| ሕዳሴ ወይስ ግምገማ |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ አዘጋጅነት ጥር 6 ቀን 2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ አንድ ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፡፡ የኮንፈረንሱ አጀንጃ "ትልልቅ አገራዊ የወል እሴቶችን ማበልፀግ፤ በአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የጋራ ፖለቲካ መድረክ መፍጠር" የሚል ነበር፡፡ በእለቱ ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች አንዱ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተዘጋጀው "የአዲሱ ሚሌኒየም ፈተና፤ ሕዳሴ ወይስ ግምገማ" የሚል ርዕስ ነው፡፡ አዲሱን ሚሌኒየም ስንቀበል "እንኳን ደስ ያላችሁ!" እንጂ "እንኳን አደረሳችሁ!" አልተባልንም፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊያን ለዘመን አቆጣጠር "እንኳን ደስ ያላችሁ"" የሚባሉ ብቸኛና የተለዩ ዘሮች ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ደስታ ላይ የተረጋጋና የተመጣጠነ የአለፈው ሚሌኒየም ግምገማ ይቀረናል በማለት ፕሮፌሰሩ ትልቅ ግን የተዘነጋ ያሉትን ነጥብ ያስታውሳሉ፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሚሌኒየም ዋዜማ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር የመጀመሪያውና የሁለተኛው ሚሌኒየም የመጀመሪያ አጋማሽ ተከታታይ እድገቶች የተመዘገቡበት የሁለተኛው ሚሌኒየም ሁለተኛ አጋማሽ ግን ወደ ኋላ የሄድንበት የውድቀት ዘመን ነበር ማለታቸውን ተቃውመዋል፡፡ የመጀመሪያውን ሚሌኒየም ስናጠናቅቅ በጉዲት ጦርነቶች የተነሳ በተፈጠረው አለመረጋጋትና ህግና ስርዓት ባለመኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለህልውናቸው ይጨነቁ ነበር እንጂ ሚሌኒየሙን ለማክበር እድል አላገኙም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በተከታታይ እድገት ወይም ውድቀት ብቻ አሊያም ብርሃን ወይም ጨለማ ብቻ የተከሰተበት ጊዜ በግልጽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሚሌኒየም የራሱ የሆነ እድገት ወይም ውድቀት ከመያዙም ባሻገር እያንዳንዱ ስልጣኔ በውስጡ ጭቆና አለው በማለትም የተቃውሟቸውን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ከየት ተነስተን ወደ አዲሱ ሚሌኒየም እንዴት እንደደረስን በመከለስ ምን እንዳገኘን፣ ምን እንዳጣን፣ ምን እንዳለማን፣ ምን እንዳጠፋን ዘርዘር አድርገው ከገመገሙ በኋላ ስለ አዲሱ ሚሌኒየም ፈተናዎች በመጨረሻ እንዲህ ብለዋል፡፡ "የአገሪቱ የልማት ፈተናዎችን ለመቋቋም እንድረዳ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ጥሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች በቀላሉ እንዲወገዱ በአዋጅ መመኘት ከሃይማኖት ቀኖና የዘለለ ሚና አይኖረውም፡፡ ከሁሉም በላይ ብሔራዊ መግባባት የሚገነባው ታማኝ የሆነ የመድብለ ፓርቲ ባህል ሲዳብርና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሲፈጠር ስርዓቱም እነዚህን ነገሮች ሲያቅፍ ነው፡፡ ፍትሃዊና መድልኦ የማይደረግበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሰረቱን ለመጣል እንኳ ረጅም ዘመናት ተጉዘናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በፈጠርነው ስርዓት ውስጥ ያሉትን ድርጅታዊ መዋቅሮች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግና ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ገና አልተሰራም፡፡ ለብዙ ዘመናት ጥረት ሲደረግበት የነበረው ሕገመንግስታዊ አገዛዝ ግንባታ በ1987 ዓ.ም የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት መታወጅ የተነሳ አላማውን የመታ መስሎ ነበር፡፡ በብዙ መንገድ አገሪቱ ከነበራት ህገ-መንግስቶች ሁሉ ነፃ አስተሳሰብን የሚያራም ነው፡፡ ነገር ግን ህገ መንግስት መቅረጽ አንድ ነገር ሲሆን ለእሱ መገዛት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 (የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት የሚያረጋግጥ) ላይ የነበረው ክርክር ያለቦታው እንደተቀመጠ አረጋግጧል፡፡ ይህን መብት ለማረጋገጥ የተቀመጡት አንቀፆች የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ ከባድ መሆን መቼም ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያስችል ሲሆን ለዚህ ተግባራዊነት ሲታገል የነበረው ፓርቲ ዛሬ መገንጠልን እንደ ዋነኛ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ አይደግፍም፡፡ ነገሩን ምፀታዊ የሚያደርገው አንቀጹ ታሳቢ አድርጎ የተቀረፀላቸው ኤርትራና ኦጋዴን አሁን ለአገሪቱ ትልቁን ውጥረትና ደም መቃባት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አንቀጹን ተግባራዊ እንዲያደርግ ስለተፈቀደለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለመገንጠል በሚያደርገው ትግል ነው፡፡ አንቀጽ 39ኝን ተግባራዊ ከማድረግም በላይ አስፈላጊው ነገር የሲቪክ ነፃነቶችን ተግባራዊነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ከባለፈው አስር ዓመት ወዲህ በተለይም ከምርጫ 97 ወዲህ የታየው ነገር የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የመረጃ ነፃነትን፣ የመደራጀት መብትንና የመሳሰለውን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ እንደሚቀረን ነው፡፡ ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት አካል፣ ነፃና ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ፣ እንዲሁም ጠንካራ ነገሮችን የሚጋፈጥና ጤናማ የሆነ ሲቪክ ማህበረሰብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምዕላዶች ናቸው፡፡ በሁሉም የህይወት ዘርፎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚወድ መንግስት እየተፈራረቀ ባህሉን ባሰረፀበት አገር በሕግ አስፈፃሚው ተጽዕኖ ስር የወደቀ የዳኝነት አካል፣ ተጽዕኖ የሚደረግበት ሚዲያ፣ ድብቅ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረገባቸው ህዝባዊ ድርጅቶች ማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ካለፉት አገዛዞች በጣም ብዙ ነገር ስለተማረ በእነዚህ ውሳኔዎች አይታለልም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የምትፈልገው የፖለቲካ አመራር ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚፈጠር ሳይሆን የአለፉት አመራሮች ያጡትን ጥበብና አርቆ አስተዋይነት በመያዝ አገሪቱ ላይ የተከሰቱት አስቀያሚ ችግሮች የሚቀርፍ ነው፡፡ ለማኅበራዊ ፍትህ የነበረን ጥማት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሻገረው የመሬት ማሻሻያ አዋጅ የመሬት ባላባትነትን ባስወገደበት ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም የቀሩ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የገበሬውን ኑሮ ማሻሻል አለመሻሻሉን ወደ ጎን ብንተውም እንኳ ገበሬው መሬቱን ሙሉ በሙሉ ባለቤት እስካልሆነ ድረስ ነፃ ስለመውጣቱ ማውራት እንችላለን? ከባድ ጫና ከሚያሳርፉት እና ጣልቃ ከሚገቡበት የመንግስትና የወኪሎቹ እጅ ነፃ ሆኖ የእለት ከእለት እንቅስቃሴውን እንዲመራ የሚያስችል ነፃነት አግኝቷልን? ጥቂት የገበያ አዝርዕት (እንደ ቡና እና ጫት. ወዘተ) የሚያመርቱ ገበሬዎች ኑሯቸው መሻሻሉ ብቻ የተለየ እድገትን ይጠቁማል ወይ? ስለዚህ አሁንም በጣም አብላጫ ቁጥር ያለውን ገበሬ ህይወት ለማሻሻል ያለብንን ፈተናዎች እንዳሉ ናቸው፡፡ የማኅበራዊ ፍትህ የሚረጋገጠው የገጠሩን ድህነት ለመቅረፍ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ያለውን የከተማ ድህነት በማሻሻልም ጭምር ነው፡፡ የኃይማኖትም ሆነ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት በማረጋገጥ በኩል ያለውን ጥማት ወሳኝ እድገት በማሳየት ተወጥተነዋል፡፡ በትንሹ ያለፈው ስርዓት ስህተቶች ላይ መግባባት በመፈጠሩ ችግሮቹን ለማስወገድ ሙከራዎቹ ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የቀሩት ፈተናዎች ትኩረት የሚነፈጋቸው አይደሉም፡፡ በኃይማኖት በኩል ትልቁ ፈተና በመግባባት የተሞላ የመቻቻል ባህል ማቀፍ ነው፡፡ ይህን መፈፀም የብሔራዊ ሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን በአክራሪዎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ቀደም ብሎ በመደብና በብሔር ተከስተው የነበሩ ግጭቶች የፈጠሩት ውጤት ዳግም እንድናይ እንገደዳለን፡፡ በብሔር እኩልነት በኩል የቀረው ፈተና በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን እኩልነት የብዙሃኑ መብት እንጂ የጥቂት ተጠቃሚ ልሂቃን መብት መሆን ያለመሆኑን የማረጋገጥ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ማረጋገጥ ያለብን ሁሉም ዜጎች የዘር ግንዳቸውና ውልደታቸው ሳይታይ አገሪቱ ለማሳደግ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ እኩል እድል እንዲሰጣቸው ነው፡፡ በመጨረሻም ጥያቄ የማይነሳበትን ማኅበረሰብ ተነሳሽነትና ራስን መስዋዕት የማድረግ መንፈስን እያዳበርን እራሳችንን ከጽንፈኝነት ባህል ነፃ በማድረግ አሸናፊ ሁሉንም የሚወስድበትን ልምድ እንዲሁም ከግራ ዘመሙ የኢትዮጵያ የተማሪ ንቅናቄ የወረስናቸውን ድርጅታዊ ሥራ ማስቀረት አለብን፡፡ በተቃራኒው ወደ ኋላ በመመለስ ታሪክን ጣልቆ በመመርመር በጎ ጎኑን መውሰድ እንችላለን፡፡ እነዚህም እስልምናና ክርስትና በሰላማዊ ሁኔታ እርስ በርስ ተቻችለው የኖሩበት አስደናቂ ሪከርድ፣ የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ አስፈላጊ ሰዋዊ ምልከታ፣ በኦርቶዶክስና በካቶሊኮች መካከል ደም መቃባት እንዳይፈጠር ሲል ራሱን ከንግስናው ያነሳው አፄ ሱስንዮስ ውሳኔ፣ አገርን ዘመናዊ የማድረግ የአፄ ቴዎድሮስ ራዕይ (ግጭት መፍጠሩና ደካማ የመቻቻል ባህሉን በመተው"፣ የንጉስ እያሱ የእኩልነት ቀስቃሽ ስሜት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለማህበራዊ ፍትህ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ምሁራን ያላቸው ጠንካራ ትኩረትን ይጨምራሉ" ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ወደ ሚሌኒየሙ ፈተና ከማምራታቸው በፊት ለእነዚህ ፈተናዎች አስተዋጽኦ (በበጎም በክፉም) ያደረጉ ያሏቸውን አንኳር የታሪክ አጋጣሚዎች ገምግመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ወደ 15ኛው እና 17ኛው ክፍለ ዘመን በመመለስ ሁለቱን ዘርአያዕቆቦች ያነፃፅራሉ፡፡ ፈላስፋው አምባገነን ንጉስ ዘርአያዕቆብ ከነፃ አስተሳሰብ አራማጁ ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ ሁለት ክፍለ ዘመን ቢቀድምም ለተፈጥሮ ህግና ለልቦና በሚሰጠው ትልቅ ቦታ መንፈሳዊም ሆነ ቀኖናዊ ጫናዎችን የሚቃወመው ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ ለመቻቻል ፖለቲካ ተምሳሌት መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያወሳሉ፡፡ ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጥተው አፄ ቴዎድሮስን ያነሱት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ከዘመናዊ የኢትዮጵያ ነገስታት እንደ ቴዎድሮስ ለአፄያዊ ሥልጣን ገናናነትና ለአገር አንድነት ተግቶ የሰራ፣ በአገሪቱም ኋላ ቀርነት እጅግ የተቆጨ ንጉስ የለም፡፡ ዘመናዊ ስልጣኔ ለማስረጽ የእንግሊዝን መንግስት እርዳታ በብርቱ ተማጠነ፡፡ ይህን ኋላ ቀርነትም በማያሻማና በማያወላዳ ቋንቋ ነበር የገለጠው፡፡ ራሱንም ሕዝቡንም "እውር"፣ "ደንቆሮ"፣ "አህያ" እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የሕይወቱ ፍፃሜ ሲቃረብ ለወራሪው ጦር መሪ ለጀኔራል ናፒየር በፃፈው ኑዛዜ መሰል ደብዳቤ "ያገሬ ሕዝብ ገብር ስራት ግዛ ብዬ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በስራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ" ማለቱን ገልፀው ይህን የሥርዓታዊ አስተዳደርን አስፈላጊነት ገብረ ሕይወት ባይከዳኝም "አጼ ምኒሊክና ኢትዮጵያ" በተሰኘ ጽሁፍ "አእምሮ የሌለው ህዝብ ስራት የለውም፡፡ ሥራት የሌለው ሕዝብም የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥራት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች" በማለት በአጽንኦት መግለፁን ጨምረዋል፡፡ ስለዚህ ከሁሉም በላይ ገዥም ተገዥም የሚዳኙበትና የሚያከብሩት ደንብ በሕገ-መንግስት መልክ ለአምስት ያህል ጊዜ ቢቀረጽም የዘመነውን አሰራር የተከተለው የኢፌዲሪ ሕገመንግስት አሁን የያዘውን ቅርጽና ይዘት እንዲይዝ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ፋይዳቸው ብዙ ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን በተደረገው ጥረትም በ17ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ ዛድንግል የተጀመረ ሲሆን በአፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዳብሮ በአብዮታዊ አዋጅ ተደምድሟል፡፡ ይሁንና የመሬት ባላባቱ ከመሬት ባለቤትነቱ ቢፈናቀልም ባለቤትነቱ ከገበሬው ይልቅ ወደ መንግስት ተሻግሯል፡፡ አሁንም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ሲሆን የመሬት ወደ ግል ይዞታነት መዘዋወር ያለው ጥቅምና ጉዳት እንዳለ ሆኖ ገበሬው አሁንም ቢሆን ከዚህ ሰውነት ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመጨረሻ የዳሰሱት የእኩልነት ጥያቄን ሲሆን የመሐል አስተዳደሩ የጠረፍ አካባቢ ብሔረሰቦችን ይጨቁን ነበር በማለት ጭቆናው በአፄ ምኒሊክ ይብስ ነበር ያሉት ፕሮፌሰሩ ጭቆናው በሐይማኖትና በብሔር ነው፡፡ ለዚህ የእኩልነት ጥያቄ የመጀመሪያ መልስ የሰጠው ንጉስ እያሱ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 11 የመንግስትንና የሃይማኖትን መለያየት እንዲያውጂ እንዲሁም በአንቀጽ 39 ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት መረጋገጡ እና በአንቀጽ 47 ሁሉም ክልሎች እኩል መብትና ስልጣን እንዲኖራቸው መደረጉ በገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ሜጫና ቱለማ ማህበር እንዲሁም በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተደረገ ተከታታይ ጥረትና ትግል ውጤት ነው፡፡ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ጥናታዊ ጽሁፍ ርዕስም ሆነ ይዘት አዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ከሕዳሴ ይልቅ ግምገማ ይበልጥ እንደሚጠቅመው ያሳያል፡፡ የትናንት ታሪክ ተገምግሞ ጥሩውን ይበልጥ አጎልብተን እንድንቀጥልበት መጥፎውንም ቢሆን ሳንክድና ሳንዘነጋው ልንማርበት ይገባል፡፡ ነገ በበጎ አልያም ባልተጠበቀ መልኩ ሊጓዝ የሚችል ውጤት የሚያስከትለው የዛሬ ውሳኔን ስንወስን አስቀድመን ውጤቱን የምናውቀውን የትናንትን ታሪክ ማስታወስ ይገባናል፡፡ አዲሱ ሚሌኒየም በሕዳሴ ዘይቤ በአንድ ጊዜ የምንቀየርበት ሳይሆን በጥፋታችንና በልማታችን ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንድንችል ሁሉን አቀፍ ግምገማ እናድርግ የሚል ይመስላል፡፡ ለዚህ ግምገማ መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ህብረተሰቡ በአጠቃላይ ይዘጋጁ መልዕክቴ ነው፡፡ በሰለሞን ጎሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |