| ሃያ ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት... |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
ሃያ ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በመስኖ ለማልማት ኘሮጀክት ተቀረፀ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለሚከናወኑ የመስኖ ልማት ኘሮጀክቶች የዓለም ባንክ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሊሰጥ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደተገለፀው፣ በአማራ ክልላዊ መንግሥት በተለይ በሰሜን ጐንደርና በጣና ዙሪያ ለሚከናወን የመስኖ ልማት ኘሮጀክት ማስፈፀሚያ 95 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማምቷል፡፡ በሰሜን ጐንደርና በጣና ዙሪያ ግምቱ 100,000 ሄክታር በሚሆን ቦታ ላይ ጥናት ተካሂዶ 20,000 ሄክታር የሚጠጋውን መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ኘሮጀክት እንደተቀረፀ በስብሰባው ላይ ተገልጿል፡፡ የኘሮጀክቱ ዋና አላማም ኘሮጀክቱ በሚተገበርበት አካባቢ የግብርና ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በኘሮጀክቱ ሊከናወኑ የታቀዱ ተግባራት በአራት ዘርፎች የተከፈሉ ሲሆን ከሚገኘው ብድር ውስጥ ለመስኖ ልማት 65 ሚሊዮን ዶላር፣ ለግብርናና ገበያ ልማት 13.8 ሚሊዮን ዶላር፣ ለመስኖ አስተዳደር 12.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኘሮጀክት አስተዳደር 3.7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ በመስኖ ልማት ኘሮጀክቱ 20,000 ሄክታር የሚጠጋ መሬት የከርሰምድርና ከመሬት በላይ ያለን ውሀ በመጠቀም ይለማል፡፡ ወደፊትም 80,000 ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ተግባር ይከናወናል፡፡ በዕለቱ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ይህ የሥራ ዘርፍ ሲጠናቀቅ 12,000 የሚጠጉ አባወራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ኘሮጀክቱን ለማስፈፀም ከሚያስፈልገው 11ዐ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ የዓለም ባንክ 95 ሚሊዮን ዶላር በብድር ይሰጣል፡፡ ቀሪው የኘሮጀክቱ ወጪ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት በሚመደብ 12 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላርና ከተጠቃሚዎች በሚሰበሰብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚሸፈን ተጠቁሟል፡፡ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር በብድር የሚገኘው ገንዘብ በኤስ.ዲ.አር 65,600,000 ሲሆን ለእቃዎችና መሳሪያዎች ግዢ 11,800,00፣ ለግንባታ ሥራዎች 29,300,000፣ ለምክር አገልግሎትና ለኦዲት፣ 19,410,000፣ ለሥልጠና እና ለአውደ ጥናት 23,600,00፣ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ድጋፍ 13..200.00፣ ለሥራ ማስኬጃ 17..700..00፣ ለኘሮጀክት ዝግጅት የወጣና የሚተካ ሂሳብ 460,000 እና ያልተደለደለ 98,000,00 በድምሩ 65,600,000 ዶላር ይሆናል፡፡ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር በብድር የሚገኘው ኤስ.ዲ.አር ስልሳ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከወለድ ነፃ ነው፡፡ ብድሩ የአስር ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመታት ውስጥ ይከፈላል፡፡ አቶ ተመስገን ዘውዴ የብድር ስምምነቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ለኘሮጀክት ማስፈፃሚያ የሚውለው ገንዘብ በክልሎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ቢሆንና ገንዘቡን ለመጠቀም ያላቸው አቋም ቢታይ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ የአገር ውስጥ አማካሪዎችም ከዚህ የኘሮጀክት ገንዘብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡ የኦፊዴን ተወካይ አቶ መስፍን ነመራ የልማት ሥራ ማከናወን ጥሩ ቢሆንም ብድር ተገኘ ተብሎ እዳ ከምሮ ማለፍ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የኢዴአፓ መድህን ተወካይ አቶ አብዱራህማን አህመዲን በበኩላቸው የብድር ስምምነቱ የአማራ ክልል ብቻ ከሚሆን ሌሎች ክልሎችም ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የብድር ስምምነቱን እንደሚደግፉ የገለፁት አቶ መሀመድ አሊ ለምክር አገልግሎትና ለኦዲት ተብሎ የተቀመጠው ገንዘብ በጣም ብዙ መሆኑንና ለግንባታ ሥራዎች የሚውለው ወጪ ከፍ ቢል እንደሚሻል አስረድተዋል፡፡ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት በፓማርላማ የመንግሥት ተወካይ አቶ ሽፈራው ጃርሶ የመስኖ ልማትን ለመጠቀም ብዙ ጥናቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አመልክተው፣ በዚሁ ጥናት መሠረትም ሌሎች ክልሎችም የተለያዩ ኘሮጀክቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ በአዋሽ ላይ ከ90 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የሚለማበት ሁኔታ እየተስተካከለ መሆኑንም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |