Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow “እኔ ምን አግብቶኝ ነው?”
“እኔ ምን አግብቶኝ ነው?” Print E-mail
Wednesday, 23 January 2008

…መርድ ሊያገባት የነበረችውን ደጃች ገሠሠ ሊወስዳት ነው ብለህ ላክብኝ፡፡ ቀድሞስ አንተ ወይዘሮ ላቀች እሺ ብላለች፤ ነገር ግን አለ ጃንሆይ ፈቃድ አይሆንም አለች ብለህ ብትነግረኝ እኔም እሺ ምን ከፋኝ ታግባ ብዬ ላክሁ፡፡ እስዋ እንደወደደች ነው እንጂ እገሌን ታግባ እገሌን አታግባ የምለው እኔ ምን አግብቶኝ ነው፡፡ አንተስ ቀድሞውን የሷን ልብ ሳትይዝ እሷን ሳትለማመጥ ወደኔ ምን ያስለምን ነበር፡፡

አሁንስ ደግሞ ከጀመርከውስ ወዲያ የሷን ዝምድና ከፈለግኸው አባቷ የሞተባት ችግረኛ ነበረች ይህን ገንዘብ ለችግርሽ ጉዳይ አድርጊ ይህች በቅሎ ላንቺ ትሁን ይሄነን ጉልት ሰጥቼሻለሁ ብለህ እዚያው አባቷ አገር ሲሆን ሁለት ጉልት ሳይሆን አንድ ጉልት ሰጥተህ አቆላምጠህ ባታለልካት ነበር እንጂ አሁን እሷ አይሆንልኝም የወደድሁትን አገባለሁ ስትል ጊዜ የንጉሥ ተክለሃይማኖትን ልጅ ገረድ ይመስል በግድ አንቄ ልሰጣት ነውን ምን ይሁን ማለትህ ነው፡፡

እንግዲያውስ ቆርቦ ያንሳኝ ያለች ጊዜ ፈቃድዋ አለመሆኑን በዚህ አታውቅምን፡፡ ነገር ግን እኔ ያገባኝ የነበረ እሷ ከቀድሞ ንጉሥ ላሉት ስጡኝ ብላኝ ፈቃድ ሰጥታኝ ቢሆን እንግዲያውስ የለመነኝ መርድ ነው ብዬ እበይን ነበር፡፡ እሷ ሳትፈቅድ ማን በግድ ይላል፡፡ አንተ ግን ሁልጊዜ የጌትነት ሥራ እኔ ያልሁት ለምን ይቀራል ብለህ ነው እንጂ ይህስ ነገር የሚያስልክ ሆኖ አይደለም፡፡ እንኳን ይህቺ የወለድካት እንኳ ልጅህ ላቀች አልታዘዝ ብላ አሸነፋ ቀረች፡፡ ደግሞም የዚህ ነገር በደብዳቤ አያልቅም፡፡ በተገናኘን ጊዜ እንነጋገራለን፡፡

የአፄ ምኒልክ ደብዳቤ ኅዳር 5 ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተፃፈ፡፡
(ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒልክ፣1999)

የአዞ ገበያ

ትላልቅ አዞዎችን ለማየት ወደ ጫሞ ሀይቅ መሄድ ይመከራል፡፡ የአፍሪካ ትልልቅ አዞዎች የሚገኙት የአርባ ምንጭ ደቡባዊ ክፍል በሆነውና በተለምዶ የአዞ ገበያ እየተባለ በሚጠራው ጫሞ ሀይቅ ነው፡፡ በጫሞ ሀይቅ የሚገኙት አዞዎች መጠናቸውም ትልቅ ነው፡፡ ለአባያ ወደብ አቅራቢያ በሚገኘው “ክርክዳይል ፋርም” ጎብኚዎች የአዞዎችን እድገት ከመጀመሪያ ጀምሮ የመመልከት እድል ይኖራቸዋል፡፡

(ስፔክትረም ጋይድ ቱኢትዮጵያ፣1995)

ሲ አይ ኤ አባ መርዞ

ያንን ትልቅ ዋርካ ሶቭየት ኅብረትን፣
ለሰባ ዓመት ያህል የበቀለውን፣
በኃያልነቱ የወፈረውን፡፡
በትንሽ መጥረቢያ ገዝግዞ ገዝግዞ፣
ቆርጦ ገነደሰው ሲ አይ ኤ አባ መርዞ፡፡
ቅርንጫፎቹንም እየመለመለ፣
ጨርሶ አጋዛቸው እያከታተለ፡፡
ግንዱንም ተርትሮ በድጅኖ መራጃ፣
ዳቦ ጋገረበት እየቆሰቆሰ በትልቅ ምድጃ፡፡

(ታደሰ ገድሌ፣ ትንቅንቅ፣ 1993)

 ገብሩና አለቃ ታዬ

እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ሩቅ አገር ተሰደው ወይም ወደ አበሻችን ከመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችንን መናፍቃን የሌላም መንግሥት ሰላዮች እየባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን? የእነዚያን መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠረው? የሚከተሉት የሁለት ሰዎች ስም እንዲወሱ የግድ ነው፡፡ እነርሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታዬ ናቸው፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አድርጎ መንግሥቱን የሚወድ ሰው አላየሁም፡፡ ይህ ደግነታቸው ግን እስከ ዛሬ ድረስ አልታወቀላቸውም ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የእነሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ለወዳጅ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቆርጣል፡፡

(ሰሎሞን   2000)                        


መድኃኒት


ይድረስ ከቢትወደድ ኢልግ የነገርከኝ የቁንጫ መድኃኒት በሳህን አድርገን ብንሞክረው የሚያልቀው ቁንጫ እጅግ በጣም ጉድ ነው፡፡ አንተው እንዳልከው እውነተኛ መድኃኒት ሆነ፡፡

የአፄ ምኒሊክ ደብዳቤ መስከረም 7 ቀን አዲስ ዓለም ከተማ ተፃፈ 1894 ዓ.ም

(ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒሊክ፣ 1898)

በድሬዳዋ ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚነገሩ የአራዳ ቃላት
ቁቅ፣ ድንቡኮ - አምስት ሳንቲም
አርስተርቆ፣ ሲታ  -  አስራ አምስት ሳንቲም
መጋዳ/ከርክ -  ሃያ አምስት ሳንቲም
ካሩ፣ ገበሬው -  አንድ ብር
ዲዝ -  አስር ብር
ችኳንታ  -  አምሳ ብር
አርበኛው - መቶ ብር

 (ድሬ መፅሔት፣2000)

ሊዮ ናርዶ

ለመጀመሪያ ጊዜ የሰዓት ደቂቃ ቆጣሪ (አመልካች) ያለው ሰዓት የሠራው ሊዮናርዶ ነበር፡፡ ዘመናዊ መኪናዎች ያላቸው የተጓዙትን ርቀት የሚያመለክት መሣሪያ ለመሥራትም ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ መሣሪያ የሚሠራው በተሽከርካሪው ዙር ሲሆን ከማርሽ ጋር በሚያያዙ ጥርሶች በማስተላለፊያ ሽቦ አማካኝነት ወደ ማይል ይለወጣል፡፡ ይህንን መሣሪያ ሊዮናርዶ እንዲሠራ ምክንያት የሆነው አቅዶት የነበረው የካርታ ሥራ ነበር፡፡ ለዚህም በእጅ የሚገፋ ጋሪ መሰል ተሽከርካሪ ሠርቶ ይህንን የርቀት መለኪያ መሣሪያ መጠቀም ጀምሯል፡፡

ሊዮናርዶ ከዘመናችን የአሠራር ዘዴ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን የፈጠራ ሥራዎች አከማችቷል፡፡ በአብዛኛው ከሱ የተወሰዱ የአሠራር ስልቶች መሻሻል ተደርጎባቸው በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ከመኪና ማንሻ (ክሪክ) ጋር በጥቂት የሚመሳሰል የዕቃ ማንሻ መሣሪያ ሠርቷል፡፡ የተለያዩ ዳያሜትር ያላቸው በማርሽ አሠራር ዘዴ የሚሠሩ እንደ አመቺነቱ የተያያዘ በተለያየ ፍጥነት ለማሽከርከር የሚያስችል ክፍል ያለው ሞዴል ተሽከርካሪ ሠርቷል፡፡ ሊዮናርዶ የሠራው “ዲፍረንሺያል” በዘመናችን ያሉ ተሽከርካሪዎች ከበስተኋላቸው ያላቸው ዓይነት ሆኖ በሚዞሩበት (በሚታጠፉበት) ጊዜ አንዱ ጎማ (ተሽከርካሪ) ከሌላኛው ፈጠን ብሎ እንዲሽከረከር የሚያስችል ነበር፡፡ በዚህም የተሽከርካሪ አሠራር ጥበቡ ሊዮናርዶ ከጊዜው እጅግ የመጠቀ ነበር ለማለት ያስችላል፡፡ “

(አቪዬሽን፣ ሰኔ 1982)

ማቆራኘት

ብቃትን የሚያስገኘው ዓይነተኛ መንገድ የማያቋርጥ ትግል ነው፡፡ ከአሸናፊነትና በተሸናፊነት መሐል ያለችው መስመር እንደ ጸጉር የቀጠነች ከመሆኗ የተነሣ ስናልፋትም ሆነ ቆም ስንልባት አናስተውላትም፡፡ ጥቂት ተጨማሪ ጥረት በማድረግ ጥቂት ተጨማሪ ትዕግሥት በማሳየት ፋንታ እጃቸውን እየሰጡ አሸናፊነታቸውን የተነጠቁ ስንቶች ይሆኑ? ጥረትን ከማቋረጥ በቀር ሽንፈትን የሚወልድ ምንም ነገር የለም፡፡ መንፈሳችንን እስካላዳከምንና የገዛ ዓላማችንን እስካላኮላሸን ድረስ የማንወጣው ዳገት አይኖርም፡፡

(መስፍን ወ/ማርያም፣ ብልጭታ፣ 1982)

ገራገር

ሊሰረቅ የማይችል መኪና

ኤሌክትሮኒክ ቁልፍ ያለውና ሰባ አምስት ሺህ ፓውንድ የወጣበት የጀርመን ፖሊስ ስፔሻል ቢኤም ደብሊው መኪና በርሊን ከተማ ውስጥ ተሰረቀ፡፡

ባለው የረቀቀ ቴክኖሎጂ የጀርመን ፖሊስ ኩራት እንደሆነ የሚነገርለት ይህ መኪና ውስጥ የነበሩት ሁለት ፖሊሶች አንድ ግለሰብን በእግር አስረው ለመያዝ በሞከሩበት ወቅት ነው፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች ግለሰቡን አግደው መኪናቸውን ወደ አቆሙበት ቦታ ሲመለሱ መሰረቁን ተረዱ፡፡ ማን ሊሰርቀው እንደሚችል ምንም አይነት ፍንጭ ያልተገኘ ሲሆን ሁለቱ ፖሊሶች እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

በመቶ የሚቆጠሩ እባቦች በአውሮፕላን

ከባንኮክ ወደ ቬትናም ይጓዝ በነበረ አውሮፕላን ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ እባቦች በሳጥን ውስጥ ታሽገው መገኘታቸውን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡

“ፍሬሽ አሳ” የሚል ጽሁፍ በተለጠፈባቸው ስልሳ ሳጥኖች ውስጥ ያሉት አሳዎች ሳይሆኑ እባቦች መሆናቸውን የደረሱበት የቬትናም አየር መንገድ ባለሥልጣናት እባቦቹ ቬትናም ውስጥ ለሚገኙ ሬስቶራንቶች የመጡ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

አውሮፕላኑ በጉዞ ላይ እንዳለ ሳጥኖቹ በአጋጣሚ ቢከፈቱ አስከፊ ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር የገለፁት ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ቬትናም ከደረሰ በኋላ ሳጥኑ ሲከፈት አብዛኞቹ እባቦች ሞተው መገኘታቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ እንስሳት ፓርክ መወሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

መላ ሰውነቱ በፀጉር የተሸፈነ ሰው

2002 ላይ የዓለም ፀጉራሙ ሰው ተብሎ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ የሰፈረው ዮ ዜንዋን በድረ ገጽ የፍቅር ጓደኛ እየፈለገ መሆኑን ዤዲያን የተሰኘው ድረ  አስታውቋል፡፡

የሀያ ዘጠኝ ዓመቱ ዮ “መላ ሰውነቴ በፀጉር የተሸፈነ ነው፡፡ በዚህ ቤተሰቦቼ ሚስት አያገኝም የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ብዙ ሴቶች ሰውነቴን ሲያዩ ይደነግጣሉ፡፡ አንዳንዴ ኪንግ ኮንግን የሆንኩ ይመስለኛል” በማለት ሩህሩህ ልብ ያለው መሆኑን ተናግሯል፡፡

እድሜ ጠገቡ ማቀዝቀዣ

77 ዓመት የሆነው ማቀዝቀዣ/ፍሪጅ እንዳላት በእንግሊዝ ድርሀም ግዛት ውስጥ የምትኖር የስልሳ ዓመት አዛውንት አስታውቃለች፡፡ አራት ጫማ ርዝመት ያለውን ይህ ፍሪጅ የባለቤቷ ከሰው ላይ የገዛችው 1969 ሲሆን የተመረተው 1932 መሆኑን የተሰራበት የፋብሪካው ምልክት እንደሚያመላክት ዘ ሰን አስነብቧል፡፡

ፍሪጁን ከገዛችው ጀምሮ ምንም ብልሽት አሳይቶ እንደማያውቅና ረዥም ዘመን ከመቆየቱ የተነሳ እንደቤተሰብ እንደተቆጠረ የፍሪጁ ባለቤት ማውረን መስ አመልክታለች፡፡

 
< Prev   Next >