| “ኮንትራክተር ሌባ ነው... |
|
| Sunday, 09 November 2008 | |
|
“ኮንትራክተር ሌባ ነው የሚለውን አመለካከት ማጥራት እንፈልጋለን”
አቶ ደምሰው አባተ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ደምሰው አባተ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በሞያቸው ሲቪል ኢንጂነር ሲሆኑ በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡ ራሳቸው ያቋቋሙት ኢኳቶር ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግ.ኩ ማኔጅግ ዳይሬክተርም ሆነው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ዳዊት ታዬ በወቅታዊ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴና በሚመሩት ማህበር ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለበትን ደረጃ ማወቅ ይቻላል? አቶ ደምሰው፡- የአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተከፈተው ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ሥርዓት የሶሻሊስት በመሆኑ ይኸንን ሥራ ይሰሩ የነበሩት ሁሉም የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ግን የግል ዘርፉ በየአቅጣጫው መስራት ከጀመረ አጭር ጊዜው ስለሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም ገና እንጭጭ ነው አላደገም፡፡ በዚህ ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂውም ብዙ መጥቷል ማለት አንችልም፡፡ የካፒታል፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልም ብዙም ስለሌለ ዘርፉ ገና በእድገት ላይ ያለ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ወደ ሦስት ሺ የሚሆኑ የኮንስትራክሽን ኩባያዎች ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ነው፡፡ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት በአብዛኛው በውጭ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ነው፡፡ ለምን? አቶ ደምሰው፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ እድገት በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ለመሆኑ ዋናው ምልክት ይሔ ነው፡፡ የተደራጁና የጠነከሩ ድርጅቶች ገና የሉንም፡፡ ገና እየመጡ ነው ያሉት፡፡ በትክክለኛው ደረጃ ላይ ቆመዋል ለማለት አይቻልም፡፡ በራሱ የውስጥ አደረጃጀት ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ቫርኔሮን ብትወስድ፣ ከአያቱ የወሰደው ድርጅት ነው፡፡ እኛ ግን እንኳን ከአያቶቻችን ልንወስድ እኛም ከጀመርን ቅርብ ጊዜያችን ነው፡፡ አዲስ የተጀመረ ሥራ በመሆኑ፣ አንተ ያሰለጠንከው የሰው ሃይል ሌላ የተከፈተ ሲያይና የተሻለ ክፍያ ሲያይ ይሄዳል፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን በስራ ላይ ያሉት አገር በቀል ኮንስትራክተሮች የብቃት ደረጃስ? አቶ ደምሰው፡- ጠንካራ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የመፍጠር ፍላጐቱ አለ፡፡ ግን ያቅም ችግር አለ፡፡ የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ ካናጢው፣ ከግንበኛው ጀምሮ ችግር አለ፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ነው ኮንትራክተሮቻችን እየሠሩ ያሉት፡፡ ሪፖርተር፡- ችግሮቹ ምንድናቸው? አቶ ደምሰው፡- በፋይናንስ በኩል የተመለከትን እንደሆነ የባንክ ብድር አስቸጋሪ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን መሳሪያ መግዛት ብትፈልግ ከባንክ ብድር ማግኘት ችግር ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ተከልክሏል፡፡ ኮንስትራክሽን ደግሞ ብዙ ገንዘብ ይፈለጋል፡፡ ደረጃህ ከፍ ባለ ቁጥር ከባድ ማሽኖችን መግዛት ግድ ይለናል፡፡ ማሽኖቹ ደግሞ በሚሊዮን ብር የሚገዙ ናቸው፡፡ እነዚህን ማሽኖች ለመግዛት የባንክ ብድር ያስፈልጋል፡፡ ግዥውን ለመፈፀም ግን ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ማስያዣ (ኮላትራል) ይጠይቁሃል፡፡ የአስር ሚሊዮን ብር ማሽን ለመግዛት ከፈለግህ የ10 ሚሊዮን ብር ኮላተራል ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ይኸ ከየት ይገኛል? አብዛኛዎቹ ኮንስትራክተሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ እውቀቱና ፍላጐቱ ያላቸው ቢሆኑም ገንዘብ የላቸውም፡፡ ስለዚህ በፋይናንስ በኩል ያለው ችግር ለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እድገት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ባንኮች ለኮንስትራክተሮች ብድር አይሰጡም ማለት ነው? አቶ ደምሰው፡- በአሁኑ ሰዓት ለኮንትራክተሮች ባንኮች ብድር አይሰጡም፡፡ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ብሔራዊ ባንክ ከልክሎናል የሚል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ አመታዊ ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ባንኮች ለኮንስትራክሽንና ህንፃ ለግንባታ ብዙ ሚሊዮን ብር መስጠታቸውን ይገልፃል፡፡ አቶ ደምሰው፡- ለማሽነሪ ግዢ በሚል ለነጋዴዎች በተለይ ለገልባጭ መኪና መግዢያ ብዙ ብር ሰጥተዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ማሽኑንም ሆነ ገልባጩን ለኪራይ አውለውታል፡፡ ስለዚህ ወደ ገበያ በብዛት ስለገባ ነጋዴዎቹ የተበደሩትን መመለስ አልቻሉም፡፡ ኮንትራክተሩ ግን ለራሱ ሥራ ነው ብድር የሚፈልገው ሌሎች የተበደሩትን ባለመመለሳቸው ምክንያት አጠቃላይ የማሽነሪ ግዢ ብድር ጥያቄን አይቀበሉም፡፡ ይህም ባለመሆኑ ብዙ ኮንትራክተሮች ለሚሠሯቸው ሥራዎች እንደ ዋነኛ ግብዓት የሚፈልጉትን ማሽነሪ መግዛት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የያዝነውን ሥራውን በአፋጣኝና በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት አቅም እንዲያንሰን አድርጓል፡፡ ሪፖርተር፡- ይህን ችግር ለመንግሥት አሳውቃችኋል በማህበራችሁስ ችግሩን ለመቅረፍ ምን የሰራችሁት ሥራ አለ? አቶ ደምሰው፡- መንግሥት ይህንን ያውቃል፡፡ አውቆም በሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር በኩል ዶዘሮች፣ ገልባጮችን እያስመጣ እየሸጠ ነው፡፡ እራሱ ከተማ ልማት የኮንትራክተሩን ችግር አውቆ የሚያስመጣቸውን ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ 30 በመቶ በማስከፈል ቀሪውን ከባንክ ተበድሮ እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የተጠቀመበት አንድ ዘዴ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ የኮንስትራክሽን እቃ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ይህ ጭማሪ ያሳደረው ተፅዕኖ ምንድነው? አቶ ደምሰው፡- የገበያ ዋጋ ችግር እከሌ ከእከሌ ሳይል በሁሉም ላይ ያለና እየታየ ያለ ችግር ነው፡፡ ጫና ፈጥሮብናል፡፡ ይህ ጫና ደግሞ ሥራዎች በወቅቱ እንዳያልቁ ችግር ፈጠሯል፡፡ ለዚህም ብዙ ድርጅቶች እየጠፉ ነው ያሉት፡፡ ትልቅ ፕሮጀክት የያዙ በጣም ተቸግረዋል፡፡ በብዙ ዕቃዎች ላይ ከሰላሣ በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ አለ፡፡ የመቶ ሚሊዮን ብር ሥራ የያዘ አንድ ኮንትራክተር በዚህ ጭማሪ ስሌት መሰረት 30 ሚሊዮን ብር ይጨምርበታል፡፡ ይህንን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ለውጥ ከየት አምጥቶ ይሸፍነዋል? ስለዚህ ያለው አማራጭ ተከታታይ ፕሮጀክት ካገኘ እየተንከባለለ ሊሄድ ይችላል፡፡ እዛው ላይ ከቆመ ግን እዚያው ሊቀር ይችላል ይህ ችግር በእያንዳንዱ ላይ እያደረሰ ነው፡፡ ማህበራችንም እንዲህ ያለ አቤቱታዎችን በየጊዜው ይቀበላል፡፡ ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ያስከተለውን ችግር ለማካካስ ወይም መፍትሔ እንዲገኝለት በማህበራችሁ ደረጃ ምንድነው መደረግ ያለበት ብላችሁ ታምናላችሁ? አቶ ደምሰው፡- በማህበር ደረጃ አጠቃላይ ያስከተለውን ችግር እያጠናን ነው፡፡ መንግሥትም ችግሩን ያውቀዋል፡፡ ግን መንግሥትም በአስቸኳይ ተነስቶ እርምጃ ቢወሰድ በኢኮኖሚው ላይ ችግር ያመጣበታል፡፡ ስለዚህ እኛም አጥንተን ከመንግሥት ጋር ተመካክረን መንግሥትም ችግራችንን ተረድቶ ይፈታልናል ብለን እናምናለን፡፡ መጀመሪያ ግን እራሳችን እያጠናን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በጣም የጨመረው የኮንስትራክሽን እቃ የትኛው ነው? አቶ ደምሰው፡- ምን ያልጨመረ ነገር አለ፡፡ እኛ አገር አንድ ነገር ሲጨምር ሁሉም ነገር ይጨምራል፡፡ ከድንጋይና አሸዋ ጀምሮ ሁሉም ጨምሯል፡፡ በተለይ ትራንስፖርት በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ሪፖርተር፡- ይህ የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም የተለያዩ ግንባታዎች ሥራ አልቆመም፡፡ የእቃ መወደድ ችግር እየፈጠረ ከሆነ እንዴት እየሰራችሁ ነው? አቶ ደምሰው፡- ሥራዎች በአግባቡና በሰዓቱ የማያልቁበት ምክንያቱ ይሔ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሥራዎችን በተከታታይ ካገኘህ ያንዱን ወደ ሌላው እያንከባለልክ ትንሽ መሄድ ትችላለህ፡፡ እንደፈለክ ለመሄድ ግን አትችልም አንድ ቦታ ላይ መቆምህ አይቀርም፡፡ ሪፖርተር፡- ለቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተለየ እድል ስለሚሰጥ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሥራ ማግኘት አይችሉም ይባላል? አቶ ደምሰው፡- በዋጋ ተጫርተው ስለሚያሸንፉ እንጅ ልዩ ጥቅም ለማንም አይሰጥም፡፡ እነሱ (ቻይናዎቹ) ካገራቸው ድጋፍ ስለሚያገኙ ሙሉ ትጥቃቸውን ይዘው ይመጣሉ፡፡ የሰለጠነ የሰው ሃይል አላቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለሌለባቸው የግንባታ እቃዎችን እንደፈለጉ ያስገባሉ፡፡ በተባሉበት ጊዜና ፕሮግራም ስለሚጨርሱ ዋጋቸውን የመቆጣጠር (የጨረታውን) እድል አላቸው፡፡ ግን ጨረታው ግልፅና ለማንም የማያዳላ ነው፡፡ እኛ ግን መሣሪያ የለንም፡፡ መሣሪያው ሲገኝ የሰለጠነ የሰው ሃይል የለንም፡፡ የማቴሪያል ችግርም አለብን፡፡ በዚህ ሁሉ ችግሮች ላይ የማቴሪያል ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ ስለሚሄድ፣ የመጫረቻ ዋጋቸውን እንዲንር ያደርጉታል፡፡ የቻይናዎቹ ግን ይኸ ችግር የለባቸውም፡፡ እኛ ቅድሚያ ስንወስድ ማሽነሪ ልንገዛ እንሄዳለን፡፡ እነሱ ግን ቅድሚያ በመውሰድ የግንባታ ማቴሪያል ስለሚገዙ ግንባታቸው የተፋጠነ ነው፡፡ እኛ ያዘዝነው ማሽን ለመግዛት እስከ ስድስት ወር ሊፈጅ ይችላል፡፡ ማሽኑ ሲመጣ ጊዜው እያጠረ ይሄድብናል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ይፈጠርብናል፡፡ ግንባታዎችም በወቅቱ ለማስረከብ ስለምንቸገር በዚህ ክፍተት የቻይናም ኩባንያዎቹ ይጠቀማሉ፡፡ ሪፖርተር፡- አገር በቀል ኮንትራክተሮች በጥምረት ለመስራተግ ችግር አለባቸው፡፡ ለምን? አቶ ደምሰው፡- በኮንትራክተሮች መከከል በሽርክና የመሥራት ነገር የለም፡፡ ይኸንን ወደ ተግባር የሚተረጉም ህግ ስለሌለ የአገር ውስጥም ኮንትራክተሮች በጋራ ወይም በሽርክና ለመስራት አልቻሉም፡፡ በሌላ በኩል ግን በሽርክና ለመስራት እንድንችል በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ይኸንን ህግ አስወጥታችሁ ከመጣችሁ በኛ በኩል ችግር የለብንም ብለውናል፡፡ በሽርክና ለመስራት የሚያስችለው ሕግ በንግድ ምክር ቤት በኩል ጥናት እየተደረገበት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥም በሚወጣው ህግ ውስጥ በሽርክና ለመስራት የሚያስችለው አንቀፅ እንዲካተትልን ማህበራችን እየሠራ ነው፡፡ ለጊዜው ግን ከተማ ልማት “ጆይንት ቬንቸር” ፈቅዷል፡፡ ስለዚህ አባሎቻችንን አሳውቀን ከሚመቻቸው ጋር እንዲገቡ እያደረግን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ማህበራችሁ ከ16 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ቢሆንም እንቅስቃሴው ደካማ ነው ይባላል? አቶ ደምሰው፡- ማህበራችን ብዙ አባላት አሉት፡፡ አባላቱ ገንዘብ በእጃቸው ላይ የሚያንከባልሉ ናቸው፡፡ ብዙም ባይሆን ገንዘብ አላቸው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ማህበር መጠናከር ብዙ አስተዋፅኦ ማድረግ ይችሉ ነበር ግን አልሆነም፡፡ አባላቶች የሉትም ማለት ይቻላል፡፡ አሁን የአባላትን ቁጥር ለመጨመር እየቀሰቀስን ነው፡፡ ማህበሩ ጠንካራ የሚሆነው አባላቱ ሲበዙ ነው፡፡ አሁን አባላቱ ውስን ናቸው፡፡ ቀደም ብሎም ተመራጭ የነበሩት ሰዎች ብቻቸውን ነበር ሲንቀሳቀሱ የነበሩት፡፡ የቦርድ አባል ብቻ ለውጥ አያመጣም፡፡ ሁሉም አባላት ከተሳተፈ ነው ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፡፡ አንዳንድ ጥናቶችን ለማስጠናት ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ተብሎ ቢጠየቅ ተቀባይነት ላይኖር ይችላል፡፡ ማሳመኛ የሚሆን የተጠና ማስረጃ ተይዞ መኬድ አለበት፡፡ ለጥናቱም ባለሙያ ተቀጥሮ መሥራት አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ገንዘብ ከሌለ ምን ይደረጋል? አብዛኛውን ጊዜ አሉባልታ የሆነውን አልባሌ ነገር ነው ይዘህ የምትሄደው”. ይኸ ደግሞ የማሸነፍ ሂደትን ያዳክመዋል፡፡ አሁን ግን እያደረግን ያለነው አባላትን ማሰባሰብ ነው፡፡ ቁጥራችን ወደ 200 እየተጠጋ ነው፡፡ በስድስት ወር ውስጥ ወደ 300 እንደርሳለን በማለት እቅድ ይዘናል፡፡ በተጓዳኝም በዋጋ ግሽበት ላይ እየሠራን ነው፡፡ በአጠቃላይ በሴክተሩ ላይ ያለው ችግር የኮንትራት አስተዳደር ህግ ደካማና ጠንካራ መሆኑን ለይተን፣ ደካሞቹ ላይ የራሳችንን መፍትሄ ሀሳብ ይዘን የራሳችንን የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ በኮንሰልታንት እያሰጠናን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ኮንትራክተር ጥሩ ስም የለውም ገንዘብ የሚሰበስብና እንደ ሌባም የሚቆጥሩት አሉ፡፡ ይህንን ስም ለመለወጥ ምን እያደረጋችሁ ነው? አቶ ደምሰው፡- በኮንስትራክሽን ማህበር ውስጥ ትልቁ ቻሌንጅ ይሄ ነው፡፡ ኮንስትራክተር ያለው ስም ጥሩ አልነበረም፡፡ ከፍተኛ ትርፍ የሚያገኝና ለሥራ የሚሠጠውን ገንዘብ ለግሉ የሚያውል፣ ግብር የማይከፍል፣ በጣም ብዙ ገንዘብ የሚሰበስብ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ግን እውነቱ ሌላ ነው፡፡ እንዲያውም ኮንትራክተር ደሀ ነው፡፡ የሚያገላብጠው ገንዘብ የባንክ ነው፡፡ ለሥራው ገንዘብ ስለሚያስፈልገው፣ በእጁ ላይ የሚሽከረከረው ገንዘብ የራሱና የግሉ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ይህ ገንዘብ ያደራ ገንዘብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኮንትራክተሩ በጥንቃቄ ሰርቶ የሚያገኛት በመጨረሻ ይታወቃል፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው ይኸንን ስም ለማደስ ነው፡፡ ኮንትራክተሩ አጋዥ ነው፡፡ ለመንግሥትም፣ ለህብረተሰቡም፣ ለልማትም አጋዥ ነው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ይህንን ተረድቶልን አብረን የምንሰራበትን መንገድ ማመቻቸት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም ማህበሩና ብዙ ሥራዎች እየሠራ ነው፡ ሪፖርተር፡- በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ ነው፡፡ በብዙ ግንባታዎች ኮንትራክተሩ ብዙ ለማትረፍ ርካሽ በሆኑ እቃዎች ግንባታዎችን ያካሄዳል የሚል ትችት ይሠነዘራል፡፡ እንዲህ አይነቱን አሰራር ለመቀየር የታሰበ ነገር አለ? አቶ ደምሰው፡- ማህበራችን በስፋት እየሠራ ያለው በአቅም ግንባታ ላይ ነው፡፡ ሁሉም ኮንትራክተር ባለሙያ አይደለም፡፡ የተወሰኑት ገንዘብ ይኖራቸዋል፡፡ የተወሰነት ባለሙያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስህተት የማይሰሩ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ይሳሳታሉ፡፡ እነዚያን ሰዎች ነው ማስተማር ያለብን፡፡ የሙያ ሥነ ምግባር አውጥተን በአባሎቻችን አስፀድቀን ለሚመለከተው ክፍል በትነናል፡፡ መመሪያችን ነው፡፡ አባሎቻችን ለህግ ተገዢነታቸውን አፅድቀዋል፡፡ ስራውን በአግባቡ የሚያሰራና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን መጀመሪያ ጠርተን እናነጋግራቸዋለን፡፡ ከተሣሣተ አካሄዳቸው እንዲቆጠብ እናደርጋለን፡፡ ያንን ካላደረገ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን ደንብና ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እርምጃ እንወስዳለን፡፡ መጀመሪያ ግን በመተዳደሪያ ደንባችን መሠረት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎቻችንና ምክሮችን እንሰጣለን፡፡ ሪፖርተር፡- የብዙ ህንፃዎች ግንባታ በጥራት እንደማይሠሩ እናያለን፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ በባለሙያ የተሠሩ እንኳን አይመስሉም፡፡ ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ አቶ ደምሰው፡- በትክክል ይሔ ችግር አለ፡፡ የአቅም ግንባታውም ሥራ ይህንን ነው የሚያጠናክረው፡፡ መንግሥትም ይኸንን ችግር አውቆት ከጀርመን ጋር እየተሰራ ያለው በኛም ማህበር የምንሰራው ይኸንን ነው፡፡ ከፍተኛ የጥራት ችግር እንዳለ እናውቃን፡፡ የድሮ አናጢዎቻችን በጣሊያኖች የሰለጠኑ ነበሩ፡፡ የተሻለ ሙያ ነበራቸው፡፡ እነሱ አለቁ ብዙም አልተካንም፡፡ ያሁኑ ትውልድ የግድ ያንን ለመተካት መሠረታዊ ስልጠና ያስፈልገዋል፡፡ የማህበራችንም አንዱ ኃላፊነት ይኸው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ስልጠናውን በምን ዓይነት ነው የምትሰጡት? አቶ ደምሰው፡- ከአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ጋር ሴንተር ኦፍ ኤክሳለንስ ፎር ኢንጂነሪንግ በሚባል ከአቅም ግንባታ አለ፡፡ በዚህ ማዕከል የሚሰጡት ጀርመኖች ናቸው፡፡ ማሰልጠኛ ከነሱ ጋር ሆነን እያንዳንዱ ኮንትራክተር ባለሙያዎች እየሳበ እንዳያመልጥ እኛ ባስተባባሪነት አብረን ሆነን ይኸንን ፕሮግራም ለመሥራት አቅደናል፡፡ ሪፖርተር፡- ይህ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ሥራ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አቶ ደምሰው፡- አሁን የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ እነዚህ ሰልጣኞች አብዛኛውን ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራም ላይ ሄደው ያሰለጥናሉ፡፡ እዚያ ያሉ ኮንትራክተሮች ለኢንጂነሮች ቅድሚያ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ሌሎቹን ደግሞ ፕሮግራም እያወጣ እንዲሰለጥኑ እናደርጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- የግንባታ ሥራዎችን በሚመለከት አንድ ሕግ ይወጣል ተብሎ ነበር? ይህ ሕግ አለመውጣቱ ችግር ፈጥሯል? አቶ ደምሰው፡- ይኸ ህግ በከተማ ልማት በኩል ለፓርላማ ቀርቧል ነው፡፡ እንደሰማነው ሕጉ በቅርቡ ሊፀድቅ ይችላል፡፡ ይህ ሕግ ከወጣ ብዙ ነገሮች ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ አለን፡፡ የኮንትራክተሮች ብቻ ሳይሆን የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይ አማካሪዎች ከዲዛይን ቁጥጥር ጀምሮ የሚያደርጉት ቁጥጥር በተግባር ላይ የሚውል ይመስለናል፡፡ ሪፖርተር፡- ይህ በኮንስትራክሽን ዘርፍና ተያያዥነት ያላቸው አካላት የሚነካካው ሕግ ላይ እናንተ ተወያይታችሁበታል? ደምሰው፡- የኛ ማህበር አልተወያየበትም፡፡ ቦርዱም ቅርብ ጊዜ የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም የነበረው ምናልባት አልተጋበዘም ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- የዚህ ሕግ ጠቅላላ መንፈስ ምንድነው? በናንተስ በኩል ይህ የግንባታ ሥራዎችን የሚቆጣጠር ሕግ አይነት መሆን አለበት? አቶ ደምሰው፡- ሁሉም ኃላፊነቱን የሚወጣበት ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ አንድ ሰው ለራሱ ሲሰራ የጐረቤቱንና ህብረተሰቡን ችግር አይቶ በጥንቃቄ መሥራት አለበት፡፡ አንድ ሰው ህንፃ ሲሠራ የጐረቤትን መንገድ ዘግቶ ይሠራል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ጐረቤትህን የምትነካው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በተቻለ መጠን በጥንቃቄ በመሥራት ጉዳቱን መቀነስ አለበት ወይም ጉዳት ሊደርስበት አይገባም፡፡ ሁሉንም የማይጐዳ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ብዙ ግንባታዎች ጥራታቸውን ባልጠበቁ የኮንስትራክሽን እቃዎች የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህም ወደፊት ትልቅ ችግር ይፈጥራል የሚል ሥጋት አለ? አቶ ደምሰው፡- እርግጥ ነው፡፡ የእቃ ጥራት ላይ ብዙ ችግር አለብን፡፡ በተለይ ብረት፣ የበር ቁልፍ፣ የሳኒተሪ እቃ፣ የባኞ ቤት ዕቃዎችና የመሣሠሉት ላይ ከፍተኛ የጥራት ችግር አለ፡፡ በዚህ ላይ ከደረጃ መዳቢዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ ደረጃዎች መዳቢ ግን አስገዳጅ ህግ ቢኖርም በእነዚህ ላይ አስገዳጅ ባለመሆኑ ከአቅማችን በላይ ነው ብለውናል፡፡ እነዚህን ለመቆጣጠር ህግ መኖር አለበት ብለውናል፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ እነዚህን ምርቶች መከልከል ያስቸግረናል ይላሉ፡፡ ይኸንን በተመለከተ ጉዳይ የጥራትና ደረጃዎች ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገር በጋራ ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘናል፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለነው አንድ የጋራ መድረክ ተፈጥሮ በተወሰኑ እቃዎች ላይ እንኳን ቁጥጥር ለማድረግ እየጠበቅን ነው ያለነው፡፡ ሪፖርተር፡- ማህበራችሁ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ለብቻቸው ማህበር መስርተዋል፡፡ በተናጠል መጓዛቸው አይጎዳችሁም? አቶ ደምሰው፡- አንድነት ሀይል ነው፡፡ ሁለታችን አንድ ብንሆን የበለጠ ጠንካራ ሆነን ልንሰራ እንችል ይሆናል፡፡ ብንለያይም መጥፎም አይደለም፡፡ ለየብቻ ጠንካራ ብንሆንም፣ ሁለት ጠንካራ ሀይል ይኖራል፡፡ ሁለታችንም ብንጠነክር ለህብረተሰቡም ለራሳችንም እንጠቅማለን ብለን እናስባለን፡፡ ችግራችን አንድ በመሆኑ በቅርቡ ደግሞ ወደ ውህደት ወይም አብሮ ሊያሰራን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ አጀንዳችን አንድ ስለሆነ አንድ ላይ ሆነን ብንሰራ የበለጠ ውጤት እንደምናመጣ እናምናለን፡፡ በሂደት ወደ አንድ የምንመጣበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የሚደረግባቸው የመንገድ ሥራዎች ለውጭ ኮንትራክተሮች እየተሰጡ ነው ለምንድነው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በመንገድ ሥራ በስፋት የማይገቡት? አቶ ደምሰው፡- ይሔ የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ ህንጻ ሥራ ብዙ ካፒታል አይፈጅም፡፡ ስለዚህ ከትንሽ ጀምረህ እያደግህ ትሄዳለህ፡፡ መንገድ ግን ገንዘቡም፣ የሰው ሃይሉም፣ ማሺነሪውም ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ የአቅም እንጅ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- የማህበራችሁ በአዲስ መልክ እየተንቀሳቀሰ ነው ከተባለ የወደፊት ራዕያችሁ ምንድነው? አቶ ደምሰው፡- የማህበራችን ራዕይ፣ በመጀመሪያ ኮንትራክተር “ሌባ ነው” የሚለውን አመለካከት ማጥራት ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ሌላ ሳይሆን የልማት አጋር ነው፤ የህብረተሰቡ አገልጋይ ነው፣ ስለዚህ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ የሚሰራ አካል ነው ተብሎ ስማችን እንዲቀየር እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡ በሁሉም ኮንትራክተር ጋ ችግር አለ፡፡ በዚያ ሴክተር ውስጥ ገብተን ሰዎችን እያሰለጠንን፣ የኮንትራክተሩን ጫና መቀነስ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ ግንባታዎች በኮንትራክተሮች የሚሠሩ አለመሆኑ ይታወቃል የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምንድነው? አቶ ደምሰው፡- ይኸ አስቸጋሪ ነው፡፡ በኔ ግምት በመኖሪያ ቤት ላይ አንድ ፎቅ ሁለት ፎቅ ነው፡፡ ይኸ በግል ቢሰራ ችግር አያመጣም፡፡ ከዛ በላይ ግን በግለሰብ ማሰራቱ በአገር፣ በኢኮኖሚ ላይ ብዙ ችግር ያስከትላል፡፡ በሴክተሩም ላይ የገበያ መዛባት ያመጣል፡፡ ስለዚህ ሁለት ደረጃዎች መኖር አለባቸው፡፡ እስከ G+3 ድረስ በግል ቢሰራም ብዙም ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ ከዚያ በላይ ላለው ግን ሕግ ወጥቶ ፕሮፌሽናል ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ኮንትራክተር ቢሰራው ለህብረተሰቡም ለኮንትራክተሩም ለመንግሥትም ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት የሚፈጠርበት አንዱ ምክንያት ግለሰቦች ተቀጥሮ መስራቱ ነው፡፡ ይህ አሠራር ተቀጣሪውን ታክስ እንዳይከፍል ያደርጋል፡፡ በትክክል ታክስ ላይሰንስድ የሆነ ኮንትራክተር ከሆነ ግን እያንዳንዱ ነገር በትክክለኛ የሒሳብ መዝገብ የሚያዝ ስለሆነ በአግባቡ ታክሱን ይከፍላል፡ በግል የሚሰራ ከሆነ ለባለሙያ የሚሰጠው ክፍያ ከኪስ የሚከፈልበትና ታክስ የማይከፈልበት ነው፡፡ ስለዚህ ለመንግሥት የሚከፈለው ግብር ይቀንሣል፡፡ ሕጋዊ ኮንትራክተሩ ግን በእያንዳንዱ ነገር ታክስ ይከፈልበታል፡፡ በእቃ ግዥ ላይም ይህ ችግር ይታያል፡፡ በግል የሚሰራው ሰው ያለቫት ገዝቶ ስራውን ይሰራል፡፡ እኛ ግን ቫት ይቆረጥብናል፡፡ ዋጋ ይጨመርብናል፡፡ ዋጋ የሚጨምርብንም ነጋዴዎቹ ዕቃ ስንገዛቸው በቫት ወይስ ያለቫት ይሉናል፡፡ በቫት ካልን ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ በግል ለሚሰሩት ደግሞ ቫት ስለማይጠይቋቸው ቀንሰው ይሸጡላቸዋል፡፡ ምርጫ ስለሌለን ግን በጭማሪውም ቢሆን የግድ እንገዛለን፡፡ ሪፖርተር፡- ይህንን ችግር ለማስቀረት ምን እያደረጋችሁ ነው? አቶ ደምሰው፡- አሁን ካገር ውስጥ ገቢ ጋር ንግግር ጀምረናል፡፡ አንድ የጋራ መድረክ ለመክፈት እየሠራ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በባለሙያዎች ወይም በኮንትራክተሮች የማይሰሩና ቁጥጥር የማይደረግባቸው ግንባታዎች ዋነኛ ምክንያት አስገንቢዎቹ ናቸው ይባላል? አቶ ደምሰው፡-በዚህ ጉዳይ እኔ ያጋጠመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ አንድ ሰውዬ ባለ ሰባት ፎቅ እየሰሩ ነው፡፡ የሚሰሩትም በግል መሀንዲስ ቀጥረው ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ወደ ግንባታው ቦታ ይሄዱና የሚሰራውን ሥራ ያያሉ፡፡ በዲዛይኑ መሰረትም የሚገነባው ሕንጻ ላይ ብዙ ብረት ተደርድሮ ያያሉ፡፡ ይህንን ብረትም ሲያዩ በጣም ይናደዳሉ፡፡ ምንድነው ይሄ ሁሉ ብረት በኔ ገንዘብ ነው የምትጫወቱት ብለው ይቆጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ መሀንዲሶች ብረት ያበዛሉ ብለው ከተደረደረው ብረት ውስጥ የተወሰነ ብረት መዝዘው በራሳቸው ከወጡ በኋላ መንገድ እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ በዚህ መንገድ ግንባታ የሚሰራ ከሆነ እጅግ ብዙ ችግር ስለሚከሰት እንዲህ አይነቱ አደገኛ ሁኔታ ለማስቀረት አንድ ሕግ ሊወጣ ይገባል፡፡ በኮንትራክተር ቢሰራ ደግሞ እንዲህ አይነት ችግሮች አይፈጠርም፡፡ ኮንትራክተር አለ ማለት ተቆጣጣሪ አለ ማለት ነው፡፡ ከሚሰጠው ዲዛይን ውጭ አይሰራም፡፡ ጥራት ተጠብቆ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለኮንትራት የምትሰጠው ከሆነ ተጠያቂነትም ይኖራል፡፡ የተበላሸ ነገር ካለም አሠሪውም መንግሥትም በሕግ የመጠየቅ መብቱ ይጠበቃል፡፡ ሪፖርተር፡- በምሥራቅ አፍሪካ አገራት አካባቢ ሠፊ የኮንስትራክሸን ገበያ አለ፡፡ የአገር ውስጥ ኮንስትራክተሮች በዚህ ገበያ ለመግዛት የማይችሉት ለምንድነው? አቶ ደምሰው፡- ይህም የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ የኛ ኮንትራክተሮች ውጭ ወጥተው ለመስራት የሚያስችላቸው የአይኤስኦ ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ነው፡፡ እስካሁን ስምንት አግኝተዋል፡፡ አርባ የሚሆኑ ደግሞ ማረጋገጫውን ለማግኘት የሚያስችላቸው ስልጠና የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ አቅሙ ከዳበረ ምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ወደ መካከለኛውም ምሥራቅ ዘልቀው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪም ይገኝበታል፡፡ |
|
| Last Updated ( Tuesday, 11 November 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |