማህበር የበላይ ተጠሪዋ ዶክተር ቬቪያን ናታንሰን ደግሞ መጠነኛ፣ ፣ከባድ፣ ፣ቀላል፣ የአልኮል መጠን በማለት ግልፅ ያልሆነ ነገር በማስቀመጥ አልኮል በእርግዝና ወቅት ችግር የለውም የሚል ምክር ከመስጠት ይልቅ ቀላሉና ለደህንነት አስተማማኙ ነፍሰጡር ሴቶች ሙሉ በሙሉ ከአልኮል መጠጦች እንዲቆጠቡ ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |