| የዓለም ማህበረሰብ ዲዛይን... |
|
| Wednesday, 05 November 2008 | |
|
የዓለም ማህበረሰብ ዲዛይን ያደረገው ኮምፒውተር ሊፈጠር ነው
በዓለም ላይ ያሉ ኮምፒውተር ተጠቃሚዎች ሁሉ የሚፈጠረው ኮምፒውተር ሊኖሩት ስለሚገባው ነገሮች አስተያየትና ጥቆማ የሚሰጡበት ዊ ፒሲ ዶት ኮም (WePc.com) የተሰኘ ድረገፅ መከፈቱን ቢቢሲ አስታውቋል፡፡ ኢንቴል እና ማኒፋክቸራር አሱስ የተሰኙት ሁለት ካምፓኒዎች መረጃውን ለቢቢሲ የሰጡት ማህበረሰቡ ኮምፒውተሩ ላይ ሊያያቸው የሚፈልጋቸው ነገሮች ምን፣ ምን እንደሆኑ የጠየቁበትን አዲሱን ኘሮጀክታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ ሁለቱም ካምፓኒዎች "ኘሮጀክቱ የተቀረፀው ዝም ብሎ አስተያየት ለመቀበልና ለማውራት ብቻ አይደለም፡፡ ማሽኑን ለመስራት ቁርጠኞች ነን" ብለዋል፡፡ "የፈጠራ ሃሳቦቹ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ሊመጣ ይችላል" የሚሉት የኢንቴል ካምፓኒ ሰራተኛ ማይክ ሆፊንገር ሁለቱ ካምፓኒዎች አንድ ላይ በመሆን የተጠቃሚዎችን የፈጠራ ኃይል ተጠቅመው ቴክኖሎጂውን ዲዛይን ለማድረግ እንደሚጥሩ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ በአሱስ ካምፓኒ የማርኬቲንግና ኘላኒንግ ዳይሬክተር የሆኑት ሊሊያን ሊን በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ዘወትር የደንበኞቻቸውን አስተያየት የሚጠይቁ መሆኑን ጠቁመው የአሁኑን የነሱን ጥያቄ ለየት የሚያደርገው ግን "አዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር የህብረተሰቡ ጣልቃ ገብነት የተጠየቀበት መሆኑ ነው" ብለዋል፡፡ ቢቢሲ በዘገባው እንደገለፀው የኢንቴል እና ማኒፋክቸራር ካምፓኒዎች ላሰቡት ሥራ ይረዳቸው ዘንድ የከፈቱት ዊፒሲ ዶት ኮም ድረ ገፅ መሪ ቃል "የምታልመውን የኮምፒውተር አይነት ተናገር፤ አሱስና ኢንቲለም ይፈጥሩታል" የሚል ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም. ውስጥም ኮምፒውተሩ እውን እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ስለስኪዝፍሬንያ መንስኤ ፍንጭ ተገኘ ከስኪዘፍሬንያ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የአእምሮ መልዕክት መቀበያቸው ኤሌክትሪካል ዌቭ ለምን ጤናማ እንዳልሆነ የሚጠቁም አዲስ ፍንጭ ማግኘታቸውን ሳይንቲስቶች አስታወቁ፡፡ በኒው ካስትል ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ስኪዘፍሬንያ ያለባቸው ሰዎች ጤናቸው የሚቃወሰው ዋናውና የአእምሮ መልእክት መቀበያዎችን የሚቆጣጠረውሴል ከጥቅም ውጭ ሲሆን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ምክንያቱን ለማወቅ በአይጦች ላይ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በውጤቱም በመድሃኒት ዋናው የአእምሮ መልዕክት መቀበያ ሥራ እንዲያቆም ሲደረግ ወደ መልእክት ተቀባይ ሴሎቹ የሚደርሰው ሞገድ እንደሚቀየር አረጋግጠዋል፡፡ ቢቢሲ ሳይንቲስቶቹን ጠቅሶ እንደገለፀው ለስኪዘፍሬንያ የሚያጋልጠው ዋናው መንስኤ ምን እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም በዘር የሚተላለፍን አካባቢያዊ ተፅእኖ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይገመታል፡፡ በዘር የመተላለፍ እድል አለው፡፡ በዚህ ከባድ የአእምሮ ህመም ላይ አዲስ የተገኘው ፍንጭም ለበሽታው አዲስ መድሃት ለመፍጠር እንደሚጠቅም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ስኪዞፍሬንያ መዳን የማይችል ከባድ የአእምሮ በሽታ ሲሆን መገለጫዎችም የሙድና የስሜት መዘበራረቅ፣ የማይታይን ምስል የማየትና የሌለን ድምፅ እንዲሰማ የማድረግ ችግሮች ናቸው፡፡ በለንደን የኪንግስ ኮሌጅ የሳይካትሪ ኢንስቲቲዩት የሚሰሩት ዶክተር ጀምስ ግኝቱ በከኪዘፍሬንያ በሽተኞች አእምሮ ውስጥ ምን እንደሚከሰት የመጀመያው መረጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም ፍንጩን ያገኙት አጥኝዎች ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ለልብ ህሙማን ሙሉ በሙሉ ሰው ሰራሽ ልብ መተካት ይቻላል? ለመጀመሪያ ጊዜ ለልብ ህሙማን ሙሉ በሙሉ ሰው ሰራሽ የሆነ ልብ ለመተካት የሚያስችል ስራ በመስራት ተግባራዊ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ሳይንቲስቶች አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና አንዳንድ የልብ ኤክስፐርቶች ከዚህ ቀደም ተደርጎ እንደነበረው ግኝት ሰዎች ላይ ሲሞከር ላይሳካ ይችላል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አዲሱ መሳሪያ የኤሌክትሪክ ሴንሰሮችን በመጠቀም ልክ እንደተፈጥሮ ልብ የልብ ምትንና የደም ዝውውርን መቆጣጠር እንደሚችል ታውቋል፡፡ ለልብ ህሙማን ሰው ሰራሽ ልብ ሙሉ በሙሉ ለመተካት የሚያስችል ስራ ሰርተናል የሚሉት ሳይንቲስቶች ሥራቸውን ሰዎች ላይ ከመሞከራቸው በፊት ከፈረንሳይ ባለሥልጣናት ስራቸው ሊፀድቅላቸው ይገባል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ግኝቱ ስኬታማ ከሆነ በበጎ ፈቃደኛ ልብ ለጋሾች እጥረት የተነሳ በዓለም ላይ ህይወታቸውን ለመታደግ የልብ ቀዶ ህክምና ማድረግ ያልቻሉ 20 ሺህ ያህል በሽተኞች ማከም ይቻላል አዲሱን ሰው ሰራሽ ልብ የሰሩት የልብ ስፔሻሊስት አሊያን ካርፐንቴር ስራው 15 ዓመት እንደወሰደባቸው ጠቅሰዋል፡፡ የመሳሪያው የላይኛው ክፍልም በልዩ ጥንቃቄ ከተሰሩ ቲሹዎች ተሸፍኗል፡፡ ይህም መሳሪያው የሰው አካል ውስጥ ሲገባ በሰውነት የበሽታ መከላከያ ሴሎች ተቃውሞ እንዳይገጥመው ለማድረግ እንደሚያስችል ስፔሻሊስቱ ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ይህ ቲሹ ለልብ መድረስ ያለበትን በቂ የደም አቅርቦት እንዳያገኝ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ * * * ለሁለት ዓመት የቀጠለው የጭቃና አቧራ ፍንዳታ ምክንያት ታወቀበኢንዶኔዥያ ሉሲ ደርሶ የነበረው የመሬት ናዳ በዘይትና ጋዝ ፍለጋ ይደረጉ በነበሩ የከርሰ ምድር ቁፋሮዎች ምክንያት የደረሰ እንደሆነ 74 ዋና ዋና ጂኦሎጂስቶች ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ በሉሲ የመሬት ናዳ የደረሰው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን በአካባቢው አቧራና ጭቃ እንደ እሳተ ገሞራ ወደ ላይ መፈንዳቱን ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ 30 ሺህ ያህል የምስራቅ ጃቫ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከከርሰ ምድር ዘይትና ጋዝ ለማውጣት በአካባቢው ቁፋሮ ሲያካሂድ የነበረው ላፒንዶ ብራንታስ የተሰኘው ተቋም ግን የአቧራ ፍንዳታው ከ280 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ደርሶ በነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን ይችላል በሚል ይከራከራል፡፡ በደቡብ አፍሪካ በተደረገ የጂኦሎጂስቶች ስብሰባ ክርክር ከተደረገ በኋላ ብዙ መረጃዎች የደረሰው ናዳ በቁፋሮው ምክንያት እንደሆነ ስለሚጠቁሙ በዚሁ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የጀመረው የአቧራና ጭቃ ፍንዳታ እስካሁን ድረስ አራት መንደሮችና 25 ፋብሪካዎች ወድመዋል፣ 13 ሰዎችም ሞተዋል፡፡ ፍንዳታው እስካሁን የቀጠለ ሲሆን በአስርት ለሚቆጠሩ ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችልም ጂኦሎጂስቶች አስታውቀዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Wednesday, 05 November 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |