| አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ... |
|
|
| Wednesday, 23 January 2008 | |
|
አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ለማስገባት ተደርሶ የነበረው ስምምነት ፈረሰ ሜን ስቴል ስክራፕ ሪሣይክሊንግ የተባለ አገር በቀል ኩባንያ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ በማስመጣት በጅንአድ በኩል ለማከፋፈል ተደርሶ የነበረው ስምምነት ሳይሳካ ቀረ፡፡ የሜን ስቲል ስክራፕ ሪሣይክሊንግ የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ሲሚንቶውን በፍራንኮ ቫሉታ ለማስመጣት ፈቃድ በማግኘታቸውና ለማስመጣት ያቀዱት የሲሚንቶ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ከጅንአድ ጋር በመስማማት ሥራዎች በመሠራት ላይ እያሉ መንግሥት አንድ ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ አስመጣለሁ በማለቱ ለሥራቸው አለመሳካት አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በጅንአድና በሜን ስቲል ስክራፕ ሜታል ኩባንያ መካከል ተደርሶ በነበረው ስምምነት መሠረት ጅንአድ ገበያ በማፈላለግና በመሸጥ ጭምር ይሠራ እንደነበር ያመለከቱት ኃላፊዎቹ የታቀደው ቢሣካ ኖሮ የሲሚንቶ ዋጋው አሁን በአገር ውስጥ ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ በታች ለመሸጥ ያስችል እንደነበር ገምተዋል፡፡ ሲሚንቶው በፍራንኮ ቫሉታ ለማስመጣት ኩባንያው ፍቃድ ማግኘቱ የመንግሥትን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ይቀንሳል ከሚል እሳቤ ጭምር እንደነበር የሚገልፁት እኒሁ ኃላፊዎች መንግሥት ሲሚንቶ ሊያስመጣ ነው የሚለው ዜና ጅንአድም ሆነ ኩባንያውን ስላሳሰበው መንግሥት ካስመጣ እንከስራለን በማለት ጉዳዩ በእንጥልጥል እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የጅንአድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይማም መሐመድ በበኩላቸው ኩባንያው የሚያስመጣውን ሲሚንቶ በጅንአድ ቅርንጫፎች በኩል ለማከፋፈል እየተነጋገሩ እንደነበርና የቀረቡትንም መረጃዎች መመርመራቸውን ቀሪውንም በመመርመር ላይ እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ በክልል ጭምር የሚሰሩ የቤቶች ፕሮጀክቶች ከጅንአድ ግዥ እንዲፈፅሙ ለማድረግ በተደረገ ጥረት አዎንታዊ መልስ ሰጥተው እንደነበርና የአንዳንዶቹንም መልስ በመጠባበቅ ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሲሚንቶውን ያስመጣል የተባለው ኩባንያ አቅምና ሌሎች መመዘኛዎች በበቂ ሁኔታ በማየት ላይ እያሉ መንግሥት ሲሚንቶ ሊያስገባ መሆኑንና ለቤቶች ፕሮጀክትና ለተለያዩ ግንባታዎች እንደሚያቀርብ ሲነገር ጉዳዩን ማዘግየትና ድጋሚ መመልከት እንደሚኖር በማመን ከኩባንያው ጋር ያለው ግንኙነት ሊቋረጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ይማም ገለፃ ይህ እቅድ ባይሳካም ጅንአድ ከሜድሮክና ከሌሎች ኩባንያዎች ሲሚንቶ በመቀበል በየቅርንጫፎቹ በማከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |