Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ...
ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ... Print E-mail
Wednesday, 23 January 2008

ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአካባቢና የማሟያ ምርጫ

የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችል ካርድ ለመውሰድ እንዲረዳ ምዝገባ ሲካሄድ ከርሞ በመጭው ቅዳሜ ይጠናቀቃል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ 4 ሚሊዮን እጩዎችን ለምርጫው ማቅረቡንና የአካባቢና ማሟያ ምርጫው በሠላማዊ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚከናወን በምርጫው ሕዝቡ የላቀ ተሳትፎ የሚያደርግበትና ፓርቲዎች ገንቢ ውድድር የሚያደርጉበት ምርጫ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኢህአዴግ እንደሚፈልግ የኢህአዴግ የምርጫ ኮሚቴ አመራር አባላት የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ማሞና አቶ ታደሰ ካሳ ባለፈው አርብ አስታውቀዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዚሁ ምርጫ በምን ዓይነት ዝግጅት ላይ እንዳሉ ለማወቅ ሪፖርተር ጋዜጣ የኦፌዴን ፕሬዚዳንት የሆኑትን አቶ ቡልቻ ዴመቅሳን፣ የኢዴኅህ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ የቅንጅት ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶንና የኢዴአፓ መድህን ፕሬዚዳንት የሆኑትን አቶ ልደቱ አያሌውን አነጋግሯል፡፡

አቶ ቡልቻ ዴመቅሳ ከስርዓቱ የሚያስወጣ ዓይነት ችግር እየደረሰባቸውና  እጩዎቻቸው በየሀገሩ እየታሰሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ "በአጋሮና ገብረጉራቻ እጩዎቻችን ታስረዋል፡፡ ይሄን ደግሞ ከምርጫ ቦርድም አልፈን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉ አስታውቀናል፡፡ ምርጫ ቦርድ ግን ምንም ነገር አልደረሰኝም እያለ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ እኛም ከምርጫው የመውጣትና ያለመውጣት ጥያቄ ላይ ወድቀናል፡፡"

እጩዎቻቸው ከተፈቱና ቢሮዎቻችን ከተከፈቱ በምርጫው እንደሚሳተፉ አለበለዚያ ግን ከምርጫው ራሳቸውን እንደሚያገልሉ የሚናገሩት አቶ ቡልቻ ውሳኔያቸውን በዚህ ሣምንት መጨረሻ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡ "መንግሥት በየወረዳውና ቀበሌው ያሉ የምርጫ አስፈፃሚዎች ወከባ እንዳይፈፅሙ በሚድያ መመሪያ ቢያስተላልፍ ሁሉም ነገር ይቆም ነበር፡፡ በማፈን በማሰርና በማዋከብ ምርጫ" እንደማይካሄድ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

እርግጥም አቶ ቡልቻ የሚሉት እውነት ከሆነና የምርጫ ሂደቱ ላይ ነፃና ገለልተኛ አስፈፃሚዎች ከሌሉ እጩዎችም እጩ ስለሆኑ ብቻ የሚታሰሩ ከሆነ ምርጫው የይስሙላ ምርጫ ብቻ ስለሚሆንና ኢህአዴግ ከላይ ምርጫው "በሠላማዊ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ" እንዲከናወን መፈለጉ ከንቱ ምኞት ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመወዳደር የወሰኑ ፓርቲዎችን ኢህአዴግ የምርጫ አጋሮቹ አድርጎ እንደሚያያቸው አቶ ታደሰ ካሳ ይናገራሉ፡፡ "ፅህፈት ቤታቸው እንደተዘጋና አባሎቻቸው እንደታሰሩ የሚገልፁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ አሁን ድረስ ያቀረቡት አንድም ማስረጃ" አለመኖሩንም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይገልፃሉ፡፡

አቶ ቡልቻ ችግሮች እንዳሉ ቢገልፁም እንዲሁም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ቢክድም ነገሮች አልጋ ባልጋ አልሆኑም ብሎ ራስን ከምርጫ ማግለል ግን ተመራጭ ስልት አይሆንም፡፡ "ጥማት የፈጠራ እናት" በመሆኗ ለነፃነት ለህግ የበላይነት እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለን ጥማት የሚቆረጠው ወደ እነሱ በመቅረብና ነገን ብሩሀማ በማድረግ እንጅ በቀላሉ ተስፋ በመቁረጥና በመራቅ ሊሆን አይችልም፡፡ ገዥው ፓርቲም የምርጫ አጋሮቹን ችግር ሊፈጥርባቸው አይገባም፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው "በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ለደጋፊዎቻቸው ለምርጫ ለማዘጋጀት እንኳን መንግሥት እድል እንደነፈጋቸው ገልፀዋል፡፡ ከመንግሥት ጋር ለመወያዬት የተደረገው ጥረት መንግሥት በሩን በመዝጋቱ አለመሳካቱንና የምርጫው መድረክ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤና በአካል ማስረዳታቸውንም አውስተዋል፡፡ እጩዎቻችን፣ የወረዳ ተጠሪዎቻችን በብዙ የደቡብ ክልል አካባቢዎች እየታሰሩ ነው፡፡ መራጮቻችን ካርድ ለመውሰድ ሲመዘገቡ እየተቸገሩ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን ለአባሎቹ ለአንድ ሰው እስከ 10 ካርድ ሁሉ የሰጠበትና ይህንንም ለምርጫ ቦርድ የገለፅንበት ሁኔታ አለ፡፡ የምርጫ አስፈፃሚ የተባሉት በሙሉ የኢህአዴግ ሹመኞችና ባለስልጣናት ናቸው፡፡ በምርጫ 97 ከአስፈፃሚነት የተባረሩ አሁን መልሰው አስፈፃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ለምርጫ ቦርድ በዝርዝር ለማስታወቅ በዝግጅት ላይ ነን፡፡"

የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ 29"5) "በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት  ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል" ይላል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ማቋቋሚያ አዋጁም ሚዲያዎቹ መንግሥትን ሕዝብና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን የማገልገል ግዴታ እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡

ታዲያ ይህ በሆነበት ሁኔታ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ገዥውን ፓርቲ እንዲያ ካለም ህብረተሰቡን እንጅ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶችን ሲያገለግሉ አይስተዋሉም፡፡ ፕሮፌሰር በየነ እንዳሉትም ይህ እንደ ልዩ ጥቅም መንግሥት በችሮታ ሊሰጣቸው የሚገባ ነገር ሳይሆን እንደመብትም ሊጠይቁት የሚገባ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መብት ነው፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ደልዳይነት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንን አጠቃቀም በተመለከተ አዋጅ የወጣ ሲሆን ብዙ የህግ ባለሙያዎች በምርጫ ጊዜ ብቻ ለምን ይህ መብት ይሰጣል? አንቀፅ 29"5) በማንኛውም ጊዜ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጉን ተከትለው መጠቀም ይችላሉ በማለት ሲሟገቱ ነበር፡፡ አሁን ግን በምርጫ ጊዜ እንኳን ይህን መብታቸውን እንዳይጠቀሙ መከልከላቸው ህገ ወጥ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ካልተወያየና የጋራ መግባባት ላይ እስካልደረሰ ድረስ ቅሬታዎቹ ይቀጥላሉ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር በሌላ ሀገር ሕግ እስከማውጣት መድረሳቸው ኢህአዴግን ያስኮረፈውና ያስቆጣው ብሎም በሩን ለድረድር ያስዘጋው ቢሆንም መንግሥት ከተወዳዳሪ ፓርቲነትም በላይ ሆደ ሰፊና ቻይ እጅግ የተራራቁ ስሜትና ፍላጎቶችንም ለማስታረቅና በልዩነትም ውስጥ አንድነትን መፈለግ ያለበት ትልቅ ግዴታና ኃላፊነት ያለበት አካል እንደመሆኑ ውይይትን ክርክርንና መተማመንን ከደጁ ሊያጠፋ አይገባም፡፡

የምርጫ አስፈፃሚዎችን ጉዳይ በተመለከተ ሁሉም ጥርጣሬ ያለበት ጉዳይ ቢሆንም ኢህአዴግ እንዳለውም ጥርጣሬዎቹ ተጨባጭ እንዲሆኑ ማስረጃ አስፈላጊ ነው፡፡ "የኢህአዴግ ሹመኞች፣ ባለስልጣናት እና የተባረሩ አስፈፃሚዎች" መሆናቸውን ማረጋገጥ ከባድ ባለመሆኑ ጉዳዩን ከምርጫ ቦርድም ባሻገር በመደበኛ ፍ/ቤት ክስ በማቅረብ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ "ዛሬ ስለዋሸኸኝ ነገ አላምንህም" ማለት ፖለቲካ ውስጥ ዋጋ የለውም፡፡ ጥርጣሬ፣ ተስፋ መቁረጥና መራቅ ሳይሆን የፍትህ አባላትን ለማሳመን በየጊዜው አቅምን ማጎልበት፣ ጠንካራና የማያከራክሩ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንዲሁም በውትወታና የተሻለውን እውነት በማሳየት የፍትህ አካላቱን የሚመሩትን ግለሰቦች አመለካከት መለወጥና ለህሊናቸው የሚታዘዙ ዜጎች ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ 

ከብዙ ውዝግብ በኋላ የቅንጅት ስምን በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ያገኙት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው ምርጫው እንዲራዘም ጠይቀው አለመሳካቱን ቢሆንም ባለው ቀሪ ጊዜ የተቻላቸውን ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ትግራይ በትራንስፖርትና በገንዘብ ችግር ለመግባት ባንችልም በመላው ኢትዮጵያ ለመወዳደር እቅድ አለን፡፡ ምርጫ ቦርድ ሊሰጥ የሚገባውን ገንዘብ አዘግይቶብናል፡፡ በሌላ በኩል ስሙ ለእኛ ተሰጠ እንጂ ገንዘቡ ያለው ሌላ አካል ጋር ነው፡፡ ቢቻለን ግን 75 ከመቶ መወዳደሪያ ቦታዎችን ለመሸፈን እቅድ አለን"

75 ከመቶ መወዳደሪያ ቦታዎችን ለመሸፈን ቢያንስ 375"000 እጩዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ይሄን ያህል እጩ ለማግኘት የሚያቅዱት እነአቶ አየለ ገንዘብ የላቸውም፡፡ ከምርጫ ቦርድ የሚደረገውን ድጎማና ስሙን ከመጠቀም የተከለከለው ቅንጅት እንዲያስረክባቸው በሚፈልጉት ገንዘብ ተማምነው ይህን ትልቅ እቅድ ሊያቅዱ አይችሉም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራዕይና እቅዳቸው ከተጨባጭ እውነታ ጋር እንደሚራራቅ ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ ጊዜ ይተቻል፡፡ ደርግ ይህን የአቶ አየለን እቅድ ያየ የኢሕአዴግን ትችት ስህተት ነው ለማለት አይቻልም፡፡

አቶ  ልደቱ አያሌው በመርህ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲ እስከሆኑ ድረስ በችግር ውስጥም ቢሆን መወዳደር እንዳለባቸው የትኛውንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ችግር ቢኖርም በምርጫ አለመሳተፍን እንደጠቃሚ ስልት እንደማይወስድ ምርጫ በመርህ ደረጃ ለድርድር የሚቀርብ ነገር ለመሆኑን ያብራራሉ፡፡

"አሁን ያለንበት ሁኔታ ለኢዴአፓ መድህንም ሆነ ለሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመቺ ጊዜ አይደለም፡ ይህም የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ ከግራም ከቀኝም በተፈጠሩ ስህተቶች የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ በምርጫ የምንሳተፈው ለተሳትፎ እና ለአክብሮት ያህል ነው፡፡ ፓርቲያችን ለመርሁ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ነው፡፡ ሰፊ እጩ ማቅረብም ሆነ ለማሸነፍ የሚረዳ አቅም የለንም፡፡ ካለፈው ምርጫ ሲነፃፀር አሁን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ የተቃዋሚ ደጋፊ የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ከምርጫ 97 በኋላ በአጠቃላይ ሞራሉ ተነክቷል፡፡ የምርጫ ተሳትፎ ስሜቱ በጣም የቀዘቀዘ ነው፡፡ እጩዎቻችን ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ምረጡን ብለው ለመቀስቀስ ያላቸው ፍላጎት በጣም የወረደ ነው፡፡ የገንዘብ አቅማችንም በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል፡፡ በአካባቢና ማሟያ ምርጫ በሁሉም ቦታዎች ለመወዳደር ከ500"000 በላይ እጩዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እንኳን አሁን የመራጩም የተመራጩም ስሜት በቀዘቀዘበት ጊዜ ይቅርና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ10 እና 15 ዓመት ጊዜ ውስጥም መንግሥት እስካልሆኑ ድረስ ይህን ቁጥር ማሟላት አይችሉም፡፡" አቶ ልደቱ እንደሚሉት ኢዴአፓ - መድህን የተመዘገበ የአባላት ቁጥሩ 36"000 ሲሆን፡፡ አዲስ አበባ ብቻ 30"000 እጩዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ይህን ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ የሚተቹት አቶ ልደቱ ከሌሎች አገሮች ልምድ ጋርም የማይጣጣምና ምናልባትም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሀይልና የአቅም መዳከም ተከትሎ ታስቦበት የተደረገ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ልደቱ እንዳሉት በችግርም ውስጥ ሆኖ በምርጫ ለመሳተፍ ፈቃደኝነት ማሳየት የውዴታ ግዴታ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አማራጭን በማሳየት ደጋፊዎችን መሳብ ማደራጀትና መንቀሳቀስ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በተለይ ለእንደኛ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ስርዓት የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መዳበር ለሐገሪቱ ህልውና ጭምር የሚያስፈልግ ነገር ነው፡፡ ለአንዱ አካል ያለው ድጋፍ በሚጠፋ ሰዓትና እውቅና ሲነፍግ ሀሳቡን በመግለፅ የተለዬ አቋም የመያዝ መብቱ የተጠበቀለት መሆኑን ሀሳቡን በነፃ ገበያ ለሌሎች አሰምቶ ማሳመን እንዲችል እድሉ ካልተመቻቸለት አጥፊ ሀይል መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ለሀገር ሠላምና ደህንነት ሲባል ምርጫ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

"ለተሳትፎ ያህል" ነው የምንሳተፈው የሚባለው ግን አግባብ አይደለም፡፡ አቅም ቢጠፋም የሚሠራው ሥራ ውጤታማና አስተማማኝ እስከሆነ ድረስ በጥራት መወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ትንሿ ድል ለሌላ ትልቅ ድል በር ከፋች ትሆናለች፡፡ የተጀመረውን እያፈረሱ ከዜሮ ከመጀመር ባለው ላይ እያጐለበቱ የቁስ ሀይል፣ የሰው ሀይልና ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር መመሥረት ይቻላል፡፡ ለተሳትፎ ያህል የሚወዳደር የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሀገሪቱ አትፈልግም፡፡ ስለዚህ ይህን የስነ ልቦናና በራስ መተማመን ስሜት የሚያጠፋ ቃል መጠቀም አያስፈልግም፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይደግፍ የነበረው ህብረተሰብ አሁን የምርጫ ስሜቱ መቀዝቀዙን እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ሁሉ በርካታ ሰዎች የሚጋሩት እውነታ ነው፡፡ መንግሥት ላይ ይታዩ የነበሩ ድክመቶች ተቃዋሚው ፈፅሞ የማይሞክራቸው ይመስለው የነበረው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የተቃዋሚዎችን ዘርፈ ብዙ ችግር ተመልክቶ ግራ በመጋባቱ የምርጫ ስሜቱ ቀዝቅዟል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ይህ አጋጣሚ ህብረሰሰቡ ከስሜት ወጥቶ ለውሳኔዎቹ በስነ አመንክዮ እንዲመራ ስለሚያደርግ በአዎንታዊ መልኩ መታየት አለበት እያሉ ነው፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ ከፖለቲካው ሊርቅ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ፖሊሲ፣ እስትራቴጂና መርሆች ላይ ጊዜ ወስዶ ሊያስብ፣ ሊወያይና ሊከራከርበት እንደሚገባና በመጨረሻው ባመነበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በመታቀፍ የሚካሄደውን ሰላማዊ ጦርነት ሊቀላቀል ይገባል፡፡

አቶ ልደቱ እጩዎቻቸው ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ምረጡኝ ብለው ለመቀስቀስ ያላቸው ፍላጎት በጣም የወረደ መሆኑን መግለፃቸው የማይጠበቅ አይመስልም፡፡ ሲጀመር ህብረተሰቡ በመብቱ እንዲጠቀምና ግዴታውን እንዲወጣ ለማስቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ለመብትና ግዴታወቹ ዝርዝር ተፈጥሮና አፈፃፀም ደግሞ እጩዎች የበለጠ ቅርብና በሌሎችም ላይ ለማስረፅ ብልሀቱን የተካኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የራስ ፍላጎት የወረደ እጩ እንዴት ብሎ ነው የሌሎችን ስሜት መኮርኮርና መቀስቀስ የሚችለው፡፡ እጩዎች የዛሬ እንቅስቃሴአቸው ለነገ ትልማቸው መዳረሻ መሆኑን የሚያውቁ በራስ መተማመናቸው ከፍ ያለና ሀሳባቸውን ለመግለፅና ለማሳመን ተቺዎቻቸውንም ለመከላከል በቂ ስንቅ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡

ለአካባቢና ለማሟያ ምርጫ በሁሉም ቦታዎች ለመወዳደር ከ500"000 በላይ እጩዎች ያስፈልጋሉ መባሉ ልክ አይደለም፡፡ በእርግጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ 97 ውጤት ከኢህአዴግ ጋር ከልክ በላይ እልክ መጋባታቸውና ተቃዋሚዎቹ "በትንሽ አቅም የሚሊዮኖች ድጋፍ አግኝተናል" ማለታቸው ኢህአዴግን እልህ ውስጥ ማስገባቱ አይዘነጋም፡፡

የመጀመሪያው እልህ መንፈሳዊ እልህ ሲሆን ይህም ተቃዋሚዎች ህብረተሰቡን የሳቡበትን መንገድ በመከተል ከምርጫ 97 በኋላ በርካታ አባላትን አግኝቷል፡፡ ወደ ህብረተሰቡም በመውረድ የመወያዬትና "ህብረተሰባዊነትን" የማጐልበት እርምጃ ተስተውሏል፡፡ በተለይም በተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ልቡ የሻከረውን የህብረተሰብ ክፍል ወደራሱ ንፍቀ ክበብ ለማስገባት ሰላማዊና ህጋዊ መንገዶችን ተከትሎ ድል አስመዝግቧል፡፡ በሌላ በኩል አንዳንዶቹ የኢህአዴግ እልሆች የተጀመረውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው፡፡ 500"000 እጩዎች ለአካባቢና ማሟያ ምርጫ ማቅረብ የአሁኑኖቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ፈፅሞ እንደማይችሉ ኢህአዴግ በትክክል ይረዳል፡፡ አለመቻላቸው ኢህአዴግን እንደ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ከወሰድነው ግድ ባይሰጠው ላይገርም ይችላል፡፡ አባላቶቻቸውን መጨመር ማደራጀትና በርካታ ጥራት ያላቸው እጩዎች መመልመል የእነሱ ግዴታ ነውና፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲና መንግሥት እንደመሆኑ መጠን የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን መድከም ሀይልና አቅም ማነስ ሊያስደስተው አይገባም፡፡ መድብለ ፓርቲ ስርዓቱ በህብረ ብሔር ፖለቲካ ላይ ላተኮረው ፌደራል ስርዓት መዳበሩ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ ነው፡ እንደመንግሥት ሌሎችንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሎም አባሎቻቸውን የማስተዳደር ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥት የወደዱትን ብቻ ሳይሆን የጠሉትንም ሰዎች ፍላጎት ለመጠበቅ መጣር አለበት፡፡ ስለዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች በነፃነት እንዲደራጁና ህጋዊ አላማዎቻቸውን እንዲያስፈፅሙ ሊያግዝ ይገባዋል፡፡ አለአግባብ የታሰሩ እጩዎች እንዲሁም የተዘጉ ቢሮዎች ካሉ አቤቱታውን ሰምቶ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ አቤቱታው ከንቱ ጥርጣሬና ስም ማጥፋት ከሆነም ይህንኑ እውነት ሕዝቡ እንዲያውቀው (በማስረገጥና በማያወላውል ቋንቋ) ማድረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ ምርጫው አማራጭ ከሌለው "ብቻውን የሮጠ አይሸነፍም" እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለድክመታቸውና ችግራቸው ሁሉ ወደ መንግሥት እጃቸውን ከመቀሰር የውስጥ ችግራቸውንና ስንፍናቸውን በመገምገም ንቃተ ህሊናቸውን በማዳበር ወደ ውድድር መድረኩ በጥንካሬ ይግቡ፡፡

በሰለሞን ጐሹ

 
< Prev   Next >